ምህረት ሞገስ
የዘገየ ፍርድ እንደተነፈደ ይቆጠራል ይባላል። ፍርድ ተሰጠ ተብሎ ተፈፃሚ ካልሆነ ደግሞ ምን ይባል ይሆን? አቶ ሕዝቅኤል ማራ ይባላሉ። የህግ አገልግሎት ሃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ሳሉ እርሳቸው እንደገለፁት፤ የዜግነት ድርሻቸውን ለመወጣት ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ሊፈፀም የነበረ ሙስናን አስመልክቶ ይፋ በማድረጋቸውና ለመንግስት በማሳወቃቸው ይሰሩበት የነበረው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንገዶች ባለስልጣን ከህግ ውጪ የሥራ ውላቸውን አቋርጦባቸዋል።
አቶ ሕዝቅኤል ባለስልጣኑ የሰሩበትንም ያልከፈላቸው በመሆኑ ክፍያው እንዲፈፀምላቸው እና ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ለሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተቋሙ ላይ ክስ ይመሰርታሉ።
ፍርድ ቤቱ አቶ ሕዝቅኤልን እና መስሪያቤቱን ካከራከረ በኋላ፤ ተቋሙ ግለሰቡን ከስራቸው ያሰናበታቸው ከህግ ውጪ ስለሆነ ወደ ነበሩበት የሥራ መደብ እንዲመለሱ እና ያልተከፋላቸው ክፍያ እንዲከፈላቸው ይወስናል።
አቶ ሕዝቅኤል ፍርድ አገኘሁ ብለው በደስታ የአፈፃፀም ፋይል ከፍተው ወደ ስራቸው ለመመለስ ቢከራከሩም፤ እርሳቸው ቀድሞ ሲሰሩበት የነበረው የህግ አገልግሎት የሥራ ሃላፊነት በመዋቅር ተለውጦ በሹመት የሚፈፀም በመሆኑ በስራ መደቡ ላይ ሊመደቡ አይችሉም ብሎ ተቋሙ የፍርድ አፈፃፀሙ ላይ ክርክር ያነሳል።
በመጨረሻም በፍርድ ቤቱ የተወሰነው ውሳኔ ሊፈፀም አይችልም በሚል የፍርድ አፈፃፀም ላይ ትዕዛዝ ይተላለፋል።
አቶ ሕዝቅኤል በዚህ የአፈፃፀም ትዕዛዝ ቅር ይሰኛሉ። ቅር ከመሰኘት አልፈው ጉዳዩን ለክልል ሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት ያቀርቡታል። ሰበር ሰሚ ፍርድ ቤቱ ከሳሽ የተሰናበቱት ከህግ ውጪ መሆኑ ተረጋግጦ እንዲመለሱ ውሳኔ ይሰጣል።
‹‹በአፈፃፀም ደረጃ የእርሳቸው የቀድሞ መደብ በሹመት የሚሰጥ ነው መባሉ ፍርዱን ላለመፈፀም የቀረበ አዲስ የመከራከሪያ ሃሳብ ነው›› ያለው የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት፤ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ እንዲሁም ያልተከፈላቸው ክፍያ እና ጥቅማጥቅም እንዲከፈላቸው ውሳኔ ያሳልፋል።
ይህ የአፈፃፀም ውሳኔ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ድረስ ታይቶ ውሳኔው ፀንቷል።
አቶ ሕዝቅኤል በአፈፃፀሙ ላይ በተወሰነላቸው መሠረት በድጋሚ ፍርድ እንዲፈፀምላቸው የሥር ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ግን በሌላ የክስ መዝገብ በሰበር ‹‹በሥራ ላይ በሌለ መዋቅር መሰረት የተሰጠ ፍርድ ማስፈፀም አይቻልም›› በማለት ትርጉም የተሰጠበትን ውሳኔ በመጥቀስ ለአመልካች የተፈረደውን ፍርድ ማስፈፀም አይቻልም ተብሎ በድጋሚ ብይን ይሰጣል።
አቶ ሕዝቅኤል አሁንም ፍርድ እየተፈረደላቸው አፈፃፀም ላይ የሚያደነቃቅፋቸው ነገር ቢያሳዝናቸውም፤ በብይኑ ቅር በመሰኘት በድጋሚ ጉዳያቸውን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀርባሉ።
ችሎቱ የአንድ የፍርድ ይዘት አሻሚ ሆኖ ተገቢ ያልሆነ ክርክር እንዳይነሳ ተገቢው ሙግት በስርዓቱ ቀርቦ ከተጠናቀቀ በኋላ ፍርድ እንዴት ሊሰጥ እንደሚገባ የተቀመጠ መሆኑን በዝርዝር በመጥቀስ እና የፍታብሔር ሥነሥርዓት ሕግ የፍርድ አሰጣጥ ሥርዓት ለአሰሪ እና ሰራተኛ ጉዳዮችም ተፈፃሚነት ያለው ስለመሆኑ በማብራራት፤ ወደ ሥራቸው ይመለሱ በሚል የተሰጠው ውሳኔ መፈፀም ያለበት መሆኑን ያስቀምጥላቸዋል።
በመሆኑም በአዲሱ አደረጃጀት ምክንያት ወደ ተለወጠው የሕግ ድጋፍ የሥራ ሂደት ባለቤት የሥራ መደብ እንዲመለሱ በማድረግ ሳይሆን ለዚሁ የሥራ መደብ ተመጣጣኝ የሆነ የሥራ መደብ ላይ ተመድበው መብት እና ጥቅማቸውን እንዲያገኙ በማድረግ የቀድሞ ፍርዱን በማሻሻል በድጋሚ ይወስናል።
ነገር ግን ከዚህ ውሳኔ በኋላም፤ የስር ፍርድ ቤት የአፈፃፀም ፋይል አስከፍተው ቢከራከሩም፤ አቶ ሕዝቅኤል በዲሲፒሊን ከስራ የተሰናበቱ በመሆኑ መስሪያ ቤቱ ስልጣን ላለው መደበኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቅ ይችላል ብለው በአቶ ሕዝቅኤል የቀረበውን አቤቱታ አለመቀበላቸውን መዘገባቸው ያሳያል።
አቶ ሕዝቅኤል በመቀጠል ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በማምራት በደል እንደተፈፀመባቸው ጠቅሰው፤ ሙስና ተፈፅሟል ብለው በመጠራጠራቸው እና በመጠቆማቸው የህግ ከለላ የሚያደርግላቸው አካል አጥተው እንደነበር ፍርድ ቤቱ ቢወስንላቸውም ውሳኔውን የሚያስፈፅም ማጣታቸውን፤ ፍትህ የማግኘት መብታቸው የተጣሰ መሆኑን እና ጉዳዩ የህገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጠው ሲሉ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ አቅርበዋል።
ምክር ቤቱ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ከህገመንግስቱ አንፃር በማገናዘብ መርምሯል። በሐዋሳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን አከራክሮ የመስሪያ ቤቱን ውሳኔ በመሻር አመልካቹ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ደመወዝና ጥቅማጥቅማቸው እንዲከፈላቸው መወሰኑን ይህ ውሳኔ በበላይ ፍርድ ቤቶችም መፅናቱን አረጋግጧል።
የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሕገ መንግስቱ ላይ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት በአቶ ሕዝቅኤል ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ የሥር ፍርድ ቤቱ ፍርዱን እንዲያስፈፅምላቸው ሲጠይቁ ፍርዱን ማስፈፀም ሲገባው የመጨረሻው ውሳኔ በሰበር ደረጃ ከተወሰነ በኋላ አመልካች በዲሲፒሊን ተሰናብተዋል የሚል እና በህገመንግስቱ አንቀፅ 9 ላይ ከህገመንግስቱ የበላይነት ጋር እንዲሁም በህገመንግስቱ አንቀፅ 37 ላይ ከተደነገገው ፍትህ የማግኘት ህገመንግስታዊ መብት ጋር የሚቃረን መሆኑን ጉባኤው በሙሉ ድምፅ በመስማማቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለውሳኔ እንዲተላለፍ አቅርቧል።
ሆኖም የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በጉባኤው የቀረበውን ከማፅደቁ በፊት በዝርዝር ጉዳዩን ተመልክቷል። አቶ ሕዝቅኤል በውሳኔው መሰረት እንዲፈፀምላቸው ሲጠይቁ ቀደም ሲል ሲሰሩበት የነበረው የህግ አገልግሎት ሃላፊ የሥራ መደብ የሹመት የሥራ መደብ እንዲሆን በመወሰኑ በዚህ የሥራ መደብ ላይ አመልካችን መመደብ እንደማይችል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱንም አይቷል። ይሁንና በተደረገው ማጣራት መስሪያ ቤቱ አቶ ሕዝቅኤልን በሌላ መደብ ላይ መድቦ ሲያሰራቸው እና ደመወዛቸውን ሲከፍላቸው መቆየቱ ተረጋግጧል።
አቶ ሕዝቅኤል በፍርድ ቤት ያገኙትን ውሳኔ በፍርድ ቤት እስከ መጨረሻ በአፈፃፀም ሄደው ማስወሰን ሲገባቸው ወደ ህገመንግስት አጣሪ ጉባኤ በመሄድ በአቋራጭ የሄዱበት አካሄድ ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመግለፅ፤ የህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤም ጉዳዩን ተቀብሎ ከተመለከተ በኋላ የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ የለበትም ካሉ በኋላ ሆኖም አቶ ሕዝቅኤል በሹመቱ የሥራ መደብ ላይ መመደብ አለብኝ በማለት በአፈፃፀም መዝገብ እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በመውሰድ ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ማረጋገጡን አሳውቋል።
አቶ እዝቅኤል፤ ለአጣሪ ጉባኤ ሚያዚያ 17 ቀን 2008 ዓ.ም የህገመንግስት ትርጉም አቤቱታ ማቅረባቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመልካች የሹመት የሥራ መደብ በሆነው የህግ ድጋፍ የሥራ ሂደት ባለቤት የሥራ መደብ ላይ ይመደቡ ማለት ተገቢ እንዳልሆነ በመግለፅ፤ አቶ ሕዝቅኤል ቀደም ሲል ይሰሩበት ከነበረው የህግ አገልግሎት ሃላፊ የሥራ መደብ ጋር ተመጣጣኝ በሆነ የሥራ መደብ ላይ ሊመደብ ይገባል በማለት የቀድሞ ውሳኔውን ማሻሻሉን እና ሆኖም ውሳኔው እንዲፈፀም ለሃዋሳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ ሲቀርብ ተቋሙ አቶ ሕዝቅኤልን በዲሲፕሊን ከሥራ የተሰናበቱ መሆኑን በመግለፁ፤ ፍርድ ቤቱ አቶ ሕዝቅኤል በዲሲፕሊን ጉዳይ ላይ ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችሉ በመግለፅ መዝገቡን መዝጋቱን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀረበ መዝገብ እና በተካሄደ ተጨማሪ የማጣራት ሥራ ድርጊቱ መፈፀሙን ማረጋገጥ መቻሉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በውሳኔ አሳቡ ላይ በግልፅ አብራርቶ አስቀምጧል።
አቶ ሕዝቅኤል በተለያየ ጊዜ ጉዳያቸውን በየደረጃው ለሚገኙ የክልሉ እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በማቅረብ ውሳኔ አግኝተዋል። ይህ ሆኖ ሳለ የሃዋሳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የግለሰቡን ህገመንግስታዊ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ አለመፈፀሙ የህግ የበላይነትን የሚቃረን ነው በማለት የህገመንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት በጉባኤው የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ አግባብ ሆኖ አልተገኝም በሚል በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩ በሙሉ ድምፅ ተወስኗል።
የውሳኔው ዋነኛ የመነሻ ጭብጥ አቶ ሕዝቅኤል በየደረጃው ላለ ፍርድ ቤቶች እያቀረቡ ውሳኔ በማግኘታቸው የየፍርድቤቶቹ ውሳኔ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ ወስኗል። በዚህም ምክንያት በየደረጃው የተሰጠው ውሳኔ ተግባሪ ሊሆን ይገባል እንጂ ጉዳዩ የህገ መንግስት ትርጉም አያስፈልገውም በሚል ጉዳዩን መቋጨቱን በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገመንግስት ትርጉም ውሳኔዎች ሰነድ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013