በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ ( ተሓህት ) ወደ አማርኛ ሲመለስ “ የትግራይ ሕዝብ አርነት ግንባር « የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ ም በ11 ወጣቶች በምዕራብ ትግራይ ቆላማ አካባቢ በሽሬ አውራጃ ልዩ ስሙ ደደቢት በተባለ ጎጥ ሲጠነሰስ ፤ ከእነ አረጋዊ በርሔ ፣ ግደይ ዘርአጸዮን ፣ ስዩም መስፍኔ ፣ ሙሉጌታ ሓጎስ ፣ ዑቁባዝጊ በየነ ፣ ዓባይ ፀሐዬና ሌሎች በእድሜ በሰል ያለው ወልደስላሴ ነጋ ነበር።
ለጣሊያን ያደሩት የአድዋው ባንዳ ፊታውራሪ ነጋ ፤ ወልደስላሴን በትግል ስሙ ስብሀትን ጨምሮ የ18 ወንድና ሴት ልጆች አባት ናቸው። ብዙዎቹ የትህነግ ቀደምት መስራቾችና አባላት በባንዳነት የሚከሰሱት በዚህና በዚህ መሰል መነሻ መሆኑን ያስታውሷል።
ብዙዎቹ የፊታውራሪ ነጋ ልጆች በወንድማቸው ስብሀት አጥማቂነት የትህነግ አባል ናቸው። ከአባልነትም በላይ እንደ እህቱ ቅዱሳን ነጋ ያሉት ላለፉት 30 አመታት ከፍተኛውን የፓርቲም ሆነ የመንግስት የስልጣን እርካብ ተቆናጥጠው ኖረዋል።
የትህነግ ስራ አስፈጻሚ ወይም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ ከስብሀት ነጋ ጋር በስጋ ወይም በጋብቻ ያልተዛመደ የለም። በፌደራልም ስልጣን ለመያዝ በዘረ ወይም በጋብቻ ከስብሀት ወገን የሚመዘዝ ሀረግ ግድ ይላል።
የትህነግ ስብስብና ጭፍራ የስብሀት ስረወ _ መንግስት ( Dynasty ) የሚባለው ለዚህ ነው። ስረወ መንግስት ማለት በዘር ግንድ ላይ የተመሰረተ ተከታታይነት ያለው የንግስና ሃረግ ነው። ትህነግ በፌደራልም ሆነ በትግራይ ክልል ስልጣን ላይ እያለ ስብሀት ሞቶ ቢሆን ኖሮ የትህነግን ዙፉን የሚረከበው ከስብሀት ቤተሰቦች አንዱ ነበር የሚሆነው።
ከሀገሪቱ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ( GDP ) ከ30 በመቶ በላይ ያህላል ተብሎ የሚታመነው ትዕመት (EFFORT ) የተሰኘው የኢኮኖሚ ኢምፓየርም የተገነባው ለስብሀት ቤተሰብ ነው። በዚያ ሰሞን የትህነግ ስብስብ ማጣፊያ ሲያጥረው ከንግድ ኢምፓየሩ የተወሰነ ድርሻ ለትግራዋይ በሽርክና ይሸጥ ሲባል ስብሀት በደም ፍላት ምን አግብቷችሁ !? ትዕመትን የማዝዘበት እኔ ነኝ በማለት ስብሰባ ረግጦ ወጥቷል።
ለነገሩ ስብሰባውን ረግጦ ወጣ እንጅ ተሰብሳቢው እንዳለ የማዕከላዊ ኮሚተው ቤተዘመድ ነው። በ17 አመቱ የትጥቅ ትግል 70 ሺዎች የሞቱት ከዚህ የማይተናነሱት አካል ጉዳተኛ የሆኑት ለስብሀት ነጋ መጻኢ የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ የበላይነት ነው።
ለዚህ ነው ትህነግ የተመሰረተውም፣ ለ27 አመታት በፌደራሉ አገዛዝ በአስኳልነት፣ በክልሉ ለሶስት አመታት ከዚያ በፊት ለ17 አመታት በትጥቅ ትግል የኖረው ፣ የተጋደለውና የሞተው ለትግራይ ሕዝብ ሳይሆን ለስብሀትና ለቤተሰቡ ነው የሚባለው።
ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለውን የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም ክህደት ተከትሎ በተከፈተው የሕግ የበላይነትን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ከእናት አባታቸው ጉያ ተነጥቀው የተማገዱት ብላቴናዎች ደመ ከልብ የሆኑት አካላቸው የጎደለው “ለአደይ ትግራይ ወይም የትግራይን ሕዝብ ሕገ መንግስታዊ መብት ለመከላከል ወይም የትግራይን ሕዝብ አንገት ለማስደፋት የሚንቀሳቀሰውን አህዳዊ አገዛዝ ለመመከት” ሳይሆን የስብሀትንና የቤተሰቡን ጥቅም እና ስረወ መንግስቱን ለማስቀጠል ነው።
በጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን የስብሀት ( “አቦይ” የማልለው መጠሪያው ስለማይገባው ነው ፤ ) ከእነ ጀሌዎቹ በቁጥጥር ስር መዋል የሕዳር 19ኙን ድል ሙሉኡ ያደርገዋል።
ትህነግ
ከማዕከላዊ መንግስት አምባገነናዊ
አገዛዝ በሕዝባዊ ተቃውሞና
ከራሱ በወጡ የለውጥ
ኃይሎች ከተፈነገለ በኋላ
በመማጸኛ ከተማው መቐለ
መሽጎ ሴራ ሲያሰር ፣ ደባ ሲዶልት ፣ ልዩነት ሲጎነቁል ፣ ሽብር ሲቀፈቅፍ ፣ ክህደት ሲጠነስስ ፣ ወዘተረፈ የነበረባት የመጨረሻ ምሽግ ተደርጋ ትታይ የነበረችው መቐሌ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓም ያለ ኮሽታ በሚባል ደረጃ እደግመዋለሁ በጀግናው መከላከያ ሰራዊት ከከሀዲው ትህነግ ጭቆናና አፈና ነጻ ስትወጣ ሕግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻው ወደ ወሳኝና አንጸባራቂ ምዕራፍ መሸጋገሩን ያረጋገጠ ነበር። አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ በአድናቆትና በአግራሞት እጁን በአፍ ያስጫነ አኩሪ ድል ቢሆንም ውሎ አድሮ ግን የከሀዲው ትህነግ ከፍተኛ ጠርናፊዎች አለመያዝ ማሳሰቡ አልቀረም።
ከሀዲውን ትህነግ እንደአስፈላጊነቱ ከተለያየ ማዕዘን አንጻር ማየት ፣ መበየንና መተንተን ይቻላል። በመጀመሪያ የትህነግ ወካይ ምልዕክትና ራስ ከዚያ ፤ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሩን በአንድ በኩል ርዕዮታለማዊና ፕሮፓጋንዳዊ ክንፉን በሌላ በኩል።
ትህነግ ሲነሳ ቀድሞ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው ወካይ ምልክት ”አቦይ“ ስብሀት ነው። መለስ ዜናዊን ጨምሮ የጉግማንጉጉ ትህነግ ሱስሎቭ ( አይዶሎግ ) የሚያመለከው ይህን ምልክት ነው። ፓርቲው የተዋቀረው በስብሀት ምሰሶነት ዙሪያ ነው።
ስብሀት የፓርቲው አስኳል ነው። ስብሀት የፓርቲው አንጋሽ ( kingmaker ) ነው። ስብሀት ሿሚ ሻሪ ነው። በትህነግ የምስረታ የመጀመሪያ አመታት በሊቀ መንበርነት ከመምራቱ በስተቀር በተለይ ከ1983 ዓም ወዲህ አንድም የመንግስት ኃላፊነት በይፋ ይዞ አላየንም።
ይህ ምን ያህል ፓርቲው በቁጥጥሩ ስር እንደሆነ ያረጋግጣል። ከመጋረጃው ጀርባ ሆኖ ግን ያሻውን ያደርጋል። ትህነግ ለእሱ እንደ ንግድ ኩባንያ ነው። እሱ የበላይ ጠባቂ ሆኖ መለስን በትህነግ ዋና ስራ አስፈጻሚነት ( CEO )መድቦ ሀገርን እንዳሻው እንደ ኩባንያ ያገላብጣል። ፓለቲካ ያስነግዳል።
ስብሀት ለትህነግ የጡት አባት ነው። መንፈሳዊ መሪም ነው። ሰለሞን ሰለሞናዊ ስረወ መንግስት መነሻ እንደሆነው ፤ ስብሀት የስብሀት ስረወ መንግስት መነሻ ነው። መድረሻም ነው። በእሱ ተወጠነ በእሱ ተፈጸመ።
ለእኔ የእሱ መያዝ መቐሌን ከመቆጣጠር፤ 200ሺህ ልዩ ኃይልንና ሚሊሻን ደምስሶ ትግራይን ነጻ ከማውጣት አይተናነስም። የዚችን ሀገር መጻኢ እድል በአዎንታ እንደ አዲስ የሚበይን ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
ይሁንና ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሩ በአንድ በኩል ርዕዮተ አለማዊና ፕሮፓጋንዳዊ ክንፉ በሌላ በኩል ለስብሀት ስረወ_ መንግስት እስትንፋስና ጋሻው ነበሩ። የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት የሀገርና የሕዝብ ሳይሆኑ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስሁት ርዕዮት አለም ተጠቅመው ስረወ _ መንግስቱን ቀን ከሌት የሚጠብቁ የአንድ ቤተሰብ የበላይነት የገነነባቸው የቅጥረኞች ስብስብ ነበሩ።
ከሀዲውን ትህነግ ለ27 አመታት በፌደራል ለሶስት አመታት በትግራይ አምባገነናዊ አገዛዝ ላይ ያቆየው ይሄው ስብስብ እንጂ የትግራይ ሕዝብ አልነበረም። የትግራይ ሕዝብና ይህ እፉኝት ስብስብ የተለያዩ መሆናቸውን በሕግ የበላይነትና የህልውና ዘመቻው በማያሻማ ሁኔታ ተረጋግጧል።
ከዚህም በላይ የከሀዲውን ትህነግ አመራሮች የገቡበትን ጉድጓድ እየጠቆመ ከማሲያዙ ባሻገር “ ለምን መጣችሁብኝ !?” በማለት መጠለያና መደበቂያ እንዲሁም ምግብና ውሃ በመንፈግ አንቅሮ እንደተፋቸው እየተመለከትን ነው። ኢትዮጵያን እንዲወጋ ያስታጠቁትን የጦር መሳሪያም በገዛ ፈቃዱ እየፈተ እያስረከበ ነው።
የስረወ _ መንግስቱ ሌላው እስትንፋስ ኢኮኖሚው ነው። ዘራፊው ትህነግ ገና አዲስ አበባን ሳይቆጣጠር ከደርግ ነጻ ባደረጋቸው ከተሞችና አካባቢዎች የሚገኙ የመንግስት ንብረቶችና ሀብቶች ወደ ትግራይ ይጭን ነበር።
በ1983 ዓም በጎጃም ክፍለ ሀገር ባደግሁባት የፍኖተ ሰላም ከተማ የሚገኘውንና በምህጻረ ቃል ኢዲዲሲ የተባለውን የመንግስት የጅምላ አከፋፋይ ንብረት ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ቅርንጫፍን ገንዘብና ንብረት፤ ከከተማው በቅርብ እርቀት የሚገኘውን የሁለቱን ብር ሸለቆዎች የመንግስት እርሻዎችን ተሽከርካሪዎች ፣ ትራክተሮች ፣ ኮምባይነሮችን፣ ገንዘብና በቆሎን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን ፣ የመንግስት መሰሪያ ቤቶችን እና በፍኖተሰላም ከተማ ይገኝ የነበረውን የሴቶች ማህበር ገቢ ማስገኛ ሆቴልን አልጋ ፍራሽና አንሶላ ሳይቀር እየዘረፈ ወደ መቐሌ ሲጭን እማኝ ነበርሁ::
ለነገሩ የትግራይ ሕዝብ በርሀብ እንደ ቅጠል እየረገፈ እርዳታን እየሸጠ የጦር መሳሪያ ይሸምት ከነበረ ወንበዴ ሌላ ምን ሊጠበቅ ይችላል።
ትግሉን ያሟሸው ባንክና ፓሊስ ጣቢያ በመዝረፍ አይደል። መንግስት ከሆነ በኋላም ይህን ዘረፋውን መዋቅራዊና ተቋማዊ አድርጎ ቀጥሎበታል።
ኤርምያስ ለገሰ ፤” የመለስ ልቃቂት“፤ በሚል ርዕስ ባስነበበን የትዕምት ስንክሳር እንደገለጸው ትህነግ ከዘላን ወንበዴነት (roving bandits ) ወደ ቋሚ ወንበዴነት (stationary bandit ) ነው የተቀየረው።
ለዚህ እንዲረዳውም ትካል ዕግሪ ምትካል ትግራይ (ትዕምት) ወይም የትግራይ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት ( Endowment Fund for the rehabilitation of Tigrai) EFFORTን አቋቁሟል።
በትዕምት ስር ካሉ ወደ 100 ከሚጠጉ ፋብሪካዎችና ድርጅቶች ውስጥ 11 ኩባንያዎች ሲመሰረቱ የተመዘገ ካፒታላቸው 798 ሚሊዮን ሲሆን ከ20 አመታት በኋላ ግን በሚደረግላቸው መንግስታዊና ፓለቲካዊ ከለላ ፤ በኮንትሮባንድ ፣ በግብር ስወራና የንግድና የልማት ባንኮችን ብድር በመጠቀምና ባለመክፈል ፤ ካፒታላቸው በ72 እጥፍ ተተኩሶ 52 ቢሊዮን መድረሱን ያረዳናል።
ይህ እንግዲህ በሰነድ የተደረሰበት ነው። በጨለማና በህቡዕ ላለፉት 30 አመታት የተዘረፈውን አይጨምርም። ይህ የንግድ ኢምፓየር ነው እንግዲህ የስረወ _ መንግስቱ ሌላው የደም ስር የነበረው።
ርዕዮታለማዊና ፕሮፓጋንዳዊ ክንፉ የስብሀታውያን መተንፈሻ ሳምባቸው ነበር። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በአንድ በኩል በማንነት ላይ የተመሰረተ አስመሳይ ፌደራሊዝም በፌደራል መንግስትነት 27 አመታትን ፣ በትግራይ ክልል ወደ ሶስት አመታት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ላይ አምነሽንሿቸዋል።
የማርክስን የኮምኒዝም ርዕዮተ አለም ሌኒንና ስታሊን አጣመውና የማንነት ፓለቲካን በአናቱ ዱለው እንደተጠቀሙበት ሁሉ የስብሀት ስረወ _ መንግስትም በመለስ ዜናዊ ቀማሪነት የማርክሲዝምንና የሌኒኒዝም ርዕዮት አለም በማዳቀልና እንዲመቸው አድርጎ አብዮታዊ ዲሞክራሲን በመተግበር ዜጎች በማንነታቸው እንዲከፋፈሉና እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩ በማድረግ በመሳሪያነት ተጠቅሞበታል።
ፕሮፓጋንዳውንና አስገድዶ ማጥመቁን ( ኢንዶክትሬሽን )በመንግስት ፣ በኢህአዴግ ሚዲያዎችና በማህበራዊ ሚዲያ ጭፍራዎቹ አማካኝነት ላለፉት 27 አመታት እንዲሁም ካለፉ ሶስት አመታት ወዲህ በትግራይ ቴሌቪዥን ፣ በድምጺ ወያኔ ፣ በወይን ፣ በትግራይ ሚዲያ ሀውስ ፣ በዲጂታል ወያኔ ፣ ወዘተረፈ ሌት ተቀን ልዩነትን ፣ ሀሰተኛ መረጃን ፣ ጥርጣሬን ፣ ጥላቻን ፣ የሴራና የውሸት ትርክቶችን በማራገብና በመንዛት አገዛዝ ላይ ለመቆየት ከመጠቀሙ ባሻገር በተለይ ማህበራዊ ሚዲያውን ጀንበሩ ከጠለቀችና ከወደቀ በኋላም እንደ ጦር መሳሪያ ( weaponry )በመጠቀም አፈር ልሶ ለመነሳት ባደረገው ሙከራ ቢላላጥም ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ትግራዋይን ፣ የውጭ ሀገር ዜጎችንና ሚዲያዎችን ማሞኘታቸው አልቀረም።
የከሀዲውን ትህነግ ሽንፈትና የእነ ስብሀትን መያዝና መደምሰስ ላለመቀበል በማህበራዊ ሚዲያው ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ በመናበብ ሌት ተቀን የሚያንበለብሉትን የውሸት ፍላጻ እየታዘብን ነው።
(የስብሀት ስርወ _ መንግስት ራሳቸውን የቻሉ ዳጎስ ዳጎስ ያሉ ተከታታይ መጽሐፎችም የማይበቁት ቢሆንም እኔም በተከታታይ ክፍሎች የምመለስበት ሆኖ ለዛሬ እዚሆ ላይ እልባት ላድርግ። )ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች።
አዲስ ዘመን ጥር 6/2013