ኃይለማርያም ወንድሙ
ከአሥራ አምስት ቀን በፊት የታመመ ዘመዴን ለመጠየቅ በሰንበት ወደ ሰንዳፋ ሄጄ ነበር፤ ወደዚያው ከሚሄዱ ሌሎች ሁለት ሰዎች ጣፎ ላይ ልንገናኝ ተቀጣጥረናል። ሰባት ሰዓት እመጣለሁ ብዬ ቀጥሬያቸው በትራንስፖርት ችግር ስምንት ሰዓት ነበር የተባባልንበት ቦታ የደረስኩት፤ ሕፃን ልጅም ይዘዋል።
ወደ ሰንዳፋ ለመጓዝ መኪና መጠበቁን ተያያዝነው፤ ከግማሽ ሰዓት በላይ ብንጠብቅም ልናገኝ አልቻልንም። ወደ ዘጠኝ ሰዓት አራት አንበሳ አውቶቡሶች ፌርማታውን አልፈው እየከነፉ ሄዱ፤ በጣም ሞልተው መሰለኝ። ታክሲዎች ቢታዩም የሚጭኑ ግን ማግኘት አልቻልንም።
ታክሲ የመጠበቅ ትዕግስቱ ስለሌለኝ በቃ እንመለስና በሚቀጥለው ሳምንት እንሂድ ብላቸውም አብረውኝ ያሉት ሰዎች በሀሳቤ አልተስማሙም። መንከራተት ሆነ። አብሯቸው ያለው ሕፃን ልጅ የፀሐዩ ሙቀትና ድካሙ ታክሎበት እንቅልፍ ወሰደው።
ወደ ሰንዳፋ ለመሄድ መኪና ስንጠብቅ አስር ሰዓት ሆነ፤ ሰለቸኝ፤ ታከተኝ። አንዲት እናት በማዳበሪያ ሙሉ ዕቃ ይዘዋል፤ ከኛ ጋር ወዲያ ወዲህ ተወዛወዙ። ላነጋግራቸው ሞከርኩ። ወደ ሰንዳፋ ለመሄድ ጣፎ የተገኙት ከቀኑ አምስት ሰዓት መሆኑን በኦሮምኛ ገለጹልኝ። እጠብቃለሁ እንጂ የት እሄዳለሁ? ቤቴ ሰንዳፋ ነው አሉኝ። በእርጅና ዘመናቸው በትራንስፖርት ሳቢያ በመንከራተታቸው አሳዘኑኝ።
እሳቸው ከተበረታቱ እኔስ ከማን አንሼ ብልም ብዙም መታገስ ግን አልቻልኩም። 11 ሰዓት ሆነ፤ አብረውኝ የሚጓዙት ግን መጠበቅ አልታከታቸውም። ወደ ታመሚው ዘመዳችን ስልክ ደወልን፤ መኪና ዛሬ አታገኙም፤ ተሳፋሪ ይበዛል፤ ሌላ ቀን በጠዋት ተሳፍራችሁ ብትመጡ ይሻላል አሉን። እኛም እያመነታን እያለ አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ የሕዝብ ማመላለሻ መጣና ተሳፈርን።
ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ ሰንዳፋ ደረስን። ቤት ደርሰንም ታማሚውን ጠይቀን፤ ሻይ ቡና ብለን ተሰነባብትን፤ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሊሆን ሲል አንበሳ አውቶቡስ አግኝተን ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ሆነ። አሁንም ሌላ ፈተና ይገጥመናል የሚል ስጋት ቢያድርብኝም፣ ቀን የተንከራተትነውን ማታ በአንበሳ አውቶቡስ ተካስን፤ ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ መሳለሚያ እህል በረንዳ ደረሰን።
ይህ የጉዞ ታሪኬ ትራንስፖርት ለማግኘት ያለውን ውጣ ውረድ የሰውን መንከራተት ያሳያል ብዬ አምናለሁ። ቀን ከጣፎ ወደ ሰንዳፋ ለመሄድ ሰልፍ ባይኖርም፣ በርካታ ተሳፋሪዎች ግን ነበሩ። የኦሮሚያ ትራንስፖርት በፊንፊኔና በዙሪያዋ ለሚገኙ ከተሞች አገልግሎት የሚሠጡ ተሽከርካሪዎች በበቂ ሁኔታ ቢያሰማራ ኖሮ በመጠነኛ ዋጋ እንደ ልባችን ተሳፍረን ተዝናንተን ንጹህ አየር በነፃ፤ ምርጥ ስጋ ደግሞ በርካሽ ዋጋ ሸምተን ወደ ሸገራችን እንመለስ ነበር።
ሸገር እንደ አንበሳ አውቶቡስ ወደ ፊንፊኔ ዙሪያ አገልግሎት መስጠት ቢጀምሩ ምንኛ መልካም በሆነ ነበር። ከፊንፊኔ ወደ ዙሪያ ለጉዳይም ሆነ ለሥራ የሚመላለሱ በርካታ ናቸው። አዳማን ጨምሮ ከሆለታ፣ ከሰበታ፣ ከሱሉልታ፣ ከቢሾፍቱ፣ ከአሌልቱና ከመሳሰሉት በፊንፊኔ ዙሪያ ላሉ ከተሞች በመንግሥት የሚደጎም ትራንስፖርት አገልግሎት ቢሰጥ ሕዝብም መንግሥትም አትራፊ ይሆናሉ።
የአዲስ አበባ ነዋሪ ሥራ ሲጀምር ተሰልፎ ሥራ ሲሰናበትም ተሰልፎ ነው። በፊት በፊት አንበሳ አውቶቡስ ላይ ወረፋ ሳይ እስቅ ነበር። ይግረምህ ብሎ ነው መሰለኝ የታክሲና የባጃጅ ወረፋ ያሳየኝ ጀመር። የባሰ ደግሞ ከመጣ በአቃቂ ቃሊቲና በመሳሰሉት የከተማዋ ዳርቻዎች የጋሪ ተሳፋሪ ልናይ እንችላለን፤ ጊዜ ደጉ ብሎ መጠበቅ ወይ መጠንቀቅ ነው።
መናኸሪያዎቹ ሰልፍ ናቸው፤ ብዙ ተሳፋሪ ባለባቸው የመርካቶው አውቶቡስ ተራ ሰልፍ ብትይዙም ተራ አስከባሪዎች በር ላይ ባሻጥር አንድ ሁለት ሰው ወረፋ ሳይዝ የኪስ ተቀብለው ያስገባሉ። ቃሊቲም ሆነ ላምበረት ብትሄዱ ተመሳሳይ ነገሮች ታያላችሁ።
የሰልፉ ዓይነት የተለየ ቢሆንም ባንኮችም ብር ለማግባት በሉት ለማውጣት ሰልፍ ነው፤ ሰልፉ ይበልጥ የሰለጠነ ዓይነት ነው። ሆስፒታል ካርድ አውጥተን እንደምንታከመው ዓይነት ነው። ባንኮችም ገና ስንገባ ተራ ያስይዙናል። ፀሐይ የለብን፤ ብርድ የለብን። አቧራ አያገኘን። ብር የምናወጣው ለጉዳይ ነውና ጉዳዩ ሳይረፍድ ማውጣት አንድ ነገር ነው። ቶሎ እንዲፈጸም እንፈልጋለን።
የባንኮች ክፍተት በቅርንጫፎች እየበዙ መምጣት፣ በኤቲኤም እየተሞላ ነው። አሁን ችግሩ ያለው በሌሎቹ ነው። ቀበሌም፣ ጤና ጣቢያም ሆነ ሆስፒታል ብትሄዱ ሰልፍ ነው። የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት ያለው ሰልፍ አያድርስ ነው፤ ድርጅቱ ከውሃና ፍሳሽ ከኢትዮ ቴሌ ቴሌኮም አይማርም እንዴ።
ይሄ ሰልፍ የማደጋችን ምልክት ሊሆን ይችላል ብዬ ተስፋ አደረግኩ። ማለቴ በምጣኔ ሀብት ሳይሆን በሕዝብ ብዛት። የመብራት ክፍያው ጉዳይ የሰልፉ ብዛትና ቢሮክራሲው ብዙኃኑን አማሯል፤ የሚመለከታቸው አካላት አንዳች እልባት ሊያበጁለት ይገባል።
የሰልፍ ዓይነቱ በመብዛቱ ለምርጫ እያለማመዱን እንዳይሆን? ያው ምርጫ ረጃጅም ሰልፎች እንደሚታዩበት ከሀገራችንም ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እንመለከታለን። የገና ሰሞን ኢትዮቴሌኮም አነስተኛ የኪስ ስልክ እሸጣለሁ ብሎ ቢሮዎቹን ሰልፍ በሰልፍ አድርጎት ነበር።
አንዳንድ ቦታ መብራት በካርድ ቆጣሪ የሚጠቀሙ ተገልጋዮች ሊከፍሉ ሲሄዱ መብራት ስለተቋረጠ የቴሌም ችግር እንዳለ ሳይዘነጋ፤ ሲስተም የለም የሚባሉበት ጊዜ አለ። አያስቅም? ለኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያስከፍለው ድርጅት ኤሌክትሪክ ስለሌለ ክፍያ አንቀበልም ሲላችሁ ምን ትሉታላችሁ? ዘመናዊ የክፍያ ዘዴዎችን ቢከተሉ መልካም ነው።
በአሁኑ ወቅት እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ሁሉ ነገር ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር የተገናኘ ነው። ካርድ ለማስሞላት አርብ ለመክፈል ስትሄዱ ሰልፍ በዝቶባችሁ አልያም ሲስተም አይሠራም ተብላችሁ ስትመለሱ፤ ዜናና ሙዚቃ መስማትና መዝናናት አትችሉም፤ ኧረ ዋናውን ነገር ረስቼው። ማብሰል አትችሉም፤ ጨለማ ውስጥ ታድራላችሁ። ጨለማው ገጠር ነው እንዴ ያለሁት ሊያሰኛችሁ ይችላል። ለሦስት አራት ቀን ኤሌክትሪክ ልታጡ ትችላላችሁ፤ ነገሮች ምን ያህል ሊወሳሰቡ እንደሚችሉ ገምቱ።
ኤሌክትሪክ ከሌለ ምግብ አብስሎ እንጀራ ጋግሮ መብላት አይቻልም። ወጣ ወጡንና ጥብሱን ቡናውንና ሻዩን በማገዶና በከሰል ብታበስሉና ብታፈሉ፤ እንጀራ መጋገሩን አትችሉም፤ ያላችሁ የኤሌክትሪክ ምጣድ ብቻ ነዋ! በዚያ ላይ በመሀል ከተማ በማገዶ እንጀራ መጋገር እኮ ድሮ ቀርቷል፤ ማገዶው እንኳ ቢኖር ምጣዱና አክንባሎው ከየት ታመጣላችሁ? ያ ምጣድና አከንባሎ ወደ ሙዚየም እንደገባ ነው የሚቆጠረው።
ቴሌም ኤሌክትሪክ አገልግሎትም ሰልፍ አቀላጥፉ፤ አሠራራችሁን አዘምኑ ተገልጋዩ አይንከራተት። እርግጥ ነው ሰልፍ ካልነበረባቸውና ግፊያ ይበዛባቸው ከነበሩት ከእነዚያ ጊዜያት ጋር ሲወዳደር ሰልፍ ጥሩ ነው፤ ነገሮች በሥርዓት እንዲፈጸሙ ያስችላል፤ አሁን ደግሞ ከኮሮና ይታደጋል። ስርቆትን ይቀንሳል፤ የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል አይደል የሚባለው?
በሸገር ከጠዋት እስከ ማታ የምናያቸው ሰልፎች ቢበዙም ደግነቱ ሰላማዊ ሰልፎች ናቸው፤ የድጋፍ ወይም የተቃውሞ ሰልፎች ለማለት ፈልጌ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። ግፊያ እና ሁከት የማይታይባቸው ማለቴ ነው። እነዚህን ሰልፎች ግን በዚሁ ይቀጥሉ አልልም። መቅረትና መቀነስ ግን እንዳለባቸው ይታሰበኛል። ሰልፎቹን ለመቀነስ ሰላማዊ ሰልፍ እናድርግ ይሆን?
አዲስ ዘመን ጥር 15/2013