ተገኝ ብሩ
ህምምም ደሞ ብለህ…ብለህ ራስ ወዳድነትን ማበረታታት ጀመርክ።ወቸው ጉድ! ትሉ ይሆናል።ራስ ወዳድ ሁን ማለቴን ልክ አይደለም ማለታችሁም አይቀርም።እኔ ግን አሁንም ደግሜ ልላችሁ ነው።አብዝታችሁ ራስ ወዳድ ሁኑ፡፡
አንዳንድ ልማዳዊ ምክሮችን አልቀበልም። ይልቁንም ምክሮቹን በሌላ አቅጣጫ መመልከት / ባልታዩበት መመርመር / እወዳለሁ።ለምሣሌ “ራስ ወዳድ አትሁን” የሚለውን ልማዳዊ ብሂል እኔ “ሁን” በሚለው መለወጥ ፈለኩ። ጎበዝ ሰው ራሱን ካልወደደ እንዴት ሌሎችን ሊወድ ይችላል።ቀድሞ ለራሱ ክብር ካልሰጠ ለሌሎች ክብር እንዴት ሊጨነቅ ይችላል?
ሰው ከምንም በላይ አስቀድሞ ራሱን መውደድ አለበት።ራሱን ማክበር ቅድሚያ ተግባሩ ሊሆን ይገባል።ሰው ራሱን ካልወደደ ስለራሱ ክብር ካልተሰማው እንዴት ሌላውን ሊወድና ክብር ሊሰጥ ይቻለዋል? በፍፁም ስለዚህ መጀመሪያ ራሱን መውደድ፣ ለራሱ ክብር መስጠት፣ ለራሱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር የመጀመሪያ ተግባሩ ሊሆን ይገባል።ራስ ወዳድ የሆነ ስለራሱ ዋጋ የሚሰጥ ሰው ራሱን ስለሚወድ ሰውን አይጎዳም።ምክንያቱም ሰዎች መልሰው የሚወደውን ማንነቱን ክብሩንና እሱነቱን እንዲነኩበት ስለማይፈልግ ራሱን መውደድ ይገባዋል።
በአንፃሩ ራሱን ለማይወድና ራሱን ለሚጠላ ሰው ዓለም ምኑም ናት። ቀድሞውንም ራሱን ጠልቷልና፤ ሰዎች እሱን ቢያከብሩት፣ ቢያዋርዱት ከፍና ዝቅ አድርገው ያልዋለበትና ያልተገኘበት ቢያደርሱት ምኑም አይደለም።ስለዚህ እሱም ለሌሎች ክብርና ፍቅር ሊሰጥ ከቶም አይችልም። ሌሎችን ማክበርና ማላቅ እንዴት ሊለምድስ ይችላል?። ራሱን በመናቁና በመጥላቱ ውስጥ ጥሩነት ከየት ሊቀርበው ይችላል?
ራሱን የጠላ ሰው ሰዎችን በፍጹም ሊወድ አይችልም።የሚታየው ራሱን የጠላበትን ጥላቻ ሌሎች ላይ አግዝፎ ለማሣየት ይጥር ይሆናል እንጂ ራሱን የጠላበትን ምክንያት ሰዎች በመውደዱ ነው ብሎ አያምንም።በዚያ ራሱን በጠላበት ምልከታው ሌሎችን ያያል፤ በዚያ ራሱን በናቀበትና ባዋረደበት ስብዕናው ውስጥ ሌሎችን ማዋረድ እንጂ ማክበር አይሆንለትም፡፡
ነገር ግን ይህ ሰው ራስ ወዳድ ቢሆን የሚወደው ማንነቱና ክብሩ እንዳይነካበት የሌሎችን ማንነትና ክብር ይጠብቃል።የሚወደው እሱነቱ ምቾት እንዳያጣ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩለት ሰዎችን ይፈጥራል ፤ይቀርባልም።ሰው ሰዎችን ለመግደል መተኮስ የሚፈራው እኮ የተኮሰው ሰው እንደሚሞት ያውቃል። ከዚያ በኋላ ራሱ ተጠያቂ እንደሚሆንና የነበረበትን ማንነትና ነፃነት እንደሚያጣው የሠራው ወንጀልም ራሱን እንደሚጎዳው ስለሚያውቅ ያን ከማድረጉ በፊት አስልቶ ያስባል። ቢያደርግ እንኳን ተግባሩ ወይም ድርጊቱ የሚያመጣበትን ፈተና ለመጋፈጥ ራሱን ዝግጁ አድርጎ ነው፡፡
ራሱን ከሚጠላ ሰው ራስ ወዳዱ ሰው የተሻለ ስብዕና ይላበሣል።በራስ መውደዱ ውስጥ የሚጠብቀው የሌሎች ክብር አለ። በራስ መጥላቱ ውስጥ ደግሞ የከፋ ጥላቻ ከመፍጠርና በዚያ ጥላቻ ምክንያት ሌሎችን መጉዳት እንጂ የሌለ ተፈጥሮው ከየትም ከርሱ ሊመነጭ አይችልም። ስለዚህ የተሻለው ራስ ወዳድ መሆን ነው።ያኔ ለራስ ምቾት ተብሎ የሌሎችን መልካም ሁኔታ መፍጠር ይቻላል።ስለዚህ ጎበዝ ማንንም እንዳትሰማ፤ ራስህን ውደድ፤ ኧረ እንዲያውም የመውደድ ጥግ ላይ ደርሰህ ራስህን ውድድድድድድ አድርግ።
የራስ ወዳድነት ሌላ ምልከታ ሰጥተነው የሌሎችን የራስ ለማድረግ መሞከር እኔ ብቻ ከፊት ልሁን ሌሎችን ተከታይ ላድርግ ስለሚል ስግብግብነት ግን አይደለም እያልኩ ነው ያለሁት። እንደዚያ ከተረዳችሁኝ ፍሬን ያዝ አድርጉ፤ አደራ።
የራስ ወዳድነት ምልከታዬ ወይም የሐሳቤ ማጠንጠኛ ትርጉሙ ካልገባችሁ ልክ ነው።የተሳሳታችሁት እናንተ ሣትሆኑ እኔ ነኝ።ስትረዱኝ ግን እውነትም ሰው ራስ ወዳድ መሆን አለበት ትላላችሁ።ራስ ወዳድ መሆን ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይገባችኋል።ከዛሬ ጀምሮ እያንዳንዳችሁ ራሣችሁን ከምንምና ከማንም በላይ መውደድና ማክበር እንዳለባችሁ ትረዳላችሁ፡፡
ራስ ወዳድነትን እኔ በገለፅኩት መንገድ ተረድተን ከተገበርነው ምድር ላይ ያለ ሁሉ ለራሱ ሲል ሌሎችን ማስከፋቱን የሚተው አይመስላችሁም። ሰው ለራሱ ምቾት ዘላቂነት የሌሎችን ምቾት ይጠብቃል።በዚህም የተሻለ እና መልካም የሆነች የሰው ልጆች የእርስ በርስ መከባበርና መተሳሰብ ከፍ ያለባት ምድር ማየት ይቻላል፡፡
ይኼኛው ራስ መውደድ ግን ይበልጥ ጨለማ እንጂ ብርሀን አያቀርብም።ከሌላው እየነጠቁ የኔ ብቻ ማለትን፣ ሌላውን እየነሱ ራስን ብቻ ማጋበስን ግን አላልኩም።ሥግብግብነት እኮ በቃኝ ከማለት የሚያፈነግጥ ጥራዝ ነጠቅነት ነው።ይኼኛው ራስ ከመውደድ በጣም የተለየና በማንኛውም ሰውና ፍጥረት የሚጠላ ስብዕና የሚያላብስ ነው፡፡
ምድር ላይ በክፋት የሚነሱ፤ የሰው ልጆች ሲያስታውስዋቸው ምነው እነሱ ባልተፈጠሩ የሚባሉ ሰዎችን በደንብ ብንመረምራቸው ራሳቸውን ፍፁም የጠሉና በዚያ ጥላቻ ውስጥ ባተረፉት እብሪት ሌሎችን ፍፁም በሆነ ጥላቻ የረሸኙ፣ የገደሉና ለሰዎች ክብር ያልነበራቸው ናቸው።ራሣቸውን ስለጠሉ መልካም የሆነ ምቾትን ከመፍጠር ይልቅ በውስጣቸው ያለ የግል ጥላቻ ሌሎች ጋር ለማድረስ ተጉ።በዚህም ዓለም በመጥፎ የምታነሳቸው ክፉዎች ሆነው አለፉ፡፡
ሰው በራሱ በተለየ ከሌሎች ፈፅሞ በራቀ መልኩ የተገኘ ወይም የበላይ ነኝ ብሎ ካመነ ነው ችግሩ። ራስ ወዳድ መሆኑ ነውርነት የለውም፤ ፍፁም ትክክለኝነት እንጂ።ውዶቼ ራሱን የሚወድ ሰው ሰዎች የሚወደውን ማንነቱን እንዲነኩበት የሚያከብረውን እሱነቱን እንዲያጎድፉበት ይፈልጋል? በፍፁም። ስለዚህ እሱ ራሱን ስለሚወድ ሌሎች የሚወዱትን ማንነት አይነካም፤ የሰዎችን መብት አይጋፋም፤ ምክንያቱም ሰዎችም እንደ ራሣቸው የሚወዱት ማንነት እንዳላቸውና ያን ማንነታቸውን በማንም በምንም እንዲጎል ወይም በተሳሳተ መልኩ እንዲነካባቸው አይፈልጉማ።
ሰው ሆይ! በድጋሚ ልንገርህ፤ ራስ ወዳድ ሁን።ከማንም እና ከምንም በላይ ራስ ወዳድ ሁን ወዳጄ።ራስህን ጢነኛነት በተሞላበት መንገድ ስትወድ ሌሎች የምትወደውን ማንነትህን እንዳይጋፉብህ ብለህ ሣትወድ ተወዳቸዋለህ። ለራስህ ምቾት ስትል ለሌሎች ምቾት ትተጋለህ።ያኔ አንተም ሌሎችም ውድ የሆነ ዓለም ትፈጥራላችሁ።አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013 ዓ.ም