ካሳቫ በአሜሪካ ሞቃታማ ክፍል ውስጥ የሚበቅልና በዕፅዋት ውስጥ የሚመደብ የተክል አይነት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ቁጥቋጦዎችና ሰፋፊ ቅጠሎች ያሉት ሲሆን አበቃቀሉም እንደቡና እንጨት ረጃጅም ዘንጎች አሉት::
ተክሉ በአሁኑ ጊዜም ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ተስፋፍቷል:: ለምግብና ለመድኃኒትነት አገልግሎት ይውላል::መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በተለይ ትሮፒካል በሚባል ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በስፋት ለምግብነት ያውሉታል::በአካባቢው ከሩዝና በቆሎ ቀጥሎ የሚመረት ሲሆን፣ድርቅን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ በብዙ አርሶአደሮች ዘንድ ተመራጭ ነው::
የካሳቫ ተክል የአካባቢ ሥነምህዳርን በመጠበቅም ጠቀሜታው የጎላ ነው:: በተለይ መሬቱ በጣም የተጎዳና የአፈር ለምነቱ በቀነሰ አካባቢ ላይ ቢተከል አፈሩ መልሶ በማገገም ለምነቱ እንዲመለስ ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ::
ካሳቫ ከሦስት ሜትር በላይ ከፍታ፣ ውበት ካለው የአበባ ዝርያ እኩል የሚያድግ ቁጥቋጦ ሲሆን፣ማዕከላዊ ግንዱ እየተንሰራፋ ወይም እየተስፋፋ ይሄዳል:: ከሚሰጠው ምርት በላይ ትላልቅ የሆኑ ጥቁር አረንጓዴ ቀለም ያለው ረዣዥም ቅጠሎች በስፋት በግንዱ ላይ መኖሩ ለየት ያደርገዋል::
የካሳቫ ተክል በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም በሚፈለገው ልክ የለማ ባለመሆኑ ለአካባቢ ጥበቃም ሆነ ለምግብነት በመዋል ደረጃ ዝቅተኛ ነው::
አዲስ ዘመን ጥር 20/2013