ተገኝ ብሩ
የተዛነፉትን በማቅናት የታረሙትን በማበርታት መጓዙን ቀጥለናል።አገር ለመምራት ሕዝብን ለመወከል ምርጥ ሐሳብ ይዘው የማይቀርቡ፣ ዘመኑን የማይመጥኑ ፖለቲከኞች የዛሬው ዋነኛ ትኩረታችን የወጋ ወጋ ወጋችን ተረኞች ናቸው። ለዚህች ግዙህ አገር ያነሰ ሐሳብ ማቅረብ፣ ይህን ክቡር ሕዝብ የሚያሣንስ መንገድ ማመላከት የሚያዘወትሩ ተሳስቶ አሳሳቾችን በወጋ ወጋ – መውጋትን አሰብን።
ማነህ ተወጊው ና ግባ! ለሕመምህ ፈውስ ይሆንህ ዘንድ ይህን ተቀበል። ከሕመምህ ትፈወስ ዘንድ ከያዘህ ደዌ ትላቀቅ ዘንድ የአንተ ችግር ከሌላው በአሁኑ ወቅት ጎልቶ ታይቶናልና ይህን አዘዝንልህ።መድሀኒቱን ቀመም ቀመም አድርገን ወደ ስሪንጁ ሞልተን አዘጋጅተናል፤ የታመመ ሁሉ በሠልፍ ገባ ገባ እያለ ተወግቶ ይውጣ፤ ጤናው ተመልሶ አገር የምትፈልገውን ሐሳብ ያፍልቅ፤ አገር የምትለወጥበት ትውልድ ይሁን፤ ይኸው ብለናል፡፡
ይህቺን ታላቅ አገር በትንንሽ ሐሳብ ለመግዛት ይህንን ታሪካዊ ምድር በማያሻግር ትርክት ለመግፋት አስበህ ከሆነ ፖለቲከኛው ተው ተብለሀል። እሣት ለኩሶ እሣቱን ሙቁ የሚል ራሱን አቅቦ ሌሎችን የሚማግድ ፖለቲካኛ፣ የእኔ እንጂ የእነሱ ጉዳይ አያገባኝም የሚል ጎጠኛ፤ ትልቅዋን አገር ባነሰ እሣቤ የሚመለከት “አርበኛ” ተብዬ ከዘመኑ ጋር ያልታረቀ ከትውልድ ፍላጎትና መድረሻ ግብ ጋር የማይስተካከል ነውና ወላ በል በሉት።ታክሞ መዳን ከፈለገ በዚህ መርፌ ተወግቶ መሻር ካማረው ግባ በሉት።ድኜ ለእምዬ ኢትዮጵያ መቆም እፈልጋለሁ ከያዘኝ ደዌ ተፈውሼ ለአገሬ እቆማለሁ የሚልን አዎን ግባ በሉት።
አዎ አሻጋሪ የሆነ ትልቅ ሐሳብ ሐሳቡን የሚወልድ በትክክል የሚረዳ ብሎም የሚተገብር ትውልድ፤ ለእኛ መፅናትና ችግር መፍትሄ ነው፤ ለዚህ ደግሞ በጋራ ቆመን ይህንን እንተግብር፤ በዚህ በጎ መንገድ መጓዝ ለሁላችን ጠቃሚ ነው የሚል መፍትሄ አቅራቢ የሕዝቡ ምርጫና የዚህች አገር ዋንኛ ፍላጎት ነው።ያነሱ ሐሳቡችን አሽቀንጥሮ የማይጥል ለዚህች ታላቅ አገር የሚመጥን ትልቅ ሐሳብ ይዞ የማይቀርብ ላስተዳድርህ ምረጠኝ እኔ የተሻልኩ ነኝ ተከተለኝ፤ እኔን ብትመርጥ ወደፊት የተሻለ ዕድል ይገጥምሀል የሚል ፖለቲከኛና የፖለቲካ ድርጅት ለዚህች አገር ፈፅሞ አያሻትም።
ሀገር ለመምራት ካሰባችሁ ይህንን ሕዝብ ማስተዳደር ምኞታችሁ ከሆነ ኢትዮጵያን ያህል ገዝፋችሁ ቅረቡ። ዘመኑን የሚመጥን፣ ትውልዱን የሚገራ የተሳሳተውን የሚያርቅ አገር…አገር የሚሸት ፖሊሲና ስትራቴጂ የሕዝብን እንባ የሚያብስ መፍትሄ ችግራችንን ከሥሩ የሚነቅል አቅጣጫ አመላክቱ። ለዘመናት አልላቀቅ ያለን ለሕዝባችን ትልቅ ሣንካ የሆነው ድህነት እንዲያበቃ፤ ያላግባብ የሕዝቡን ሐብትና ንብረት የሚነጥቁ፣ ሠላምና መተሳሰሩን ብሎም አብሮ መቆሙን የማይወዱ ጠላቶቹን፣ የኢትዮጵያን አንገት መድፋት የሚመኙትን ሴረኞች ተሥፋ የሚያስቆርጥ መላ ይዛችሁ ወደኛ ቅረቡ፡፡
መሠረት በሌለው ትርክት ያለፈን እያነሱ የነገን መንገድ መዝጋት ለዚህ ትውልድ የሚገባው አይደለምና ይህንን አማራጭ አታቅርቡ። ካለፈው ተምሮ የፊቱን አለማቅናት በቂም በቀል ወደኋላ መመለስ ቀድሞ የጀምረነውን ከኋላ ተነስተው እንዲቀድሙን አስደርጎናልና መመለሣችሁ ይብቃ።
የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን የተሻልኩ ነኝና እኔን ምረጡ፤ ቀጣዩ ጊዜያችሁ ብሩህ እንዲሆን እኛን ተከተሉ ብለው ሊወተውቱን ቀጠሮ ይዘዋል። ቁጥራቸው የበዛው እኚሁ የፖለቲካ ድርጅቶች ሥማቸውን ሁሉ ለመያዝ ሣንቸገር አንቀርም። የሐሳብ ልዩነትን ተቀብለው ጥሩውን አድንቀው የተሳሳተውን ተችተው መግራት ባህላቸው ያላደረጉ ፓርቲዎች፤ የውስጥ የእርስ በርስ የፖለቲካ መጠላለፍ ውስጥ ገብተው አሥሬ ፈርሰው የሚጣመሩት ከሥመው አዲስ ሥያሜን ይዘው ብቅ የሚሉት የማናውቃቸው መስለው፤ ይህችን ታላቅ አገር ልምራ እናንተን ልናስተዳድር እችላለን እያሉን ነው።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ የሥልጣኔ ጣራ ነክቷል፤ ዓለም በየዘርፉ መጥቋል በሚባልበት ዛሬ ላይ ተገኝቶ ከክፍለ ዘመናት በፊት አውሮፓዊያን አያዋጣም ብለው ገሸሽ ያደረጉትን ወገኔ ይሉት ጥሪን ማስተጋባት፣ ወገንን መልሰው ከማስቀጠል፣ ሰውን እርስ በርሱ ከማባላት የዘለለ ፋይዳ የለውም። ከዘመናት በፊት ያደረጉህን አትርሣ፤ እወቅ የወጉህን መልሰህ ውጋ መፍትሄ አይደለም፤ ወገኔ ተበድለሀልና ተነስ፤ ተጎድተሀልና ውጣ ለኛ ዛሬ አይመጥንም።
ተበድለሃል ተነስ፤ አንተም ተረኛ ሆነህ ሌሎችን በድል፤ ሌላውን ጉዳ ሣይሆን ማህበረሰቡ ያለበትን ችግር ለይቶ ከችግሩ ሊያላቅቀው የሚችል መላ የሚያሣይ ፖለቲከኛና መሪ ነው የምትፈልገው። እንደ ልቡ ዳቦ ጠግቦ ያልበላ አንዲት ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር በረሐብና በእርዛት የሌሎችን ዕርዳታ የሚጠብቅ ሕዝብ፤ እንደ አገር በምግብ እህል ራሱን ያልቻለ ሕዝብ ለክፍለ ዘመናት ተመፅዋች የሆነን ባላገር ግራ ማጋባት ምን ይሉታል?
ለገበሬው ማረሻና ማለስለሻው ያው፣ መሬቱ ፆሙን እንዳያድር የሚዘራውን ሠብል እንካ እንጂ አገሩን እንዲወጋ ወገኑን እንዲጨርስ፣ እንዲጨራረስ ጥይት የሚያከፋፍል፣ ነገን የማያስብ ፖለቲከኛ፣ ትውልድ እንዳይሻገር እንዳይለወጥ የሚመኝ ምረጡኝ ባይ አያስፈልግም።ረሐብህን ማስታገሻ ይሆንህ ዘንድ ማረሻ ዝግጁ አርግ፣ በሬዎችህን ጠምደህ እረስ፣ ይህንን ዘርተህ አጭደህ ጎተራህን ሙላ ከማለት ይልቅ እንካልህ ጠብመንጃ የገላመጠህን ግደል፤ ይኼውልህ ጥይት እርስ በርስህ ተጫረስ ብሎ ማስታጠቅ ምን ያስገኛል?
ከድህነት የተላቀቀ ሕዝብና በአንድነት የቆመ ማህበረሰብ የሚዳፈር ፈጽሞ አይኖርም። ለዚህ ደግሞ አገር በአንድነት እንዲቆም መስበክ ነው መፍትሄው።ሕዝብ ለእርስ በርስ መዋደድና ለአገር ክብር እንዲያብር፣ ጠንካራና የማይደፈር አገር እንዲኖረን፣ ራሱን ከተመፅዋችነት ያላቀቀ ሕዝብ እንዲበረክትልን፤ በዓለም አቀፍ መድረክ ድምፁ የሚሰማ ሀያል አገር ለመመሥረት ተበድለሀል እያሉ መስበክ ሕዝቤ ውጣ እያሉ መፎከር መፍትሄ አይሆንም።
አዎ! ለምርጫው ምርጥ ሐሳብ እንጂ የእኔ ብቻ ተቀበሉ የሚል አያሻንም። እኛን ብሎ የሚያስተሳስረን፣ አገራችን የሁላችን ናት ሁላችንም በእኩል እንጠቀም፤ ለዚህ ደግሞ እንዲህ ዓይነት የጋራ መፍትሄ አለን የሚለን ነው ለአገራችንም ለእኛም የሚመጥን፤ የሚገጥምም።
ፓርቲዎቻችን አገሬ ሕዝቤ ትሉ የለ? ማለታችሁ የእውነት ከሆነ ይህንን አድርጉ። ቀድማችሁ አገሬን በሉ፤ እሷንም ውደዱ፣ ለእርስዋ መስዋዕት ለመሆንም ተዘጋጁ። ከዚያም “ሕዝብ ምን ይፈልጋል?” መነሻችሁ ይሁን። መመረጥን ከፈለጋችሁ ለምርጫው አሻጋሪና አሣታፊ ተተግብሮም መፍትሄ የሚያመጣ ሐሳብ አቅርቡ። በዚያም አገር ይምረጣችሁ፤ ሕዝብ ይቀበላችሁ። አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013 ዓ.ም