በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
(ክፍል ሦስት )
በቀደሙት ሁለት መጣጥፎቼ ስለ ስረወ_ መንግሥቱ ቁንጮ ስብሀት ነጋ ግለ ታሪክና በትህነግም ሆነ በኢህአዴግ ከፍ ሲልም በሀገር ላይ የተወውን የዝሆን ዳና ያነሳሳሁ ሲሆን የመጨረሻ በሆነው በዚህ መጣጥፌ ደግሞ ከትህነግ/ኢህአዴግ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊት የዕዝ ጠገግ እና ጥብቅ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዲሲፕሊን ባፈነገጠ መልኩ እንዲሁም ስለ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ቁብ ሳይሰጥ በዕብሪትና በማንአህሎኝነት ይሰነዝራቸው የነበሩ አወዛጋቢ አስተያየት መሰል ሟርቶችንና ማስፈራሪያዎችን በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ ወደ ኋላ መለስ ብዬ እቃኛለሁ።
የመጀመሪያው ቀደም ባሉት መጣጥፎች ለማሳየት እንደሞከርሁት ስብህት ላለፉት 46 ዓመታት በተለይ ደግሞ ለ30 ዓመታት በትህነግ/ኢህአዴግም ሆነ በሀገሪቱ ሰራአካላት ላይ ተሰራጭቶ የነበረውን ተፅዕኖ ማሳየት ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እነዚህ አወዛጋቢ ንግግሮቹም ሆኑ አስተያየቶቹ የትህነግ ማንነት ማንጠሪያ ስለሆኑ ሦስተኛው ደግሞ የሕዝብ በተለይ የልሒቃኑ ልብ ትርታ ማዳመጫ አራተኛውና የመጨረሻው ምክንያት ደግሞ የፓርቲውን የወደፊት ፈለግ አልያም ንግር /foreshadow / በመሆናቸው ነው ።
የአወዛጋቢው ጁሊያን አሳንጁ ዊኪሊክስ በእኛ ሚሊኒየም 2000 ዓ.ም ላይ በአደባባይ ባሰጣው የአሜሪካ የደህንነትና የዲፕሎማሲ ምስጢራዊ ስብሀት በድፍረት፤ “ ትህነግ ከሌለ ኢትዮጵያ ትበተናለች፤ “ ሲል ያሟርታል። ሟርቱ በኢትዮጵያ ከአሜሪካ ኤምባሲ መገኘቱ አጋጣሚ እንዳልሆነ ልብ ይሏል።
ስብሀትና መለስ እንዲሁም ጭፍራዎቻቸው የሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ልሒቃን የኢትዮጵያ ህልውናም ሆነ ዕጣ ፈንታ ከትህነግ ጋር የተቆራኘ እንደሆነና በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ሥልጣኑን ቢያጣ ኢትዮጵያ ትበታተናለች በማለት ዓለምአቀፍ ማህበረሰቡንና ምዕራባውያንን ያስፈራራል። የጸረ ሽብር ግንባር ቀደም አጋር ኢትዮጵያ ከተበታተነች አልሻባብን ጨምሮ ሌሎች ዓለምአቀፍ አሸባሪዎች ቀጣናውን ሊያምሱት፤ የዓለምአቀፍ የንግድ መርከቦች መስመር የሆነውን ቀይ ባሕርን ያውካል።
ይህ ብቻ አይደለም ሀገሪቱ ከተበተነች ደግሞ በወቅቱ ከ80 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶው ወጣት የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል አውሮፓንም ሆነ ጎረቤት ሀገራትን በስደተኞች ይጥለቀለቃሉ ብሎ ያስፈራራል። በዚህ ማስፈራሪያ ዓለምአቀፍ ማህበረሰቡና ምዕራባውያን ትህነግ/ኢህአዴግ ጎን ለመቆም ይገደዳል።
የሆነውም ይሄው ነው። ይህ ቡድን የፖለቲካ ምህዳሩን ጥርቅም አድርጎ ሲዘጋው፤ ተቃዋሚዎችን፣ ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በጅምላ ሲያስር፣ ሲገድል፣ ሲያሰቃይ፣ ሲያሳድድ ከየይስሙላ መግለጫ ውጪ ሰምቶ እንዳልሰማ፣ አይቶ እንዳላየ ከማለፍ ተሻግሮ በእርዳታና በድጋፍ ፈላጭ ቆራጩን አገዛዝ ለ27 ዓመታት ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የአንድነት ኃይሉንም ሆነ ሀገር ወዳዱን በዚህ የሀገር ትበተናለች ሟርት በተወሰነ ደረጃ ማስፈራራት ችሏል። ሀገር ከምትፈርስ እያለ የግፍ ጽዋውን ሲጎነጭባጅቷል።
የአማርኛው ቢቢሲ ከሀዲው ትህነግ ጓዙን ቀርቅቦ በመማጸኛ ከተማው መቐለ መሽጎ ሳለ ለአያ እንደልቡው ስብሀት እንዲህ የሚል አሽቃባጭ ጥያቄ አቅርቦለት ነበር፤«ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው የሚለው ሃሳብ እያከራከረ ነው። በአንድ ወገን፣ ህወሓት እንደ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አዳራሽ ውስጥ የተመሠረተ ሳይሆን ከትግራይ ሕዝብ አብራክ የተገኘ ነው። ይህን የሚቃወሙ ድርጅቶችና ግለሰቦች በበኩላቸው፣ ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ከሆኑ ታዲያ ለምን አማራጭ ኃይል ያስፈልጋል? ምርጫስ ለምን ያስፈልጋል? በማለት የሚከራከሩ አሉ።
እዚህ ላይ ያለዎትን አቋም ይንገሩኝ ? » ፤ ስብሃት ምን ገዶት ልቡ እንደ ፈርኦን በእብሪት እንደደነደነ እንዲህ ሲል መለሰ ፤ «አሁን ባለው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ህወሓት መተኪያ የለውም።
በሌላ የፖለቲካ ድርጅት ሊተካ አይችልም። ህወሓት ደግሞ መጥፋት አለበት። » ይሄን ግብዝነት እዩልኝ ስብሀት ይሄን የሚለው ከሀዲው ትህነግ በሕዝባዊ አመጽና በለውጥ ኃይሉ አለአግባብ ይዞት ከነበረ ኢፍትሐዊ አገዛዝ ወርዶ መቐሌ መሽጎ ነው። ትህነግ መሩ አገዛዝ ይከተለው የነበረ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የእሱን ሥልጣንና ዘረፋ ከማደላደሉ ባሻገር ሀገሪቱን ወደለየለት ሁለንተናዊ ቀውስ ዘፍቆለተከታታይ ሦስት ዓመታት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተቀጣጠሉ ሕዝባዊ አመጽ ከተወገደ በኋላ ነው እንግዲህ እቡዩ ስብሀት ህወሓት መተኪያ የሌለው መለኮታዊ ኃይል ነው የሚለን። ትህነግ/ኢህአዴግ ወደ ብልፅግና የመለወጡ ሒደት አሀዱ ከተባለ በኋላ።
ዛሬ ላይ ሆነን ስንመዝነው ደግሞ «መተኪያ የለውም !? » የተባለው ትህነግ በትግራይ ብልፅግና ፤ ትህነግ በአንድ ለአምስት ጠርንፎ ከ30 ዓመታት በላይ እጅ ከወርች አስሮ የገዛው ትግራይ ክልልም ያሳድዳቸው፣ ያሳቅቃቸውና ያስር ይፈታቸው በነበሩት፣ በገዛ ሀገራቸው ባይተዋርና እንደ ሁለተኛ ዜጋ ይታዩ በነበሩት በአረናዎች አብርሀ ደስታና አንዶም ገብረስላሴ፤ ከመሰረተው ፓርቲ በሴራ አባቱ ስብሀት ለቆ እንዲሰደድ የተደረገው የእነ አረጋዊ በርሄ (ፒኤችዲ) የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲ እና በትግራይ ብልፅግና በጥምር ሊባል በሚችል አሳታፊ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት እየተዳደረ ነው። ነጮች እንደሚሉት ቀሪው ታሪክ ነው።
ስብሀት «ትህነግ መተኪያ የለውም !? » ይልህና መልሶ ደግሞ «ህወሓት መጥፋት አለበት !?» ብሎ ግራ ያጋባሃል። በወለፈንዲ ንግግር ያምታታሀል። ይህ የስብሀት ነፃነት በመለስ ዜናዊ የፖለቲካ ሕይወት እንኳ ለአንድ ቀን አልተንጸባረቀም። ስብሀትን ከቡድ ከሚያደርጉት መገለጫዎች አንዱ ይህ ወጣ ያለ ሰብዕናው ነው። በዚህ የስብሀት ወለፈንዲ መልስ ንግግር ግራ የተጋባ የሚመስለው የቢቢሲ አማርኛ ጋዜጠኛ ፤ «ህወሓት በአንድ በኩል የትግራይን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመለወጥ ሚናዬን መጫወት አለብኝ እያለ ፤ በሌላ በኩል የመጨረሻ ግቤ ህወሓትን እና ኢህአዴግን ማጥፋት ነው ይላል። ይህ ምን ማለት ነው ? » ሲል ይጠይቃል። ሽማግሌውም ፤ «የህወሓትን ሕዝባዊ መሠረት ካየነው ገበሬው ፣ ወዛደሩ፣ ንዑስ ባለሀብቱና አብዮታዊ ምሁሩ ናቸው።
ዋነኞቹ ደግሞ ገበሬውና ወዛደሩ ናቸው። ገበሬው ከተለወጠ ህወሓት የእኔ መጥፋት ጸጋ ነው ብሎ ይቀበላል። ትግራይ የወዛደር እና የልማታዊ ባለሀብት መሆን አለባት። ገበሬው ቢበዛ ከሦስት እስከ አራት በመቶ ነው መሆን ያለበት። ገበሬው ባለሀብት መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ የወዛደር ድርጅት በግራ የሀብታም ባለሀብት ድርጅት ደግሞ በቀኝ የህወሓት ወራሾች ሆነው መምጣት አለባቸው። እነዚህ ድርጅቶች ገና አልተወለዱም። በትግራይ ተተኪ ድርጅት መምጣቱ ጸጋ ነው።
ዛሬ ካልተወለደ ነገ መወረስ አይችልም። ስለዚህ ወዛደሩን ወይም ባለሀብቱን መሠረት ያደረገ ድርጅት መምጣት አለበት። መደብ መሠረት ያላደረገ የፖለቲካ ድርጅት ጫጫታ ነው ። » ነው እያለ ይኮምካል። ስረወ _ መንግሥቱን በቤተሰቡና ለእሱ ታማኝ በሆኑ ግለሰቦች በእጅ አዙርና በሞግዚት እያስተዳደረ ላለፉት 30 ዓመታት የትህነግ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረቴ ነው የሚለውን የላብ አደርም ሆነ የገበሬ መደብ ሳይፈጥር ኖሮ ፤ ተተኪ የፖለቲካ ሥርዓት ከስር ከስር ሳይፈጥር ሩብ ክፍለ ዘመን አልፎት እና ምንም የተጨበጠ የመውጫ ሥርዓት እንደሌለው ልቡ እያወቀ ቁጭ በሉ ላሞኛችሁ ይላል። ሜካናይዝድ ግብርና ገና ባልታሰበበት የገበሬው ድርሻ አሁን ካለበት 80 በመቶ እንደነ አሜሪካና አውሮፓ ወደ ሦስትና አራት በመቶ መውረድ አለበት ይላል አያ እንደልቡ።
ይህ የቢቢሲ ጋዜጠኛም በትህነግ ወዳጅነት የሚታሙት አለቆቹ ጠይቅ ያሉትን ጥያቄዎች መጠየቁን ቀጥሏል።« ስለዚህ ተተኪው ድርጅት እስኪመጣ ድረስ ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው እያሉኝ ነው? » አያ እንደ ልቡ ስብሀት ምን ገዶት። ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ጉዳዩ አይደል። የመጣለትን ይናገራል። አድማጭ ተመልካች ደግሞ ይከካል። ይፈጫል። ይሰልቃል። የንግግሬ አንድምታ ተዛብቶ ይጠቀስና ድርጅቴ ይገመግመኛል ወይም ይጠይቀኛል ብሎ አይሰጋ።
ወለም ዘለም ሳይል ፣ «አዎ አንድ ናቸው። ወያኔ ይህ ድክመት አለበት ተብሎ ድርጅት ይመሠረታል እንዴ ? ፖለቲካዊ ድርጅት ማለት ፖለቲካ ማለት ነው። ፖለቲካ ደግሞ መደብ ነው። ወያኔ ወዛደሩን እና ባለሀብቱን መሠረት ያደረጉትን የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ ጸጋ ነው የሚያያቸው ፤ ልጆቹ ናቸው ። » በሰው ልጅ ታሪክ የፖለቲካ ፓርቲ ተከታይና ደጋፊ ሊኖረው ይችላል እንጂ ሕዝብና ፓርቲ አንድ ሆኖ አያውቅም።
ለዚያውም የትግራይ ሕዝብና የስብሀት ስረወ_መንግሥት አንድ ሊሆኑ አይችሉም። ሆነውም አያውቁም። ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይሉት ጥቃት በሰሜን ዕዝ ከተፈጸመ ወዲህ በተካሄደ የሕግ የበላይነትና የህልውና ዘመቻም ሆነ ዛሬ የትግራይ ሕዝብ በእርግጥም ከከሀዲ ትህነግ ጋር አንድ የሚያደርገው ነገር እንደሌለ በተግባር አሳይቶናል። ስብሀትን ጨምሮ ጓዶቹን የገቡበትን ሸለቆና ዋሻ እየጠቆመ እያሲያዘ ሲሆን ፤ ስረወ_መንግሥቱን እንዲጠብቅ ያስታጠቁትን ትጥቅ አንድ ጥይት ሳይተኩስ መፍታቱ የትግራይ ሕዝብና ከሀዲው ትህነግ አንድ እንዳልሆኑ ይልቁን ሆድና ጀርባ እንደነበሩ አረጋግጧል።
እንደ መውጫ
ከለውጡ ማግስት አንስቶ የትግራዋይና የኢትዮጵያ ድምጽ ሆነው የምናደምጣቸውና የምንመለከታቸው በኢትዮጵያዊነታቸው ድርድር የማያውቁት ቅንና የዋሁ የትግራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ አረጋዊ በርሄ (ፒኤችዲ) ፤ “A Political History of the Tigray People`s Liberation Front 1975-1991” በሚል ርዕስ በፃፉት የሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናታዊ ጽሑፍ የስረወ_መንግሥቱ ቁንጮ ስብሀት የአድራጊ ፈጣሪነቱ አንዱ መገለጫ ስለነበረ ኃላፊነቱ የጻፉትን በመዋስ በሦስት ተከታታይ ክፍሎች ያስነበብኋችሁን መጣጥፎቼን እቋጫለሁ። በነገራችን ላይ ይህን የማሟያ ጽሑፍ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የመለሰው አክቲቪስት ስዩም ተሾመ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እወዳለሁ።
“ ‘ Exchequer ‘ የምትለዋ ቃል ከደደቢት እስከ ቤተመንግሥት ባለው የህወሓት ታሪክ ውስጥ የአቦይ ስብሃት ትክክለኛ ሚና ምን እንደነበር በግልፅ ትጠቁማለች። “Exchequer” የሚለው ቃል በአጭሩ የዘውዳዊ መንግሥትን የፋይናንስ ገቢና ወጪ በበላይነት የሚቆጣጠር ማለት ነው።
በዚህ መሰረት በህወሓት የትግል ታሪክ ውስጥ የአቦይ ስብሃት ድርሻና ሚና የስረወ_መንግሥቱን የፋይናንስ ገቢና ወጪ በበላይነት መቆጣጠር እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። ከትማሌሊ /ትግራይ ማርክሲስት ሌኒንስት ሊግ /ምስረታ በኋላ የአቦይ ስብሃትና መለስ ዜናዊ ቡድን የህወሓት መስራቾችን በማስወገድ የድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በበላይነት ለመቆጣጠር ችሏል።
ስለዚህ ከትማሌሊ ምስረታን በኋላ ባለው የህወሓት የትግል ታሪክ አቶ መለስ ዜናዊ የድርጅቱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲመራ፣ አቦይ ስብሃት ነጋ ደግሞ የድርጅቱን ፋይናንስ በማስተዳደር ኢህአዴግን መርተዋል። ይህ ጥምረት ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር በመሆን የደርግን መንግሥት ከሥልጣን በማስወገድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥልጣን በበላይነት መቆጣጠር ችሏል። »
አቶ አረጋዊ (ፒኤችዲ) ስለ ስብሀት ይጽፋሉ፣ «በመሰረቱ ሥልጣን ማለት በራስ ፍላጎትና ፈቃድ የመወሰን ነፃነት ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ በራሳቸው ፍላጎትና ፈቃድ የመወሰን ነፃነት የነበራቸው አቶ ስብሃት ነጋ እና መለስ ዜናዊ ናቸው።
ሌሎች የህወሓት አመራሮች እና አባላት በራሳቸው ፍላጎትና ፈቃድ ቀርቶ በድርጅቱ ደንብና መመሪያ መሰረት የመወሰን ነፃነት የላቸውም። ከራሳቸው ህሊና እና ከድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ይልቅ ለአቦይ ስብሃት እና መለስ ዜናዊ ፍላጎትና ምርጫ ተገዢ መሆን አለባቸው ። »ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር ! አሜን።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013