ተገኝ ብሩ
ትምህርት ቤት ሆና የወላጆች በዓል ዝግጅት ላይ ከሌሎች የትምህርት ቤቱ ጓደኞቿ ጋር በመሆን የምታቀርበው ድራማና ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች እንዲሁም ለስሜቷ መተወንና መድረክ ላይ ዝግጅት ማቅረብ ስለምትወድ የምታደርገው እንጂ ዛሬ ለምትገኝበት እውቅና እና ዝና አንድ መሰረት ይጥልልኛል ወደፊት ልምዴና አቅሜን ያሳድግልኛል ብላ አስባ አታውቅም ነበር በእርግጥ በአገኘቻቸው መድረኮች ሁሉ ሰዎችን ለማዝናናት የሚያስችሉ ሥራዎች ማቅረብ እጅጉን ትወድ ነበር።
በአንድ የወላጆች ክብረ በዓል ላይ ተጋብዞ ያኔ ትርዒት አቅራቢ ተማሪ የነበረችው የዚህች ዝነኛ አርቲስት ድንቅ ችሎታ የተመለከተው የፊልም ፅሑፍ ደራሲና አዘጋጅ ምስጋናው አጥናፉ በችሎታዋ ተገርሞ በትወናዋ አጨብጭቦ ብቻ አላለፋትም ወደፊልሙ ትቀላቀል ዘንድ ፍቃዷ መሆኑን ጠይቆ ጋበዛት የትምህርት ቤት የኪነ ጥበብ ሥራ ላይ ያዘወተረችበት የትወና ችሎታዋንም ያሳደገችበት ያ መድረክ ለዛሬ መገኛዋና ለኪነ ጥበብ ሥራዋ ጅማሮ ምክንያት ሆናት በዚህም ወደ ፊልሙ ዓለም ተቀላቀለች፤ ዝነኛና ተወዳጇ አርቲስት ማክዳ አፈወርቅ ሳቅና ጨዋታ አዋቂነት መለያዋ ነው።
ያኔ ገና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነበረችና ወላጆቿ በቀላሉ የፊልም ሥራ እንድትጀምር አልፈቀዱላትም “ትምህርትሽን ያዘናጋሻልና ወደ ፊልም ሥራ ለመቀላቀል የምታደርጊውን ጥረት ብትገቺው ይሻላል” የሚል ሃሳብ በቤተሰቦቿ ቢቀርብላትም እሷ ግን ትምህርቴንም ትወናውንም ጎን ለጎን ማስኬድ እችላለሁ በሚል ወኔ ጥረቷን ቀጠለች በመጨረሻም በፊልሙ ዕውቅናና ዝና በትምህርቱም ገፍታ ያለመችውን ማሳካት ቻለች።
የመጀመሪያ ሥራዋ በሆነው “ማራ” በተሰኘ አማርኛ ፊልም ድንቅ ችሎታ በማሳየት ተስፋ የሚጣልባት ምርጥ ተዋናይ መሆኗን አሳየች እስከአሁን በ14 የተለያዩ ፊልሞች ላይ በመሳተፍ የፊልም አፍቃሪያን በምታሳየው የትወና ብቃት የተለየ ክብር የሚሰጧት ድንቅ ተዋናይት ናት በተለይ በፊልም ተመልካቾችና አፍቃሪያን ዘንድ ማክዳ በአሳዛኝና የማይረሱ ፊልሞች ላይ ባሳየችው ችሎታ በተደጋጋሚ ስሟ ይነሳል ማራ፣ ስስት፣ ማክቤል፣ በአንድ አፍ፣እፉዬ ገላ ተሳትፋባቸው በልዩነት ምርጥ ተዋናይት መሆኗን ካስመሰከረችባቸው ፊልሞች ውስጥ በዋናነት ይቀሳሉ በማክቤልና በስስት ፊልሞች የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ ዕጩ ሆና “ስስት” በተሰኘ ፊልም የዓመቱ ምርጥ ተዋናይት ሆና ተመርጣ ተሸልማለች።
አርቲስት ማክዳ የተወለደችው በውቧ ከተማ አስመራ ሲሆን፤ ገና የአራት ዓመት ልጅ ሆና መዲናችን አዲስ አበባ ከቤተሰብ ጋር በመሆን መጣች አዲስ አበባ እስከዛሬ የከተመችባትና አድጋ እውቅናን ዝናን የተጎናፀፈችባት የምትወዳት መኖሪያዋ ናት አርቲስት ማክዳ ከተሳተፈችባቸው በርካታ የፊልም ሥራዎች መሀከል “ማክቤል” የተሰኘውና በትወና ብቃቷ በወቅቱ የተወደሰችበት ፊልም ተጠቃሽ ነው በዚህ ፊልም ማክዳን የፊልም ተመልካቾችን ልብ አንጠልጥላ፣ በዕንባዋ ብዙዎችን አስተክዛ በትወናዋ የብዙዎችን አድናቆት አትርፋለች ተዋናይዋ በተወንችባቸው ፊልሞች ላይ ባሳየችው ድንቅ በችሎታ የፊልም ተመልካቾች በአድናቆት አወድሰዋታል።
የዝነኛዋ የዕረፍት ጊዜ
ከሰዎች ጋር በቀላሉ የመግባባት እና መጫወት፣ከሰዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ቁም ነገር አዘል ውይይት ማድረግ ያስደስታታል ሥራ ካልሆነ እና ጉዳይ ካልገጠማት ዕረፍት ስትሆን ቤት ማዘውተር ትወዳለች “ቤት ውስጥ መሆን የምወደው ስለራስ ለማሰብና ለማንበብ ምቹ አጋጣሚ ስለሚፈጥርልኝ ” የምትለው ማክዳ በአብዛኛው የዕረፍት ሰዓቷ በቤቷ ውስጥ በማንበብና የተለያዩ ፊልሞችን በማየት ትዝናናለች።
ከመፅሐፍት በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርተው የሚፃፉና ታሪክ ቀመስ የሆኑትን ትመርጣለች አዳዲስ የሆኑ እውቀት የሚሰጡ በእውነተኛ መረጃ ላይ የተመረኮዙ መፅሕፍትም በማክዳ ተመራጮች ናቸው
ከፊልም በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱና ጠንከር ያለ አስተማሪ ጭብጣቸው ያላቸው ማየት ትወዳለች አመቹ ገጠሞኝና ጊዜ ካገኘች ከከተማ ወጣ ብሎ ተፈጥሯዊ ቦታዎችን ልዩ ልዩ ሰው ሠራሽ መስህቦች መጎብኘት ማክዳ አስደስቷት የምታደርገው ነው።
ሀገርን በማወቅ የዕረፍት ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም እንደ አገር የተሻለ ልምድ የለንም፤ ይህ መለወጥና ያለንን ሀብት ማወቅ የዕረፍት ሰዓታችንም ባህልና ያለንን ሀብት በመለየት የተሻለ ጊዜ ማሳለፍ እንደሚቻልም ታስረዳለች
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባገኘቸው አጋጣሚ ሁሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የተፈጥሮ መስህቦችና ሰው ሠራሽ ቅርሶችን በመጎብኘት የማይረሳ ጊዜን ማሳላፏን ትናገራለች በመኖሪያ አካባቢዋ ካለው ማህበረሰብ ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቷንም በመወጣት ላይ ትገኛለች።
አሁን ላይ ከሌሎች የሙያ አጋሮቿ ጋር በመሆን የአባይ ግድብ ላይ ታላቅ ዶክመንተሪ በመሥራት አሁን ለህዝብ በመገናኛ ብዙኃን በማቅረብ አገራዊ ኃላፊነቷን በመወጣት ላይ ትገኛለች ወደፊት በአገር ደረጃ ብሎም በአፍሪካ የተሻለ የፊልም ኩባንያ በማቋቋም በዘርፉ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆንና ዘርፉን ለማሳደግ አበክራ ለመሥራት ትልቅ ዓላማን አንግባ በመሥራት ላይ ትገኛለች ።
የዝነኛዋ መልዕክት ለአገሬው
“ዓይናችንን በደንብ መግለጥና ዓለም ላይ የተገኘንበትን ዓላማ ማወቅ መቻል ይኖርብናል በአመለካከትና በነገሮች ላይ ያለንን እይታ መለወጥና ማደግ ይኖርበታል ሰው በጉዳዮች ላይ ያለው እውቀት ካደገ፤ እይታውና ነገሮችን የሚረዳበት መንገድ የተሻለ ይሆናል ለሌሎች ሃሳብ ከመስጠት በፊት እራስ ላይ በደንብ መሥራት ይገባል ምክንያታዊ ሆነን መጠየቅና በምክንያት ማስረዳት ልምድ ማድረግ ይኖርብናል ያኔ አገራችንም እኛም ሰላም እንሆናለን፤ ሰላም ደግሞ የሁሉ ነገር መሰረት ነው ”በማለት ታለቅ መልዕክቷን ገልፃለች እኛም ከዝነኛዋ ጋር በነበረን ቆይታ ያገኘነውን መረጃና ያጠናቀርነውን ፅሑፍ በዚህ መልክ ቋጨን፤ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013