መሄድ እወዳለው…መራመድ ደስ ይለኛል። በመሄዴ ውስጥ ብዙ ነገር አይቻለሁ…ከኛው የኛው የሆኑ ብዙ ትዝብቶችን ታዝቤያለው።ከትዝብቴ አንዱን እነሆ። ወቅታዊው የሀገራችን ጉዳይ ግርም ያላለው ማን አለ? እርግጠኛ ነኝ። ሁላችሁም ግርም ብሏችኋል።ከመገረም አልፋችሁም ይቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው የምትሉም እንዳላችሁ አልጠራጠርም።እኔም ከእናንተ ውስጥ አንዱን ሆንኩና ትዝብቴን ላካፍላችሁ ብዕሬን ከልሙጥ ሉኬ ጋር አወዳጀሁ። አገር የልዕልና ጥግ ናት።የእኔና የእናንተ፣ ያንቺም የእሱም የሁላችንም እውነት።አገር መከበሪያ ናት፣ በትናንት በዛሬና ነጋችን ውስጥ የተሳለች አምላካዊ ሥዕል። አገር የእያንዳንዳችን የማንነት ማህተማችን ናት። ስለ አገር ሲነሳ ጥላሁን ገሠሠ ትዝ ይለኛል።ስለ አገር ሲነሳ በባንዲራዋ ፊት ያነባው ሀይሌ ገብረ ሥላሴ ይታወሰኛል።አገር ይቺ ናት…በልባችን በነፍሳችንም ውስጥ ያለች፣ የትም ይዘናት የምንዞር። ሥሟን በሰማን ቁጥር፣ ባንዲራዋን ባየን ቁጥር እንባችን የሚመጣ፣ ስለ ደግ ሕዝብ ሲወራ ባር…ባር የሚለን ይቺ ናት አገር።ይህቺን ነው ኢትዮጵያ የምላችሁ።ስለ ሀገራቸው ክብር ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ከሀገሬ በፊት እኔን ያሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እዚያም እዚህም ሞልተዋል።እነበላይ ዘለቀ፣ እነአብዲሣ አጋ፣ እነዘርዓይ ደረስ የአገር ፍቅርን ጥግ ድረስ ያሳዩን ምልክቶቻችን ናቸው።
የአሁኑ የእኔና የአንተ ትውልድ ግን ይኼን እውነታ ዘንግቶታል።አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ እስኪጠፋው ድረስ ሩጫው ሁሉ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሆኗል።አሁን…አሁን እማ ጭራሽ የምናየው፣ የምንሰማው ሁሉ ከኢትዮጵያዊነት ባህልና ሥርዓት ያፈነገጠ የጭካኔ የመጨረሻው ማሣያ እየሆነ የመጣበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።ወጣቱ በምክንያት ከመኖር ይልቅ በሥሜት መመራትን የመረጠበት ጊዜ፣ የተማረው በእውቀቱ አገር ከመጥቀም ይልቅ የውሸት ተረት እየፈጠረ በሕዝቦች መካከል የጠብ ቁርሾ መንዛትን የተካነበት ዘመን ላይ ነን።በየቦታው በየሀገሩ የምንሰማው አንድ ዓይነት ሆኗል።ሐዘን፣ ሞት፣ ስደት ያልሰማንበት ጊዜ የለም።በየቀኑ በየሚዲያው የምንሰማው ክፉ ወሬ ብቻ ነው።በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ይኼ ሁሉ በደልና ጭቆና እየደረሰ ያለው ተማርን በሚሉ ራስ ወዳዶች መሆኑ ነው።ከአገርና ሕዝብ ሀብት ላይ ቀለብ እየተሰፈረላቸው ተምረው መፍትሄ እንደመሆን ተመልሰው አገር የሚያፈርሱ ተበራክተዋል።ያጎረሳቸውን የእናታቸውን እጅ መልሰው የሚነክሱ ወጪት ሠባሪ ትውልድ የበዛበት አስከፊ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
የእስካሁኗ ኢትዮጵያ ባልተማሩ ልጆቿ የተሠራች ናት።ይኼ ሁሉ ገናናነታችን በነሱ የመጣ ነው።እኛ የተሠራ ከማፍረስ፣ አንድ ሆኖ የቆመን ሕዝብ ከመለያየት ባለፈ አሁን ላለችው ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ጥቅም እየሰጠን አይደለም።በብዙ ችግር፣ በብዙ ድህነት፣ በብዙ ማጣትም ተተብትባ የምትኖር አገር ተሥፋዋን በሰነቀችባቸው ልጆቿ እንዲህ መሆኗ አሣዛኝ ነገር ነው።ወጣቱን ለልማት ከመጠቀም ይልቅ ጦርና መሣሪያ አስታጥቀው ለእኩይ ዓላማ የሚያሰለጥኑ፣ መብቱን በሠለጠነ መንገድ ከመጠየቅ ይልቅ በረብሻ እንዲጠይቅ በማድረግ የግል ጥቅማቸውን የሚያስፈጽሙ አላስፈላጊ ተልዕኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ በየቦታው እየታዩ ነው።በተለያዩ ቦታ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ የሚደርሱ ውድመቶች ሥሜታዊውን ወጣት መጠቀሚያ በማድረግ የተከሰቱ ናቸው። እነሱ በሞቀ ቤታቸው ጮማ እየቆረጡ፣ ውስኪ እየተጎነጩ ተቀምጠው ወጣቱን በጊዜያዊ ጥቅም በመደለል ወደ እሣት ሲማግዱት ኖረዋል። መማራችን ለአገርና ወገን ካልሆነ ጥቅሙ ምን ላይ ነው? እኔ ካልተጠቀምኩ፣ የእኛ ሐሳብ ካልሆነ በሚል አጉል አስተሳሰብ የነገውን ተሥፈኛ ወጣት ለጥፋት ማነሳሳት ተገቢ ነው ብዬ አላስብም። በውስጧ በርካታ ዩኒቨርስቲዎችን ገንብታ እያስተማረች የተማረ ዜጋ አፈራለሁ ብትልም የተማሩ መሃይማንን አፍርታለች።ዓለም በሥልጣኔ መጥቃ ጨረቃ ላይ ቤቷን በሰራችበት በዚህ ሥልጡን ዘመን ላይ እየኖርን ለዓለም ሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ የሆነን ቀደምት ሕዝቦች እኛ እርስ በርስ መግባባት አለመቻላችን የምንጊዜም ጥያቄዬ ሆኖ ጭንቅላቴ ውስጥ አለ፡፡
ወጣቱ ከጥፋት ሀይሎች ራሱን በማራቅ ለአገር የሚጠበቅበትን ወጣታዊ ግዴታውን መወጣት ሲኖርበት ከድሀ እናት መቀነት በተዋጣ ገንዘብ የተሰራን መሠረተ ልማት ማፍረስ እስኪ ይኼ ምን የሚሉት ሥልጣኔ ነው? ኢትዮጵያዊነት እንዲህ አይደለም።የአባቶቻችን ሥርዓት ይኼ አይደለም።ወጣቱ በቤተሰቡ መሠራት አለበት። ፈርሀ እግዚአብሄር እንዲኖረው ሆኖ ማደግ አለበት። የተባረከ ሆኖ ስለ አገር ፍቅር እየተነገረው ማደግ ነገ ለሚኖረው ሕይወት ወሣኝነት አለው እላለው። አሁን ላይ ነውጥ የሚፈጥሩ፣ ለአገር ሥጋት ሆነው የምናያቸው ሰዎች በሥርዓት ያላደጉ ልጆች ናቸው። አገር…አገር ሆና እንድትቀጥል ታላላቆቹን የሚያከብር፣ የአባቶቹን ሥርዓት ያልናቀ ትውልድ ያስፈልጋል። ሰሞኑን ወደ ፒያሣ እየሄድኩ ታክሲ ውስጥ ነበርኩ። ሕጻን ልጅ የታቀፈች አንድ ሴት መንገድ ላይ ትሣፈራለች። ከፊት ለፊት ቦታ ስላልነበረ ኋላ ወንበር መቀመጥ ግድ ነበረባት። ከልጇ ጋር ስላልተመቻት ከፊት የተቀመጠውን ወጣት ‹አባ ቦታ አትቀይረኝም፤ ልጅ ስለያዝኩ ነው› አለችው። ‹ኋላ መቀመጥ አልወድም› ሲል መለሰላት።በሚቀጥለው ወንበር ላይ የተቀመጡ አንድ አባት በወጣቱ ንግግር እያዘኑ ‹ምናለበት ብትነሣላት? መታዘዝክ እኮ ትልቅነትህን ነው የሚያሣየው› ሲሉት።
‹እኔን ከሚሉ ለምን እርሶ አይነሱላትም? ሲል ትዕቢታዊ ምላሽ ሰጣቸው።መልስ አልሰጡትም…በልባቸው ግን ትውልዱን የሚረግሙ ይመስለኛል። ‹አምላኬ ሆይ ምነው እዚህ ዘመን ላይ ጣልከኝ? የሚሉ ይመስለኛል። ልጅ ለያዘችው ሴት ቦታቸውን ለቀው ኋላ ወንበር ተቀምጠው ሲተክዙ ነበር፡፡
ብዙ የዓለም አገሮች ልጆቻቸውን የሚያስጠኑት አንድ አባባል አለ… ‹ሀገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ ሣይሆን እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩላት› የሚል።ይህ አባባል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበረው የጆን ኦፍ ኬኔዲ ይሁን እንጂ ብዙ አገራት የሚጋሩት እውነታ ነው።ብዙ ኢትዮጵያዊያን ከአገር መውሰድ እንጂ ለአገር መስጠትን አያውቁበትም። የሁልጊዜ ጥያቄያቸው ሀገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ? የሚል ነው። እንዲህ ዓይነት እኩይ አመለካከት አገር ከማጥቃት ባለፈ ጥቅም የለውም። ይኼ አስተሳሰብ ነው ዛሬ ላይ ሀገሬን እንደ በግ ያረዳት። ለሙስናና ሥልጣንን ያላግባብ ለሚጠቀሙ ሕገ ወጦች በር የከፈተው። ወጣቱ ለሀገሩ ተሥፋና የብልፅግና ምንጭ እንጂ የጥፋት ምክንያት መሆን የለበትም። በመልካም ሐሳብ ተሞልቶ ለወገኑ አለኝታ እንጂ ሥጋት የመሆኑ ነገር ማክተም አለበት። አባቶቻችን ታላቅ አገርና ታላቅ ሕዝብ እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም ለነገ ልጆቻችን የምናስረክባት መልካምና በሁሉ ነገሯ የምትደነቅ አገር ልንፈጥር ይገባናል። ይኼ የመንግሥት ወይም የተወሰኑ ሰዎች ሀላፊነት ሣይሆን የሁላችንም ሀላፊነት ነው። መማር ማለት መፍትሄ መሆን ማለት ነው። እኛ ግን እውቀታችንን፣ ጥበባችንን ሁሉ አገር ለማፍረስና ለዘመናት ተዋዶና ተከባብሮ ተቻችሎም የሚኖርን ሕዝብ ለመከፋፈል እየተጠቀምንበት እንገኛለን።
ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ራስ ተኮር ሆነን ብዙ የሆነችልንን አገርና ሕዝብ ስንጎዳ ስናስጎዳም ቆይተናል። መማራችን ምኑ ላይ እንደሆነ አልገባኝም። የድሮ አባቶቻችን ባልሰለጠነ ዘመን አክሱምና ላሊበላን የመሰለ ለዘመናዊው ዓለም ትንግርት የሆነ ታላቅ የሥልጣኔ ምልክትን ትተውልን ከማለፋቸውም ባሻገር በአንድነቷ የምትደነቅን አገር ሰርተውልን አልፈዋል። እኛ ተማርን የምንለውና እጅግ በሠለጠነው ዘመን ላይ ያለነው የዛሬዎቹ ግን ያልተማሩ አባቶቻችን ያወረሱንን ታላቅ አገር በማፍረስ ደፋ ቀና እንላለን። በሕዝቦች መካከል ጥላቻና መለያየት እንዲኖር፣ በፍቅር ፈንታ ጥላቻን፣ በአንድነት ፈንታ መለያየትን በመስበክ
ለአገራችንም ለሕዝባችንም ነቀርሣ ሆነን እየኖርን ነው። በተለያየ የአገራችን ክፍል እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ ፊደል በቆጠሩ ከሥማቸው በፊት ማዕረግ በቀጠሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ነው።የአገራቸውን ትንሣዔ በማብሰር ለመጪው ትውልድ የበለፀገች አገርን በማውረስ ፈንታ ሥር በሰደደ እኔነት አገር ማፈራረስና ሕዝብ መለያየት ከነውርም በላይ ነውር ሆኖ ነው የሚታየኝ። እስኪ የትኛው የተማረ ዜጋ ነው ለዚች አገር መድህን ሲሆን ያያችሁት? ጎኗ ላይ ተጣብቀው እንደ መዥገር ደሟን ከመምጠጥ ባለፈ የፈየዱት መላ አለ ብዬ አላስብም። አስተምራ ለቁም ነገር አብቅታቸው ነበር፤ ካላት ላይ ከሌላት ላይም ቀንሳ ቀን አውጥታቸው ነበር፣ በድህነት ጎኗ ብዙ…ብዙ ሆናላቸው ነበር። ዛሬ ላይ ለክብሯ ፊታውራሪ ከመሆን ይልቅ ውርደቷን ናፍቀው ከፊት ቆመው በለው ይላሉ። ድህነት ለዘመናት ተብትቦ በያዛት አገር ላይ እንዲህ ዓይነት ጭካኔ ሥርየት የሌለው በደል ሆኖ ነው የሚታየኝ።በፖለቲካው፣ በምጣኔ ሀብቱ፣ በማህበራዊው በሁሉም ውስጥ የክፋት እጃቸው አለ።በእውቀታቸው ውስጥ እውነት የለም።በልባቸው ውስጥ አምላክ የለም። ትናንት ራስ ወዳድ ነበሩ፤ ዛሬም ራስ ወዳድ ሆነው ይኖራሉ፡፡
አብዛኞቹ የአገራችን ባለሥልጣናት ሕዝብ ከማገልገል ይልቅ ራሳቸው እየተገለገሉ ያለበት የፖለቲካ መዋቅር ነው ያለው። በሕዝብ ገንዘብ ልጆቻቸውን አውሮፓና ኤሽያ ውድ ትምህርት ቤት በውድ ክፍያ የሚያስተምሩ ብዙዎች ናቸው። ለድሀው የሚሆን ግን ምንም የላቸውም። በአገር ሥም በሣምንት ሦስት ቀን ስብሰባ ይቀመጣሉ፤ ለውጥ ግን የለም። በዓመቱ መጨረሻ የውሸት ሪፖርት ለበላያቸው ያቀርባሉ። ወጣቱ በሥራ አጥነት ወደ ዘረፋ በገባበት ሰሞን ለዚህ ያክል ወጣት የሥራ ዕድል ፈጥረናል ሲሉ ይዋሻሉ።ሕዝብ የተማረ ሣይሆን የተባረከ መሪ፣ የተባረከ ባለሥልጣን፣ የተባረከ አገልጋይ ይፈልጋል። ሰባ ከመቶ ወጣት በሆነባት አገር ላይ ለወጣቱ ምንም የለንም ማለት አደጋ አለው።ወጣቱን ከፍጅት፣ ከተሥፋ መቁረጥ የሚያርቅ ሥራና የሥራ ፈጠራ ዕድል መመቻቸት አለበት።መንግሥት ለወጣቱ የሚሆን ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን አቅዶ መንቀሳቀስ አለበት። የአስተሳሰብ አብዮት ያስፈልገናል።የአንድነት የፍቅር ዓለም መገንባት ግድ ይለናል።
ተምረን የተገነባ ከማፍረስ፣ መኪና ከማቃጠል፣ ሕዝብ ከማፈናቀል የዘለለ ለዚች ድሀ አገር የጠቀምነው ነገር የለም። የራሳቸውን የሥልጣን ጥም ለማርካት ካልሆነ በስተቀር ለሕዝብና አገር ወግነን ያደረግነው ምንም የለም። በትንሹ እንኳን ወቅታዊውን የአገራችንን የፓርቲ አቋም ብናየው ተማርን በሚሉ ሰዎች ተሞልቶ እዚህ ግባ የማይባል ሐሳብ ሲያራምዱ ማየት አዲስ ነገር አይደለም። ብዙ ነገር ባጣ ድሀ ሕዝብ ውስጥ እየኖሩ ለድሀው የሚሆን አንድ እንኳን ተስፋ ሰጪ ሐሳብ የላቸውም። የሕልማቸው መጀመሪያም መጨረሻም ሥልጣን ነው።ሕዝብ የእናንተን ወሬ የሚሰማበት ጊዜ ላይ አይደለም – ወደ ልማት ግቡ። እውቀታችሁን ላስተማራችሁ ወገናችሁ አድርጉ እንጂ ምንም የማያውቀውን የድሀ ልጅ መጠቀሚያ ከማድረግ ወጥታችሁ ፊታችሁን ወደ አንድነት መልሱ። በእናንተ ፍቅር ማጣት፣ በእናተ የፖለቲካ ሽኩቻ ምንም የማያውቀው ምስኪን ሕዝብ እየተሰቃየ ነው።ከጥያቄ በቀር መልስ በሌላት አገር ላይ ነን።በቀን ሦስቴ መብላት ባቃተው ድሀ ሕዝብ መካከል ናችሁ፤ በሥራ ማጣት መሄጃ ባጣ ወጣት መካከል ናችሁ። የውስጥና የውጪ ሀገራዊ አጀንዳ የበረከተበት ሰሞን ላይ ናችሁ መፍትሄ አምጡ እንጂ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አትሁኑን። በሚጠቅመን ላይ እንጂ በማይጠቅመን ጉዳይ ላይ የራሳችሁንም የሕዝባችሁንም ውድ ጊዜ አታባክኑ ስል ምክር ብጤ ጣል በማድረግ ላብቃ።መቋጫዬን ግን በሁለት ሥንኝ ግጥም አደረኩ፡፡
‹አገር ማለት ሰው ነው የኔና የአንተ ሐቅ፣
በተጋፋን ቁጥር ተያይዘን ምን
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013 ዓ.ም