ብስለት
ሀገር ማለት ሰው ነው። ሰው ነው ሀገር ማለት። የሚል አበባል በጆሮዬ እየሰማሁ መኖር ከጀመርኩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ሀገር ሰው ከሆነ ያለሰው ሀገር ካልኖረ ኢትዮጵያ የማን ሀገር ናት? የማናት እማማ ኢትዮጵያ? ሰው ማለት ሀገር ከሆነ ሰው ለሀገሩ ሠርቶ ለእናቱ ታዞ ሀገርን ቤቱ አድርጎ መኖር ነው የሀገር ሰውነት ልኩ ከተባለ የዚህች ሀገር ልጅ መሆን ሀገርን ሀገር የሚያሰኛት ሰው ውስጧ እንዳይኖር ለምን ተፈረደባት? ለምን ይሆን የልጆቿ አንዳንድ ጡብ ተገንብቶ ውቡን የኢትዮጵያ አልፍኝ መሠራት ያቃተው እያልኩ አስባለሁ።
ለምን ይሆን ሰው ማለት ሀገር ሰው ደግሞ ፍጥረቱ ከእናት በሆነባት ምድር የእናት እንባ እንዳይደርቅ ችግርን በችግር ላይ መከፋትን በመከፋት ላይ ደራርበን ደራረተን ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ደስታ የምናጠፋ፤ የኛ የሆነውን የሥራ ድርሻ ወደ ላይ በመግፋት መሰረቱ ይናጋ ዘንድ የማድረጋችንስ ምስጢር ምንድነው። የሰው መሆን ውሉ ማሰሪያው የፍቅር ገመድ መቋጠሪያው በአረንጋዴ ቀይ ብጫ ቀለማት ህብር የተገመደበት ሆኖ ሳለ ቀዩን ከቢጫው ቢጫውን ከአረንጓዴው በመለያየት የእያንዳንዷ ችግር መነሻ ምክንያት መሆናችን ሳያንስ ጣታችንን በሌሎች ላይ መቀሰር የሚመለከተው አካል ልብ ይበል ማለት ያበዛንበት ምክንያትስ ለምን ይሆን ነው ጥያቄዬ?
ሀገር የልጆቿ ቤት፣ ልጆቿ ደግሞ የእርሷ ውበት ከሆኑ ኃላፊነትን በመሸሽ ወይም ለመወጣት ባለመፈለግ ሰበብ ይህን የሚመለከተው አካል ይመልስ የሚሉት ቢህል ከየት ይሆን የመጣው። የሀገር ሰው መሆንን ልኬት ወደ ጎን ትቶ መንግሥት የሾመው ሚኒስትር እንኳን ይህ የመንግሥት ሥራ ነው እያለ ኃላፊነቱን በይደር ሲያቆየው መመልከት ህመም በሆነባት ሀገር መንግሥት ማነው? ንገሩኝ እስኪ ማነው መንግሥት? ኃላፊነት ተሰጥቶት የህዝብ እንደራሴ እንደልቤ እንደሃሳቤ ብሎ ወደፊት ያስቀመጠው ሰው ይህ የመንግሥት ሥራ ነው ካለ፤ ይመራናል ብለን እላይ ያስቀመጥነው ሌላ መሪ ከሻተ ማነው ሀገር ማለት ሰው መሆኑን የሚያጠይቀን።
ከማህበረሰቡ እንጀምር። ከግቢው ጠራርጎ ያወጣወን ቆሻሻ ከአጥር ጊቢው ወጪ አዝረክረኮ የሚመለከተው አካል መጥቶ ያንን ለሱም ይሁን ለልጆቹ ጤና ጠንቅ የሆነ ቆሻሻ እንዲያነሳለት ይጠብቃል። በሰፈር ውስጥ ቤት ለማሠራት ያሰበ ሰው የአካባቢው ነዋሪ የሚገለገልበት መንገድ የግንባታ ቁሳቁስ ማስቀመጫ አድርጎት፣ መተላለፊያ ጠፍቶ ህብረተሰቡ ከመቸገሩም በላይ መንገዱ ጉዳት ሲደርስበት የሚመለከተው አካል መጥቶ እንዲጠግንለት ይጠብቃል። ለአሰሱም ለገሰሱም የራሳችንን ኃላፊነት ሳንወጣ ሥራዎችን በአጠቃላይ ለሚመለከተው አካል አሳልፈን ከሰጠን ሀገር የሰው ናት ሀገር የህዝቦች ናት ለማለት የሚያስችል ድፍረትን ከየት ይሆን የምናገኘው።
እንቀጥል ከታች በቅርበት ህብረተሰቡን ለማገልገል የተመሰረቱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማለትም ወረዳዎች ውስጥ አገልግሎት በተገቢው መንገድ የማገኘቱ ነገር ጭንቅ ሆኖ ይታያል። ምን ይሻላል የሚል መፍትሔ ስጠይቅ እስኪ ለሚመለከተው አካል እናመልክት ይሆናል መልሱ፤ ለሥራው ይመጥናል ቦታው ላይ ተቀምጦ ዜጎችን ያገለግላል ተብሎ ዜጎች ከሚከፍሉት ግብር ደሞዙን እየተቀበለ እንዴት ነው እሱ የተቀመጠበት ወንበር ከልኩ በላይ ሆኖ ለሱ ሥራ ለሚመለከተው አካል ስሞታ የሚኬደው? የህግ አገልግሎት ለማግኘት እንደው ፍርድ ቤት ከመሄድ ይልቅ ጥቃቴን ውጬው ዝም ልበል በሚሉ ዜጎች የተሞላች ሀገር፣ ሰው ደግሞ ለሰው መድሃኒቱ ነው በተባለላት ሃገር፣ ሰው ለሰው ተሳስሮ በሰውኛ መስተጋብር ተደጋግፎ ታላቋን ኢትዮጵያ በሚያነሳባት፤ በዚህች ቅድስት ምድር ሁሉም ኃለፊነቱን እየገፋ የመንግሥት ጫንቃ ላይ መጣሉ ከታች የተጀመረው ብልሹ አሠራር መሆኑ እሙን ነው። ሆድ የባሰው ህብረተሰብ ብሶትና ዕንባ ብቻ ሆኖ ቀለቡ ምን ሀገር አለ ሲል ሀገር ማለት ሰው በሆነባት እናት ሃገር፤ ምን ሰው አላት፤ ኦና ቤት ነው እየኖርን ያለነው የሚሉት ብሂል በጣም ተንሰራፍቶ ሰው አልባ ምድር ሊያሰኛት የተዘጋጀበት ወቅት ላይ መድረሳችን ለምን ይሆን እያልኩ አስባለሁ።
የመንግሥት ሠራተኛ ተብሎ ህዝብን ለማገልገል የተቀመጠ በተለያየ የሙያ ዘርፍ ሀገር ከፍላበት ያስተማረችው ማህበረሰብ ወንበሩ ይሁን ሌላ በትእቢት ተወጥሮ ኃለፊነትን ለመወጣት ትውውቅን የሚያስቀድም አገልግሎት ለመስጠት በገዛ ሀገሩ በገዛ ወገኑ ቤት አንዱ ልጅ አንዱ የእንጀራ ልጅ የሚሆንበት አካሄድ የት ያደርሰን የሆን እያልኩ አስባለሁ። የወደቀውን ለማንሳት እጅ እንደመዘርጋት በተኛበት ረጋገጦ ከታች እየሠራ የመጣውን የችግር ቁልል እንኳን ሳያፈርስ ከላይ ሲደርሱ ወደታች ማየትን መጠየፍ ምን ይሉታል? የረገጡት የችግር ቁልል ከድቷቸው መሬት ላለመፈጥፈጣቸው ምን ዋስትና ኖራቸው ነው ጆሮ ዳባ ልበስን ዓይነት ብሂል የተለማመዱት።
የሀገር መሰርት የሚጣለው ሰው በመሆን ውስጥ ሆነ የሰውንት መስፈርት ከላያችን ተገፎ እንስሳዊ ከእንስሳ ያነሰ የወረደ ስነ ምግባር ውስጥ ገብተን ሀገር የሌላ ሰው እስኪመስለን ግራ በመጋባት ባለመከባበር ስሜት ውቧን ሀገራችንን በፍቅር ገመድ እስረን ማገሩን ለማቆም አለመታደላችን ለምን ይሆን? ለምን ይሆን የኛ የሆነውን የቤት ሥራ ሳንሠራ የሌሎችን ኃላፊነት በመጠበቅ ብቻ አንድ ዕርምጃ ሳንራመድ ተራራውን መሻገር የሚያምረን፤ ሀገራችን ጨለማ ውስጥ ገብታ እንኳን ድቅድቁ ሳያስፈራን ያለችውን ጭላንጭል ቦግ ብላ እንዳትነድ አለማድረግ ለምን አልተቻለንም።
እኛ አባቶቻችን ያቆዩልንን፤ የደም ዋጋ የተከፈለላትን ሀገራችንን ይዘን እንዳናስቀጥል ያደረገን የክፋት ገደል ደፍነን፤ የተከፈለላትን የደም ዋጋ እንድታወራርድ አድርገን በመጠፋፋት ያጨቀየናትን ሀገራችንን፤ ከታች ጀምሮ የሚጠበቅብንን የቤት ሥራ ባለመሥራታችን ውሉ የጠፋበት ትብትብ ውስጥ ከተትናት፤ ለሚመለከተው አካል የተውናትን ሀገራችንን በጋራ በአንድነት በመደማመጥና በመከባበር ስሜት በመሥራት ለልጆቻችን ሰውና ሀገር አንድ ሆነው የተጣጣሙባትን የአንድነት ሀገር እናስረክባቸው። እንደሚያምርብን ያኑረን እላለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 24/2013