አስናቀ ፀጋዬ
ለረጅም አመታት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳትፈዋል:: ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆንም መፅሄት አዘጋጅተው በማሳተም ለገበያ በማቅረብ ጥረት አድርገዋል፡፡ የመፅሄት ስራው አላዋጣ ሲላቸው ደግሞ ከሁለት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ወደ ማስታወቂያና ህትመት ስራ ገብተው ለመስራት ሞክረዋል፡፡
በመጨረሻ ግን የራሳቸውን የማስታወቂያና የህትመት ድርጅት ከፍተው ውጤታማ ለመሆን ችለዋል- የማሊዲቭስ ማስታወቂያና ህትመት ስራ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ታደለ፡፡
አቶ ቢኒያም ትውልድና እድገታቸው አዲስ አበባ ይሁን እንጂ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እስከ አስራ አንደኛ ክፍል የተከታተሉት በአዳማ ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ነው፡፡
የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ደግሞ በአዳማ አፄ ገላውዲዎሰ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ በ1997 ዓ.ም ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
የዩኒቲ የኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉ ባላቸው ትርፍ ሰአት በጓደኛቸው የፅህፈት መሳሪያ መደብር ውስጥ በማሳለፍና ኢንተርኔት በመጠቀም እውቀታቸውን ማዳበር ጀመሩ፡፡ ጓደኛቸውም የፎቶሾፕ ሶፍትዌሮችን መማርና ራሳቸውም ማስተማር ጀመሩ፡፡
ሆኖም ከእርሳቸው ይልቅ ጓደኛቸው ለዚህ ሶፍትዌር አብዛኛውን ትኩረት ስለሚሰጡ ‹‹ሁለታችንም ከምንማር ሶፍትዌሩን ለምን ወደ ገበያ አንለውጠውም?›› የሚል ሃሳብ አመነጩ፡፡
ቀላል ከሆኑ የቢዝነስ ካርድ ዲዛይኖች ስራ በመነሳትም የአፍሪካና የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታ ፕሮግራሞችን፣ ፖስተሮችንና የልደት ፖስት ካርዶችን በማዘጋጀት አትመው መሸጥ ቀጠሉ፡፡ ሁለቱ ጓደኞቻቸው በዲዛይን ስራው ላይ በስፋት ሲገፉበት አቶ ቢኒያም ደግሞ ይበልጥ ገበያው ላይ በማተኮር ስራቸውን በጋራ ቀጠሉ፡፡
ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው እንደወጡም አንዳንድ ስራዎችን በግላቸው መሞካከሩን ተያያዙት፡፡ ከሁለቱ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆንም ‹‹አርምሞ›› የተሰኘና የግል ስብእና ማበልፀግ ላይ ያተኮረ መፅሔት አዘጋጅተው በማሳተም ገበያ ላይ ለማዋል ሞከሩ፡፡
ስልጠናዎችን በማዘጋጀትና በመፅሃፍት ዙሪያ ውይቶችን በማካሄድ፣ ወርክሾፖችንና ሴሚናሮችንም ጭምር እንዲዘጋጁ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራም ሰሩ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ለረጅም ግዜ በሮትራክትና በሮተሪ ክበቦች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጡ፡፡
የመፅሄቱ ህትመት ሁለት እትም ከታተመ በኋላ እንደተቋረጠ አቶ ቢኒያም ከቀድሞው ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በቀጥታ ወደ ማስታወቂያና ህትመት ስራ ገቡ፡፡ ከጓደኞቻቸው ጋር አብረው እየሰሩ በመሃል የራሳቸውን የማስታወቂያና ህትመት ድርጅት ቢከፍቱም ብዙም ሳይዘልቁ አቆሙ፡፡ ተስፋ ባለመቁረጥ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ‹‹ማልዲቭስ›› የተሰኘ የራሳቸውን የማስታወቂያና ህትመት ድርጅት በአዲስ አበባ ሃያ ሁለት አካባቢ እንደገና ከፍተው መስራት ጀመሩ፡፡
የራሳቸውን ማስታወቂያና ህትመት ስራ ሲጀምሩ አንዲት አነስተኛ ኮምፒዩተርና ጠረጴዛ በመያዝ አነስተኛ ቢሮ ተከራይተው የነበረ ሲሆን በእጃቸው የነበረው መነሻ ካፒታልም ከ40 ሺህ ብር የበለጠ አልነበረም፡፡ በጊዜው ወደ ማስታወቂያና ህትመት ስራው ሲገቡ ትልቁን ቦታ የያዘው የመስራት ፍላጎታቸው፣ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ያካበቱት የስራ ልምድና የገነቡት የቢዝነስ ግንኙነት ነበር፡፡
አቶ ቢኒያም በወቅቱ የማስታወቂያና የህትመት ስራውን የጀመሩት ለብቻቸው ቢሆንም በሂደት ግን አንድ ስራ ተቀባይ ፀሃፊ በመቅጠር የቢዝነስና ኢንቬቴሽን ካርዶችን እንዲሁም አነስተኛ የህትመትና የማስታወቂያ ስራዎችን ይሰራሉ፡፡ ቀስ በቀስ ድርጅታቸው እያደገ ሲመጣም በራሪ ወረቀቶችንና ብሮሸሮችን ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ እያደርም የውስጥና የውጪ ማስታወቂያዎችን ተቀብሎ መስራት ቀጠለ፡፡
በዚህ ሁኔታ እያደገ የመጣው ድርጅታቸው በአሁኑ ወቅት የህትመት ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ቢሆንም በአብዛኛው የውስጥና የውጪ ማስታወቂያ ስራዎችን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ ይሰራል፡፡ የህትመት ስራዎቹም እሴት ተጨምሮባቸው የሚሰሩ ናቸው፡፡ የምርት ማሻሻጫ ህትመቶችንም በብዛት ይሰራሉ፡፡
ድርጅቱ ከሚሰራቸው የውስጥና የውጪ የማስታወቂያ ስራዎች ውስጥም የህንፃ፣ የሆቴልና የንግድ ድርጅቶች ስያሜዎች፣ ቢሮን የማሳመር ስራዎችንና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ መሳሪያ በበቂ ሁኔታ ላላሟሉ የማስታወቂያ ድርጅቶችን ስራም ተቀብሎ ያስተናግዳል:: ይህም ለድርጅቱ ተጨማሪ የገበያ መዳረሻ ፈጥሮለታል፡፡
ሌሎች የቤት ውስጥና የቢሮ ማስዋብ ኢንቴሪየር ዲዛይን ስራ የሚሰሩ ድርጅቶች ደግሞ ለድርጅቱ ተጨማሪ የፓርቲሽን፣ የግድግዳና መሰል ስራዎችን ይዘው ይመጣሉ:: ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ በሀገሪቱ ጥቂት ኩባንያዎች ብቻ የሚሰሩትን የኤግዚቢሽን ስታንዶችን በማከራየትም በመሸጥም ይሰራል፡፡ የባነር፣ ስቲከር፣ የወረቀት ህትመት፣ ቲሸርት፣ ኮፍያ፣ የስጦታና የምርት ማሻሻጫ እቃዎችንና ላይት ቦክሶችንም ይሰራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ ጥራትን ከፈጠራ ጋር አዋህዶ ለመስራት ሙከራ የሚደርግ ሲሆን የተመረጡ ደምበኞቹ እንዳሉ ሆነው ሰፋፊ የማስታወቂያ ስራዎችን ከነዚሁ ደምበኞቹ ጋር ይሰራል፡፡ በአሁኑ ግዜም 12 ያህል ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ ድርጅቱ ስራ ሲጀምር መነሻ ካፒታሉ ከ10 ሺ ብር ያልበለጠ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት 100 ሺ ብር የተመዘገበ ካፒታል አለው:: ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ አመታዊ ሽያጭም ያከናውናል፡፡
አንዳንዴ ደግሞ ድርጅቱ ደምበኞች ሙሉ ስራ እንዲሰራላቸው በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት ዓመታዊ ኮንፈረንሶቻቸውን፣ ባዕሎቻቸውን፣ የምርቃት ፕሮግራሞቻቸውን፣ የፕሮግራም ማስጀመሪያ ስራዎቻቸውንና ሙሉ የመድረክ ዝግጅቶቻቸውን ይሰራል፡፡
ድርጅቱ በማስታወቂያ ስራ ለፈጠራ ቅድሚያ መስጠቱ ከሌሎች ተመሳሳይ የማስታወቂያ ድርጅቶች ለየት የሚያደርገው ሲሆን ከተለመደው የማስታወቂያ ስራ ውጪ ስራዎችን በቋሚነት፣ በጥራትና በፍጥነት በማከናወን የታሰበውን የፈጠራ ክህሎት እንዲያግዝ ባለሞያዎችን፣ ማሽኖችንና ማቴሪያሎችን አቀናጅቶ እለት በእለት ይሰራል፡፡ ሌሎች ፍላጎት ያላቸውን ባለሃብቶችም ተጨምረውበት የማስታወቂያ ስራዎቹ እንዲከናወኑም ጥረት ያደርጋል፡፡
ድርጅቱ ከቢዝነስ ድርጅቶች፣ ከመንግስት ተቋማትና ከመሳሰሉት ጋር የሚሰራቸውን የማስታወቂያ ስራቸው ለማሳደግና የተደራሽነት አቅሙን ለማስፋት ከኢንቴሪየር ዲዛይነሮች፣ ከሌሎች ማስታወቂያ ድርጅቶችና ከእንጨት ሰራተኞች ጋር ለመስራት ይሞክራል፡፡ አሁን በያዘው አቅጣጫ መሰረት ደግሞ ትዕዛዞች ሳይኖሩ ድርጅቱ በራሱ ቅድሚያ ሰጥቶ ዲዛይን አድርጎ የሚሰራቸውና ወደ ምርት ሊለወጡ የሚችሉ የማስታወቂያ ስራዎችንም ያከናውናል፡፡
እነዚህ ወደ ምርት ሊለወጡ የሚችሉ የማስታወቂያ ስራዎችም በአብዛኛው ከቢዝነስ ድርጅቶች በተጨማሪ በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ይህም የድርጅቱ የገበያ ተደራሽነት እንዲያሰፋ አግዞታል፡፡ ከውጪ ሊመጣ የሚችለውን ምርትም ለመተካት አስችሎታል፡፡ ለሚሰራቸው የማስታወቂያ ስራዎች የሚያስከፍለው ዋጋም እንደ ማስታወቂያ ስራው ዓይነትና የፈጠራ ስራ የሚወሰን ሲሆን ለአንድ ከፍተኛ የማስታወቂያ ስራ እስከ 300 ሺ ብር ሊጠይቅ ይችላል፡፡
በቀጣይም ድርጅቱ በማስታወቂያው ዘርፍ ያለውን እውቀት እለት በእለት ለመጨመርና ሰራተኞቹን ለማብቃት የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለመስራት አቅዷል፡፡ አብዛኛዎቹ የማስታወቂያ ስራዎች በማሽን የሚከናወኑ ከመሆናቸው አኳያና ወቅታዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚሹ በመሆናቸው ዓለም ከደረሰበት የማስታወቂያ ቴክኖሎጂ ደረጃ ጋር ለመሄድና ለመድረስ ውጥን ይዟል፡፡ እያንዳንዳቸው የማስታወቂያ ስራዎች በየደረጃቸው ማቴሪያል የሚፈልጉ በመሆናቸው ማቴሪያሎቹን በበቂ ሁኔታ በማሟላት ደረጃቸውን የጠበቁ የማስታወቂያ ስራዎችን የመስራት ሃሳብ አለው፡፡
ሀገሪቱ የምታካሂደውን ቀጣይ ምርጫ ተከትሎና በሌሎችም ጉዳዮች ምክንያት በርካታ የማስታወቂያ ስራዎች በቀጣይ የሚመጡ ከመሆናቸው አኳያም ይህን ታሳቢ ያደረገ አቅም የመገንባት አቅጣጫም አስቀምጧል፡፡ የማስታወቂያ ስራውን ይበልጥ ሊያሳድጉ የሚችሉ ማሽኖችን የመጨመርና የሰው ሃይሉን የማሳደግ እቅድ አለው፡፡
‹‹የማስታወቂያና ህትመት ዘርፍ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ገፅታ የሚያመላክት ትልቅ ዘርፍ ነው›› የሚሉት አቶ ቢኒያም ለግል ጥቅም ከሚውሉ ጉዳዮች ውጪ ለሌሎች አገልግሎት የሚውሉ ሁሉ በአብዛኛው ማስታወቂያ የሚፈልጉ በመሆናቸው የማስታወቂያው ዘርፍ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በዘመነ ሉላዊነት የማስታወቂያው ዘርፍ እያደገ መምጣቱን ተከትሎም ደረጃውን የሚመጥን የማስታወቂያ ስራ እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ፡፡
ዘርፉ የውጪ ባለሃብቶች ገብተው እንዳይሰሩበት የተዘጋ ከመሆኑ አኳያም ይህ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ገብተው መስራት ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥ ተወላጆች መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡
ለማስታወቂያ ስራ የሚያግዙ ማቴሪያሎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መጠነኛ ማበረታቻዎች ቢኖሩም ይህን መልካም አጋጣሚ በስፋት ለመጠቀም ግን ማበረታቻው በቂ እንዳልሆነም ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም በማስታወቂያው ዘርፍ ገና ለመግባት እየተንደረደሩ ላሉ ሰዎች ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ የሚያስገቡበትን ሁኔታ መፍጠርና ስፋት ያለው ማበረታቻዎችን በመንግስት በኩል ማድረግ እንደሚገባ አቶ ቢኒያም ይጠቁማሉ፡፡
ከዚህ ባሻገር የማስታወቂያ ስራውን በስፋት ለመስራት የቦታ እጥረት መኖሩንም አቶ ቢኒያም ተናግረው፤ ይህም አቅም ገንብቶና በርካታ ባለሞያዎችን ይዞ ለመስራት አስቸጋሪ መሆኑንና በመንግስት በኩል ቦታዎች የሚቀርቡበት መንገድ ሊፈጠር እንደሚገባም ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ብድር የሚመቻችበት ሁኔታም መፈጠር እንደሚኖርበትና እነዚህንና መሰል ችግሮችን መፍታት የሚቻል ከሆነ ዘርፉን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚመኙ ይገልፃሉ፡፡
በተጨማሪም ብዙ ተዋናዮች በዘርፉ ገብተው እንዲሰሩና በስራቸውም ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጥሩ ማበረታታት እንደሚገባና በተለይ ለውጡን ተከትሎ ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት በመሆኑ የማስታወቂያውም ዘርፍ መንግስት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ተርታ አብሮ መሄድ እንዳለበትም አቶ ቢኒያም ይጠቁማሉ፡፡
በተለይ ደግሞ የከተማ ቱሪዝም በአይን የሚታይ ከመሆኑ አንፃር የሚታየው ነገር በማስታወቂያ መታገዝ ያለበት በመሆኑ ለዚህ ዘርፍ የበለጠ ትኩረት መሰጠት እንዳለበትም ያመለክታሉ፡፡ የማስታወቂያው ዘርፍ ሰፊ ገበያ እንዳለው አቶ ቢኒያም ጠቅሰው፤ ከዚህ በተቃራኒ በዘርፉ ያለው ተዋናይ ደግሞ በጣም ጥቂት በመሆኑ በርካቶች ወደሙያው ተሰማርተው እንዲሰሩ የሚጋብዝ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
በማስታወቂያና ህትመት ስራ ዘርፍ ድርጅታቸው ውጤታማ መሆኑን የሚገልፁት አቶ ቢኒያም በተለይ ድርጅቱ ለመስራት የሚያስበውን ነገር ወይም ደምበኛ እንዲሰራለት የሚፈልገውን ሃሳብ ወደተግባር የመለወጥ ደረጃ ላይ መድረሱንና ለዚህም አቅም መገንባቱን ይናጋራሉ፡፡ የድርጅቱ ትልቁ ሃብትና የውጤታማነቱ ማሳያም የደምበኞችን ሃሳብ ወደ ተግባር መቀየር መቻሉ መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከአንድ ሰራተኛ ወደ አስራ ሁለት ሰራተኞች መቅጠር መሸጋገሩ ትልቅ አቅም እንደፈጠረለትና ከትንሽ ተነስቶ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ብሎም የደምበኞቹን ቁጥር በማሳደግ ተደራሽነቱን ይበልጥ እያሰፋ መምጣቱ የውጤታማነቱ ሌላኛው ማሳያ መሆኑን አቶ ቢኒያም ይናገራሉ፡፡
በማስታወቂያ ዘርፍ ዓለም የደረሰበትን ደረጃ በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች ላይ በመሳተፍ፣ ሞያዊ ክህሎትን ሊያዳብሩ በሚችሉ መድረኮች ላይ በመቅረብና በዘርፉ ያሉ ማህበራት አባል በመሆን ልምድና እውቀቶችን በማዳበር ድርጅታቸው ያለበትን ክፍተት በመለየትና ክፍተቱን ለመሙላት ያደረጉት የግል ጥረትም ለድርጅቱ ውጤታማነት አስተዋፅኦ ማበርከቱን ይመሰክራሉ፡፡
የማስታወቂያው ዘርፉ በአነስተኛ ካፒታል መጀመር የሚያስችልና ይህም መልካም አጋጣሚ በመሆኑ በተመሳሳይ ሌሎችም በዘርፉ ገብተው ቢሰሩበት ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉበት እድል እንዳለ አቶ ቢኒያም ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁንና ዘርፉ ሰፊ የገበያ እድል ስላለውና በትንሽ ካፒታል እንዲጀምሩ አጋጣሚ ስለፈጠረላቸው ብቻ በደፈናው ከመግባት ይልቅ ከማስታወቂያው ዘርፍ አንዱን መርጠውና በመረጡት የማስታወቂያ ዘርፍ ላይ አተኩረው መስራት እንደሚገባቸውና ይህም በተሻለ ደረጃ ውጤታማ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 22/2013