ለምለም መንግሥቱ
በልብሰተክህኖ የተዋቡ የሰንበት ትምህርትቤት ተማሪዎች ዝማሬ በማሰማት፣ካህናት በከበሮና ጽናጽል ወረብ በማቅረብ፣ከታዳሚው አጀብ ጋር የጥምቀት በዐል ቀልብን በሚስብ ሁኔታ ነው የሚከበረው፡፡ በልዩ ድምቀት ነጫጭ የባህል አልባሳት በለበሱ ምእመናን ታጅቦ ህዝበ ክርስቲያኑም ቀስቃሽ ሳያስፈልገው የአካባቢውን ታቦታት አጅቦ ታቦታቱ ወደ ተዘጋጀላቸው የማደሪያ ሥፍራ ይተማል። በዚህ መልኩ ከተለያየ አቅጣጫ የመጡት ታቦታት በአንድ ሥፍራ ይሰባሰባል፡፡ ይህ ቀን ከተራ በሚል የሚከበር ነው።
ህዝበ ክርስቲያኑ የሸኘውን ታቦት በማግሥቱ ሲመልስም እንዲሁ ደመቅ ባለ ስነስርዓት በዘፈንና በመዝሙር በማጀብ ነው። ህጻን አዋቂ፤ ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም የበዓሉ ታዳሚዎች በስፍራው የሚገኙት ማልደው ነው። የጥምቀት በዓል ከሌሎች በዓላት ለየት የሚያደርገውም በበዓሉ አከባበር ስፍራ የሚገኘው የእምነቱ ተከታይ ብቻ ባለመሆኑ ነው።
የሌሎች እምነት ተከታዮችና የውጪ ሀገር ቱሪስቶችም የበዓሉ አድማቂ ናቸው፡፡ የጥምቅት በዓል ከሀገራችንም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የባህልና የትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል። ይሄ መሆኑ ደግሞ በዓሉ አለምአቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው አድርጓል።
የበዐሉ አድማቂ ምዕመናንም ከጥቂት ቀናት ቀደም ብለው የገና በዐል በማክበራቸው ለጥምቀት በተለየ ሁኔታ በምግብና በመጠጥ ዝግጅት ስለማይጠመድ ነፃ ሆኖ ነው የሚታደሙት፡፡በተለይም ሴቶች የቤት ውስጥ ሥራ ጫና የሚቀንስላቸው በጥምቀት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፡፡
በጥምቀት በዐል የየአካባቢው ወጣት ታዳሚውን በማስተባበር፣ታቦታቱ የሚሄዱበትን መንገድ በምንጣፍ በማሳመር የሚያደርጉት እገዛም አይዘነጋም፡፡በዐሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ህግ የሚያስከብሩ የፀጥታ አካላትም ሚናቸውን በመወጣት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡በዚህ የጥምቀት ወቅት ኮቪድ 19 ወረርሽኝን የመከላከሉ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ስለሚገባ የጤናው ዘርፍም የጎላ የተሳትፎ ሚና ይኖረዋል፡፡
ከዚህ አንፃር በአዲስ አበባ ከተማ በዐሉን ለማክበር እየተደረገ ስላለው ዝግጅት፣እግረ መንገድም በከተማዋ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለጎብኝዎች ምቹ በማድረግ፣በተለይም ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ጎብኝዎችን በማስተናገድና ከዘርፉም ለመጠቀም ቀድሞ ሥለተሰራው ሥራ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር እንደሚከተለው ዳስሰናል፡፡
በቅድሚያም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥላለው ዝግጅት የቤተክርስቲያኗ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሊቀትጉሀን እስክንድር ገብረክርስቶስ እንደገለጹልን ፤በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የበዐሉ ድባብ ሳይቀንስ እንደወትሮው ሁሉ ድምቀቱ እንዲጠብቅ በቤተክርስቲያኗ አስፈላጊው ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ጤና ሚኒስቴር ያስቀመጣቸውን ወረርሽኙን የመከላከያ መርሆዎች እንዲተገበሩ ከየአድባራቱ ወደ ጃንሜዳ ማደሪያ የሚሄዱና ታቦታቱን የሚያጅቡ ምዕመናን መልዕክቱ እንዲደርሳቸው በማድረግ፣በተለይ ሁሉም በሚሰባሰቡበት በጃንሜዳ መተፋፈግ እንዳይኖር አራቱም የጃንሜዳ መግቢያ በሮች ክፍት ሆነው በሁሉም አቅጣጫ እንዲስተናገዱ ይደረጋል፡፡
በጃንሜዳ የሚያድሩት ታቦታት ከአሥራአንድ በላይ ከሚሆኑ አብያተክርስቲያናት 39 ታቦታት ሲሆኑ፣ከየአቅጣጫው ታቦታቱን የሚያጅበው ሰው ቁጥርም በዚያው ልክ ከፍተኛ ስለሚሆን አስፈላጊው ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል፡፡በቤተክርስቲያኗ ሥርአት መሠረትም በዐሉ የሚመራው ጃንሜዳ ከሚያድሩ አብያተክርስቲያናት መካከል በሚመረጥ በአንደኛው በመሆኑ የዘንድሮው ተረኛ ደብር የገነተጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊሥ ቤተክርስቲያን በመሆኑ ኃይማኖታዊ ሥርአቱንና ሌሎችንም በመምራት ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡
በሰንበት ትምህርትቤት ማደራጃ መምሪያ የአዲስ አበባ ከተማ ማዕከል ደግሞ ወጣቶች በማስተባበር የበዐል ዝግጅት ሥራው ተከናውኗል፡፡ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረሥ የቀረው ሥራ መገምገምና የተጓደለ ነገር ካለ ክፍተቱን ማስተካከል ነው፡፡
ኮቪድን ለመከላከል ሲባል የታዳሚ ቁጥርን ለመቀነሥ የተገደበ ነገር ይኖር እንደሆን ሊቀትጉሀን እስክንድር ላቀረብንላቸው ጥያቄ እስካሁን አለመኖሩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡በጠቅላይቤተክህነት አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ከፀጥታ አካላቱ ጋርም በሰንበት ትምህርትቤት የተደራጁ ወጣቶች ተጨማሪ ሆነው በማስተባበር፣በሽታውንም ለመከላከል የሚረዱ ተግባራትን በማከናውንና ግንዛቤ በመፍጠር ያግዛሉ ብለዋል፡፡
ለታቦታት ማደሪያ የሚውለው ጃንሜዳ በኮረና ቫይረሥ ምክንያት በጊዜያዊነት ከአትክልት ተራ ለተነሱ ነጋዴች አገልግሎት ውሎ እንደነበርና በቅርቡ ደግሞ ነጋዴዎቹን ከቦታው በማስነሳት ሥፍራውን ጽዱ በማድረግ ለበዐሉ ዝግጁ መሆኑ ይታወሳል፡፡ሥፍራው በጊዜያዊነት ለንግድ በመዋሉ እንዲፀዳ ተደረገ እንጂ ጃንሜዳ ለወትሮውም ቢሆን ደረጃውን የጠበቀ ንጽህና አለው ለማለት አያስደፍርም፡፡ምድረግቢው አቧራ ነው፡፤መፀዳጃቤትም ባለመኖሩ ሰዎች ባገኙት ሥፍራ ሲጸዳዱ ይስተዋላል፡፡አሁን ደግሞ ጥምቀት በዓለም ቅርስነት የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ይህን የቱሪስት መሥህብ የሆነው ታላቅ በዐል ሲከበር ለማየት ወደ ሥፍራው የሚሄዱ ቱሪስቶችን በተገቢው ለማስተናገድ የሚኖረው የገጽታ ተጽዕኖ ቀላል እንደማይሆን ይታመናል፡፡በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሀገር ውስጥና ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶችና እንግዶች በሚገኙበት በዚህ ሥፍራ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች መታረም ስላለባቸው።
ከጃንሜዳ ቅጽረ ግቢ ጽዳት እና ማሳመር ጋር ተያይዞ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። ሊቀትጉሀን እስክንድር እንዳሉት የከተማ አስተዳደሩ መሬቱን ሳር በማልበሥ ምቹ አድርጓል፡፡ታቦታት የሚያድሩበት፣አባቶች የሚቀመጡበትና እንግዶች የሚያርፉበት በተለየ ሁኔታ እንዲዘጋጅ ጥረት ተደርጓል፡፡በመሆኑም ሥፍራው ከዚህ ቀደም ከነበረው ይዞታ የተሻለ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡በጃንሜዳ የአንድ አካል ብቻ አለመሆኑም ለክፍቱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ይሁን እንጂ ውስጡ እንደ ፈረስ ጉግሥና ሥፖርታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ምድረግቢውን በጋራ በማስዋብና በመንከባከብ ኃላፊነታቸውን ቢወጡ ተጠቃሚነቱ የጋራ ይሆናል ይላሉ፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ በቤተክርስቲያኗ በኩል በበዐሉ ላይ ከተለያዩ ሀገራት የሚታደሙ የኃይማኖት መሪዎች ይመጡ ነበር፡፡ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረሥ ግን ቤተክርስቲያኗ መረጃው እንደሌላት ነው ሊቀትጉሀን እስክንድር የነገሩን፡፡ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ዓለማቀፋዊ ሥጋት የሆነው ኮቪድ ያስከተለው ችግር ነው፡፡
የጥምቀት በዓል ቱሪስቶች በኢትዮጵያ በሥፋት የሚጎበኙበት ወቅት በመሆኑ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ማረፊያና መሸጋገሪያ ሆና ታገለግላለች፡፡መውጫና መግቢያ ብቻ ሆና ከማገልገል ባለፈ የቱሪስት መሥህቦችዋን በመጠቀም የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም ጥረት ማድረግ እንዳለባት ይጠበቃል፡፡ከዚህ አንጻር እየተከናወኑ ሥላሉት ተግባራት በአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወርቁ መንገሻን አነጋግረናቸዋል፡፡
እርሳቸው እንዳስረዱት በዐሉ ሲደርስ ብቻ ሳይሆን፣ቢሮው እስከታች ቀበሌ ድረሥ በዘረጋው መዋቅር በመጠቀምና እንደ አስጎብኝ ድርጅቶችና የሆቴል አገልግሎት የሚሰጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በከተማዋ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎች በተለያየ መንገድ የማሥተዋወቂያ ዘዴዎች በመጠቀም ተደራሽ የማድረጉን ሥራ በቋሚነት ያከናውናል፡፡በጥምቀት በዐል ወቅት ደግሞ ቅንጅቱን የበለጠ በማጠናከር ተጠቃሚነትን ከፍ የማድረግ ሥራ ይከናወናል፡፡
አቶ ወርቁ እንዳሉት የቱሪዝም ሥራ ድንበር ዘለል በመሆኑ በአንድ ተቋም ብቻ ተሰርቶ ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም፡፡በመሆኑም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ለማሳተፍ የሚያስችል በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ የሚመራና የከተማው የካቢኔ አባላትንና የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎችን ያሳተፈ የቱሪዝም ፎረም ተቋቁሟል፡፡ፎረሙ ታዛቢ ሳይሆን ተሳታፊ ነው፡፡አባላቱ ቱሪዝሙን ለማሳደግ በጋራ በማቀድ እያንዳንዳቸውም የድርሻቸውን ይወጣሉ፡፡ይህ ደግሞ ገቢ ለማስገኘት፣የሀገር ገጽታን ለመገንባት በዘርፉ ከዓለምአቀፍ ተሞክሮዎች ልምድ ለማግኘት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡እስካሁንም ጥሩ ሥራ ተሰርቷል፡፡
ለአብነትም መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ የፎረሙ አባል መሆኑ ለማስታወቂያ ሰሌዳ ቦታ ሲጠይቅ አስፈላጊነቱን በቀላሉ በመገንዘቡና የቱሪዝም ልማት ድርሻንም የራሱ አድርጎ በመውሰዱ በቀላሉ ምላሽ ይሰጣል፡፡በዚህ መሠረት ቢሮው ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻዎችና ተያያዥ መረጃዎችን የያዘ 32 የሚሆኑ ቋሚ የቱሪስት ካርታዎች ወይንም ሰሌዳዎች በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ተተክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየርምንገድም ባስገነባው ስካይላይት ሆቴል ውስጥ ‹‹ስቶብ ኦቨር ቱሪዝም›› የሚል በማመቻቸት ለመሸጋገር ወይም ትራንዚት የሚያደርገውን ቱሪሥት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉትን የቱሪስት መዳረሻዎች ጎብኝቶ እንዲሄድ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ይሄ ተቋሙ የፎረሙ አባል በመሆኑ የመጣ ጥቅም ነው፡፡ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሲወጡ ቢሮው የሚያከናውነውን ተግባር ያቀላጥፍለታል፡፡ቱሪሥቱም ምቹ ነገር ሲፈጠርለት የቆይታ ጊዜው ይራዘማል፡፡ወደ መጡበት ሲመለሱም የአምባሳደርነት ሚና ሊወጡ ይችላሉ፡፡
በተዘዋዋሪም አየርመንገዱ ገቢ ያገኛል፡፡በትራንስፖርት፣በማስጎብኘትና ተያያዥ በሆነ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡በዚህ አመትም ቢሮው በአምሥት የውጭ ቋንቋዎች በሲዲ አዘጋጅቶ ወደ አምሥት ሺህ ኮፒዎች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት በመላው ዓለም ያሰራጨ ሲሆን፣ቢቢሲና አልጀዚራ ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ ለማስተዋወቅም እቅድ መያዙን ይናገራሉ፡፡
እንቅስቃሴዎቹ የአውሮፓ የንግድና ቱሪዝም ምክርቤትን አስተያየት መሠረት አድርጎ በቅርቡ ይፋ በሆነው መረጃ ኢትዮጵያ መጎብኘት ካለባቸው 10 የዓለም ከተሞች አንዷ እንድትሆን አስችሏል፡፡የብዙ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችንና ህዝቦች መገኛ፣ደረጃቸውን የጠበቁ የሆቴልቤቶች ግንባታ መሥፋፋት፣የ118 ኤምባሲዎች መቀመጫ፣በርካታ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችም መገኛ መሆኗ የኮንፈረስ ቱሪዝም እንድትስብ መንገድ ስለከፈተላት ተመራጭ አድርጓታል፡፡
ቢሮው የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃትና የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ቱሪስቱን ቢጠባበቅም ኮቪድ ያጠላበት ጥላ ዘርፉ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የጠቆሙት አቶ ወርቁ ተጽዕኖው ቢኖርም ወረርሽ ኙ አንድ ቀን ሊወገድ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ ሥራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ የቅርስ ጥናት ባለሙያ መምህር መክብብ ገብረማርያም ተጨማሪ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ ወቅቱ ከአዘቦቱ በብዛት ቱሪስቶች የሚመጡበት ጊዜ በመሆኑ ቢሮው ሁሌም እንደሚያደርገው ለአስጎብኝ ድርጅቶች፣ለሆቴልቤቶች፣የምሽትቤቶችና ተያያዥ ሥራ ለሚሰሩ ባለሙያዎች እንግዶቻቸውን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በመሥጠት የማብቃት ሥራ በአሁኑም ቀድሞ ኮቪድን መከላከል ማዕከል ባደረገ ተከናውኗል፡፡ቢሮው ከወትሮ በተለየም የሥራ ክፍሎችን በባለሙያ በማደራጀትና በዳይሬክቶሬት ደረጃ ከፍ ብሎ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
መምህር መክብብ እንዳሉት ተራራማው የከተማዋ አካባቢዎች በራሳቸው የቱሪሥት መሥህብ ናቸው፡፡በተራሮቹ ላይ የቀድሞ ነገሥታት ቤተመንግሥቶች ይገኛሉ፡፡በአሁኑ ጊዜም 26 ያህል ሙዚየሞች ሲኖሩ፣ከእነዚህ መካከልም ወደ 13 የሚሆኑት በዓለምቀፍ ታዋቂ ሆነዋል፡፡በከተማዋ ቢሮው ፍቃድ ሰጥቷቸው ወደ አራት መቶ የሚሆኑ አስጎብኝዎችና ኮከብ ያላቸው ከአንድ መቶ በላይ ሆቴሎች ይገኛሉ፡፡
‹‹ወቅቱ ለከተማዋ የቱሪዝም ትንሳኤ ነው ማለት ይቻላል››ያሉት መምህር መክብብ የአንድነት፣የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች ተጨማሪ ሆነው መሰራታቸው የቱሪሥት መዳረሻነቷን የበለጠ ከፍ እንደሚያደርገው ነው የተናገሩት ፡፡
በጥምቀት በዓል መለከት፣በገና፣መሲንቆ፣ከበሮና ጽናጽል የበዐሉ ማድሚቂያ ብቻ ሳይሆኑ መንፈሳዊ መገለጫ በመሆናቸው እነዚህን የመንፈሳዊ ግብአቶች ይዘው የሚታደሙ መንፈሳዊ ዝግጅታቸውን ቀድመው ነው የሚያጠናቅቁት ፤ በዚህ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ሀገረ ሥብከት ሥር 270 ያህል አጥቢያዎች ይገኛሉ፡፡እያንዳንዱ አጥቢያ የዝማሬ አገልግሎት የሚሰጡ ብቻ እስከ 150 አባላት ያሏቸው ሲሆን፣በአጠቃላይ ሰፊ ቁጥር ያለው መንፈሳዊ ተሳትፎ ይኖራል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2/2013