ወርቅነሽ ደምሰው
በሀገር አቀፍ ደረጃ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዲያስፖራ አባላት የነበራቸው ተሳትፎ እምብዛም እንዳልነበረ መረጃዎች ያሳያሉ ።ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የዲያስፖራው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ይታወቃል ።
ከለውጡ በኋላ የዲያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ያለው ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ የሚናገሩት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ናቸው፡፡
ወይዘሮ ሰላማዊት እንደሚናገሩት፤- በሀገር አቀፍ ደረጃ ዲያስፖራው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ በጣም ጨምሯል ።ከዚህ በፊት ዲያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ባይተዋር ተደርጎ ፤ እራሱን አግልሎ፤ ተደብቆ የሚኖር ነበር ።
ዲያስፖራው እንኳን በግልጽ ከኪስ አውጥቶ ለመስጠት ቀርቶ በተለያየ መልኩ ኢትዮጵያ ስታገኝ የነበረውን እርዳታና ድጋፍ እንኳን ሳይቀር ለሰላማዊ ነገር የሚጠቀም ሀገርና መንግሥት የለም እያለ በጣም የሚተችበትና ለማስከልከል ሰላማዊ ሰልፍ እስከ መውጣት የሚደርስበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል ።
አሁን ግን ለውጡን ተከትሎ ዲያስፖራው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ መነሳሳት በማሳየት በግል ሆነ በጋራ በተነሳሸነት ኢንቪስት በማድረግ እንዲሁም ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል ።
ኤጀንሲው መንግሥት የሰጠውን ኃላፊነት ሁሉንም በሚያቀፍና በሚያስተናግድ መልኩ በስትራቴጂና በአሠራር የተደገፈ በማድረግ በፖለቲካ አመለካካት፣ በሃይማኖት፣ በዘር ወይም በሌላ የትኛውም አይነት ልዩነት ሳይኖር በኤምባሲዎችን ጭምር መሠረታዊ የሆነ የአሠራር ማሻሻያ በማድረግ እየሰራ ይገኛል ።በዚህም ዲያስፖራው እየተበረታታ መምጣቱን ዋና ዳይሬክተሯ ይናገራሉ፡፡
ዲያስፖራው ለዘጠኝ ዓመታት አካባቢ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ያለው ተሳትፎ በቦንድ ግዥና ስጦታ በመስጠት የተሳተፈበት ሁኔታ ነበር የሚሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በተለይ ለውጡ ከመምጣት በፊት ግድቡ ችግር ውስጥ ገብቶ በነበረበት ወቅት ዲያስፖራው ጥርጣሬ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ያስታውሳሉ ።
በዚህ የተነሳ የዲያስፖራው የተሳትፎው መጠን ቀንሶ የነበረ ሲሆን፤ በመንግሥት በተደረገው ርብርብ ዳግም ግድቡ እንደገና አንሰራርቶ የግድቡ የውሃ ሙሌት ተሞልቶ ሲታይ የቀድሞውን ችግር እያለ እንኳን እንደገና በመነሳሳት ገንዘቡን እየሰጠ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዳሉ ።
በተለይ ከውሃ ሙሌቱ በፊት ተቀዛቅዞ የቆየው የዲያስፖራ ተሳትፎ የተወሰነ ቀንሶ ነበር ።ከግድቡ ውሃው ሙሌት በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ገንዘብ የተሰበሰበበት ሁኔታ መኖሩን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በ2013 በጀት ዓመት ወደ 200ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል ።
በ2013 በጀት ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 76 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፤ ከአምና የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው የስድስት ወሩ የ43 ሚሊየን ብር ልዩነት እንዳለው ጠቁመዋል ።በዚህም በስድስት ወሩ ለመሰብሰብ ከታቀደው በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በበጀት ዓመቱ 50 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 16 ሚሊዮን ብር ከዲያስፖራው ተሰብስቧል ።ዲያስፖራው በሰሜኑ በሀገራችን ክልል መንግሥት በሚወስደው ህግ የማስከበር እርምጃ መከላከያ ሠራዊትና የተጎዱ ወገኖችን መርዳት አለብን በማለት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 100 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በአይነትና በገንዘብ አሰባስቧል ።
በተለይ በአይነት ከተገኘው ሲታይ ለመከላከያ ሠራዊት ለተጎዱ ወገኖች ሊያግዝ የሚችሉና በአገር ውስጥ የማይገኙ መድኃኒቶችን ከጤና ሚኒስቴር አይነታቸውን ዝርዝር ወስዶ በመላክ የዲያስፖራው አባላትም በተላከ ዝርዝር መሠረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰብስቦ ልኳል ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ይህ የዲያስፖራው ተግባር እጅግ መደነቅ የሚገባውና ሀገር ችግር ላይ ስትወድቅ ከወገን ጎን መሆናቸው ያሳዩበት ነው ያሉ ሲሆን፤ በኮቪድ መከላከል ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በአይነትና በገንዘብ የተገኘበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል ።
በአጠቃላይ ሀገራዊ በሚባሉት ጉዳዮች ላይ የዲያስፖራው ተሳትፎ ከፍ ያለ መሆኑን ይናገራሉ ። ኤጀንሲው እንደዋና ሥራው የሚሰራው ከመጣው ገንዘብና ሀብት በላይ የተፈጠረው ሀገራዊ መግባባት በሀገር ጉዳይ ላይ የሀገር ጉዳይ የዘር፣ የአንድ ሃይማኖት ጉዳይ ሳይሆን የሀገር ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው፤ ኢትዮጵያ የሁላችንም ቤት ናት ብሎ አምኖ ከመቀበልና በጋራ ከመስራት አኳያ በከፍተኛ ሁኔታ የተሻለ ነገር እየመጣ መሆን ተናግረዋል ።
የጋራ መግባባቱ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ልዩነቶታችን መቼም ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሀገራዊ በሆነ ጉዳይ የሚኖረን አረዳድና ተሳትፎ አንድ መሆን አለበት ብለዋል ።ይሄ ደግሞ ለሀገራችንም ሆነ ውጭ ለሚኖሩ የዲያስፖራ አባላት ጥቅም ያለው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኤጀንሲው የቢዝነስ ተሳትፎ አንዱ ሥራ በመሆኑ በየጊዜው ዲያስፖራው ኢንቨስተሮችን ይዞ ይመጣል ።በዚህም ዙሪያ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለወጡ አሠራሮች ያሉ ሲሆን፤ ፕሮጀክቶቻቸውን በመገምገም ያካሄዳሉ? ወይስ አያስኬዱም? ፤ ገንዘብ አለው? ወይስ የለውም? የሚለውን በጣም ብዙ ዲያስፖራዎቹ ከሚመጡበት ሀገርና ካካበቱት እውቀት አኳያ ምን ያህል ጥቅም ሊያመጣ ይችላል የሚለውን ተገምግሞ ወደሚፈልጉትና የተሻለ ውጤት ያመጣሉ ተብሎ ወደሚታሰብበት ክልሎች በመምራት ክትትል እንደሚደረግ ይናገራሉ ።
በግማሽ ዓመቱም ከ800 በላይ ኢንቪስተሮች ፕሮጀክቶታቸውን ይዘው የመጡ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 35 የሚሆኑት ገንዘባቸው አስገብተው፤ ሰዎች ቀጥረው ወደ ሥራ ገብተዋል ። በንግድ 900 የዲያስፖራ አባላት ተሳትፈው ፈቃድ አውጥተው ሥራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ በተመሳሳይ በራይዝንግ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት በተለይ ከኮቪድ በኋላ እየተረጋጋ ሲመጣ ኢትዮጵያ እንደ አንድ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን እየተሰራ ነው ።
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በተለይ ዲያስፖራው የገጽታ ግንባታ አኳያ በተለያየ መልኩ የኢትዮጵያ የገጽታ ግንባታ የሚያጠለሹትን አካላት ከሥር ከሥር እየተከታታለ የሚያስተካከሉ ዘመቻዎች እንደሚደረግ ይናገራሉ ።
እንደ ቲዊተር ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ዘመቻዎች እየተደረጉ ሲሆን፤ ህግ በማስከበር ዘመቻ የነበረው ኦፕሬሽንና አፈጻጸም አጠቃላይ የተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋም ላይ የተወሰደው እርምጃና በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው ነገር ትተው በአሉታዊ ጉዳዮች አጉልቶ የሚያወጡ ሚዲያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ።
እውነታው ምንድነው የሚለው መረጃ በመስጠት በማስተካከልና በማረም ገጽታ በመገንባት ኢትዮጵያ እየሰራች ያለችውን በጎ በጎ ሥራዎች ከፍ የማድረግ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል ።
የዲያስፖራው አቅም ቀላል ስላልሆነ ዲፕሎማሲውን የመደገፍ የማስተዋወቅ ሥራዎች ይሰራል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሷን ውሃ የመጠቀምና አባይንም በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት እንዳላት ዓለም አቀፍ ህግ በማጣቀስ በአረበኛ፣ በፈረንሳይኛና በእንግሊዘኛ የሚከራከሩላት የዲያስፖራ አባላት እንዳሉ ጠቁመዋል ።
በተመሳሳይ ሌሎችም ሥራዎች ይሰራሉ፤ ለአብነት በህግ ማስከበሩ በአውሮፓም በአሜሪካም ያሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያወጧቸው ጉዳዮች ትክክለኛ መረጃ በመስጠት በኩል ዲያስፖራው ንቁ ተሳታፊ ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ ሲሆን፤ ኤጀንሲው ይህንን በመደገፍና መረጃ በመስጠት ሥራ የሚሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 19/2013