ሙሉቀን ታደገ
ካለፈው የቀጠለ
ባለፈው ሁለት ሳምንት ታህሳስ 28 ቀን 20013 ዓ.ም “የባለ ብሩህ አእምሮና የልማት ባንክ ውዝግብ “በሚል ለንባብ ባበቃነው ፅሁፍ ሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ አቅርበናል። በቀጣይ ከልማት ባንክ እና ሌሎች መስሪያ ቤቶች የተገኘውን መልስ ይዘን እንደምንቀርብ ቃል ገብተን ነበር ።
በገባነው ቃል መሰረት ዛሬ በሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ መካከል ስለተፈጠረው ውዝግብ የልማት ባንከን እና በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የብረታ ብረት ኬሚካል ዘርፍ ሚኒስቴር የተሰጠውን ዝርዝር ሃሳብ ይዘን ቀርበናል ።
ያለፈውን ከአሁኑ ጋር በማገናኘት ለመፍረድ ይቻል ዘንድ የሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማናጀር አቶ ሰለሞን ሰብስቤ ያቀረቡት አቤቱታ በወፍ በረር ማየቱ ተገቢ ነው ።አቶ ሰለሞን በሀገር እና በአህጉር አቀፍ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአዳዲስ ፈጠራዎች የፈጠራ የአዕምሮ ባለንብረትነትን አስመዝግበዋል ።
ይህንን የፈጠራ ችሎታቸውን ለማሳደግ፤ ኑሯቸውን ለመደገፍ ብሎም በስራቸው ሰራተኞችን በመቅጠር የዜግነት ሃላፊነታቸውን ለመወጣት በማሰብ ከልማት ባንክ ብድር በመፈለግ የብድር ፕሮፖዛል ያስገባሉ ።በፕሮፖዛሉ መሰረትም የልማት ባንክ ብር ያጸድቅላቸዋል ።
በቀን 05/ 08 /2010 ዓ.ም ብሄራዊ ባንክ ለሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በፃፈው ደብዳቤ መሰረት የልማት ባንኩ በጀመረው የካፒታል ሊዝ ፋይናንስ መሠረት የአቶ ሰለሞንን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በህዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም የልማት ባንክ የካፒታል እቃዎች ዱቤ ግዥ ኪራይ ውል መዋዋላቸው ተገልጿል ።
በዚሁ ውል መሰረት ባንኩ የሊዝ የብድር ብር 12 ሚሊዮን 586 ሺህ 231 ብር ወጪ የተደረገበት ማሽነሪዎች ተገዝተው በፕሮጀክቱ ሳይት ላይ ደርሰው በመጋቢት 5/7/ 2010 ዓ.ም ባንኩ እና ድርጅቱ ጊዜያዊ ርክክብ መፈፀማቸውን ያመላክታል ።
ነገር ግን ግዥ ተፈቅዶ ከመቅረቡ በፊት ግዥ ለመፈፀም አቶ ሰለሞን የ3 ሚሊዮን 146 ሺህ 588 ብር በዝግ አካውንት ማስገባት ይጠበቅባቸው ነበር ።ይህ ያስገቡት ገንዘብ በባንኩ ማሽነሪዎች ከተገዛላቸው በኋላ ለስራ መስኬጃ የሚለቀቅ ገንዘብ ነበር ።
ነገር ግን በውላቸው መሰረት ይህ የመስሪያ ገንዘብ ስልላተለቀቀላቸው ማሽኖቹ ከተገዙ እና ርክክብ ከተከናወነ ወደ ሶስት ዓመት የተጠጋ ቢሆንም ማሽኖቹ ያለምንም ስራ እንዲሁ ቁጭ ያሉ በመሆናቸው በአቧራ እና በሸረሪት ድር ተውጠው ያለስራ እንዲቀመጡ ተፈርዶባቸዋል ።
ባንኩ የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ አቶ ሰለሞን ያስያዙትን ገንዘብ አለመለቀቁን ቢናገርም፤ በዋነኛነት ግን ማሽኖች ያሉበት ቦታ ጠባብ ስለሆነ ምርት ማምረት የሚያስችል አይደለም የሚለው ምክንያት ተጠቃሽ ነው ።
ባንኩ ብድር የፈቀደው ከብድር በፊት ያለውን በፕሮፖዛሉ ላይ የተጠቀሰውን ቦታ ተመልክቶ ነው ። ነገር ግን አቶ ሰለሞን እንደሚገልፁት፤ ‹‹አሁን ይህን እንደምክንያት በመጥቀስ የማሽነሪ ርክክብ ከተደረገ በኋላ የቦታ ጥበት እና ሌሎች ምክንያቶች እየተደረደሩ በካፒታል እቃ ዱቤ ግዥ እና ኪራይ ውል መሰረት የመስሪያ ገንዘቡ ተለቆልኝ መስራት ባለመቻሌ ጉዳዩን ህዝብ ሰምቶት ህዝብ ይፍረደኝ›› ሲሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የዝግጅት ክፍል አቤት ማለታቸው የሚታወስ ነው። ከዚህ በመነሳት የተለያዩ አካላትን አነጋግረን ያገኘነውን መልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።
አቶ ሰለሞን፤ በባንኩ የተጠየቁት የቦታ ስፋት መጠን ከኪራይ ውል ስምምነት ውጪ ነው ሲሉ ያስረዳሉ ።ከውሉ ውጭ የቦታ ማስፋፊያ ቢጠየቁም ያላቸውን ሼድ ከክፍለ ከተማ እና ከወረዳ አካላት ጋር ተነጋግረው የመስሪያ ቦታ ማስፋፊያ ማድረጋቸውን ይገልፃሉ ።ነገር ግን በባንኩ በኩል ማስፋፊያ የተደረገበት ሼድ በቂ አይደለም በመባሉ የኢትዮጵያ ንግድ እና ኢንዱስትር ብረታብረት እና ኬሚካል ዘረፍ ማስፋፊያ የተደረገበትን ሼድ አይቶ፣ ገምግሞ እና ለስራ ምን ያህል ምቹ ነው የሚለውን ለባንኩ እንዲያስረዳላቸው በማሰብ መጠየቃቸውን ያብራራሉ ።
ገምጋሚው አካል በተጠየቀውም መሰረት ከገመገመ በኋላ ቦታው ለማምረት ምን ያህል በቂ ነው የሚለውን ለሚመለከታቸው አካላት እና ለልማት ባንክ የሚከተለውን ደብዳቤ ፅፏል ።
‹‹ኅዳር 30 ቀን 2013 በቁጥር ዕ 0117/18 ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተፅፎ ግልባጭ በተደረገልን ደብዳቤ ከልማት ባንክ ለተበደራቸው ማሽነሪዎች የርክክብ ችግር መፍትሄ እንዲሰጠው ባቀረበው ጥያቄ መነሻነት የሚከተለውን ሁለት ገጽ የያዘ ሪፖርት አያይዘን ያቀረብን መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን›› ይላል ።
‹‹ሶለሰብ ሜዲካል ኢኪዊፕመንት እና የቢሮ ፈርኒቸር ማኑፋክቸሪንግ ፒ ኤል ሲ መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንሲንግ የቀረቡለት ማሽነሪዎች በተከላ እና ርክክብ መጓተት እንዲሁም የስራ ማስኬጃ ብድር ሊለቀቅለት ባለመቻሉ ለሶስት ዓመታት በስራ ላይ እንዳልሆነ አሳውቆናል፡፡
በመሆኑም ለጉዳዩ መፍትሄ እንዲሰጠው ለብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጥያቄ አቅርቦ በተቋማችን በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያስችለን ዘንድ ሙያዊ አስተያየት እንድናቀርብ በተጠየቅነው መሰረት የሚመለከታቸውን የልማት ባንክ ሃላፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ በማነጋገር ጤነኛ ግንዛቤ መያዝ የቻልን ሲሆን፤ በቀን 15/04/2013 ዓ.ም ከምርት ልማትና ምርምና ዳይሬክቶሬት የወርክ ሾፕ ባለሙያ በማካተት በጊዜያዊነት የተረከባቸውን ማሽነሪዎችና የማምረቻ ቦታውን ሁኔታ ምልከታና ግምገማ በማድረግ መሰረታዊ የቦታ አጠቃቀም (optimized Working space & machinery dayout) አሟልቶ ስራ መጀመር የሚያስችለው ሁኔታ እንዲፈጠር በሁለቱም ወገን የተመለከትነውን/ የተረዳነውንና በቀጣይ ለመፍትሄ የሚሆን ሃሳብ በጥቅሉ አቅርበናል ።›› በማለት በዝርዝር በደብዳቤው ችግሮቹ እና የመፍትሔ ሃሳቦች ቀርበዋል ።
በቀዳሚነት የተነሳው የኢንዱስትሪው ባለቤት ከልማት ባንክ ጋር ባገቡት የማሽነሪ አቅርቦት፡ ተከላና ርክክብ ውል መነሻነት ለባንኩ ያስያዙትን 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆን ብር በስራ ማስኬጃነት ለመጠቀም ያቀዱ በመሆኑ ይህ ብር ካልተለቀቀላቸው ለሚያመርቷቸው ምርቶች በግብአትነት የሚውሉ ጥሬ እቃዎችን በባንኩ በኩል LC አስከፍቶ ማስመጣት ችግር የሆነባቸው በመሆኑ፤ የካፒታል ዕቃ ዱቤ ግዥ እና ኪራይ ውል የአከራይ ውል አንቀጽ 12 ተራ ቁጥር 12 ነጥብ 1 መሰረት አከራይ የካፒታል ዕቃውን በአቅራቢው አማካኝነት እስከ ተከራይ የማምረቻ ቦታ ድረስ በማጓጓዝ የተከላና የሙከራ ስራዎችን በማጠናቀቅ ለተከራይ እንዲረከብ ያደርጋል የሚለው ስምምነት ሙሉ በመሉ ተግባራዊ አልሆነም፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማሽነሪውን ለግለሰቡ/ ሶል-ሰብ ሜዲካል መሳሪያዎችና የቢሮ ቁሳቁስ አምራች ደርጅት /በሊዝ ፋይናንስ ሲያቀርብ ግለሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚጠበቅበትን ግዴታ /ቅድመ ሁኔታ በወቅቱ አሟልቶ የተገኘ ስለመሆኑና ይህ ከሆነ በኋላ ማሽነሪዎችን ለመረካከብ በነበረው ሂደት ሊያሰራ የሚችል በቂ ቦታ የለህም ተብሎ ለአላስፈላጊ ውጣ ውረድ የተዳረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የሚገኘው የድርጅቱ ማምረቻ ቦታ / ሼድ ያረፈበት 194 ካሬ ለቀረበለት ማሽነሪዎች በቂ አለመሆኑ ከስምምነቱ በኋላ ሲገለጽለት ተጨማሪ የሚሆን ቦታ (በአንድ ደብዳቤ በቀረበ ማስረጃ) 177 ካሬ ከክፍለ ከተማ/ ወረዳው ማስፋፊያ ያስፈቀደ መሆኑን ለባንኩ ቢያቀርብም ባንኩ ድርጅቱ የኪራይ ውል የተገባበት የሰነድ ማስረጃ ይዞ ሲገኝ ስራ መጀመር ይችላል የሚል አቋም እንዳለው መገንዘባቸውንም ጠቁመዋል ።
ከላይ የዘረዘሩትን ጉዳይ መሰረት በማድረግ እንደ ባለሙያ በተመለከቱትና በተረዱት ነገር በቅድሚያ ድርጅቱ ያስመጣቸው ማሽሪዎች በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በዋናነት ለማምረት ከታለመለት የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና ተያያዥ ቁሶች በተጨማሪ ለተለያዩ ቀላልና መካከለኛ ማሽነሪ መለዋወጫ ማምረት የሚያስችሉ ሁለገብ ( multi purpose) መሆናቸውን ማወቅ የቻሉ ሲሆን ከቦታ ጥበት ጋር ለተነሳው ጥያቄ ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሰው ማስፋፊያ / ጭማሪ ቦታ የተባለውን መጠን እንደሚያክል በእነርሱ በኩል በልኬት ባይረጋገጥም በእይታቸው ያሉትን ማሽነሪዎች በተመጣጠነ መልኩ በማስቀመት የጥሬ እቃ ምርት ቦታን ጨምሮ መጠቀም የሚያስችላቸው እንደሚሆን ማየት መቻላቸውን ጠቁመዋል ።
ሆኖም ግን ማሽነሪዎችን አቀማማጥ ስብጥር በሚመለከት በቀጣይ የሚመለከታቸው በኢንስቲትዩታቸው በኩልም ሆነ በሌላ አማካሪ ባለሙያዎች እገዛ የሚያስፈልግ መሆኑን አስታውቀዋል::
ተያይዞ በቀረበው የካፒታል ዕቃ ዱቤ ግዥ እና ኪራይ ውል የአከራይ ውል አንቀጽ 12 ተራ ቁጥር 4 ላይ በ12 ነጥብ 1 መሰረት አምራች ኢንዱስትሪው ከባንኩ ጋር በገባው ውል መሰረት ባንኩ የማሽነሪ ተከላና ኮሚሽኒንግ / ሙከራ ምርት/ አከናውኖ ለማስረከብ የተስማሙ ቢሆንም፤ እንደ ባለቤቱ ገለጻ በተደጋጋሚ ስራ እንዲጀምሩ የሚል ደብዳቤ ስለደረሳቸው ስራውን በእራሳቸው በማከናወን የባንኩ ኃላፊ እና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በተገኙበት ማሽኖቹን አስነስቶ ለምርት ስራ ዝግጁ መሆናቸውን በማሳየት ስራ ለመጀመር ርክክብ እንዲያደርጉላቸው ቢጠይቁም አዎንታዊ መልስ ማግኘት ያልቻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም መሰረት ማምረት የሚችሉ ዘርፈ ብዙ የማምረቻ መሳሪያዎች ለዓመታት እንዲሁ መቀመጣቸው ሁለቱንም አካላት በወቅቱ ሊያገኙት የሚገባውን ውጤት በማዘግየት ፕሮጀክቱን ለትልቅ የሀብት ብክነትና ኪሳራ እየዳረገው እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡
ከላይ ከተገለጸው የማምረቻ ቦታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ድርጅቱ ካስመጣቸው በቁጥር 30 የሚሆኑ ማሽነሪና ኢኩፕመንቶች መካከል አብዛኞቹ ተቀምጠው እና ቦታ ይዘው ያሉበት ሁኔታ ጥሩ እንዳልሆነ መመልከት መቻላቸውንም ጠቁመዋል ።ይህም የመሰረት ፋውንዴሽን ዝግጅትና የጣሪያ ዝቅ ማለት ችግሮች ሲሆኑ፤ ሁኔታው ከማሽነሪ ኢንዱስትሪ ሴፍቲ ፕሮሲጀርና የስራ ላይ አደጋ አንጻር በፍጥነት መስተካከል የሚገባው ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል::
በዚህ ወቅት የተመለከትነው ሌላው ጉዳይ በቦታው የነበሩ ለእንጨት ስራ የሚውሉ ትልልቅማሽነሪዎች በመነሳት በነሱ ቦታ የሚተከሉ የሜዲካል ዕቃዎች ማምረቻ ማሽኖች እንደሚኖሩ ማወቅ ተችሏል ።በአጠቃላይ ይህ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን የቅርብ ድጋፍና ክትትል ካገኘ በአጭር ጊዜ ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪነት የሚሸጋገር እና አሁንም
ሆነ ወደ ፊት በሚያከናውናቸው የምርት ስራዎች በተለይም በጤናው ዘርፍ በሀገራችን ብዙም ያልተስፋፋውን የምርት ወጤቶች እንደመሆናቸው ከሚያስተላልፈው ቴክኖሎጂ በተጨማሪ የውጭ ምርቶችን ከመተካት ኣንጻርና በቀጣይ ኤክስፖርትን ኢላማ ያደረገ የምርት ጥራት ደረጃ እንዲኖረው ከማበረታታት እኳያ ከከተማ አስተዳደሩ በሊዝ የሚያገኘው በቂ የማምረቻ ቦታ እንዲመቻችለት ጭምር ድጋፍ ቢደረግለት ውጤታማና ለብዙዎች የስራ እድል የሚፈጥር ትልቅ ኢንዱስትሪ የመሆን አቅም እንዳለው ማየት ችለናል::
በሌላ በኩል በሀገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካለው ለኢንዱስትሪ ልማት የሚሆኑ ቦታዎች እጥረት/ ውስንነት ያለውን ቦታ በአግባቡ/ በቁጠባ መጠቀም አማራጭ ስለሚሆን አሁን ባለው ሁኔታ ባለሀብቱ የማምረት ስራውን መጀመር እንዲችል በማድረግ በቀጣይ መሆን የሚገባውን ነገር እንዲመቻች የቅርብ ድጋፍ የምናደርግለት መሆኑን እንገልጻለን::
የአቤቱታ አቅራቢው ባቀረቡት ዶክሜንቶችን በመመርመር የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የሚከተሉትን ጥያቄዎችን ለልማት ባንክ ለመጠየቅ በአካል እና በስልክ ሞክሮ የተሟላ መልስ ማግኘት አልቻለም ።
ጥያቄዎችም የሚከተሉት ናቸው፡፡
- በውላችሁ መሰረት ጊዜያዊ ርክክብ የሚል የለም። ነገር ግን ጊዜአዊ ርክክብ የሚያሳይ ስምምነት ተፈፅሟል። ይህ የህግ መሰረቱ እስከምን ድረስ ነው? ጊዜያዊ ርክክብ ከተፈፀመ ከ20 ቀናት በኋላ በ26/8/2010 ዓ.ም ስራ እንድትጀምሩ የሚል ደብዳቤ ባንኩ ለሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጽፏል። በውላችሁ አንቀፅ 3 መሰረት ርክክብ ከተካሄደ በኋላ የመስሪያ ገንዘብ ብር 2, 667, 122/ ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ስልሳ ሰባት ሺ አንድ መቶ አስራ ሁለት ብር ለስራ መስኬጃ እንዲውል ለተከራይ ይለቀቃል ይላል ፡፡
- በውሉ መሰረት የመስሪያ ገንዘቡን ባንኩ ለምን አለቀቀም? ከዚህ በተጨማሪ በካፒታል ዕቃ ዱቤ ግዥ እና ውል መሰረት በአንቀጽ ባልተጠቀሰ አንድ አረፍተ ነገር ቶዮታ ፒካፕ ከEthio Arab International General Trading.L.L.c ከተባለ የUAE አቅራቢ ድርጅት ተከራይ ባቀረበው የካፒታል ዕቃ ዱቤ ኪራይ አገልግሎት እንዲሰጠው ተከራይ ያቀረበውን ባንኩ የተቀበለው መሆኑን ሰነዱ ያሳያል ።ከዚህ በመነሳት ለምን ቲዮታ ፒካፕ ተገዝቶ ለሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አልቀረበለትም? ምርት ሲጀምር የተመረቱ ምርቶች በምን እንዲያጓጉዝ ተፈልጎ ነው ፒካፑ ተገዝቶ ያልቀረበው?
- በሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ስለቦታ ጥበት እና ሌላ ማስፋፊያ እንደሚያስፈልገው ይተነትናል ።ባንኩ ሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማናጀር ያስገባውን ፕሮፖዛል ተመልክቶ አይደለም ወይ ብድሩን የፈቀደው ፤ ምክንያቱም በፕሮፖዛሉ ላይ የተቀመጠው የሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማናጀር የሆኑት አቶ ሰሎሞን በፕሮፖዛለቸው ላይ እንዳስቀመጡት ስራውን ለመስራት 194 ካሬ ሜትር መሬት እንዳላቸው አመልክተዋል ።ባንኩም ይህን አይቶ አይደለም ወይ የኪራይ ውሉን የተፈራረመው እና የማሽን ርክክብ ያደረገው ፤ መሬቱ የማይበቃ ከሆነስ ለምን ከወር በፊት ድርጅቱ ወደ ስራ ይግባ የሚል ደብዳቤ ሊፃፍለት ቻለ ፤ አሁን ላይ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው ተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታ የተጠየቀው ?
- በተራ ቁጥር 3 በተጠቀሰው ደብዳቤ ስራውን የሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማናጀር ቶሎ የማይጀምር ከሆነ የተረከባቸውን ማሽነሪዎች እንደሚነጠቅ እና ለሌላ ደንበኛ እንደሚተላለፍ ይገልፃል ።ይህስ ከተስማማችሁት ስምምነቱ ለምን ተግባራዊ አልሆነም ?
- በሰኔ 7 2010 ዓ.ም በተፃፈው ደብዳቤ መሰረት ማሽኑ ርክክብ ስለተደረገበት ሼድ ህጋዊነት ማረጋገገጫ ሰነድ እንዲያቀርቡ ለሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማናጀር የሆኑትን አቶ ሰለሞንን ይጠይቃል እዚህ ላይ መጀመሪያ ባንኩ የሼዱን ህጋዊነት ሳያውቅ ነው ወይ የማሽነሪ ርክክብ የፈጸመው ?
- በተራ ቁጥር 5 በተላከው ደብዳቤ ስለማሽኖች ተከላ አሬንጅመንት ስዕል የሚገልጽ መልዕክት ተካቷል ።በውላችሁ መሰረ ማሽነሪዎችን የመትከል የባንኩ ግዴታ ሆኖ ሳለ ለምን የሶለሰብ ድርጅት ማሽነሪዎችን እንዲተክል ይደረጋል?
- በውል ስምምነቱ መሰረት ተከራዩ በዓመት 9 በመቶ ወለድ እንዲከፍል ያስገድዳል ።ካልከፈለ ደግሞ 3 በመቶ ተጨምሮበት እንዲከፍል ይገደዳል ። በዚህ ውል መሰረት ለሶስት ዓመት ባንኩ ማግኘት የነበረበትን የወለድ ገቢ አላገኘም ።ይህ ባንኩ ላጣው የወለድ ገቢ ኪሳራው የሚሸፈነው በማን ነው? ተጠያቂውስ ማን ነው?
- በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የብረታ ብረት ኬሚካል ዘርፍ በተሰጠው ሙያዊ ትንታኔ አሁን ማሽነሪዎች የተተከሉበት ቦታ ስፋት ምርት ማምረት ያስችላል የሚል ነው ።
ባንኩ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርነው ለጥያቄዎቻችን የተሟላ መልስ ባይሰጥም የአቶ ሰለሞን ሰብስቤ ጉዳይ በልማት ባንክ በሚገኙ የተለያዩ አካላት እታየ እንደሆነ የባንኩ የኮሚኒክሽን ቢሮ ባልተሟላ መልኩ ነግሮናል ።
የአዲስ ዘመን ዝግጀት ክፍል የተለያዩ ይመለከታቸዋል በባንኩ የሚገኙ አካላት እና ጉዳዩን ይዘው ይሰራሉ የተባሉ የባንኩ ባለስልጣናት በምናነጋግርበት ሰዓት አንድ ነገር መታዘብ ችሏል ።ይህም በአካልም ሆነ በስልክ ያነጋገርናቸው የተቋሙ አመራሮች ጉዳዩን እያዩ ቢሆንም ጉዳዩ እንደማይመለከታቸው ከሚሰጡን አስተያየት መገንዘብ ችለናል ።
ለምሳሌ የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ይልማ አበበ አነስተኛ እና መከካከለኛ ኢንዱስትሪ ኢንተርፕርይዝ ሃላፊ ከሆኑት ለአቶ አስፋው እና ከድርጅቱ ማናጀር ጋር ባደረጉት ውይይት ሼዱ ህጋዊ ፈቃድ የለውም ስለሆነም የድርጅቱ ሃላፊ ከክፍለ ከተማ ወይም ከወረዳ ስለሼዱ ህጋዊነት የሚያረጋግጥ ሰነድ ያቅርቡ የሚል ነው፡፡
ይህን መሰረት አድርገን ለባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ይልማ ስልክ በደወልንላቸው ጊዜ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አስፋው የሚባሉ ሰው እንደማያውቁ እና ምንም አይነት ንግግር እንዳላደረጉ ገልጸውልናል ።
ይሁን እንጂ በክፍል አንድ በቀረበው ጽሁፍ አነስተኛ እና መከካከለኛ ኢንዱስትሪ ኢንተርፕርይዝ ሃላፊ ለሆኑት ለአቶ አስፋው ስለጉዳዩ ጥያቄ ቀርቦላቸው የሰጡት መልስ ከአቶ ይልማ ጋር ስለጉዳዩ በደንብ እንደተወያዩበት እና አቶ ሰለሞን ሰብስቤ ህጋዊ የሼዱን ማረጋገጫ ሰነድ ከክፍለ ከተማ ወይም ከወረዳ ይዘው ሲቀርቡ የስራ ማስኬጃው እንደሚለቀቅ መፃፋችን ይታወሳል ።
በአጠቃላይ የዝግጅት ክፍሉ የግራ እና ቀኙን አነጋግሮ ጉዳዩን በዝርዝር ለአንባቢ ለማቅረብ ያደረገው ጥረት ከባንኩ በኩል አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ ሊሳካ አልቻለም።
ባንኩ ለጉዳዩ ምላሽ ለመስጠት ካለበት የህግና የሞራል ሃላፊነት አንጻር በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን እውነታ ለአንባቢ ለማቅረብ ፈቃደኝነቱ ካለው በየትኛውም ጊዜ ለማስተናገድ ዝግጅት ክፍሉ ዝግጁ መሆኑን እንገልጻለን።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2013