እፀገነት አክሊሉ
ለአገር አንድነትና ሰላም ዘብ ከሚቆሙ ኃይላት መካከል የመከላከያ ሠራዊት የሚወጣው ሚና ከፍተኛ ነው። ለዚህ ግዳጁ አፈፃፀም ይረዳው ዘንድም በመንግሥት በኩል የተለያዩ ድጋፎች ይደረጉለታል።በተለይም ከወራት በፊት የጁንታው ቡድን የቃጣበትን ጥቃትና የፈፀመበትን ክህደት ተከትሎ ሠራዊቱ እራሱን አደራጅቶ ተቀናጅቶና ተናቦ የወሰደው እርምጃ ብዙዎችን ያስደመመ፣ ብቃቱንም ያሳየበት ሆኖ አልፏል።
በቀጣይም ብዙ ግዳጆች እንደሚኖሩበት የሚታሰበው ይህ ኃይል በተለይም ከሕግ ማስከበር ዘመቻው መጠናቀቅ በኋላ በምን ዓይነት ቁመና ላይ ነው ? ስንል በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመከላከያ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከሆኑት ከአቶ ዼጥሮስ ወልደሰንበት ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ ንዑስ ኮሚቴው መከላከያን በዋናነት ሲከታተል ምን ምን ተግባራትን ነው አብሮ የሚያከናውነው?
አቶ ዼጥሮስ፦ የመከላከያ ሥራ ከሰላም ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ የአገርን ደህንነት የማስጠበቅ ሰላምን የማረጋገጥ ተግባራት ደግሞ ከዋና ዋናዎቹ ሥራዎቹ መካከል የሚጠቀሱለት ናቸው።
በውስጥም በውጭም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚጎዱ ሁኔታዎች ሲኖሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆኑ አገርን በማረጋጋትና ህዝቦች በሰላም ወጥተው ሠርተው እንዲኖሩ የማድረግ ሥራን ነው ይሠራል። ከዚህ ውጭም ነፃ ሰዓቱን ህብረተሰቡን በተለያዩ ሁኔታዎች የማገዝና አብሮነቱን በሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ላይ የመሳተፍ፣ ደካሞችን የማገዝ፣ ትምህርት ቤት በሌለባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ሃላፊነቶች ሁሉ ያሉበትና እስከ አሁንም እነዚህን ተግባራት በአግባቡ እየተወጣ ያለ ስለመሆኑ በእኛም በንዑስ ኮሚቴያችን እንዲሁም በመላው ህብረተሰቡ የሚታወቅ ሃቅ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ የአገርን ሉአላዊነት ከውጭ ወራሪዎች መታደግ ቢሆንም ውስጣችን በሚፈጠሩ ግጭቶች ላይም በተለይም ሁኔታው ከፖሊስና ከአካባቢው ሰላም አስከባሪዎች አቅም በላይ ሲሆን በመንግሥት ውሳኔና ትዕዛዝ እየገባ እያገዘና እየሠራ ያለው የመከላከያ ሃይል መሆኑን እንደ ንዑስ ኮሚቴ እናያለን። በዚህም በኩል ያለውን ክፍተትና ጠንካራ ጎን ገምግመን ግብረ መልስ እንሰጣለን።
አዲስ ዘመን፦ ለውጡን ተከትሎ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች የተከናወኑት መከላከያው ላይ ነውና እንደው ቀደም ያለውንና አሁናዊ አቋሙን ስናነፃፀረው ምን ዓይነት ለውጦች መጡ ማለት ይቻላል?
አቶ ዼጥሮስ፦ የመከላከያን አጠቃላይ ሥራን ለማሻሻል እንዲያግዝ በመጀመሪያ ምክር ቤታቸውን መከላከያ የተቋቋመበትን አዋጅ ነው ያሻሻለው፤ ይህ መሻሻሉ ደግሞ ተቋሙ ሪፎርም ውስጥ ሲገባ ምን ዓይነት ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚጠብቁት ብሎም መብቶቹ እስከምን ድረስ እንደሆኑ እንዲረዳ አስችሏል። በሌላ በኩል የሰው ሃይል የማብቃት፣ የማሰልጠን እንዲሁም በአገር ውስጥና ከውጭ ዓለም ተሞክሮዎችን የሚያገኝበትን ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነው አዋጁ የተሻሻለው።
በዚህም መሰረት በተቋሙ ሥር ያሉ እንደ አየር ሃይል፣ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ዩኒቨርሲቲ፣ ሃይቴክ የሚባልና የግንባታ ሥራውም በመጠናቀቅ ላይ ያለው ሆስፒታል፣ የህትመት ድርጅቶች የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች የሚዘጋጅባቸው ክፍሎችን ጨምሮ በጣም ብዙ የሰው ሃይል የያዙ ትልልቅ ተቋማት የሚያስተዳድር እንደመሆኑ ይህንን ተቋም ውስጡ ያሉትን አቅሞች ተጠቅሞ ራሱን ተወዳዳሪ እንዲሆን የማድረግና በዘመኑ ቴክኖሎጂ እንዲጠናከር የማድረግ ከውጭ ቴክኖሎጂዎችን ከማምጣት ባለፈ የመጡትን በራስ አቅም የመጠገንና አሻሽሎ በሥራ ላይ የማዋል አቅምን ለመጨመር የሚረዱ በርካታ ሥራዎችን የመሥራት ዕድል ነው የተፈጠረው።
ከዚህ የተነሳ ከአደረጃጀቱ ጨምሮ አሠራሩን የመለወጥ፣ ዘመናዊ ትጥቆችን የሚታጠቅ የመከላከያ ሠራዊት እንዲሆን ለማስቻልና ሌሎች አገሮች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የሚያስችል ብቃትና ዝግጅት ለማምጣት የሪፎርም ሥራው ተሠርቷል።
መከላከያ ሠራዊት ከአገር ውስጥ ባሻገር በጎረቤት አገራት ላይም እየተዘዋወረ የሰላም ማስከበር ሥራን የሚሠራ ከመሆኑ አንፃር በዛ ደረጃም ብቁ ሆኖ ግዴታውን ለመወጣት የሚያስችል አቅም እንዲኖረው ለማድረግ ሰፋ ያለ የሪፎርም ሥራ ተሠርቷል።
በሪፎርም ሥራው ወቅት ትልቅ ትኩረት ካገኙ ተግባራት መካከል ሰዎች በእውቀታቸውና በችሎታቸው ልክ ደረጃን አግኝተው ወደ አመራርነት እንዲመጡ፣ የሴቶች ተሳትፎ እንዲጎለብት ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል።
በበጀትም በኩል አገሪቱ ባላት አቅም ልክ እንዲደገፍና በዚህም በስልጠና በትምህርት በኩልም ብቃት ያላቸውን እየመለመለ ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ዶክትሬት ድረስ እንዲማሩ ተደርጓል፤ በዚህም ትልቅ ለውጥ መጥቷል።
በቅርቡ ንዑስ ኮሚቴው በተለይም የመከላከያ አንዱ አካል የሆነውን አየር ኃይልን በአካል ሄዶ የመጎብኘትና ያለበትን ሁኔታ ለመረዳት ሞክሮ ነበር፤ አየር ኃይል በተለይም ህወሓት መራሹ የጁንታ ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ካደረሰው ጥቃትና ክህደት ጋር ተያይዞ የአገርን አንድነት ለማስከበር ሲሰራ የቆየ ተቋም ነው፤ ከዛ ጋር ተያይዞ እንዴት ነበር? በቀጣይስ ለሚሰጡት ተልዕኮዎች ምን ዓይነት ዝግጁነት አለው? የሚለውን በአካል ሄደን ለማየት በሞከርንበት ወቅት የታዘብነው እጅግ አስገራሚ ነገር ነው።
አየር ኃይል በዘመናዊ ትጥቅ መታጠቁ ብቻ ሳይሆን ስብዕናው ራሱ ጀግንነቱ ከስልጠና ብቻ የመጣ ሳይሆን ሠራዊቱ የጀግናው ህዝብ ነፀብራቅ መሆኑን በዚህ ጀግንነት ላይ ዘመናዊ ስልጠናዎችና ቴክኖሎጂ ቀመስ ትጥቆችና አጠቃላይ የዝግጁነት አቅሙ ሲጨመርበት የትኛውነም ዓይነት በአገር ላይ የሚደርስ ወረራ በብቃት መመከት የሚያስችል ዝግጅት ላይ ያለ መሆኑን ነው ለመታዘብ የቻልነው።
“ሰዎች ሠርግ ደግሰው እንኳን በማግስቱ ቤታቸው ተዝረክርኮ ነው የሚታየው ” አየር ኃይሉን ሄደን በጎበኘንበት ወቅት ግን በጦርነት ፍፃሜ ማግስት ላይ ያለ የማይመሰል በጣም የተረጋጋ ተልዕኮውን ፈጽሞ በቀጣይ ለሚፈለግበት የትኛውም ግዳጅ ዝግጁ ሆኖ የሚሠራ ተቋም ሆኖ ነው ያየነው፤ ይህ ደግሞ እኛም እንድንኮራ አድርጎናል። የኢትዮጵያ ህዝብም በዚህ ሁኔታ እጅግ ሊኮራ ይገባዋል።
ሪፎርሙም እስከዚህ ድረስ የተቀናጀ፣ የተዘጋጀና ምሉዕ የሆነ ተቋም እንዲፈጠር አድርጎታል ማለት ይቻላል። በእርግጥ አሁንም የሚቀሩ የተወሰኑ ሥራዎች ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን፦ መከላከያ ሲነሳ በተለይም ባለፉት ዓመታት የአንድ ፓርቲ ዘብ መሆኑ ነበር የሚነገረውና፤ አሁን ከዚህ ለውጥ በኋላ ራሱን የኢትዮጵያ ሉአላዊነት አስጠባቂ፣ የህዝቧ ዘብ ሆኖ እንዲቀጥል ሲደረግ በምን ያህል ደረጃ ገብቶት ተግባራዊ እያደረገውስ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ዼጥሮስ፦ እንድ ንዑስ ኮሚቴ መከላከያውን ስንከታተል በመስክ ጉብኝትም ያጋጠመንና ያየነው መከላከያ “አገር እንጂ ብሔር የለውም” የሚል መሪ ቃልን በግቢው ውስጥ ጽፎ ለተግባራዊነቱም ሲተጋ ነው። ከስልጠናቸው ጀምሮ ሌሎች ተግባራትን በዚህ ሁኔታ ሲመሩ እንደነበር አይተናል። ይህ ደግሞ በቅርቡም ከጁንታው ጋር በተያያዘ ከገጠመን ፈተና አንፃር በተግባር የታየና ፋይዳውም ከፍተኛ የሆነ ነበር።
ሰው ሁሉ የተወለደበት የሚናገረው ቋንቋ ያለው ነው፤ ነገር ግን ወደመከላከያ ስንመጣ መመራት ያለበት በብሔር ሳይሆን አገርን ይዞ መሪ ቃሉንም አንግቦ እቅዳቸው ላይም አስቀምጠው በዚህ መሰረት እየሄዱ መሆናቸው ትልቅ ኩራት ነው። እንደቀደመው ጊዜ ቢሆን ኖሮ መከላከያ አገር የሚመራው ፓርቲ ፕሮግራሙን አስጨብጦት ያንን ለመጠበቅ የሚቆም ሠራዊት ይሆን ነበር።
አሁን እየታየ ያለው ግን ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚጠብቅ ሕገ መንግሥትዊ ሥርዓቱ በምርጫ የሚቀየር ከሆነ ተተኪውን ሥርዓት ከመጠበቅ ውጭ ሁልጊዜ ለአንድ ፓርቲ የማይቆም ሠራዊት እንዲሆን በተሰራው መሰረት አሁን ላይም በተጨባጭ ሥራዎቹን ከብሔር ውጭ በሆነና አገርን ባስቀደመ መልኩ እየሰራም መሆኑን መናገር ይቻላል።
ከዚህ በፊት እንዴት ነበር ለሚለው አሁን በጁንታው ቡድን በኩል የተፈፀመው ክህደት በራሱ የሚያሳየው ፖለቲካው መከላከያ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ነው። ከዚህም ባሻገር መከላከያው የምትጠብቀው አብዮታዊ ዴሞክራሲን ነው ተብሎ ያደገና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሌለ ኢትዮጵያ የለችም ወደሚል ድምዳሜ የደረሰ ነበር።
ይህ ግን ከሞላ ጎደል አልተሳካም ማለት ይቻላል። ምንም እንኳን ከውስጡ የፓርቲ ዘብ የሆኑ የመከላከያ ትርጉም ያልገባቸው የነበሩ ቢሆንም አብዛኛው ሠራዊቱ ግን ዘብ የምቆመው ለአንዲቷ አገሬ ነው በማለቱ በውስጡ ያሉ ችግር እንኳን ቢፈጠርበትም ወዲያውኑ እራሱን አደራጅቶ የትህነግን ጁንታ ቡድን ለመደምሰስ ችሏል ።
እዚህ ላይ ግን መከላከያ ውስጥ ፖለቲካ ገብቶ እንደነበር ከገጠመን ችግር በመነሳት መደምደም ይቻላል። ግን ደግሞ አገርን ነው የምጠብቀው የሚለው ትንሽ እርሾ የነበረው በመሆኑ ችግሩን ተቋቁሞ ተከላክሎ አጥቅቶና አሸንፎ ነው ዛሬ ላይ አገር እንድትረጋጋ ማድረግ የቻለው።እኛም በጉብኝታችን ያየነው መሪ ቃላቸውን በተግባር መተርጎ ማቸውን ነው።
በሌላ በኩልም ያለንን አቅም የሰው ኃይል ገንዘብና ጉልበት አስተባበረን ራሳችንን እናበቃለን፤ በቁሳቁስም በስልጠናም በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ለአገራችን አለን የሚልም መሪ ቃል አላቸውና በዚህም መሰረት እኛ እንዳየነው ቴክኖሎጂን ለመለማመድ ያለው ዝግጁነት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የምንዛሪ ችግር የአቅርቦት ማነስ እንኳን እያለ ለማስተማሪያ የምትሆን አንዲት ነገር ስትገኝ እርሷን የተሻለ ለማድረግ የሚሰራው ሥራ አኩሪ ነው።
ለምሳሌ የድሮ የውጊያ አውሮፕላኖችን ከዘመ ናዊዎቹ ጋር በማቀናጀት አዲስ ነገር ለመፍጠርና አቅማቸውን ለማሳደግ በሚሰሩት ሥራ ብዙ አውሮፕላኖችን አቅማቸውን አሻሽለው ሠርተው አብርረው ተጠቅመዋል። ይህ ደግሞ ከተልኳቸው ጎን ለጎን ምን አይነት አቅም እየተፈጠረ እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የጁንታውን ኃይል ለማስወገድ በተመራው የሕግ ማስከበር ጦርነት ላይ መከላከያ ከፍተኛ የሆነ የቅንጅት ሥራን ሠርቶ አሳይቶናል፤ እንደው እንደ ንዑስ ኮሚቴ ቅንጅቱን እንዴት አገኙት? ሪፎርሙስ ይህንን መሰል ቅንጅት እንዲፈጠር ያበረከተውን አስተዋጽዖ እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ዼጥሮስ፦ መከላከያ በዚህ መልኩ ራሱን ሪፎርም አድርጎ ሲዘጋጅ የነበረው እንዲህ አይነት ክህደት ይፈፀምብኛል ብሎ አይደለም። ነገር ግን ከውስጥም ይነሳ ከውጭ ችግሮች ሲፈጠሩ ተቀናጅቶ መሥራቱ ከምንም በላይ ውጤታማ እንደሚያደርግ ግን ቀድሞ ተረድቶ ነበር።
በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅትም እግረኛው ትልቅ ሥራ ሲሰራ አየር ኃይሉ ደግሞ ሽፋን ሲሰጥ የነበረ ከመሆኑ አንፃር ከፍተኛ የሆነ የቅንጅት ሥራ ተሠርቷል። በተለይም ደግሞ አየር ኃይሉ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ሥነ ምግባር የታነፀ በመሆኑ ጁንታው ቡድን ሆን ብሎ ንፁሃንን መሸሸጊያ ሲያደርግ ቦምብ፣ መሣሪያ የታጠቀ ቢሆንም ንፁሃን እንዳይጎዱ በማለት የታጠቀውን መሣሪያ ሳይጥል ወደኋላው ሲመለስ ያየንበት ሁኔታ ነበር፤ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ መረጃ አቀባዩ እግረኛው ስለሆነ በመካከላቸው ከፍተኛ የሆነ መናበብ ስለነበር ነው። በመሆኑም ንፁሃን ሳይጎዱ የሚከፈለው ዋጋም ከሚገኘው ውጤት አንፃር በሚገባ እንዲታይና እንዲገመገም እየሆነ ስለተመራ ሥራው በጣም ቅንጅታዊ ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ሊመጣ ችሏል።
እዚህ ላይ ወደ ሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ከመገባቱ በፊት በተለይም ጁንታው ቡድን የነበረው አረዳድ 80 በመቶ መሣሪያ እኛ ጋር ነው፤ ተቆጣጥረነዋል የሚልና በምንም መልኩ አንሸነፍም ብለው ነበር፤ ነገር ግን መሣሪያ ብቻውን ውጤታማ የማያደርግ መሆኑን ከዚህ ይልቅ መደፈርን የሚጠላ ለአላማው ሟች የሆነን ሠራዊት መገንባት ከፍተኛ የሆነ አቅም እንደሚፈጥር መከላከያችን አሳይቷል። ለዚህ ደግሞ ዋናው አጋዣቸው ሪፎርሙና ይህንን ተከትሎ በተሰራው ሰፊ የማብቃት ሥራ ነው የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ እንድ አገር መከላከያ ሠራዊታችን በጁንታው ቡድን ላይ የተቀናጀው ድል ከፍ ያለ ነው፤ ነገር ግን አሁንም ቢሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የታጠቁም ያልታጠቁም ኃይሎች ሕዝቡን እያሸበሩ፣ እየገደሉ፣ እያፈናቀሉ ያሉበት ሁኔታ ነውና ያለው እንደው ፊቱን ወደነዚህ አካባቢዎች መልሶ ሕዝቡን ከሥጋት ነፃ ለማድረግ ያለው ዝግጁነት ምን መልክ አለው?
አቶ ዼጥሮስ፦ በአገር ውስጥ በየክልሉ ጎጡና መንደሮች ውስጥ የሚከሰቱትን የፀጥታ ችግሮች የማረጋጋትና ሰላምን የማፍፈን ሃላፊነት በዋናነት የህዝብ ነው። ከህዝብ ጋር የሚሠራ ደግሞ ፖሊስ አለ፤ ፖሊስን የሚያግዙ ደግሞ የተለያዩ አደረጃጀቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ መከላከያ ጋር የምንመጣው ከነዚህ ሃይሎች አቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም ነው። አሁን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ እየተስተዋለ ያለውን ችግር የምንፈታው በሃይል ብቻ ነው የሚል እምነትም የለኝም።
ምክንያቱም በተለያየዩ የፖለቲካ አመለካከትና ከግል ፍላጎት በመነሳት ታጥቆ አልያም ሳይታጠቅም ለህዝቡ አጀንዳ እየሰጠ የሚያተራምስ፣ የውጭና ሌሎች በኢትዮጵያ ላይ የተለየ ፍላጎት ያላቸውን አካላት አጀንዳ ይዞ ከሚዞር በቀር ከውጭ መጥቶ እዚህ አገር ውስጥ ገብቶ የእኛን ሰላም ለማተራመስ የሚችል ኃይል አለም ብዬ አላምንም።
በመሆኑም በአካባቢያችን ለሚነሳ ችግር መጀመሪያ ተጎጂውም ህዝቡ ስለሆነ በተባበረ ክንድ ራሱን መከላከልና መጠበቅ ያለበትም ራሱ ነው። በዚህም ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ያስፈልጋል ፣ ባህልዊ አደረጃጀቶችን መጠቀም የግድ ይሆናል።
ነገር ግን አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእኛ ያልሆነ እስከ ዛሬም ሰምተነውም አይተነውም በማናውቀው መልኩ ሰው ሰውን ኢ- ሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ህይወት ሲነጥቅ እየተመለከትን ነው፤ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ የእኛ ባህል፣ ሃይማኖታዊ አስተምሯችንን የማያንፀባርቁ በፍፁምም የእኛ ያልሆኑ ናቸው።
እኛ የኖርነው እንኳን ለሰው ለዱር አውሬ አዝነን ከቻልን አላምደን አብረን እየበላን እየጠጣን ነው። ይህ ጭካኔ እንዲመጣ ያደረጉ እጆች ደግሞ እዚህም እዚያም አሉ። የማይሆን ጥቅም እንሰጣለን እያሉ እየሰጡም መሣሪያ ገዝተው እያስታጠቁ የሚሰሩ ሃይሎች አሉ።
ኢትዮጵያውያን የትኛውንም ሃይማኖት ተከታይ ብንሆን አስተምርዎቻችን የሚጀምሩት አትግደል ከሚለው ነውና ለእነዚህ ሃይላት ጆሮ ሳንሰጥ አጥፊዎችንም ሳንሸሽግ ለራሳቸን ሰላም ዘብ መቆም አለብን።
በዚህም ብዙ ዓመታትን ተቻችለን ተፈቃቅረን ኖረናል በኑሮ ሂደት ውስጥ እንኳን በደምፍላት የሰው ህይወት የጠፋበት ሰው እራሱ ከሚፀፀተው አልፎ ችግሩ ወደቤተሰብና ዘመድ አዝማድ እንዳይሄድ በሽምግልና የምንፈታበት የዳበረ ባህልና ወግም ያለን ሕዝቦች ነው አሁን አሁን እያየን ያለነው ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ውጭ የሆነ እጅግ ዘግናኝና አሳፋሪ ተግባር ነው።
እንደ እኔ ለዚህ ዋናው ምክንያት በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ያለማቋረጥ የተዘራ የጥላቻ ዘር ነውና ይህንን ከጁንታው ጋር አብረን ቀብረን በሚያምርብንና አብሮን በኖረው ባህልና እሴታችን ልጆቻችንን መቅረፅ ይገባናል።
ከዚህ አንፃር መከላከያው ወደ እነዚህ ሁሉ ቦታዎች ተጉዞና ተቆጣጥሮ ሰላም ያስከብራል የሚል እምነት ባይኖረኝም አንዳንድ ጊዜ ከአካባቢው አቅም በላይ ከሆነ ግን መከላከያው እየገባ ችግሮቹን እየፈታ ህይወቱን እየሰጠ የቆየበት ሁኔታ አለ። ወደፊትም ይኸው ሁኔታ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፦ ለምሳሌ መተከል ላይ እየታየና እየተሰማ ያለው ጭፍጨፋ በአካባቢው ሕብረተሰብና በፖሊስ ኃይል ብቻ ይፈታል? ወደዚህ አካባቢስ መከላከያ ቢሄድ ከግዴታው ውጭ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ዼጥሮስ፦ የሆነ ክልል ላይ የሆኑ ሰዎች ተጋጭተዋል ከተባለ መከላከያ ጠመንጃ ይዞ እንዲሄድ አይደረግም፤ መጀመሪያ አካባቢው ላይ ያሉ የፀጥታ አካላት ችግሩን ይፈታሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው፤ በአካባቢው ያለው የመንግሥት አመራርም ተገቢውን ትዕዛዝ ሰጥቶ ህዝቡን አወያይቶ ያስታርቃል፣ ያግባባል ተብሎ ነው የሚታሰበውና ይህ ዕድል ተሰጥቶ ግን በታሰበው ልክ በቀላሉ መፍታት ካልተቻለና ክልሉ ለመከላከያ ጥሪ ሲያቀርብ መከላከያ ወደ ስፍርው እንዲሄድ ይደረጋል እንጂ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚዘምት ሃይልም አይደለም። አደረጃጀቱም ይህንን አይፈቅድም።
ነገር ግን ጥሪ ቀርቦ በትክክለኛው ሰው ትክክለኛው ትዕዛዝ ቀርቦ መከላከያ ከገባ በኋላ ላለው ትልቅ ሃላፊነት ወስዶ ተልዕኮውን በብቃት ይፈጽማል። መፍትሄም ይሰጣል። አሁን መተከል ላይ ያለው ሁኔታም ይህ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ክልሎች ውስጣቸው ላይ ችግር ሊኖር፣ የጥፋት ሃይሎችም በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥሩት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ፣ በሂደቱ ውስጥም ጠላትና ወዳጅን የመለየት ሁኔታውም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በዚህ ወቅት ህዝቡም ይህ ጠላቴ ነው ብሎ እስከሚለየው ድረስ ለመከላከያም ፈታኝ ነው።
በመሆኑም መከላከያ በህጋዊ መንገድ እንዲገባ ከታዘዘ በኋላ ራሱ ህብረተሰቡ የአካባቢው አመራሮች ከመከላከያ ጋር መቀናጀት ይኖርባቸዋል። አሁን ባለው ሁኔታ በመተከልም ይሁን በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ እየታዩ ያሉ ለውጦችም አሉ።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ ከሚመሩት ቋሚ ኮሚቴ ባሻገር የኢ.ፌ. ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልም ነዎትና እንደው ከመተከል ጀምሮ በኦሮሚያ፣ በደቡብ በአማራ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች እየተፈፀሙ ላሉ ሕገ ወጥ ተግባራት እንዲሁም የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ዘላቂ መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ዼጥሮስ፦ መጀመሪያ ጊዜያዊና ወቅታዊው ምላሽ ከተሰጠ በኋላ ለዘለቄታዊ መፍትሄው ማሰብ አስፈላጊና ጎን ለጎንም መሄድ ያለበት ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እነዚህ ችግሮች እንደተፈጠሩ አጀንዳ ይዞ በስፋት ተወያይቷል፤ ለህዝቡም ግልጽ ለማድረግ ሞክሯል። መጨረሻ ላይም በተለይም ከጁንታው ቡድን ችግር ጋርም ተያይዞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን እስከማውጣትም ደርሷል።
አዋጁን ሲያውጅም ያንን የሚከታተል መርማሪ ቦርድም አብሮ አቋቁሟል፤ ቦርዱም ምክር ቤቱን በመወከል ችግሮቹ ወደተከሰቱባቸው ቦታዎች በአካል እየሄደ ምን ዓይነት መፍትሄ እየተሰጠ ነው? ሰብዓዊ መብቶች ተጠብቀዋል ወይ? ለህዝቡ እንደ ህክምናና ምግብ ያሉ ድጋፎች እየቀረቡ ነው? የሚሉትንና ሌሎችንም ሁኔታዎች እየተከታተሉ ሪፖርቶችን ያቀርባሉ። ከዚህ አንፃር የምክር ቤቱ ሚና ቀላል አልነበረም።
በመተከል ላይም ቢሆን ሌላ አዋጅ አናወጣም። ቀደም ብሎ የወጣው አዋጅ በአንቀጽ ሦስት ላይ በዝርዝር ያስቀመጣቸው እንዲሁም ማስፋትና ማጥበብ ሲፈለግም የሚቻልበት ሁኔታ ስላለ በዚሁ አዋጅ መሰረት በክልሉ ያለው ሁኔታ ቁጥጥር እንዲደረግበት ምክር ቤቱ ፈቅዷል።
ከዚህ ከዚህ አንፃር ስናየው ምክር ቤቱ እያደረገ ያለው ወቅታዊውን ችግር ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲፈታ የማድረግ ጎን ለጎንም የነበሩትን ሁኔታዎች አጥንቶ ለምክር ቤቱ የሚያቀርብ አደረጃጀት እንዲፈጠር የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ ፀድቋል።
በዛ መሰረትም በተለይም መተከልና ቤኒሻንጉልን በተመለከተ ሰዎች ተመድበው ጥናቶች አድርገው በዘላቂነት እንዴት መፈታት ይችላል የሚለውን የመፍትሄ ሀሳብ ይዘው ይመጣሉ ተብሎ ይታሰባል።
ይህም ቢሆን ግን የምክር ቤቱ ጥረት ብቻውን ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል ወይም ያመጣል ተብሎ አይታሰብም። ከዛ ይልቅ ሰላም ከራስ የሚጀምር መሆኑን ማወቅና ከራስ ጀምሮ ለቤተሰብ አልፎም ለጎረቤት ሰላም መስጠት ለአገርም የሚተርፍ በመሆኑ ህብረተሰቡ በዚህ ልክ እራሱን ለሰላም ማስገዛት ይገባል።
በሌላ በኩልም ህብረተሰቡ ባህላዊ እሴቶቹን በመጠቀም የእርቅና የመግባባት ሥርዓቱን እንደገና ወደነበረበት በመመለስ አብሮነቱን የሚያዳብርበትን መንገድ በማመቻቸት ሃይማኖት ተቋማትም አስተምርዎቻቸውን በመፈተሽ በተለይም ወጣቱ በሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚያድግበትን ሁኔታ ማምጣት፣ ትምህርት ቤቶች ከቀለም ትምህርት ባሻገር ለተማሪዎች ሥነ ምግባር ከፍተኛ የሆነ ትኩረት መስጠት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። መገናኛ ብዙሃኑም፣ የማህበራዊ ሚዲያውም ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ የህዝብን ሰላም ሊያጎሉ የሚችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት ከቻሉ በጠቅላላው እንደ ኢትዮጵያዊ መለያየትን ከተጠየፍን አገራችንን ወደፊት ማራመድ እንችላለን።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ከፊታችን ትልቅ እንደ አገርም ብዙ የምንጠብቅበት ምርጫ አለና፤ እሱን ተከትሎም የአገር ሰላምና ፀጥታ እንዳይናጋ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
አቶ ዼጥሮስ፦ ትክክል ነው፤ ከፊታችን ለሰላማችን ትልቅ አስተዋጽዖ የሚያደርገው ምርጫ እየተቃረበ ነው። እንደ ህዝብና አገር ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ አጠናቅቀን አገራችንን ማስቀጠል ያለብን ከመሆኑ አንፃር ህዝቡ በሰላምና ምንም አይነት እንቅፋት ሳይገጥመው ይወክለኛል የሚለውን አካል የሚመርጥበትን አግባብ አሁን ያለው መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታዎችን ከወዲሁ መፍጠር ይኖርባቸዋል።
በእርግጥ በመንግሥት በኩል ምርጫውን ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ዝግጁነት እንዳለ እያየን ከመሆኑም በላይ መንግሥት ከሱ የሚጠበቅበትን ምርጫ ቦርድን የማጠናከር የተለያዩ ሕጎችን የማውጣት አሠራሮችን የማዘመን የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ሥራዎች በጉልህ ሁኔታ እየሠራ በመሆኑ ይህንን እድል ሁሉም ተጠቅሞ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ምርጫችንን መርጠን ላሸነፈው ፓርቲ ስልጣኑን የምናስተላልፍበት ሥርዓት መፍጠር ከቻልን የሰላማችን ዋጋ ይጨምራል።
ኢትዮጵያውያን በዚህ ደረጃ ሰላማችንን አረጋግጠን አንድነታችንን ጠብቀንና ጠንክረን መውጣታችን ለምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ተወካይ ሆነን ለመቆም በዴሞክራሲም ተምሳሌት ልንሆን የማንችልበት ምክንያት የለም። ይህ ደግሞ ስማችንንም ታሪካችንንም የሚቀይር በመሆኑ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላሙ ዘብ መቆም ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ በክልል ደረጃ የሚዋቀሩ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የሚታጠቁት መሣሪያ፣ የሚሰለጥኑበት መንገድና የሚሰጣቸው ስልጠና በራሱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አይነት መሆኑ ችግር እያመጣ ነው መስተካከል አለበት የሚሉ ሰዎች አሉና፤ ከዚህ አንፃር እንደ ንዑስ ኮሚቴ ያያችሁበት ምልከታ ምን ይመስላል?
አቶ ዼጥሮስ፦ በእርግጥ የፀጥታ ኃይል አደረጃጀት የፖሊሲ ጉዳይ ነው የሚሆነው፤ ከሕገ መንግሥቱ ብንነሳ እንኳን ለፌደራል መንግሥቱ እንዲሁም ለክልሎች የሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት አለ፤ የፌደራሉ መንግሥት መከላከያን የማቋቋም፣ በዛም አገርን የመጠበቅና የመከላከል፣ ከውጭ አገራት ጋር የሚኖርን አገራዊ ግንኙነት መምራት፣ የወንጀል ጉዳዮችን በባለቤትነት ሕግ የማውጣትና ሌሎችም ኃላፊነቶች አሉበት።
በዚህ ልክ ለክልሎችም ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸው ስልጣንና ሃላፊነቶች አሉ፤ ከዚህም መካከል የራሳቸውን ሰላምና ፀጥታ ይጠብቃሉ። ለዛም የሚሆን የፖሊስ ኃይል ያደራጃሉ ይላል። እንግዲህ ሰዎች እንደየ ሁኔታው የተለያየ ትርጉም ሰጥተውት ሊሆን ይችላል እንጂ ሕገ መንግሥቱ ክልሎች ልዩ ሃይል ያደራጃሉ የሚል አልጻፈም። ዝርዝር ሕጎችም ላይ ቢሆን በዚህ ደረጃ መከላከያን የሚተካ አደረጃጀት ይኖራል የሚል አላየንም።
በክልሎች ላይ የተሻለ ፖሊስ ህብረተሰቡን የሚጠብቅ መኖሩ ክፋት ነው ብዬ አላስብም። ነገር ግን ደግሞ ሲቀረጽ ሌሎች የመከላከያ ተልዕኮን ጭምር በሚይዝ ደረጃና አመለካከት ከሆነ ስህተቱ የሚነሳው እዛ ጋር ነው። መከላከያን የሚተካ ሃይል ክልሎች እንዲያደራጁ ከዛም ትህነግ እንዳደረገችው በልዩ ሃይል መከላከያን የሚወጉ አካላት እንዲዘጋጁ ሕገ መንግሥቱ አልፈቀደም። በመሆኑም ይህንን መፈተሽ እንደገና ማየት ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ልዩ ሃይል በየክልሉ በመኖሩ ምን ተጠቀምን? ምንስ ተጎዳን? የሚለውን መንግሥት ቆም ብሎ ማየትና ማሰብ አለበት። በዚህም ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ አላማው መከላከያን ማጠናከር ከሆነ በዛ መንገድ የክልልን የፖሊስ ሃይል የሚያጠናክር የሚያደራጅም ከሆነ እንደዛው በተሰጠው ስልጣንና ገደብ ልክ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ሊቀረጽ ይገባዋል።
አሁን ባለንበት ሁኔታ የልዩ ኃይልን ጥቅምና ጉዳት ለመለየት እድል አግኝተናል። ይህንን መነሻ በማድረግም መንግሥት የፖሊሲ ጉዳዩንም ሌላውንም እንዴት አድርጌ መስመር ላስይዘው የሚለው ላይ መመካከር በተለይም ኢንዶክትሪኔሽኑ ላይ ያለ ችግሮችንም ማረም፤ አደረጃጀቱንም ለአገር በሚበጅ መልኩ በጥናት ላይ ተመሰርቶ መቃኘት ያስፈልገዋል።
አዲስ ዘመን፦ የህወሓት ጁንታ ቡድን በሕግ ማስከበር ዘመቻው መወገዱ እንደ አገር ለሚኖረን ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት የሚኖረውን ድርሻ እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ዼጥሮስ፦ ጀንታው ቡድን በዚህ አገር ታሪክ ላይ ተወቃሽ የሚያደርገውን አፀያፊ ተግባር ፈጽሞ አልፏል። ከዚህ በኋላ የሥጋት ምንጭም ሆኖ የሚቀጥልበት እድሉና አጋጣሚው የለውም። ምክንያቱም ህዝቡን ነበር እንደ ጥላ ሲጠቀምበት እኔን መንካት ማለት ትግራይን መንካት ነው እያለ ብዙ እድል አምክኗል፤ አሁን ደግሞ ትህነግ ማለት የትግራይ ህዝብ አለመሆኑን ሁላችንም ዓለምም ተረድቷ፤ ተገንዝቧል። የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ለዚያውም በአገሩ ጉዳይ የማይደራደር ኩሩ ህዝብ ነው፤ በነገራቸን ላይ እዛ ትግራይ ላይ ያሉትን ብቻ እያልኩ አይደለም፤ እዚህም መካከላችን ሆነው ሥራ ወዳዶች ሠርተው ለመለወጥ የሚጥሩትን ጭምር እንጂ።
ጁንታው ቡድን ባደራጀው ልዩ ኃይል ውስጥም ሆነው እኩይ ተግባሩን የማይቀበሉ ሰዎች እንደነበሩ እናውቃለን። እንግዲህ ትምህርት ከጥሩም ከመጥፎውም በመሆኑ አሁን ትግራይ ላይ በሆነው ነገር ክልሎች የሚማሩት ነገር የሚኖር ይመስለኛል። እንደዚህ አይነት ተግባር ዳግሞ የትም ቦታ ላይ ይደገማል ብለን አናስብም፣ እንደዚህ አይነት ፈተናም አንጠብቅም። ነገር ግን አሁንም ለዚህ ዓይነቱ ክህደት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ከወዲሁ ማረም ደግሞ አለበት። በመሆኑም ለቀጣዩ ዘላቂ ሰላማችን ከመጥፎ ነገሩ ተምረናል ብዬ አስባለሁ።
የትህነግ ቡድን በፈፀመው ሸፍጥ ብዙ ዋጋ ከፍለናል፤ ከዛም መማር ያለብንን እንማራለን። ነገር ግን አሁን ክልሉ እንዲያገግም ባልፈለጉት መልኩ ለጉዳት የተዳረጉ ሰዎች ተገቢው ድጋፍ ሊደረግላቸውና በዘለቄታዊነት ሊቋቋሙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊመቻችላቸው ይገባ፤ ይህም እየተከናወነ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ዼጥሮስ፦ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ጥር 26/2013