አስናቀ ፀጋዬ
አብዛኛዎቹ ወጣቶች ከአካባቢያቸው ችግርና ክፍተት ተነስተው አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦችን በመፍጠርና ወደ ተግባር በመቀየር ራሳቸውን ለመለወጥ የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም አይደለም።
ብዙዎቹም የራሳቸውን የቢዝነስ ሃሳብ ከመፍጠር ይልቅ ተቀጥሮ መሥራትን እንደመጨረሻ አማራጭ ይወስዳሉ። ይህን ለማድረግ ለምን እንደማይችሉ ሲጠየቁም የአብዛኞቹ መልስ ‹‹መነሻ ገንዘብ የለኝም›› አልያም ‹‹ቢዝነስ ብጀምር ልከስር እችላለው›› የሚል ይሆናል።
ከዚህ በተቃራኒ ግን ከአካባቢያቸው ችግር ተነስተውና የተመለከቱትን ችግር ወደ ቢዝነስ ሃሳብ በመቀየር የተሳካ ንግድ አካሂደው ለውጤት የሚያበቁ ወጣቶች ቁጥርም ቀላል አይደለም። የእነዚህ ወጣቶች ውጤታማነት ሚስጥር ታዲያ ይዘው የተነሱትን የቢዝነስ ሃሳብ ለማሳካት በቂ ጥረት ማድረጋቸውና ለሥራቸውም ቁርጠኛ መሆናቸው እንጂ ሌላ የተለየ ተአምር ፈጥረው አይደለም። የቢዝነስ ሃሳባቸውን ወደ ንግድ በመቀየር ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያካሄዱ ካሉ ወጣቶች ውስጥም አንዷ ኢማን ዝናብ ናት።
ኢማን ዝናብ የሥራ ፍቅር ያደረባት ገና ልጅ እያለች ነው። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ትምህርቷን እየተከታተለች ቤተሰቦቿን በሚገባ በሥራ አግዛለች። ያደረባት ጥልቅ የሥራና የንግድ ፍቅር ትምህርቷን ከአስራ ሁለተኛ ክፍል እንድታቋርጥ አስገድዷታል። የሞሪንጋን ቅጠል በመፍጨትና በተለያዩ መጠኖች አሽጎ ለገበያ በማቅረብ ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረው የንግድ ህይወቷ በጥቂት መነሻ ካፒታል ተንደርድሮ ዛሬ ላይ ወደ ዲተርጀንትና ኮስሞቲክስ ንግድ ተቀይሯል።
ይህን የዲተርጀንትና ኮስሞቲክስ ንግድ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ታዲያ ወጣቷ ዛሬም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛልች። እኛም የወጣት ኢማን ዝናብ የሥራ ትጋትና የንግድ እንቅስቃሴ ለሌሎችም ወጣቶች አስተማሪ ይሆናል ብለን ስላሰብን የዛሬ የሲራራ እንግዳችን አድርገን ጋብዘናታል።
ወጣት ኢማን ዝናብ ትውልዷና እድገቷ ጅማ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በህብረት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ ጅሬን በተሰኘ ትምርት ቤት ተከታትላለች። የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቷን ሳታጠናቅቅ ከጅማ ወደ አዲስ አበባ ከአስር ዓመት በፊት ተመለሰች። ወደ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላም ትዳር ይዛ ኑሮን መግፋት ቀጠለች። ከባለቤቷ በኩል ብቻ የሚገኘው ገቢ በቂ አለመሆኑን በመረዳትም ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንዳለባት ተረዳች።
እናቷ የስኳር በሽታ ታማሚ በመሆናቸው ለመድሃኒትነት የሞሪንጋን ቅጠል በሻይ መልክ አፍልተው በመጠቀም በሽታው ሲሽርላቸው የተመለከተችው ወጣት ኢማን ቅጠሉን በዱቄት መልክ በማዘጋጀት ለገበያ የማቅረብ ሃሳብ መጣላት። በወቅቱ የሞሪንጋ ቅጠል ለጤና ጠቃሚ መሆኑ ሲነገር የነበረበት ጊዜ ከመሆኑ ጋር ታዳምሮ ሃሳቧን ወደ ተግባር በመለወጥ የሞሪንጋን ቅጥል ከደቡብ ክልል በማስመጣት በዱቄትና በሽርክት በተለያየ ኪሎ አዘጋጅታ መሸጥ ጀመረች።
የሞሪንጋ ተፈላጊነት እየጨመረ በመምጣቱም ምርቱን በብዛት ለገበያ ማቅረቧን ቀጠለች። በዚህም ትርፍ እያገኘች መጣች። በሞሪንጋ የሻይ ቅጥል ንግድም ለአምስት ዓመታት ያህል ቆየች።
ከሞሪንጋ ሻይ ቅጠል ጎን ለጎን ተጨማሪ ንግድ የመጀመር ፍላጎት ያደረባት ወጣት ኢማን የኮሮና ወረርሽኝ የፈጠረውን የፅዳት እቃዎች ፍላጎትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከአምስት ወር በፊት የንግድ ፍቃድ በማውጣት በሃምሳ ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ሊና የተሰኘ ዲተርጀንትና ኮስሞቲክስ ማምረቻ ድርጅት አቋቁማ ወደ ሥራ ገባች። የሞሪንጋ ቅጠል ከሚሰጠው ሁለንተናዊ ጥቅም አኳያም በዚሁ ቅጠል የፀጉር ሻምፖ፣ ኮንዲሽነሮች፣ ቅባቶችንና የፊት ሳሙናዎችን ማምረት ጀመረች።
ከሞሪንጋ ቅጠል የተዘጋጁ የኮስሞቲክስ ምርቶችን በማምረት ወደ ገብያ ማቅረብ እንደጀመረች ምርቶቹ አዲስ ከመሆናቸው አንፃር ከሸማቹ ህብረተሰብ በኩል ምርቶቹን አምኖ የመግዛት ችግሮች ቢያጋጥማትም በሂደት ግን ሸማቹ ምርቶቿን እየለመደላት መጣ። የገበያ ሁኔታውም ተሻሻለላት። ጊዜው የኮሮና ወረርሽኝ በሀገሪቱ የተከሰተበትና የፅዳት እቃዎችም በእጅጉ የሚፈለጉበት በመሆኑ የዲተርጀንት ምርቶቿንም በስፋት በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘት ቻለች።
አስኮ በብርጭቆ አካባቢ በሰምንት ሺህ ብር ወርሃዊ ክፍያ በተከራየችው ቤት ውስጥ ዲተርጀንትና ኮስሞቲክሶችን እያመረተ የሚገኘው ድርጅቷ ከአዲስ አበባ ከተማ የመድሃኒትና ምግብ ቁጠጥር ባለስልጣን የጥራት ማረጋገጫ አግኝቷል። የልብስ፣ የእጅና የእቃ ፈሳሽ ሳሙናዎችን፣ በረኪናዎችን፣ የመስታወትና የሴራሚክ ማፅጃዎችን፣ ከሞሪንጋ ቅጠል የተዘጋጁ ሻምፖዎችን፣ ኮንዲሽነሮችን፣ ቅባቶችንና የፊት ሳሙናዎችን አምርቶ ለገበያ ያቀርባል። እዛው አስኮ ብርጭቆ አካባቢ ባለው አነስተኛ የመሻጫ ሱቅም ምርቶቹን ለአካባቢው ማህበረሰብ ይሸጣል።
ድርጅቱ ለዲተርጀንት ማምረቻ በግብአትነት የሚያገለግሉ ኬሚካሎችን ከአስመጪዎች በመረከብ ትክክለኛውን የአመራረት ሂደት ተከትሎ ምርቶቹን ያመርታል። ምርቶቹንም በተለያየ መጠን በፕላስቲክ ማሽገያዎች አዘጋጅቶ ለገበያ ያቀርባል። በእያንዳነዱ ምርቶች ማሸጊያዎች ላይም ምርቱን የሚገልፁ መረጃዎች በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች በማስፈር እንዲሰፍር አድርጓል። የምርትና የአገልግሎት ማብቂያ ጊዚያትንም እንዲሁ።
እንደገበያው ሁኔታና እንደ ትእዛዙ መጠን የሚወሰን ሆኖ ድርጅቱ በቀን አስከ 500 ሊትር የልብስ ፈሳሽ ሳሙና የማምረት አቅም ያለው ሲሆን የልብስ ሳሙናውን በባለአንድ፣ ሁለትና አምስት ሊትር መጠን አዘጋጅቶ ለገበያ ያቀርባል። የእቃ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና ደግሞ በ750 ሚሊ ሊትርና በአምስት ሊትር ያዘጋጃል።
የእጅ መታጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና በ500 ሚሊ ሊትርና በአምስት ሊትር ያቀርባል። የመስታው ማፅጃ በ750 ሚሊ ሊትር እንዲሁም በረኪና በ300 እና 800 ሚሊ ሊትር እና በአምስት ሊትር መጠን ያመርታል።
ድርጅቱ የልብስ ፈሳሽ ሳሙና አምስት ሊትሩን በ35 ብር፣ ሁለት ሊትሩን በ60 ብር እንዲሁም አምስት ሊትሩን በ125 ብር ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን የእጅ ፈሳሽ ሳሙና 500 ሚሊ ሊትሩን በ26 ብር አምስት ሊትሩን ደግሞ በ120 ብር ይሸጣል።
የመስታዎት ማፅጃ 750 ሚሊ ሊትሩን በ25 ብር፣ በረኪና 300 ሚሊ ሊትሩን በ8 ብር፣ 800 ሚሊ ሊትሩን በ12 ብር እንዲሁም አምስት ሊትሩን በ100 ብር ለገበያ ያቀርባል። የመፀዳጃ ቤት ማፅጃ ዲቶል ደግሞ በአርባ ብር ይሸጣል።
ከኮስሞቲክስ ምርቶች ውስጥ ደግሞ የሞሪንጋ ሻምፖ አንዱን በ60 ብር፣ ኮንዲሽነር በ70 ብር፣ ቅባት 120 ሚሊ ሊትሩን በ80 ብር እንዲሁም ደረቅ የፊት ሳሙና በ35 ብር ለገበያ ያቀርባል። እነዚህ የኮስሞቲክስ ምርቶች ሞሪንጋ ገብቶባቸው የሚሰሩ ከመሆናቸው አኳያና ተፍጥሯዊ ይዘት ያላቸው በመሆናቸው ከሌሎች የኮስሞቲክስ ምርቶች የተለየ ያደርገዋል።
ድርጅቱ ምርቶቹን መርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ በሚገኝ በአምስት ሺህ ብር ኪራይ የማከፋፈያ ሱቅ አማካኝነት ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን የክፍለ ሀገር አከፋፋይ ነጋዴዎች ሲያዙም ምርቶቹን በስፋት ያቀርብላቸዋል።
በተጫማሪም ድርጅቱ በተከራያቸው አይሱዙና ዳማስ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ለሚገኙ ለተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች እንዲደርሱ ያደርጋል። ካጠቃላይ የምርት ሽያጭ በየወሩ የሚያገኘው የሚለያይ ቢሆንም በአማካይ ከፍ ሲል አስከ 16 ሺህ ዝቅ ሲል ደግሞ እስከ 10 ሺህ ብር ገቢ ያገኛል። በአሁኑ ጊዜም ሁለት ሠራተኞችን በመያዝ 200 ሺህ ብር የሚገመት ካፒታል አስመዝግቧል።
የሞሪንጋ ቅጠልን በሻይ ቅጠል መልክ በማዘጋጀት አሁንም ድረስ ለገበያ እንደምታቀርብ የምትናገረው ወጣት ኢማን፤ አሁን አሁን የገበያ ፍላጎቱ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ተከትሎ በዲተርጀንትና በኮስሞቲክስ ማምረት ሥራው ላይ ብቻ አተኩራ የመሥራት ሃሳብ እንዳላት ትገልፃለች።
ከሞሪንጋ ተክል የምታዘጋጃቸው የኮስሞቲክስ ምርቶች በሸማቹ ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራች እንደምትገኝም ትጠቁማለች። በተመሳሳይ የፈሳሽ ሳሙና ምርቶቿም ይበልጥ እንዲታወቁ ባዛርና ኤግዚቢሽኖችን በመጠቀም የማስተዋወቅ ሥራ መሥራቷንም ታስረዳለች።
የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ሀገሪቱ ከገባ በኋላ ሰዎች የፅዳት እቃዎችን ገዝተው የመጠቀም ፍላጎታቸው እጅግ በመጨመሩ የድርጅቷ ምርቶችም ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩንም ገልፃ፤ ሆኖም በአሁኑ ወቅት በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋቶች የሚታዩ ከመሆናቸው አኳያ የፅዳት እቃዎችን የመጠቀሙ ዝንባሌም መቀነስ ማሳየቱን ትጠቅሳለች።
ይሁንና የፅዳት እቃዎች ሁሌም ተፈላጊ ከመሆናቸው አኳያ እንደበፊቱም ባይሆን አሁንም ምርቶቿ እየተሸጡ እንደሚገኙና ሸማቹም ምርቶቹን ተጠቅሞ የሚሰጠው አስተያየት ገንቢ መሆኑን ትጠቁማለች።
በቀጣይም ድርጅቱ በዲተርጀንትና ኮስሞቲክስ ምርቶች ላይ በስፋት በመሥራትና ጥራትን በመጨመር ለገበያ የማቅረብ እቅድ መያዙን ወጣት ኢማን ትገልፃለች። ድርጅቱ ምርቶቹን በኪራይ ቤት ውስጥ ሆኖ እያመረተ ከመሆኑ አኳያም ከመንግሥት በኩል የማምረቻ ሼድ ቢያገኝ አሁን ካለው የማምረት አቅም በላይ የማምረት ውጥን እንዳለውም ታመለክታለች።
ከሌሎች ወጣቶች ጋር በማህር በመደራጀትና የመሥሪያ ቦታ በመውሰድ የመሥራት ፍላጎት እንዳላትም ጠቅሳ፤ ምርቶቹ በሸማቹ ህብረተሰብ ዘንድ ይበልጥ እንዲታወቁም የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት የመሥራት ፍላጎት እንዳላት ጠቁማለች።
‹‹በዚህ የዲተርጀንትና የኮስሞቲክስ ማምረት ሥራ ውጤታማ ብሆንም ገና ጀመርኩ እንጂ አልጨረስኩም›› የምትለው ወጣት ኢማን፤ ሥራው ትንሽ ልፋት የሚጠይቅ ከመሆኑ አኳያ ወደፊት በዚህ የቢዝነስ ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንደምትፈልግ ትናገራለች። ለዚህም ቀን ከሌት ጠንክሮ መሥራትና ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ትጠቅሳለች።
ካለባት የቤት ኪራይና ሌሎች ወጪዎች አንፃርም በአሁኑ ወቅት እምብዛም ትርፍ እንደሌላትም ተናግራ፤ በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ከሠራሁ ትርፉ ላይ እደርስበታለሁም ትላለች። እዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ የቻለችውም በጥረቷና በሚመጡላት አዳዲስ ሃሳቦች መሆኑንና የእህቷም እገዛ እንዳለበት ትጠቅሳለች።
በተመሳሳይ ሌሎችም በዚሁ የቢዝነስ ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን ለሚፈልጉ ወጣቶች ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው መልዕክቷን ታስተላልፋለች። ሠርቶ የማይለወጥ ሰው የሌለ በመሆኑም ለሥራቸው ጊዜ ሰጥተው በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ታስገነዝባለች። በዚህም ከራሳቸው አልፈው ቤተሰባቸውን፣ አካባቢያቸውንና ሀገራቸውን መለወጥ እንደሚችሉ ትጠቁማለች።
ወጣትነት ሠርቶ የማትረፊያ እድሜ ነው። በወጣትነቱ የሠራም በጉልምስና እድሜው ብዙ ሳይሯሯጥ ማትረፍ ይችላል። ወጣት ኢማንም የወጣትነት እድሜዋን በሚገባ በመጠቀም ነግዳ የማትረፊያ መንገዱን ተያይዛዋለች። በቀጣይም ከዚህ በተሻለ ሠርታ ውጤት ማምጣት እንደምትችል አሁን እየሠራችው ባለው ሥራ አስመስክራለች።
በመሆኑም ሌሎችም ወጣቶች ከአካባቢያቸው ችግርና የንግድ ክፍተት በመነሳት በሚፈልጉት የቢዝነስ ዘርፍ ውስጥ በመግባት አትርፈው ለመገኘት ፍላጎቱ ካላቸው ነገ ሳይሉ ዛሬ መነሳት አለባቸው፤ የዕለቱ መልዕክታችን ነው። ሰላም!!
አዲስ ዘመን ጥር 15/2013