አስናቀ ፀጋዬ
ወጣት ነው፤ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ የልብስ ስፌት ሙያን ተምሮ ሰርቷል። የኮሌጅ መሰናዶ መግቢያ ውጤት ባይመጣለትም ሰርቶ ለመለወጥ ካለው ፍላጎት የተነሳ የመንጃ ፍቃድ አውጥቶ በከባድ መኪና አሽከርካሪነት ስራ ላይ ተሰማራ።
ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ማሽከርከር ሲሰለቸው በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሰራተኞች ሰርቪስ አሽከርካሪ ሆነ። በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በነበረው ቆይታ ለሰራተኞች የፅዳት መጠበቂያ ሳሙና ሲታደል ማየቱ ዛሬ ላይ የራሱን ንግድ ለመጀመር በር ከፍቶለታል- የቤስት ጄኔራል ትሬዲንግ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ወጣት ክፍሉ መንገሻ።
አቶ ክፍሉ መንገሻ ተወልዶ ያደገው ሰሜን ሸዋ ዞን መርሐቤቴ ነው። ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ትምህርቱን እዛው መርሐቤቴ በኸር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሎ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ከስድስት እስከ ስምተኛ ክፍል በተስፋ ኮከብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ እስከ አስረኛ ክፍል በመድሃኒዓለም ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተምሯል።
የአስረኛ ክፍል ውጤት ስላልመጣለት ፊቱን በቀጥታ ወደስራው በማዞር የልብስ ስፌት ሙያ ተምሮ መስራት ጀመረ። ሆኖም ስራው ብዙም ስላላዋጣው አምስተኛ መንጃ ፍቃድ አውጥቶ በከባድ መኪና አሽከርካሪነት ተቀጥሮ ቀጠለ። በዚሁ የሹፍርና ስራም ከአምስት አመታት በላይ ቆየ።
ሆኖም ወደ ጅቡቲ በየግዜው በርሃውን አቋርጦ ማሽከርከሩ ቢሰለቸው ስራውን በማቆም በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሰራተኞች ሰርቪስ ሹፌር ሆኖ ተቀጠረ።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ እንደጀመረ በፓርኩ ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞች የፅዳት ሳሙና ሲሰጣቸው ይመለከታል። ለሰራተኞች ሳሙናው በምን መልኩ እንደሚቀርብላቸውም ጠይቆ በጨረታ ተግዝቶ እንደሚገባ ተረዳ። በዚህ መነሻነትም ‹‹ሳሙናውን ለምን እኔ አላቀርበውም?›› የሚል ጥያቄ በውስጡ ተፈጠረ። ባለው ትርፍ ግዜም በፈሳሽ ሳሙና አመራረት ዙሪያ የሶስት ወር አጭር ስልጠና ወስዶ ሰርተፍኬት አገኘ።
በ2011 ዓ.ም ሰርተፍኬቱን ይዞ ወደ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት በማቅናት በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅቶ በወረዳው በሚገኝ አንድ አነስተኛ የመስሪያ ሼድ በ50 ሺ ብር መነሻ ካፒታልና ራሱን ጨምሮ ከሶስት ሰዎች ጋር በመሆን ቤስት ጄኔራል ትሬዲንግ በሚል ስያሜ በፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራ ተሰማራ።
ሹፍርናውን ጧትና ማት እየሰራም ሳሙናውን ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ማቅረብ ቀጠለ። በየወሩም ከአራት እስከ አምስት ሺህ ሊትር ፈሳሽ ሳሙናዎችን ለፓርኩ ማቅረብ ቻለ።
በሂደትም የጀመረው የፈሳሽ ሳሙና ንግድ አዋጭ መሆኑን በመገንዘብ የአሸከርካሪነት ስራውን ሙሉ በሙሉ በመተው በዚህ ስራ ላይ ብቻ አተኩሮ መስራት ቀጠለ።
የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎም (የእጅ ንጽህና መጠበቂያ) ሳኒታይዘር፣ በረኪናና የፀረ ጀርም ኬሚካሎችን በማምረት ምርቶቹን እያሰፋ መጣ።
ጨረታዎችን በመከታተል ራሱ ተንቀሳቅሶ ምርቶቹን መሸጥ የተያያዘው አቶ ክፍሉ ቀስ በቀስ አንድ ተሽከርካሪ በመከራየትና የራሱን ተጨማሪ ተሽከርካሪ በመግዛት ቀደም ሲል በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ለኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚያቀርበውን አምስት ሺ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና በአንድ ሳምንት ብቻ ከአምስት እስከ ስድስት ሺ ሊትር በማሳደግ በቋሚነት ማቅረብ ቻለ።
በሂደትም በሄሎ ማርኬት ውስጥ በመካተት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዲስ አበባ ፅህፈት ቤትና ለአሜሪካ ኤምባሲ ምርቶቹን ማከፋፈል ጀመረ። ምርቱን በስፋት ለገበያ ማቅረብ እንዲችልም ያኔት የተሰኘው ኬሚካል አቅራቢ ድርጅት ትልቅ ድጋፍ አድርጎለታል።
የአቶ ክፍሉ ድርጅት በአሁኑ ወቅት በአራዳ ክፍለ ከተማ እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ መንግስት በአነስተኛ ኪራይ በሰጠው የመስሪያ ሼድ ውስጥ ገብቶ የልብስና የእጅ ፈሳሽ ሳሙናዎችን በተለያየ መጠን እያመረተ ይገኛል።
የልብስ ፈሳሽ ሳሙናዎችንም በአንድ፣ በሁለትና በአምስት ሊትር ያቀርባል። በረኪና የፀረ ጀርም ኬሚካል እና ሳኒታይዘር እንዲሁም የሴራሚክ ማጠቢያ ኬሚካሎችንና ሌሎችንም በአጠቃላይ አስራ ሁለት አይነት ምርቶችን በማምረት ለገበያ ያቀርባል።
ድርጅቱ ኬሚካሎችን ከአስመጪ ድርጅት በመረከብና በመደባለቅና ወደ ፈሳሽ ሳሙና ምርት በመቀየር ለተጠቃሚዎች ያቀርባል። በሚሰራው ስራም ከአዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንም የጥራት ማረጋገጫ አግኝቷል።
አጠቃላይ የድርጅቱ ካፒታል በአሁኑ ወቅት እስከ 500 ሺ ብር የሚገመት ሲሆን የመኪና አሽከርካሪዎችን ጨምሮ 12 ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል።
በቀን 800 ሊትር የልብስ፣ 200 ሊትር የእጅ፣ 200 ሊትር የእቃ ፈሳሽ ሳሙና እንዲሁም 500 ሊትር በረኪና የማምረት አቅም እንዳለው ይናገራል። የሴራሚክ ማፅጃ ኬሚካሎችንና የመስታወት ማፅጃዎችንም በሳምንት 200 ሊትር ያህል እንደሚያመርት ነው የሚናገረው።
ከነዚህ ምርቶች በተጨማሪም ድርጅቱ የጸጉር ሻምፖና ኮንዲሽነሮችን እያመረተ የሚገኝ ሲሆን የማምረት አቅሙ አነስተኛ በመሆኑና ለዚሁ ምርት የሚውለው ኬሚካል ውድ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ለገበያ መቅረብ አልጀመረም። ሆኖም በባዛርና በተሽከርካሪ በመዞር ምርቱን ለማስተዋወቅ ሞክሯል።
የኮሮና ወረርሽኝ በሀገሪቱ መከሰቱ ከተረጋገጠ ወዲህ መጀመሪያ አካባቢ የድርጅቱ ምርቶች በተለይም የበረኪናና ሳኒታይዘር ምርት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት የህብረተሰቡ ጥንቃቄ እየላላ መምጣቱን ተከትሉ ፍላጎቱ እንደቀድሞው መሆን አልቻለም። የፅዳት ምርቶች ሁሌም ተፈላጊ ከመሆናቸው አኳያ ግን የድርጅቱ ምርቶች አሁንም ገበያ አላቸው።
በአሁኑ ወቅትም ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ፍቃድ አግኝቶ አስራ ስድስት ለሚሆኑ ድርጅቶች ለኮሮና መከላከያ የፀረ ጀርም ኬሚካሎችን ያቀርባል።
ለቂርቆስ ፖሊስ ጣቢያ፣ ለአስኮ ቅዱስ ገብርኤል፣ ለመብራት ሃይል ደቡብ ሪጅንና ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች የፀረ ጀርም ኬሚካሎችን በነፃ በማቅረብም የበጎ አድራጎት ስራ መስራቱንም ይናገራል።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ ድርጅቱ ከሚያመርታቸው የፈሳሽ ሳሙና ምርቶች በተጓዳኝ በሄሎ ማርኬት ውስጥ ካለ አንድ ድርጅት ጋር ስምምነት በመፍጠር የቧንቧ፣ የመፀዳጃ ቤትና የግንባታ እቃዎችን ለገበያ ማቅረብ ጀምሯል።
በቀጣይም ድርጅቱ ራሱን በማስፋፋት ምርቶቹን በብዛት፣ በአይነትና በጥራት በማሳደግ ለገበያ የማቅረብ አቅድ ይዟል።
ከዚህ በተጓዳኝ በሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ውስጥ በመሳተፍ በተለይ ደግሞ ከሌሎች አስመጪዎች የሚገዛቸውን የሳሙና ኬሚካሎች በራሱ በማስመጣትና ዋጋ ቀንሶ ምርቶቹን ለተጠቃሚው የማቅረብ ፍላጎትም አለው።
ይሁን እንጂ ድርጅቱን በማስፋት የምርቱን መጠንና ተደራሽነት ለመጨመር ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፈልግና ገንዘቡን በብድር ለማግኘት ለወረዳው ብድርና ቁጠባ ተቋም ጥያቄ ማቅረቡን አቶ ክፍሉ ይናገራል። ጥያቄው ምላሽ ቢያገኝም እስካሁን ድረስ ግን ገንዘቡን እንዳላገኘ ይገልፃል።
በመሆኑም የፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራውን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት በማየትና ለወረዳው የሚያደርገውን የሳኒታይዘርና የፀረ ጀርም ኬሚካል ነፃ ድጋፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት ወረዳው ብድሩን እንዲፈቅድለት ይጠይቃሉ።
ይህን ብድር ማግኘት የሚችል ከሆነም ድርጅቱን በማስፋት የተሻለ ምርት በተሻለ ጥራት፣ ብዛትና ዋጋ ለገበያ ማቅረብና ብዛት ያለው የስራ እድል መፍጠር እንደሚችልም ይጠቁማል።
ምርት በበዛ ቁጥር ቦታ የሚያስፈልግ በመሆኑ በቀጣይ ሰፋ ያለ የመስሪያ ቦታም እንደሚፈልገው ያምናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ገንዘቡ ቢገኝ በአንድ ግዜ ከሁለት እስከ ሶስት ሺ ሊትር ማምረት የሚችሉ ማሽኖችን ገዝቶ በመጠቀም የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚፈልግም ይናገራል።
በተመሳሳይ የደረቅ ሳሙና ማምረቻ ማሽንም ማስገባት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ብድሩ መጣም ቀረ ዘግይቶም ቢሆን ይህን ፍላጎት ለማሳካት እንደሚሰራም አቶ ክፍሉ ያስረዳል።
‹‹በፈሳሽ ሳሙና ማምረትና ሽያጭ ውጤታማ ነኝ›› የሚለው አቶ ክፍሉ ከአሸከርካሪነት ስራ ተላቆ የራሱን የንግድ ስራ መጀመሩ የስኬቱ አንዱ ማሳያ መሆኑን ይጠቁማል። ከዚህ በፊት በአሽከርካሪነት ተቀጥሮ ሲሰራ የሚያገኘው ገቢ ዝቅተኛ እንደነበርና የራሱን የንግድ ስራ ከጀመረ ወዲህ ግን የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደቻለም ያስረዳሉ። ድርጅቱን ከዚህ በላይ ማስፋት ከቻለም አሁን ከሚያገኘው ገቢ በላይ ሊያገኝ እንደሚችልም ይጠቁማል።
እዚህ ውጤት ላይ መድረስ የቻለውም ሰርቶ ለመለወጥ ካለው ፍላጎትና በንግድ ውስጥ ያየውን ክፍተት በማየትና ይህን ክፍተት ለመሙላት ጥረት በማድረጉ መሆኑንም ይጠቅሳል። በዚህ ሁሉ ሂደት ታዲያ የእርሱ ቀንና ሌሊት መስራት እንዳለ ሆኖ የባለቤቱ ያልተቆጠበ ድጋፍ ለውጤቱ ማማር የራሱን አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ይመሰክራል።
በተመሳሳይ ሌሎች ወጣቶችም በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ገብተው ውጤታማ መሆን ከፈለጉ በቅድሚያ ንግድ ሲጀምሩ ውጣ ውረዶች እንደሚያጋጥማቸው አምነው መግባት እንዳለባቸውና ለኪሳራም ሊዳረጉ ስለሚችሉ በቀላሉ ተስፋ ሊቆርጡ እንደማይገባ ይመክራል።
በመሆኑም ትርፍ በቀላሉ ሊገኝ እንደማይችል በመገንዘብ በቅድሚያ ለኪሳራ ያበቃቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ቆም ብለው ማሰብ እንዳለባቸውና ከኪሳራው ለመውጣት መንገድ መፈለግ እንደሚኖርባቸው ይጠቁማል።
በዚህም ለኪሳራ ካበቃቸው ስህተት በመማር ወደ ትክክለኛው የቢዝነስ መስመር መግባት እንደሚችሉና ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው ይጠቁማል። ወደ ቢዝነሱ ከገቡም በኋላም ስራው ምን እንደሚያስፈልገው መለየት እንዳለባቸውና ለስራቸው መስዋዕትነት መክፈል እንደሚገባቸው መልእክቱን ያስተላልፋል።
ወጣትነት ሰርቶ የማትረፊያ እድሜ ነው። በወጣትነቱ የሰራ በጉልምስና እድሜው ብዙ ሳይሯሯጥ ማትረፍ ይችላል። ወጣት ክፍሉም የወጣትነት እድሜውን በሚገባ በመጠቀም ነግዶ የማትረፊያ መንገዱን ተያይዞታል።
‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› እንዲሉ በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ሰርቶ መለወጥ እንደሚችል አሁን እየሰራ ባለው ስራ አስመስክሯል። በመሆኑም ሌሎችም ወጣቶች በሚፈልጉት የንግድ ዘርፍ ውስጥ በመግባት አትርፈው ለመገኘት ፍላጎቱ ካላቸው ነገ ሳይሉ ዛሬ መነሳት አለባቸው የእለቱ መልእክታችን ነው። ሰላም!!
ወጣት ክፍሉ መንገሻ፤
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013