ኸይረናስ አብደላ (ሳይኮሎጂስት)
ክፍል አንድ
በብዙ ሰዎች ዘንድ ኦቲዝምን እና አእምሮ እድገት ውስንነትን በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይ አድርጎ የመመልከት ልማድ ይስተዋላል። ይህ አመለካከት ደግሞ ጎላ ብሎ የሚታየው መናገር የማይችሉ (ቃል አልባ) (non- verbal autistic) ልጆች እና አዋቂዎች ላይ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላው የተሳሳተ ግንዛቤ የዚህ ችግር ተጠቂ የሆኑ ሕፃናት እና አዋቂዎች እስከ መጨረሻው ባሉበት እንደሚቆዩ እና በመማር መለወጥ አይችሉም የሚለው እሳቤ ነው።
የአእምሮ እድገት ውስንነት በበፊት ስያሜው `የአእምሮ ዝግመት`ያላቸው የሚባሉት የአእምሮ ብስለት ውጤታቸው (Intelligence quotient score) ሰባ እና ከሰባ ያነሰ ሲሆን እንዲሁም እራስን ችሎ ለመኖር አስፈላጊ ናቸው ከሚባሉት ዋና ዋና አስሩ ክህሎቶች መካከል ቢያንስ ሁለቱን ማድረግ ሲሳናቸው ነው። ለአእምሮ ብስለት እንደ መለኪያ ከምንጠቀማቸው ውስጥ (የማመዛዘን ችሎታ፤ ችግር የመፍታት አቅም፤ እቅድ ማውጣት፤ ውሳኔ መስጠት እና መማር) የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። የአእምሮ ብስለት መለኪያ ጥያቄዎችም ከላይ የጠቀስናቸውን መመዘኛዎችን መሰረት አድርጎ የሚዘጋጁ ናቸው።
እራስን ችሎ ለመኖር አስፈላጊ ክህሎት (Adaptive functioning) ደግሞ ሁለተኛው መመዘኛ ሲሆን እነዚህ ክህሎቶች አንድ ሰው በሕይወት ሲኖር እራሱን ችሎ (ከሌላ ሰው ድጋፍ ሳያገኝ) ያደርጋቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ሲሆኑ፤ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ዋና ዋናዎቹ አስር ናቸው፤ ማህበራዊ ክህሎት፤ ተግባቦት፤እራስን መንከባከብ (እራስን ችሎ መመገብ፤ ፀጉርን ማበጠር፤ ልብስ መልበስ፤ ምግብ ማብሰል፤ ገንዘብን ማስተዳደር) ጤና እና ደህንነትን መጠበቅ፤ የቤት ውስጥ ሥራ መከወን (ቤት መጠበቅ እና ምግብ ማዘጋጀት…)፤ የማህበረሰብ ሀብቶችን መጠቀም፤ እራስን መምራት፤ የመማር ክህሎት ሥራ እና የመዝናናት ፍላጎትን ያካትታል።
በሥነ-ልቦናው ዘርፍ ለመለያ (Diagnosis) የሚጠቀሙበት (DSM 5) እንዳስቀመጠው አንድ ሰው የአእምሮ እድገት ወስንነት አለበት ለመባል (Diagnose) ለመደረግ ሁለት መመዘኛዎችን ያስቀመጠ ሲሆን የመጀመሪያው የአእምሮ ብስለትን በመለካት ሲሆን እነዚህ ጥያቄዎች ዓለምአቀፋዊ (Standardized) ናቸው።
ከላይ እንደተገለፀው በዚህ መመዘኛ መሰረት የአእምሮ ብስለት ውጤታቸው ሰባ እና ከ ሰባ በታች የሆኑ እና ከላይ ከተጠቀሱት እራስን ችሎ ለመኖር አስፈላጊ ናቸው ከተባሉት ክህሎቶች መካከል ቢያንስ ሁለቱን መከወን ካልቻሉ ነው።
በአማካይ የሰው ልጅ የአእምሮ ብስለት (Intelligence quotient) 100 ሲሆን ከ 85-115 መካከል ባለው ወስጥ አብዛኛው ሰው ይገኛል፤ 70 እና ከ 70 በታች ያሉት የአእምሮ እድገት ውስንነት ሲኖራቸው፤ ሌሎቹ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው (Gifted) የሚባሉት ሲሆኑ እነዚህ ደግሞ የአእምሮ ብስለት ውጤታቸው ከ115 በላይ ያሉ ናቸው።
የተቀሩት የአእምሮ ብስለት ውጤታቸው በ 70 እና በ 85 መካከል ያሉት (Border line) የሚባሉት ሲሆኑ ችግራቸው እምብዛም አይደለም ፤ እነዚህ የሁለቱም ማለትም የጤናማዎቹን እና የአእምሮ እድገት ውስንነት ያላቸውን ምልክት ያሳያሉ::
የአእምሮ እድገት ውስንነት በአጠቃላይ ሊከሰት የሚችለው ከ 18 ዓመት በታች ባሉ ታዳጊዎች ላይ ነው። ከአጠቃላይ ሕዝቡ 1 በመቶ የሚሆኑት የአእምሮ እድገት ውስንነት ያላቸው ሲሆኑ ከእነዚህ 1 በመቶ ከሚሆኑት መካከል 10 በመቶዎቹ በተጓዳኝነት ኦቲዝም አብሯቸው ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ ኦቲዝም ያላቸው ብዙ ልጆች ላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት ይስተዋላል።
የበሽታዎች ቁጥጥር ማእከል (Centers for Disease Control; CDC) እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ 2008 ሪፖርቱ እንዳስቀመጠው በአጠቃላይ ካሉት ኦትስቲክ ልጆች 38 በመቶ የሚሆኑት በተጓዳኝነት የአእምሮ እድገት ውስንነት ይገኛል። ወንድ ሆነው ኦቲዝም ያላቸው ልጆች ከሴት ኦቲዝም ካላቸው ጋር ሲነፃፀሩ ሴት ኦትስቲክ ልጆች ላይ በብዛት በተጓዳኝነት የአእምሮ እድገት ውስንነት ይስተዋላል።
የዚሁ ተቋም ጥናት እንዳሳየው 46 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ኦትስቲክ ሴቶች ላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት በተጓዳኝነት ሲኖር 37 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ወንድ ኦትስቲክ ልጆች ላይ ደግሞ የአእምሮ እድገት ውስንነት በተጓዳኝነት ይገኛል። የኦቲዝም ስርጭት ከሴቶች ወንዶች ላይ በአምስት እጥፍ እንደሚልቅ ጥናቱ አሳይቷል።
በአጠቃላይ ተቋሙ እንደገለፀው የኦቲዝም ስርጭት ከፍ ብሎ የሚስተዋለው በአማካይ የብዙ ታዳጊ ልጆች የአእምሮ ብስለት ውጤት (Intelligence quotient) ከ 70 በላይ በሆነባቸው ሀገራት ላይ ነው።
የዘርፉ ባለሙያዎች አሁንም ድረስ በኦቲዝም እና በአእምሮ እድገት ውስንነት የጋራ ባህርይ ላይ ጥናታቸውን የቀጠሉ ሲሆን አንዳንድ ሥነ-ባህርይያዊ እክሎች (Fragile X, Rett Syndrome, Tuberous Sclerosis, Down Syndrome, phenylketonuria, Angelman…) የመሳሰሉ ችግሮች ከከፍተኛ የአእምሮ እድገት ውስንነት እና የኦቲዝም መከሰት ጋር ያያይዙታል።
ለጊዜው ምክንያታዊ ተያያዥነታቸውን ወደ ጎን ትተን ስንመለከት ግን የሁለቱም ተጠቂዎች የጋራ የሆኑ ተግዳሮቶች አሏችው በተለይም ማህበራዊ እና የተግባቦት ክህሎቶች ላይ፤ እነዚህ ክህሎቶች ደግሞ ኦቲዝምን ለመለየት (Diagnos) ለማድረግ ዋነኛ የሚባሉ ናቸው።
ኦትስቲክ ተብለው በተለዩ (Diagnos) በተደረጉ ልጆች ላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት በተጨማሪ መኖሩን ማረጋገጥ የግል ትምህርት ፕሮግራም (Individualized Education Program; IEP) ለማዘጋጀት ወሳኝ ነው፤ ይህም ተገቢውን መማር እና እራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርጋቸውን ድጋፍ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ለምሳሌ፡- ከሌሎች እድሜ እኩዮቻቸው ጋር ተካተው እየተማሩ ባሉበት ሁኔታ ሲሆን፤ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያላቸው ልጆችን ለማስተማር መደጋገም ያስፈልጋል።
በተለይ ደግሞ ላቅ ያሉ የአእምሮ ብስለትን የሚጠይቁ ተግባራት ላይ ወሳኝ ነው። እነዚህ ልጆች የከፍተኛ ትምህርታቸውን ቢጨርሱም እንኳን የሚኖሯቸው የሥራ አማራጮች በቀላሉ መማር ከሚችሉት ጋር ሲነፃፀር እምብዛም ነው።
ቀጣዩን ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት ይዘን እንቀርባለን።
አዲስ ዘመን ጥር 25/2013