አዲስ ዘመን፡– ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱን ስትሰማ እንደ አንድ ዜጋ ምን አይነት ስሜት ተሰማህ?
ጌትነት፡– መንግስት የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የህወሓት ጽንፈኛው ቡድን ጥቃት ማድረሱን በሰበር ሲያሳውቅና የሕግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ ሲገልጽ ጥቃቱን የፈጸመውም ግብጽ አሊያም ሱዳን ወይም ደግሞ ሌላ አካል አልነበርምና በወቅቱ ጉዳዩ ከማሳዘን አልፎ አስገርሞኛልም ።በወቅቱም መከላከያ ጥቃት ይፈጸምበት እንጂ ጉዳዩን በብቃት በመወጣት መልሶ ቦታዎቹን ይቆጣጠራል የሚል ጽኑ እምነት ነበረኝ ። ግን በግሌ የነበረኝ ስጋት ምንድን ነው ብለሽ ብትጠዪቂኝ ይህን ክፍተት በመጠቀም ሌሎች አካላት በሚያደርጉት ሴራ ወደሌላ ነገር እንዳያመራ የሚል ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡– በእንዲህ አይነት ስሜት ውስጥ እንዳለህ ህግ የማስከበር ሂደቱ ተጀምሮ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ እንደ አንድ ጋዜጠኛ እንድትዘግብ ወደስፍራ ትሄዳለህ ተብሎ ሲነገርህስ ምን ተሰማህ?
ጌትነት፡– ልክ ጉዳዩ በሰበር ዜና ከተሰማ በኋላ ከእናቴ ጋር በመሆን ቤት ውስጥ ሰለጉዳዩና ሄጄ ልዘግብ እንደምችል አወራ በነበረበት ሰዓት የእናቴ ምላሽ ከባድ ነበር ።በፍጹም ወደስፍራው እንዳልሄድባት ነበር ደጋግማ ታስጠነቅቀኝ የነበረው ።ሂድ እንኳ ብትባል ስራው ይቀራል እንጂ እግርህን አታነሳም ትለኝ ነበርና በዚህ እቀልድባት ነበር፡፡
በዚህ አይነት ስሜት ውስጥ ሆኜ ግን ጥሪው ደረሰኝ ። ልክ ጥሪውን ስሰማ ወደስፍራው የማቀናው ልምድ ካለው አንጋፋ የፎቶ ጋዜጠኛ ዳኜ አበራ ጋር መሆኑን ስሰማ የበለጠ ደስ አለኝ ።ምክንያቱም ልምድ ካለው ጋር መሄድ በመቻሌ ለነገሮች አዲስ እንደማልሆን እንዳምን ስላደረገኝ ነው ።በቦታውም ተገኝቼ ስራውን መስራት እችላለሁ የሚል እምነት ነው ያደረብኝ ።ወደስፍራው ስሄድ ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብኝ ከኃላፊዎች ጋርም ሆነ በራሴ አንዳንድ ስለውጊያ እና ጦርነት ዘገባን የተመለከቱ ጠቃሚ ናቸው የምላቸውን መረጃዎች በማንበብ ዝግጅት ማድረግ ጀመርኩ ። ስለዚህ ምንም አይነት ፍርሃት አልነበረኝም፡፡
እናቴን ግን ጎንደር መስክ ልወጣ ነው ስል ነገርኳት። አክዬም በአካባቢው ኔትዎርክ ላይሰራ ስለሚችል ስልክ አልደወልክልኝም ብለሽ እንዳታስቢ ብዬ ከወጣሁ በኋላ ከተለያየ የሚዲያ ተቋም የተሰባሰብን ጋዜጠኞች ከአዲስ አበባ በአንቶኖቭ እንነሳ እንጂ የት እንደምንደርስ ምንም አይነት መረጃ የለኝም ።እኔ በግሌ አስብ የነበረው ጎንደር ደርሰን ከዛ በመኪና ደግሞ ወደሌላው አካባቢ እንሄዳለን የሚል ነበር ።እንደቀልድም አድርገን ወዴት ነው ማረፊያችን ስንል የሚወስዱንን አካላት ብንጠይቅም እነሱም በቀልድ መልክ ምንም እንደማይታወቅና ስናርፍ ብቻ እንደምናውቅ ነበር ሲገልጹልን የነበረው፡፡
የጉዟችን መዳረሻ ሆኖ አንድ አየር ማረፊያ እንረፍ እንጂ አካባቢው የት እንደሆነ ላውቅ አልቻልኩም ነበር። ስናርፍ ደግሞ በዙሪያው የአገር መከላከያ ሰራዊት ነበር ። በመጨረሻ ግን ሽሬ አውሮፕላን ማረፊያ መሆኑን ተረዳሁ። በወቅቱ ሽሬ ሰላም ይሁን ውጊያ ይኑርበት ምንም መረጃ ባይኖረኝም እንዳልኩሽ በዙሪው ያለውን ሰራዊት ሳይ መሃል ጦርነቱ ውስጥ የገባሁ ያህል እንደተሰማኝ ልሸሽገው አልችልም ።
አዲስ ዘመን፡– ወደስፍራው ከተጓዝክስ በኋላ ወደ 21 ቀናት ያህል አሳልፈሃልና በቆይታህ ያስተዋልከውና ያጋጠመህ ነገር ምንድን ነው?
ጌትነት፡– በወቅቱ ያጋጠመኝ ነገር በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ያለውን ቤተሰባዊ የሆነ ግንኙነት ነው ።ሰራዊቱ በጽንፈኛው ቡድን የደረሰበት ጥቃት አለ፤ በዛ ጥቃት ደግሞ የተወሰነው የሰራዊቱ አባል ያለበት አይታወቅም ። ከዚህም የተነሳ በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ያስተዋልኩት ነገር አባላቱን ለማስመለስ የሚደረገውን እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴና ቁጭት የተቀላቀለበትን ሂደት ነው፡፡
ሌላው የሰራዊቱን ጥንካሬ ያስተዋልኩት እኛ ቀን ስምንት ሰዓት ሰርተን ደክሞን እንተኛለን ።እነሱ ዘንድ ግን ይህ አይታሰብም ።ለመተኛት ቢሞክር እንኳ ጊዜው ከተገኘ ወታደሩ ክርታስ አንጥፎና ድንጋይ ተንተርሶ ምናልባት ጎኑን ቢያሳርፍ ነው ።ቁርና ሀሩር እየተፈራረቀባቸው ነው አገር የሚያስጠብቁት ።ይህን አይነት ኑሯቸውን ከእኛ ህይወት ጋር ሳነጻጽረው የእኛ ምንም እንደሆነ ነው መረዳት የቻልኩት ።በወቅቱ እኛ እናድር የነበረው የሰሜን እዝ አዛዦች የነበሩበት ቢሮ ውስጥ በተገኘው ነገር ላይ መጋረጃ ለብሰን ሲሆን፣ እነሱ እንዳልኩሽ አዳርና ውሏቸው በየጉራንጉሩ ነው ።እውነቱን ለመናገር ከእነሱ የአኗኗር ሁኔታ በመነሳት ብዙ ነገር አስተውያለሁ፤ በህይወቴ ከሰራዊቱ የተማርኩት ነገር ቢኖር ከዚህ በኋላ ምንም አይነት ፈተና ቢደርስብኝም ለመቋቋም አቅሙ እንዳለኝ ነው፡፡
ከዚህ ውጭ ለእኔ በወቅቱ ጥንካሬ የሆነኝ የፎቶ ጋዜጠኛው ዳኜ አበራ ነው ።እሱ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ለዘገባ ስራ ሄዶ ስለነበር ልምድ ያለው ነው ።አንዴ የመጨረሻው ምሽግ ነው ተብሎ የተነገረለት ተንቤን አካባቢ ልንገባ ባለንበት ወቅት የጁንታው ቡድን አለበት ተብሎ ውጊያ እየተካሄደ ነበር ።በወቅቱ ባለከዘራው ኮሎኔል ሻምበል በየነ እያዋጓቸው ያሉ ሻለቃዎች በውጊያው አምድ ነበሩና ወደስፍራው የፎቶ እና የቪዲዮ ካሜራ ባለሙያዎች ብቻ ናችሁ የምትሄዱት ተባለ። ይሁንና ከነበረው ስሜት የተነሳ ሁላችንም ወደምሽጉ ካልሄድን አልን ።በወቅቱ ዳኜ ወደስፍራው እንዳልሄድ ቁጣ በተቀላቀለበት ማስጠንቀቂያ ጭምር ነበር እንዳልሄድ የነገረኝ ።የእኔ መሄድ አንዳች ፋይዳ እንደሌለውና እሱ ግን ፎቶግራፍ ብቻ አንስቶ እንደሚመጣ ነግሮኝ ከሞትኩም ከመስሪያ ቤታችን አንድ ሰው ብቻ መሆን ስላለበት ቢያንስ አንተ እዚሁ ቅር በማለት ኮስተር ብሎ ስለተናገረኝ እኔም የፊቱን ቁጣ በማየት ለመመለስ ችያለሁ፡፡
እነርሱ በሁለት መኪና ወደስፍራው ሲያቀኑ እኔ ከኮሎኔሉ ጋር ሆኜ አቅርቦ በሚያሳይ መንጽር ከላይ ሆኜ ስመለከት ነበር ።በርቀት እያየናቸው በመሃል ከባድ ፍንዳታ ተሰማ ።ድምጼን በጣም ከፍ አድርጌ በድንጋጤ ጋዜጠኞቹ ባለፉበት ቦታ ነው የፈነዳው ብዬ ከተናገርኩ በኋላ በንግግሬ ደግሞ እንደማፈር አልኩ፤ ምክንያቱም በስፍራው ያሉት ጋዜጠኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ሰራዊቱም ነበሩና ነው ።አጠገቤ ያሉት ኮሎኔልም “እስኪ አካባቢውን ቀርጸው ይምጡና ሁኔታውን እናየዋለን” ሲሉ አደመጥኳቸው፡፡
እኔ በወቅቱ የፍንዳታውን ድምጽ ስሰማ ወይኔ ጋዜጠኞቹ ብዬ ወደጓደኞቼ አድልቼ መናገሬን ተከትሎ አንደኛው አጃቢ “ያው ወታደሩስ ያለው እዛ አይደል!” ሲል እርሳቸው ግን ዞር ብለው ለዛው አጃቢ አንድ ነገር ሲናገሩ አስተዋልኩ፤ አንድ ጋዜጠኛ ሲሞትና አንድ ወታደር ሲሞት ለእነሱ የሚሰጠው ስሜት እኩል አይደለም ።ጋዜጠኛ ቢሞት ለጁንታው ቡድን የድል ያህል ነውና ለጋዜጠኛው ማሰባችን የግድ ነው ነበር ያሉት ።
አዲስ ዘመን፡– በስፍራ እያለህ በርካታ ዜናዎችን ለአንባቢያን አድርሰሃልና ከእነዛ መካከል ስሜትህን የሚይዘው የትኛው ነው? ምክንያትህስ ምንድን ነው?
ጌትነት፡– የሰራኋቸው ዘገባዎች በሁለት ምክንያት ውስጤን ይነኩታል ።አንዱ ያጋጠመኝ ነገር ባለከዘራው ኮሎኔል ሻምበል በየነ እና በውጊያ ላይ ቆስለው ያገኘኋቸው ሁለት ሴት ወታደሮች ሄደው መታከም ሲገባቸው አንመለስም፤ አንደኛችንን ህጉን አስከብረን ስንጨረስ ነው የምንታከመው በሚል ትንሽ ብቻ እርዳታ ይደረግልን እንጂ ወደውጊያ እንመለሳለን ማለታቸው በጣሙኑ ካስገረሙኝ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው ።በዚህ ውስጥ ያስተዋልኩት ያላቸውን የአገር ፍቅርና ቁርጠኝታቸውን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– በቆይታህ የተከፋህበት አሊያም ደስ የተሰኘህበት ጉዳይ አጋጥሞህ ይሆን?
ጌትነት፡– አዎ አለ፤ በአንድ ነገር ተከፍቼ ነበር። ይኸውም እኛ ሽሬ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ወታደሮች አንዳንድ ነገሮችን ለመግዛት ሹፌሮች ወደገበያ ብቅ ብለው ሲመለሱ የነገሩኝ ነገር ነው ።ሹፌሮቹ ገበያ በሄዱበት ወቅት ያጋጠማቸው ነገር አንድ ህጻን ልጅ ሹፌሮቹ የለበሱትን የወታደር ልብስ ሲያይ ልክ አባቱን የሚያውቁት ስለመሰለው እያንዳንዳቸውን “አባቴን አይታችሁታል” እያለ ይጠይቅ ነበር ።አባቱ የጁንታው ቡድን ልዩ ኃይል አባል ነበር ።ህጻኑ ግን ያው የወታደር ልብስ የለበሰ ሁሉ አባቱን የሚያውቅና ለአንድ ዓላማ የተሰለፈም ስለመሰለው አባቴን አያችሁት እያለ ሲጠይቅ የነበረው የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ነው ።እዛ ውስጥ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር የጦርነትን አስከፊነት ነው ።እናም ሁኔታውን ሲነግሩኝ ስሜትን የረበሸውም ጉዳይ ነበር፡፡
የተደሰትኩበት ነገር ቢኖር በጁንታው ቡድን መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ተማርከው የተወሰዱ ከአንድ ሺህ በላይ የሆኑ የመከላከያ መኮንኖችና ከፍተኛ የመስመር ኃላፊዎች በአየር ኃይልና በመከላከያ ሰራዊቱ ጥንቃቄ በተሞላበት እርምጃ ተወስዶ መለቀቅ በመቻላቸው በእጅጉ የተደሰትኩበት ጊዜ ነበር ። ጥንቃቄ የተሞላበት ርምጃ ሲባል ለሰሚው አይመስል ይሆናል፤ ነገር ግን ጋቢና የተቀመጠን አካል ኋላ ካለው ለይቶ እስከመምታት ድረስ ሲደረግ የነበረውን ጥንቃቄ አልዘነጋውም ።ወደሞት እየተነዱ የነበሩትን ከጁንታው እጅ በጥንቃቄ አስለቅቆ ወደሽሬ ማምጣት መቻል ለእኔ እሱ ገድል ከጀግንነትም በላይ ስለሚሆንብኝ በመከላከያ ሰራዊታችንና በአየር ኃይላችን እንድኮራ ያደረገኝ ክስተት ነበር ።በህዝቡ ዘንድም የነበረው ደስታ ወደር አልነበረውም ።
አዲስ ዘመን፡– መንግስት የሕግ ማስከበሩን ሁኔታ ጀምሮ በድል ማጠናቀቁ ይታወቃልና በዚህ የተሰማህ ነገር ምንድን ነው?
ጌትነት፡– እኛ በወቅቱ እዛ አካባቢ ነበርንና የሰራነውን ዘገባ ለመላክ የተወሰንን ከየሚዲያ ተቋማት የተሰሩትን ዜናዎች በመያዝ አየር ኃይል ባዘጋጀው ሂሊኮፍተር ወደጎንደር አቀናን ።ለአንድ ሳምንት ያህል የሰራናቸውን ዘገባዎች በመላክ ላይ ሳለሁ ነው አመሻሽ ላይ መከላከያ ሰራዊቱ መቀሌ መግባቱን የሰማሁት ።በወቅቱ ዜናው ትልቅ ብስራት ነበርና በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
በዋናነት ደግሞ ህዝብ ሳይጎዳ እዛ መድረስ መቻል ትልቅ ድል ነው፤ ከተማ ውስጥ የሚደረግ ውጊያ በጣም ከባድ መሆኑን በጥቂቱም ቢሆን አስተውያለሁ ።እንዲያም ሆኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ኪሳራ ሳያጋጥም ያንን ድል ማጣጣም መቻል በእርግጥም መታደል እንጂ ምን ይሉታል ።እንደ አገር ትልቅ እፎይታ ነው፡፡
እንዳልኩሽ ኔትዎርክ ስላልነበር ለብዙ ቀናት ከቤተሰብ ጋር መገናኘት አልቻልንምና በተለይ እናቴ በጣም ስጋት ውስጥ ነበረች ።አንዴ በመሃል ጎንደር በመጣሁበት ጊዜ ደውዬ ስለነበር ነገ አሊያም ከነገ በስቲያ እመጣለሁ ነበር ያልኳት እንጂ እስከመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ የህግ ማስከበሩን ሂደት ልዘግብ ሽሬ ስለመሆኔ የምታውቀው አንዳች ነገር አልነበረም ።አንዴ ግን በሆነ አጋጣሚ ባገኘሁት ኔትዎርክ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ላገኘኋቸው ሶስት ጓደኞቼ ደህንነቴን ለቤተሰብ ደውለው እንዲነግሩ በማድረጌ እናቴ ዘንድ ደውለው “ልጅሽ ደህና ነው፤ ምንም አታስቢ” ስላሏት ለቤተሰቤ መረበሽ የበለጠ ምክንያት ሆኖ አረፈው ።ነገር ግን ጉዳዩ ተጠናቆ በመመለሳችን ትልቅ ደስታ ነበር የተፈጠረው ።እናቴም የት ሄጄ እንደመጣሁ በኋላ ላይ እውነቱን በነገርኳት ጊዜ በሰላም መመለሴ ላይ ነበር ትኩረት ያደረገችው፡፡
በቆይታችን ግን ያስተዋልኩት አንድ ነገር ቢኖር ከመከላከያ ሰራዊቱ የተማርነው በመካከላቸው ፍጹም የሆነ የቤተሰባዊነት ስሜት መኖሩን ነው፤ እኛ የሚዲያ አባላት ወደእነሱ መተሳሰብና መዋደድ ተስበን ነበር ። አንደኛው ጋዜጠኛ ከሌላው ተቋም ጋዜጠኛ ጋር ሲተባበር ነው ያስተዋልኩት ።ከዚህ በተጨማሪ እኔን ደግሞ በብዙ ነገር ሲመክረኝና ሌላው ቀርቶ የሰራኋቸውን ዘገባዎች የመጀመሪያው አርታዒ በመሆን ሲመለከትልኝ የነበረው ፎቶ ጋዜጠኛ ዳኜ አበራ ነበርና ላመሰግነው እሻለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጣም አመሰግናለሁ ።
ጌትነት፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ ።
አዲስ ዘመን ጥር 03/2013