አስናቀ ፀጋዬ
የልዩ ልዩ የተፈጥሮ ማዕድን ሃብቶች ባለፀጋ ከሆኑ የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ አንዱ የአማራ ክልል ነው። በክልሉ በርካታ የከበሩ፣ ለግንባታ፣ ኢንዱስትሪና ጌጣ ጌጥ ስራ ግብአት የሚውሉና የኢነርጂ ጥቅም የሚሰጡ ማዕድናት እንደሚገኙም በተለያዩ ጊዜያት በተሰሩ ጥናቶች ተረጋግጧል፡፡
በተለይ ደግሞ ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ የማዕድን ሃብቶች በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚገኝ ሲሆን ፍቃድ ወጥቶባቸው ከኢነርጂ ማዕድናት በተሻለ ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ።
ከነዚህ ውስጥም ለዘመናዊ ህንፃ ማስዋቢያ ተፈላጊ የሆነው ጥርብ ድንጋይ /የዳይሜንሽን ድንጋይ/ አንዱ ሲሆን በሰሜን ሸዋ፣ደቡብ ወሎ፣ ዋግኽምራ፣ አዊ፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ ዞኖች ባሉ አካባቢዎች ላይ በስፋት ይገኛል።
በዚሁ የጥርብ ድንጋይ ስር ከሚመደቡት የኮንስት ራክሽን ማዕድናት ውስጥም ዕምነበረድ፣ ላይምስቶን፣ ኢግኒምብራይት፣ ግራናይትና ሳንድስቶንም ይገ ኙበታል። የወንዝ አሸዋ፣ የአለት አሸዋ፣ ነጭና ጥቁር ድንጋይ፣ ስኮርያ፣ የሸክላ አፈር፣ ገረጋንቲና የመሳሰሉ ሌሎች የኮንስትራክሽን ማዕድናትም በክልሉ አብዛኛው አካባቢዎች ላይ በአስተማማኝ የክምችት መጠን ይገኛሉ።
እነዚሁ ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት በብዛት ከሚገኝባቸው የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ አንዱ የወልድያ ከተማ አስተዳደር ሲሆን በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተውና ፍቃድ አውጥተው በኮንስትራክሽን ማዕድናት ማምረት ስራ ላይ ተሰማ ርተው ይገኛሉ።
በከተማዋ በማህበር ተደራጅተውና ፍቃድ አውጥተው በኮንስትራክሽን ማዕድን ማምረት ስራ ከተሰማሩ ማህበራት ውስጥ አንዱ አሸናፊ ባዬና ጓደኞቹ የጠጠር አምራች ሽርክና ማህበር ነው ።አቶ ጌታቸው አበበ ደግሞ የማህበሩ ፀሐፊ ናቸው፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት ሽርክና ማህበሩ 23 አባላትን በማቀፍ ከከተማው የማዕድን ስራዎችና ፍቃድ አስተዳደር ቡድን ፍቃድ አውጥቶ በጠጠር ማምረት ስራ ለመሰማራት በጥር ወር 2008 ዓ.ም ተደራጀ። ማህበሩ ስራውን እንደጀመረ የመብራት ችግር አጋጥሞት የነበረ በመሆኑ አባላቱ ለትራንስፎርመር ግምት ማስገቢያ 72 ሺ 800 አዋጡ።
2 ሺ 520 ካሬ ሜትር የመስሪያ ቦታ በከተማው የኢንዱስትሪ መንደር ልዩ ቦታው ከወታደሮች ካምፕ ጀርባ ለማህበሩ ከተሰጠም በኋላ አባላቱ የቤተሰቦቻቸውን ቤት በዋስትና በማስያዝ ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም 500 ሺ ብር ብድር ወሰዱ ።
ማህበሩ ብድሩን እንዳገኘ በታህሳስ ወር 2009 ዓ.ም ወደ ጠጠር መፍጫ ማሽን ግዢ ገባ ።በ325 ሺ ብርም የጠጠር መፍጫ ማሽን ገዝቶ ቀሪውን ገንዘብ ለስራ ማስኬጂያ አደረገው ። ማሽኑ ተገዝቶ እንደመጣም በማምረቻ ቦታው ላይ ተተክሎ ጥር 5 ቀን 2009 ዓ.ም በአራት አይነት ደረጃ ጠጠር ማምረት ጀመረ።
ማህበሩ ጠጠር ማምረት እንደጀመረም በማምረቻ ቦታው ላይ ላስገባው ድንጋይ ክፍያ ፈፀመ። ከዚህ ግዜ ጀምሮም ማህበሩ ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም የወሰደውን የ500 ሺ ብድር በየወሩ 18 ሺ 900 ብር ገቢ በማድረግ በ2010 ዓ.ም ያለበትን ሙሉ በሙሉ ከፍሎ አጠናቋል ።
እንደ ፀሐፊው ገለፃ በአሁኑ ወቅት የማህበሩ አባላት በየወሩ ከሚያገኙት ገቢ በመጠኑ በመቆጠብ ከወንዝ ወደ ጠጠር ማምረቻ ቦታ ድንጋይ የምታመላልስ መኪና ገዝተዋል። በዚህ እንቅስቃሴ ሂደትም ማህበሩ በርካታ ውጣውረዶች ያጋጠሙት ሲሆን በተለይ የይሁንታ ፍቃድ በመከልከሉ ስራዎችን ለመስራት አልቻለም። ሆኖም ኋላ ላይ የይሁንታ ፍቃድ እንዲሰጠው በመደረጉ ከበፊቱ በተሻለ እየሰራ ቢሆንም አሁንም የይሁንታ ፍቃዱ በየዓመቱ የሚታደስ ከመሆኑ አኳያ የማህበሩ ፍቃድ አልታደሰም። ይህም በማህበሩ ስራ ላይ ተጨማሪ እክል ፈጥሯል ።
በተለያዩ ምክንያቶች ከማህበሩ የወጡ አባላትን ሳይጨምር በአሁኑ ግዜ የማህበሩ አባላት 21 ሲሆኑ ቦታ ተረክበው ጠጠር ማምረት ከጀመሩ አምስት አመት አስቆጥረዋል ።በዋናነትም ማህበሩ አራት አይነት ጠጠሮችን በማምረት ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።
መጀመሪያ አካባቢ ማህበሩ የሚያጋጥመው የኃይል መቆራረጥ ችግር እንዳለ ሆኖ በቀን 32 ሜትር ኪዩብ 02 እና 03 ጠጠር ዓይነት ሲያመርት ነበር ።ሆኖም በአሁኑ ወቅት የምርቱ መጠን በፊት ከነበረው በመጠኑ ተሻሽሏል።
ማህበሩ ጠጠር ወደማምረቻ ቦታው ድንጋይ ሲያስገባ የቀረጥ፣ የአሽከርካሪ፣ የነዳጅና የቀን ሰራተኛ ደሞዝ ወጪ አድርጎ አባላቱ ጥሩ ገበያ ካለ በወር እያንዳንዳቸው እስከ 2 ሺ 500፤ ገበያ ከሌለ ደግሞ በወር እስከ 1 ሺ 500 ብር ያገኛሉ ።የማህበሩ አባላት የሚያገኙት ገቢ ያን ያህል ከፍተኛ ባይሆንም ነገን ለማትረፍ ግን ሁሌም በጋራ ይተጋሉ ።በከተማው ካሉ ሌሎች የግንባታ ግብዓት አምራች ማህበራት ጋር ሲነፃፀርም ማህበሩ በመካከለኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።ማህበሩ ሲመሰረት የነበረው መነሻ ካፒታልም 108 ሺ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለአንዳንድ ለስራ ማስኬጃዎች የሚወጡ ወጪዎችን አካቶ 125 ሺ ብር ደርሷል ።
ፀሐፊው እንደሚገልፁት እስካሁን ድረስ ማህበሩ በቋሚነት የጠጠር ምርቶቹን የሚያቀርብባቸው ቦታዎች የሌሉ በመሆኑ በገጠመኝና በተባራሪ ገበያ ለፈላጊዎች ያቀርባል። እስካሁንም 32 ሜትር ኪዩብ 00 እና 01 ጠጠር ለወልዲያ ቴክኒክና ሞያ ተቋም አቅርቧል። ለግል ባለሃብቶችም በተለያየ የጠጠር አይነት ሽያጭ አካሂዷል ።
እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የማህበሩ አባላት ገና ብዙ ስላልሰሩ በዚሁ የጠጠር ማምረት ስራ በሚያገኙት ገቢ ህይወታቸው ብዙም እንዳልተለወጠ የሚናገሩት ፀሐፊው፤ የአሁኑ ትጋታቸው በቀጣይ ትርፍ ይዞ ብቅ እንደሚል ያላቸውን እምነት ይገልፃሉ ።ዛሬ ላይ ከአቧራ ጋር ተጋፍጠውና ጤናቸውን አደጋ ላይ ጥለው እያደረጉ ያሉት ጥረት በቀጣይ ተስፋ ሰጪ ውጤት እንደሚያመጣና አሁን ካሉበት በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱም ይጠቁማሉ ።
ሰዓታቸውን ሳይሸራርፉ ቀን ከሌሊት ደክመው መስራታቸው ከሌሎች ተመሳሳይ ማህበራት እንደሚ ለያቸውም ይጠቁማሉ ።በማህበሩ ውስጥ ያሉት ሁሉም አባላት በአራት ቡድን ተከፋፍለው የተለያዩ የስራ ዘርፎችን እንደሚሰሩም ፀሐፊው ተናግረው፤ ግማሹ ቡድን ማሽኑ ጋር ሲሰራ ከዋለ ቀሪው ቡድን ደግሞ ወንዝ ሄዶ ድንጋይ በመኪና ጭኖ እንዲያመጣ እንደሚደረግም ያስረዳሉ ።በሂሳብ አያያዝ ረገድም ማህበራቸው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ ።
ለማህበሩ ስራ መሳካት የይሁንታ ፍቃድ እድሳት ወሳኝ ከመሆኑ አኳያም የዞኑ ማዕድን ስራዎችና ፍቃድ አስተዳደር ቡድን ፍቃዳቸውን እንዲያድስ ፀሐፊው ማህበሩን ወክለው ጥያቄ ያቀርባሉ።
በእርግጥ ማህበሩ ጠጠር የሚያመርትበት ቦታ በአየር ብክለት ምክንያት ከአካባቢው ማህበረሰብ ቅሬታ የቀረበበት መሆኑን ተከትሎ የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ ሰነድን ያላሟላ ባለመሆኑ ከቦታው ላይ የመነሳት ስጋት እንዳለባቸውና እድሳቱ ባይደረግላቸው እንኳን ምትክ የማምረቻ ቦታ እንዲሰጣቸው ፀሐፊው ይጠይቃሉ ።እስካሁንም ጥያቄያቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረባቸውንም የሚገልፁት ፀሐፊው፤ እስካሁን ድረስ ግን አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኙም ይናገራሉ ።
በቀጣይም ማህበሩ በተለይ የመብ ራት ኃይል መቆራረጥ ችግር በስፋት የሚታይ መሆኑን ተከትሎ በአብዛኛው ጠጠር የማያመርትባቸው ጊዜያቶች በመኖራቸው ችግሩ በሚመለከተው አካል ምላሽ ማግኘት ከተቻለ አሁን ካለው የማምረት አቅም በላይ ጠጠር በማምረት ለፈላጊዎች የማቅረብ ፍላጎት እንዳለው ፀሐፊው ይገልፃሉ። በዚህም ገቢያቸውን በማሳደግ የማህበሩ አባላት ህይወታቸውን ማሻሻል እንደሚፈልጉም ይጠቅሳሉ ።
ከከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ ቦታ ማግኘት የሚችሉ ከሆነም ከጠጠር ማምረት ስራው ጎን ለጎን የተለያዩ ስራዎችን በተለይም ብሎኬት የማምረት ፍላጎት እንዳላቸውም ይገልፃሉ ። በቀጣይም ለዚሁ ስራ ማከናወኛ የሚሆን ቦታ ለማግኘት ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄያቸውን እንደሚያቀርቡም ያመለ ክታሉ። ይህም ከጠጠር ማምረት በተ ጨማሪ በብሎኬት ማምረት ዘርፍም በመሳተፍ ህይወታቸውን ለመለወጥ እንደሚያግዛቸውም ይጠቁማሉ ።
በማህበር በመደራጀትና በጠጠር ማምረት ዘርፍ ላይ ተሳትፈው ህይወታ ቸውን ለመለወጥ እየተጉ እንደሚገኙ የሚናገሩት ፀሐፊው፤ በተመሳሳይ ሌሎች ወጣቶችም በተለያዩ ዘርፎች ላይ በማህበር ተደራጅተው በመስራት ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ። ነገ ውጤታማ ለመሆንና ያሰቡት ደረጃ ላይ ለመድረስም ዛሬ ላይ ተግተውና ዝቅ ብሎ መስራት መለማመድ እንዳለባቸውም ይመክራሉ። በተናጠል ከመስራት ይልቅ በማህበርና በጋራ ተደራጅተው ቢሰሩ የበለጠ ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችሉም ይጠቁማሉ፡፡
ወጣቶች ያሰቡት የስኬት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ታዲያ ምክር፣ ማበረታቻና ድጋፍ ከቤተሰብ፣ ከአካባቢና ከፍ ሲልም ከመንግሥትና ከሌሎችም ከሚመለከታቸው አካላት ሊያገኙ እንደሚገባም ያመለክታሉ ።
በአማራ ክልል በተለያዩ ግዜያት በተደረጉ ጥናቶች በርካታ የከበሩ ማእድናት በተለያዩ አካባቢዎች ላይ እንደሚገኙ መረጋገጡንና በጥናት ከተረጋገጡ የከበሩ ማዕድናት ውስጥም ኦፓልና በተወሰኑ ደረጃዎች ደግሞ ወርቅ እንደሚገኙ ከክልሉ የማዕድን ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። የኮንስትራክሽን፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉና የኢነርጂ ማዕድናት እንዳሉም በጥናት መረጋገጡን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።
የወልዲያ ከተማ ወጣቶች ነገን በማለም ዛሬ ላይ ሆነው የቀጣይ ህይወታቸውን ለማሻሻል በማህበር ተደራጅተው እያደረጉ ያሉትን ጥረት እያደነቅን በተመሳሳይ ሌሎች ወጣቶችም የእነርሱን አርአያ በመከተል ስራን በህብረት ሰርተው እንዲለወጡ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 01/2013