ሙሉቀን ተደገ
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በሀገራችን ከታወኩ ማህበራዊ ጉዳዮች አንዱ እና በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የትምህርት ዘርፉ ይገኝበታል። በዚህም በሃገራችን የሚገኙ ትምህርት ተቋማት ለግማሽ መንፈቀ አመት ያህል መዘጋታቸው ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ዘርፉን ለማስጀመር መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተማሪዎችን በፈረቃ በመከፋፈል ለማስተማር ትምህርት ቤቶች ተገድደዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግስት ትምህርት ቤት መምህራን በፈረቃ ለተማሪዎቻቸው እውቀትን እየመገቡ ይገኛሉ።
የግል ትምህርት ቤቶችም መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትለው አገልግሎታቸውን ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ በፈረቃ እየሰጡ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የግል ትምህርት ቤቶች በፈረቃ ከፋፍለው ተማሪዎቻቸውን ቢያስተናግዱም ቅሉ መምህራን ላይ እየደረሰ ያለው የስራ ጫና ግን የተመለከተው አካል ያለ አይመስልም ሲሉ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ በማስተማር ላይ የሚገኙ መምህራን ይናገራሉ።
በመሆኑም በግል ትምህርት ቤቶች በማስተማር ላይ የሚገኙ መምህራን እንደሚሉት፤ በሳምንት እስከ 50 ክፍለ ጊዜ እንዲሚሰሩ ጠቁመዋል። ለዚህም እንደዋና ምክንያትነት የሚያነሱት ድግሞ አንዳንድ የግል የትምህርት ቤት አመራሮች በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የተላለፈ መመሪያ አለ በሚል ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።
በዚህም መመሪያ መሰረት በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራን በሳምንት እስከ 50 ክፍለ ጊዜ እንዲይዙ እየተገደዱ መሆናቸውን መምህራን ይናገራሉ። በዚህ የተማረሩ መምህራንም ይህንን መመሪያ
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ያውቀው እንደሆነ በማለት ለአዲስ ዘመን የዝግጅት ክፍል ጠይቁልን ባሉት መሰረት የአዲስ ዘመን የዝግጀት ክፍልም ጥያቄውን ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ የሆኑትን አቶ ብርሀኑ ተሾመ ጥያቄውን አቅርቧል ።
በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊው የሚከተለውን ምለሽ ሰጥተውናል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያስከተለው ችግር ወይም ቀውስ በአጠቃላይ እንደ አለም ብሎም በእኛ ሃገር በተለይ ደግሞ እንደ አዲስ አበባ የሚታወቅ ነው የሚሉት አቶ ብርሃኑ፤ ይህንን ችግር ለመፍታት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስተዳደር ሀላፊዎች በርካታ ውይይቶችን እንዳደረጉ ይገልፃሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከትምህርት ሚኒስቴር እንደ መመሪያ የወረደ መመሪያም እንዳለ ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮም እንደ አዲስ አበባ ተጨባጭ ሁኔታ ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ የኮቪድ ጊዜ ችግሮች ወይም ቀውሶችን መፍትሄ የሚሏቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ማስቀመጣቸውን አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ። ከነዚህ የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል አንድ ተማሪ በአንድ ዴስክ ላይ መቀመጥ እንዳለበት የሚገልፅ መመሪያ ነው። በዚህ አካሄድ የሚሄድ ከሆነ ደግሞ የክፍለ ጊዜያት ቁጥሮችን ይጨምራል። ይህ ደግሞ በመምህራን ላይ የስራ ጫና ያሳድራል።
ስለዚህ ይህንን ችግር ለመፍታት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የወሰደው እርምጃ ከወትሮው በተለየ መልኩ የሃገር ጥሪ ስለሆነ ችግሩን በጋራ የመወጣት እና መስዋእትነትን የመክፈል ጊዜ እና ሰዓት ስለሆነ የኮቪድ ጊዜ እስትራቴጂ እና ፕሮቶኮል ተዘጋቷል። በዚሁ መሰረትም አንድ አስተማሪ በትንሹ 24 እና 25 ክፍለ ጊዜ በሳምንት መያዝ እንዳለበት ነው አቶ ብርሀኑ የጠቆሙት። ነገር ግን የመጨረሻው የክፍለ
ጊዜ ጣራ ምን ያህል ነው የሚለው ላይ ምንም አይነት መመሪያ እንደሌለ ምክትል ሀላፊው ይናገራሉ።
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለፃ አንድ አስተማሪ መምህር በሌለበት ጊዜ እስከ 35 ክፍለ ጊዜ በሳምንት የሚይዝበት አጋጣሚ አለ። ነገር ግን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 35 ሆነ 40 ክፍለ ጊዜ የሚል የላይኛውን የመጨረሻ ጣሪያ አላስቀመጠም።ነገር ግን መምህር ከሌለ የግድ ተማሪዎች መማር ስላለባቸው 24 እና 25 ነው የሚል መመሪያ የአዲስ አበባ የትምህርት ቢሮ አውርዶ እየሰራ ይገኛል የሚሉት አቶ ብርሀኑ፤ 50 እና ከዚያ በላይ ክፍለ ጊዜ መምህራን መያዝ አለባቸው የሚል መመሪያ እንደሌለ ጠቁመዋል።
የሌለ መመሪያን አለ በማለት ይህን የሚያደርጉ የግል ትምህርት ቤቶች ካሉ ደግሞ ምን አልባትም ሰብአዊነት የጎደላቸው ናቸው የሚሉት አቶ ብርሀኑ፣ በዚህ አጋጣሚ የመምራንን ጉልበት መበዝበዝ ተገቢነት የለውም ሲሉ አመላክተዋል።ይህ አካሄድ ከመምህራን ጉልበት ብዝበዛ በተጨማሪ የትምህርት ጥራቱንም በከፍተኛ ደረጃ ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባው አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮም የተማሪዎችን ተጠቃሚነት መሰረት አድርጎ ስለሚሰራ ይህንን የመሰለ ሀላፊነት የጎደለው ተግባር እንደሚያጣራ እና እንደሚያስቆም አመላክተዋል። በሳይንቲፊክ ስታንዳርድ አንድ መምህር ምን ያህል ክፍለ ጊዜ ማስተማር እንዳለበት እና ምን አይነት እውቀት ማስተላለፍ እንዳለበት ይታወቃል የሚሉት አቶ ብርሀኑ፣ ስለዚህ ይህ በግል ትምህርት ቤቶች የሚሰራው ስራ ከትምህርት ቢሮ የወረደ መመሪያ ሳይሆን ምን አልባት የግል ትምህርት ቤቶች ቢዝነስ ሴንተር ስለሆኑም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ጉልበት የሚበዘብዙበት አግባብ ካልሆነ በስተቀር ከቢሮ እንደዚህ አይነት ሀላፊነት የጎደለው መመሪያ አልወረደም ሲሉ ተናግረዋል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የግል ትምህርት ቤቶች ለአንድ መምህር ከአራት ክፍሎች በላይ ዝግጅቶች ተዘጋጅቶ እንዲያስተምር እንደሚገደድ መምህራን ያነሱትን ጥያቄ መሰረት አድርገን ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ የሆኑትን አቶ ብርሀኑ ተሾመን ጠየቅን። በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊው የሚከተለውን ምለሽ ሰጥተውናል።
“ብዙ የክፍል ደረጃዎችን አንድ መምህር ቢያስተምር በትምህርት ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አያጠራጥርም።“ ነገር ግን ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ ጋር ተያይዞ የመምህር እጥረት ካጋጠመ እስከ ሁለት ክፍለ ደረጃ አንድ መምህር እንዲይዝ ቢደረግ ብዙም ችግር የለውም።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ስግብግብ የግል ትምህርት ቤቶች የመምህራንን ጉልበት ለመበዝበዝ በመፈለግ ብዙ የክፍል ዝግጅቶችን መስጠታቸው አግባብ ካለመሆኑም ባሻገር በመመሪያ የወረደ ስላልሆነ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው አቶ ብርሀኑ አመላክተዋል።በመጨረሻ የኮሮናን ተፅዕኖ ተንተርሶ ህገ ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ አካላት ካሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2013