ራስወርቅ ሙሉጌታ
በየአስፋልቱ ዳርቻ በውሃ መያዣ ኮዳዎችና በተለያዩ ጨርቆች ቤንዚንና ማስቲሽ የሚስቡት ህጻናት ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ይገኛል። የእነሱ በአደባበይ ይፋ የወጣ ቢሆንም በየሁለተኛ ደረጃና በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ተማሪ ወጣቶችም በከፍተኛ ደረጃ የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸው ይነገራል። በየመንደሩ የተሰገሰጉት የጫት ማስቃሚያና የሺሻ ቤቶች መበራከትም በኢትዮጵያ የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ ለመምጣቱ አመላካች ነገሮች ናቸው።
የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚነትን ተከትለው የሚፈጸሙ ወንጀሎችና ጥፋቶችም እስከ ቅርብ ጊዜ በሌሎች የአውሮፓና የአሜሪካ እንዲሁም በላቲን አሜሪካ ሀገራት ስንሰማቸው የነበሩ ወደኛዎቹም ከተሞች መዝለቅ ከጀማመሩ ውለው አድረዋል። ለመሆኑ የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚነት የሚያስከትላቸው ተጽዕኖዎች እንዴት ይገለጻሉ? እንዴትስ መከላከል እንችላለን? ስንል የማህበራዊ ልማትና አመራር ባለሙያ ከሆኑትና በቲቪ ዘጠኝ የክሊፍ ሞቲቬሽን ወይም አፋፍ ለመድረስ ዝግጅት አዘጋጅና አቅራቢ አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
የአደገኛ እፅ የሚያስከትላቸው ተጽዕኖዎች
ባለሙያው እንደሚያብራሩት የአደገኛ እጽ ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት ከሰው ልጅ ታሪክ ጎን ለጎን እኩል ተብሎ በሚገመት ደረጃ የእረጅም ጊዜ ታሪካዊ ዳራ እንዳለው ጥናቶች ይጠቁማሉ። ሰዎችንም በተለያዩ ምክንያቶች አነሳሽነት ተጀምሮ በጊዜያት ልምምድ ውስጥ ጥገኛና ተገዥ በማድረግ ደግሞ ተጠቃሚውን ለዘርፈ ብዙ የህይወት ችግርና ህመሞች ሲዳርግ መኖሩም ግልጽ ነው። ሱሰኝነቱም ለመዝናናት፣ ለህክምና፣ ለማወቅ ለመቅመስ በሚኖር ጉጉት፣ በጓደኛ ግፊት፣ በተትረፈረፈ አቅርቦት፣ በአካባቢ ተጽዕኖ፣ በስራ ማጣትና ሌሎችም መንስኤዎች አማካኝነት እንደቀልድ በመጠቀም እንደሚጀመር ጥናቶች ያመላክታሉ።
ከዚያም ከመቅመስ የተጀመረው ተጠቃሚነት ከማነቃቃትና ከማዝናናት ተሻግሮ በግለሰብ ደረጃ አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ አስተሳሰባዊ፣ ማንነታዊና መንፈሳዊ መታወክን የሚያስከትል ሲሆን በማህበረሰብ ደረጃ ደግሞ ለቤተሰብ መበተን፣ ለወንጀለኝነት መስፋፋት፣ ለበሽታዎች መዛመት፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎች መበራከት፣ ለሃብትና ንብረት መባከን ወዘተ ችግሮች በመዳረግ ማህበራዊ ደህንነትና ዋስትና ያናጋል። ይህም “አገር ማለት ሰው ነው” በሚል ብሂል ውስጥ የአደገኛ እጽ ሱሰኝነት የዜጎችን ሁለንተናዊ ማንነት መዘወሪያ የሆነውን አንጎል እና አዕምሮን ጤንነት በማሳመም እንኳን አገራዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ቀርቶ ለአገር ሸክም እንዲሆኑ በማድረግ በሀገር ደረጃ የሰው ሃብት ኪሳራ እንዲደርስ ያደርጋል። በድምሩም የማህበራዊ ስነ-ልቦና ቀውስ ይፈጠራል።
አደገኛ እጽ ከአገር አገር እና ከዘመን ዘመን በአይነት፣ በመጠን፣ በመልክ፣ በጉዳትና በይዘት የተለያየ ቢሆንም ከሚያደርሰው ዘርፈ ብዙ ችግር ተመሳሳይ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የዓለም ጤና ድርጅት “በሽታ” በማለት ከበሽታ ተርታ ሰይሞታል። ሱስ አስያዥ አደገኛና አደንዛዥ እጽ ከሚባሉት መካከል ደግሞ እንደ እኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ጫት፣ ሲጋራ፣ አልኮል መጠጦች፣ ሺሻ (ጋያ)፣ ጋንጃ (እጽ ፋሪስ)፣ ሳፋ (አንጋዳ)፣ ቤንዚን፣ ማስትሽ ወዘተ ቀዳሚዎቹ ተጠቃሽ ናቸው። አደንዛዥ እጽን መጠቀም በቀዳሚነት ራስን እስከ ማጥፋት ለማድረስ የሚያበቃ መሆኑን ካለመረዳት፤ በሁለተኛ ደረጃም የእውነት ከሚያደርሰው በተቃራኒ በተሳሳተ እውቀት በስሜት በመነዳት የሚጀመር ነው። በአሁኑ ወቅትም የአገራችንን ህዝብ በተለይ ወጣቱን ክፍል ለከፋ ችግር እየዳረገ ያለበትና በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋት የሚገኝበት ፈታኝ ወቅት ላይ እንገኛለን።
አደንዛዥ እጽ በዋነኝነት ተጠቃሚውን ብቻ በመጉዳት ሳይገደብ ቤተሰብን፣ አካባቢን፣ ማህበረሰብ በማካተት መላ የአገር እድገትና ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያስተጓጉል ዓለም አቀፍ ችግር ነው። ለምሳሌ ብንመለከት ሲጋራ ውስጥ ብቻ ከሰባት ሺህ 357 በላይ ጎጂ ንጥረ-ነገሮች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል ከ200 በላይ የሚሆኑት የተለያዩ በሽታ አምጭና ከ70 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ካንሰር አስያዥ ናቸው።
በዚህ ረገድ አህጉራችን አፍሪካን እንኳን ለአብነት ወስደን ስርጭቱን ለመገመት ብንሞክር (የዓለም ጤና ድርጅት በ2013 ያወጣው መረጃ) እንደሚያመለክቱት ከሆነ ከአፍሪካ ህዝብ ቁጥር መካከል ግማሹ ወይም 50 በመቶው ወጣት ሲሆን ከዚህም 22 ነጥብ ሰባት በመቶው ወይም ግማሾቹ ማለት በሚያስደፍር መልኩ የተለያዩ አይነት አደገኛ እጽ ሱሰኞች ወይም ጥገኞች ናቸው። ይህንን አሀዝ መነሻ በማድረግ አሁን ደግሞ ምን ያህል ሊስፋፋ እንደሚችል መገመትን ለአንባቢያን የምንተዎው ይሆናል?
ለመከላከል ምን መሰራት አለበት
በመሆኑም ከላይ የተደረደሩት ችግሮች የግል እና የማህበራዊ ስነ-ልቦና መቃወስ ዋናው ምክንያት የሆነውን ሱሰኝነትን በሽታ እንደሆነ ተረድቶ በማስረዳት ውስጥ የመፍትሔ ብልሃቶችን ከግለሰብ እንደዜጋ፣ ከማህበረሰብና በዋነኝነት ደግሞ ከመንግስት የሚጠበቅ ይሆናል።
ከዚህም አዋጭ የሚባሉ ቀድሞ መከላከያና ጉዳቱን መቀነሻ ዘዴዎች መካከል አንደኛ የቅድመ-መከላከል ስራ ማለት የማስተማር፣ ግንዛቤ መፍጠር ወይም የአቅም ግንባታ ስራዎች፣ ሁለተኛ ህጋዊ እርምጃ የሚወስዱ ከለላ የመስጠት ስራ ማለትም ስርጭቱንና ግብይቱን ከመቆጣጠር ጀምሮ ታክስና ግብር ላይ ጫና መፍጠር እንዲሁም በሶስተኛ ደረጃ በችግር ውስጥ የሚገኙት ደግሞ ካሉበት በሽታ ታክመው መውጣት የሚያስችላቸው የማገገሚያ ማዕከላት ግንባታ መስፋፋት ያስፈልጋል። ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ የሁሉም ሚናና አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ መታወቅ አለበት።
ከማህበረሰቡ መካከል ደግሞ እያንዳንዱ ወጣት እራሱን ከአደገኛና አደንዛዥ እጽ ሱሰኝነት በመጠበቅ አንደኛ የግል አስተሳሰቡንና ጤንነቱን ከመቃወስ በመከላከል ጤናማና ስኬታማ ህይወት ለመምራት መስራት አለበት። በጋራ ደግሞ ከማህበረሰባችን ስነ-ልቦናዊ መረጋጋት እና ከአገር እድገት፣ ልማትና ብልጽግና መፋጠን አንጻር እንደ ግለሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚቻል በመረዳትና ለችግሩ አሳሳቢነትና ስፋት ትኩረት በመስጠት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከሚመለከታቻው አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚጠበቅ ባለሙያው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ።
አዲስ ዘመን ጥር 04/2013