ክፍለዮሐንስ አንበርብር
ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም ክራሞት ኦነግ ሸኔ የተባለው የጥፋት ቡድን ትልቁ የፀጥታ ችግር ሆኖ የሰነበተ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ለሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ዋንኛ ተወናይ በመሆኑ መንግሥት ተጠያቂ አድርጎታል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የዚህ ቡድን የሎጂስትክስ እና ስልጠና ዋንኛ ምንጭ ብሎም የጥፋት መንገዶች ስትራቴጂ ቀያሽና የጡት አባት የሆነው የህወሓት ጁንታ ቡድን መወገድን ተከትሎ ኦነግ ሸኔ እየተንደፋደፈ ስለመሆኑና የበቀል እርምጃ ለመውሰድ እየተውተረተረ እንደሆነ ይነገራል። ይህንና የክልሉን አጠቃላይ የፀጥታ መዋቅር ብሎም ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ጋር የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ያደረገውን ቆይታ እነሆ።
አዲስ ዘመን፡- የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴና አሁናዊ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ እንዴት ይገለፃል?
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ፡- ከበፊቱ በአንፃሩ በአሁኑ ወቅት በጣም ሠላም ነው ማለት ይቻላል። ቀደም ሲል በክልሉ ደቡብ እና ምዕራብ አካባቢ የተወሰኑ ዞኖችን እንቅስቃሴ ገትቶ ነበር። አንዳንድ ወረዳዎች የአርሶ አደርና የንግዱ እንቅስቃሴ እንዲቆም ተደርጎ ነበር። አሁን በሁሉም የክልሉ ቦታዎች ሠላማዊ እንቅስቃሴ አለ። የኦነግ ሸኔ ቡድን በአሁኑ ወቅት እንደ ቀደሙት ወቅቶች እንደ ልቡ ተንቀሳቅሶ አደጋ የሚያደርስበት ዕድል የለውም። ከተወሰኑ ‹‹ፖኬት›› አካባቢዎች እና የተወሰኑ ወረዳዎች በስተቀር ሠላማዊ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የስጋት ቀጣና ተብለው በክልሉ ፀጥታ መዋቅር የተለዩና ልዩ ጥበቃ የሚደረግላቸው አካባቢዎች አሉ?
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ፡- በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ በስፋት ሸኔ መዋቅሩን አዳክሞ የነበረውን በተወሰደው ዕርምጃ ጥሩ ሁኔታ አለ። ግን አሁንም በቄለም ሦስት ወረዳዎች አልፎ አልፎ የሸኔ እንቅስቃሴ የሚታይበት እንዲሁም ምዕራብ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ አልፎ አልፎ አለ። ምዕራብ ሸዋ ሦስት ወረዳዎች እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፤ ግን በፀጥታ ኃይል ክትትል እየተደረገ ነው። በሰሜን ሸዋ አካባቢም በሁለት ወረዳዎች ላይ እንቅስቃሴ አለ።
በደቡብ አካባቢም ምዕራብ ጉጂ ሁለት ወረዳዎች፣ ምሥራቅ ጉጂ ሦስት ወረዳዎች አልፎ አልፎ ሸጦችንና ደን ተገን በማድረግ ተደብቆ አንዳንድ ቦታዎች የመታየት፣ አልፎ አልፎ እርሻ ላይ ያለውን አርሶ አደርና በአካባቢ ሚሊሻ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሚደረግ ሁኔታ አለ። ግን ህዝቡና የፀጥታ መዋቅሩ ተደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። በምዕራብ ህዝቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር አሰሳ የጀመረበትና ዱላ ሳይቀር ማንኛውም የጦር መሳሪያ ይዞ ኦነግ ሸኔን የማሰስና አካባቢን የማፅዳት ዘመቻ ጀምሯል። አልፎ አልፎ ይታያሉ ሆኖም በህዝብ ብርታት እየተመነጠሩ ነው።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ፡- የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ እንዲገታና ከእነዚህ አካባቢዎች ውጪ በሌሎች የኦሮሚያ ክፍሎች እንዳይስፋፋ የተቀየሰ ስትራቴጂ አለ?
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ፡- አሁን ህዝቡ ኦነግ ሸኔ መወገድና መጥፋት አለበት፣ ሽብርተኛ ነው፣ ህዝብ ጨፍጫፊ ነው ብሎ ደቡብና ምዕራብ ኦሮሚያ ህዝቡ በሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ አውግዟል። ስለዚህ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ከመስፋፋት ይልቅ አካባቢውን በማፅዳት ጁንታው እየደገፈቻው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ይፀዳሉ። ስለዚህ ወደ ሌላ ቦታ የመስፋፋት ዕድል የላቸውም። ከምንጩ የማድረቅ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ፡- በእርስዎ መረጃ መሠረት የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እና ጋምቤላ ክልል የሚዋሰኑ በመሆናቸው ከአዋሳኝ ክልሎች ጋር ምን እየተሠራ ነው?
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ፡- ኦነግ ሸኔ እንደ ትልቅ ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሱት ሃይማኖትና ብሄር ተኮር ግጭቶች እንዲፈጠሩ ነው። በአብዛኛው በኦሮሚያ ተወላጆች ላይ ዕርምጃ ይወስዳል። ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ላይም ዕርምጃ ይወስዳል። በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ አካባቢ ለዘመናት እዚያው አካባቢ በኖሩ አማሮችና አንዳንዶቹም አማርኛ ቋንቋ የማይችሉት ላይ ዘር ቆጥሮ ዕርምጃ ይወስዳል። ይህን ለማስተካከል ጥረት ተደርጓል።
ከአማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እና ጋምቤላ ክልሎች የፀጥታ መዋቅርና ከክልሎቹ ፖሊስ ኮሚሽን ጋርም በቅንጅትና በመናበብ እየተሠራ ነው።
በደራ አካባቢ ከሽፍታ ያለፈ ችግር የለም። አልፎ አልፎ እንቅስቀሴው ይታያል። ይህን የማፅዳት ሥራ እየተከናወነ ነው። የአማራ ክልልን ፖሊስ ዩኒፎርም አስመስለው ለብሰው የሚንቀሳቀሱና ዝርፊያ እና ግድያ ፈጽመው የሚሸሹ አሉ። ስለዚህ አዋሳኝ ዞኖች ተጋግዘው ዕርምጃ እየወሰዱና በወንጀል የተረጠሩትን አንዱ ለአንዱ አሳልፎ የመስጠት ሥራ እየተከናወነ ነው። በአጠቃላይ ከክልሎች ጋር ቀደም ሲል ከነበረው በጣም የተሻለ፣ የመረዳዳትና በጋራ የህዝብ ጠላት ነው ብሎ ፈርጆ ዕርምጃ የመውሰዱ ጉዳይ በጣም የተጠናከረ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኦሮሚያ ክልል ለበርካታ ጊዜ ልዩ ኃይል ማስመረቁ ይታወቃል። ዕርምጃ መወሰድ ከተጀመረም ወራቶች ተቆጥረዋል። ለመሆኑም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጭምር ኦነግ ሸኔ የሚባለውን ቡድን ሙሉ ለሙሉ ለምን ማፅዳት አልተቻለም?
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ፡- ይህ የሽምቅ ቡድን የሚጠፋው በጂፒ ኤስ እና ድሮን ሌሎች በመጠቀም አይደለም። ይህ ቡድን የሚጠፋው አንዱ ህዝቡን በማንቃት ነው። ሁለተኛው ሎጂስቲኩን ማፅዳት ነው። ሦስተኛው ደግሞ የሚደበቁበትን አካባቢ በሚገባ መፈተሽ ነው። ስለዚህ ከህዝብ ነጥሎ ሎጂስቲክን መዋቅር ውስጥ ገብቶ መረጃ አግኝቶ ሄዶ ጥቃት የሚያደርሰውን እያፀዱ ከህዝብ ለይቶ ማስወገድ እንጂ እንደ መደበኛ ቆሞ እንደሚዋጋ በጂ ፒ ኤስ የሚዋጋ አይደለም። ቴክኖሎጂ መጠቀሙ የተወሰነ አካባቢ ሊኖር ይችላል። ቀጣና ኖሮት የሚከላከል ኃይል ቢኖር እነዚህን መሳሪያዎች መጠቀም ይቻላል።
ኦነግ ሸኔ የሽምቅ ኃይል ሲሆን፤ ጁንታው ሲያደራጀው፣ ሲያሰለጥነውና ሲደግፈው የነበረ ነው። ስለዚህ ይህ ቡድን በተወሰኑ ወራት ብቻ ተመትቶ የሚጠፋ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ምክንያቱም ሽምቅ ኃይል እንደዚህ የሚጠፋ ስላልሆነ። ነገር ግን ኦነግ ሸኔ በምንም ዓይነት ህዝቡ ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር፣ እንቅስቀሴ እንዳይገደብ ማድረግ ይቻላል። አልፎ ተርፎም ማስወገድ ይቻላል ግን ሂደት ይጠይቃል።
የኦነግ ሸኔ ሽምቅ ቡድን ህብረተሰቡ ውስጥ ይዞ የሚንቀሳቀስ ኋላቀር አስተሳብ ነው። አንዱ በዳይ ሌላውን ተበዳይ አድርጎ ይንቀሳቀሳል። በጎሳ ውስጥም ይደበቃል። ሌሎች ሽፋን የሚሆኑ ነገሮችን ይጠቀማል። ይህንን የመለየት በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥራ መሥራት ይገባል። ከህዝብ ለመነጠል የማንቃት ሥራ ያስፈልጋል። ህዝቡ ከተነጠለ በኋላ የፀጥታ ኃይል የማፅዳትና ዳግም የማደራጀትና የተደራጀ ኃይል ከህዝብ ጋር ቅንጅት ፈጥሮ የማስወገድና የመምታት ሥራ ነው። ይህ ደግሞ በአንድ ጀንበር የሚሳካ አይደለም። ህዝቡን የማንቃትና የማደራጀት ሥራ ይጠይቃል። እነርሱም አንዳንዴ የሚወስዱት ዕርምጃ በጣም ዘግናኝ ስለሆነ ህዝቡ እንዲፈራ፤ ፈርቶም እንዲደብቅ የማደረግ ሁኔታዎች አሉ። ይህንን ተደራሽ አድርገን ህዝብ ካጋለጠ በኋላ የእኛ ጥበቃም ለአደጋ እንዳይጋለጥ ተደራሽ ማድረግ ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- የክልሉ የፀጥታ መዋቅር በቁርጠኝነትና በታማኝነት ከመሥራት አኳያ ችግሮች ይኖሩበት ይሆን የሚል ግምገማ ተካሂዷል?
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ፡- አዎ! ትልቁ የሽምቅ ኃይል ዘዴ አንዱ በተለያየ ሁኔታ ህዝብ ውስጥ መደበቅ ነው። ሁለተኛው መረጃ ለማግኘት መዋቅር ውስጥ በተለይም ደግሞ የፀጥታና የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ሰርጎ መግባትና ሰዎችን አደራጅቶ መያዝ ነው። ስለዚህ በክልላችን ይህን ገምግመን ቢያንስ ከ1000 በላይ በሚሆኑ የፖሊስ ኃይል ላይ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ወስደን የማፅዳት ሥራዎች ሠርተናል። አሁንም አልፎ አልፎ እዚህ ውስጥ የሚሳተፉ፣ የሚጠረጠሩ፣ መረጃ እየሰጡ ጠላትን የሚያስመልጡ፣ ከእነርሱ ጋር የሚያብሩ፣ ከጎሰኝነት፤ ከከባቢነትም ተነስተው አንዳንዶቹ ከፀጥታ መዋቅር በተለይም ከቀበሌ ሚሊሻ ጋር አልፎ አልፎ አመራር ውስጥም ዘመዶቻቸው እዚያ ውስጥ የማካተት ሁኔታ አለ።
ይህን በየጊዜው እየገመገምን ዕርምጃ በመውሰድ ላይ እንገኛለን። አሁንም የተለያዩ ወረዳዎችን ፖሊስም ይህን ተከታትሎ በጣም አምርረው የማይተጋሉት ላይ ጭምር ዕርምጃ እየወሰድን ስለሆነ እያጸዳን ነው። የማዳከም ሥራም እየሠራን ነው። መዋቅር ውስጥ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንዲከናወን እያደረግን ነው። ህዝቡም ከዚህ የጠላት ኃይል ራሱን እንዲያገልና እንዲጋልጥ በመደረግ ላይ ነው። በቀጣይም ኦነግ ሸኔ እስኪጠፋ ተጠናከሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡- የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ህግ በማስከበር ዘመቻ ላይ ትኩረት አድርጓል። አሁን የጎረቤት አገር ጋር የድንበር እሰጣ ገባ መኖሩ ይታወቃል። በመሆኑም በክልሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የተቀየሰ ስትራቴጂ ምንድን ነው?
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ፡- የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ችግር በተፈጠረ ጊዜ መንቀሳቀሱ ይታወቃል። እንደ ክልል ይህን ክፍተት ለመሙላት የፖሊስ ኃይልና በየአካባቢው ያለውን ሚሊሻ ማደራጀት እንዲሁም በክልሉ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ የፌዴራል ፖሊስ ጋር የመቀናጀት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል። ስለዚህ ከክልሉ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና ሌላ ከፀጥታ መዋቅር ጋር እየተሠራ ነው።
ሌላው ወሳኝ የሆነው ህዝብ ነው። ኦነግ ሸኔ ጠላትና ገዳይ መሆኑን፣ የኦሮሞ ህዝብና ሌሎች ብሄሮችን የማጋጨት ሥራ ላይ መጠመዱን ህዝቡ ተገንዝቦ እንዲታገል ማድረግ ነው። እንደ መንግሥትም ይህን ማድረግ ተችሏል። ሕዝቡም የማፅዳት ሥራ ሠርቷል። ይህንንም በመጠቀም ነው ከ1 ሺ 100 በላይ የኦነግ ሸኔ አባላት እንዲወገዱ፣ እንዲያዙ፣ እንዲደመሰሱና እጅ እንዲሰጡ የተደረገው። በአሁኑ ወቅትም በየቀኑ እጅ የሚሰጥ አለ። በህዝብ ትብብር እና በፀጥታ መዋቅር ዕርምጃ እየተወሰደ ነው። ህዝቡም ዕርምጃ እየወሰደና ለፀጥታ መዋቅር አሳልፈው እየሰጡ ነው። እንዲያውም ክፍተቱን ከመሙላት አልፎ ከምዕራቡ እና ከደቡብ የሀገራችን ክፍል የማፅዳት ሥራ የተጀመረበት ወቅት ነው። ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከኃይል ዕርምጃ ውጪ ቀደም ሲል በተደረገው የአባ ገዳዎች ጥሪ መሰረት ሠላማዊ አማራጮችን ለመጠቀም ዕድል ይኖራል?
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ፡- ኦነግ ሸኔ ከጥፋቱ ለመማር እጅ ሰጥቶ ወደ ሠላማዊ መንገድ የሚመለስ ከሆነ እስከአሁን ህዝቡን የበደለው ከአሁን በኋላ መጉዳትና መግደል የለብኝም ብሎ ወደ ሠላማዊ መንገድ የሚመለስ ከሆነ መንግሥት ወደ ሠላም አትመሰሉ የሚል አቋም የለውም። ስለዚህ ወደ ሠላም የሚመለሱትን ሁሉ መንግሥት በህጉ መሰረት ያስተናግዳል።
ነገር ግን አባ ገዳዎቹም ባለፈው ያስተላለፉት ኦነግ ሸኔ ሰላማዊ አይደለም። ከባህልና ከህዝብ ሁኔታ ያፈነገጠ ገዳይና ባንዳ ነው። ስለዚህ ጠላትና ባንዳ ናቸው መወገድ አለባቸው። ለሸኔ መረጃ የሚሰጥ፣ የሚደራደር ሎጂስቲክስ የሚቀርብ ጠላት ነው። ስለዚህ ሸኔን ባገኛችሁበት ቦታ ደምሰሱ ነው ያሉት። ይህ በቦረና ብቻ ሳይሆን በሰሜን ሸዋ እና ሌሎች ዞኖች ላይም የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ያወገዙትና የህዝቡ ጠላት ስለሆኑ ዕርምጃ መወሰድ አለበት እንጂ እነዚህ እንደ ሌላ ፖለቲካ ፓርቲ መቆጠር የለባቸውም ስለተባለ ህዝቡ እንቅስቃሴ የጀመረው። ስለዚህ ህዝቡ ተባብሮ ማስወገድ አለበት። አባ ገዳዎች ያስተላለፉትን ውሳኔ ተቀብሎ ህዝቡ ኦነግ ሸኔን ለማፅዳት በየዞኑ ተግባራዊ እያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ለሰጡኝ ወቅታዊ መረጃ በዝግጅት ክፍሉ ሥም አመሰግናለሁ።
ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ፡- በርታ! እኔም አመሰግናለሁ።