ሙሉቀን ታደገ
በአሁኑ ዘመን በዓለማችን ጭንቅላታቸውን ተጠቅመው አዲስ ነገር ለሚፈጥሩ ሰዎች ከግል ባለሀብቶች ጀምሮ እስከ ትላልቅ የመንግስት ተቋማት ድረስ ያሉ አካላት አዲስ እውቀትን ማፍለቅ የሚችሉ ሰዎችን በነፃ ብዙ ሚሊዮኖችን አፍስሰው ይደግፋሉ፤ ያበረታታሉ። ምክንያቱም ፈጠራ ዓለምን የማራመጃ መንገድ ሲሆን፤ ዋጋውም ብዙ ነው።
የፈጠራ ባለቤትነት እንደ ቶማስ አልቫ ኤድሰን ለቤተሰብ፣ ለተወሰነ ማህበረሰብ፣ ለአገር ብቻ ሳይሆን የዓለም ብርሃን ምንጭ እስከመሆን ለመድረስ የሚያስችል፤ በመንግስትም ሆነ በባለሃብቶች ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። በተለይ ፍላጎት፣ እውቀት እና ሞያው እያላቸው በገንዘብ እጥረት በሥራቸው ውጤታማ ለመሆን ያልቻሉትን መደገፍ አሁን አሁን እየተለመደ መጥቷል።
ነገር ግን እንደዚህ ያሉ ባለ ብሩህ አዕምሮ ሰዎችን በግል ባለሃብቶችም ሆነ በመንግስት መደገፍ በሌላው ዓለም እጅግ የተስፋፋ እና ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ ግን እምብዛም የተለመደ አይደለም። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ትኩረት በመስጠት ባለብሩህ አዕምሮዎችን እና ስራ ፈጣሪዎችን በተለያየ መልኩ ማበረታታት እና መደገፍ ጀምሯል።
ይህ እንደ ኢትዮጵያ አይነት ታዳጊ ለሆኑ አገራት በእጅጉ ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም የፈጠራ ባለሙያዎችን ከማበረታታት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የሥራ ዕድል የሚናቅ አይደለም።
የሰው እጅ ጠብቀው የሚኖሩትን ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያግዝ መሆኑ ሲታወስ፤ እንኳንስ እነሱ ወደ አደባባይ መጥተው ተገኝተው ቀርቶ ለህዝብ ሳይታዩ እንዲሁ በየሰፈሩ ‹‹እንደው ይሄማ ድጋፍ ቢያገኝ የት ይደርስ ነበር›› እተባሉ ከንፈር የሚመጠጥላቸውን ባለተሰጥኦ አካላት በባትሪ ፈልጎ ማግኘት ግድ ይላል ።
ለዛሬ አንድ ባለ ብሩህ አዕምሮ ነገር ግን የአገሪቱን የእድገት መርህ በዘነጉ አካላት በመገፋቴ ፍትህን ፈልጌ በብርቱ ተጠምቻለሁ የሚሉ አንድ የፈጠራ ባለሞያ እናስተዋውቃችሁ። አቶ ሰሎሞን ሰብስቤ የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር የብድር ውል ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፤ ባንኩ በብድር ውሉ ስምምነት መሰረት የሚጠበቀውን ባለመፈፀሙ ለችግር ተጋልጫለሁ ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በደላቸውን በማቅረብ ሕዝብ ይፍረደኝ ሲሉ አቤት ብለዋል።
አቶ ሰለሞን ሰብስቤ ማንነት እና የቅሬታቸው መነሻ
አቶ ሰለሞን በህክምና ሳይንስ ተመርቀው በሙያቸው ለበርካታ አመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በሙያቸው አገራቸውን ሲያገለግሉ በተጨማሪነት ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ችሎታ በመጠቀም ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ለመስራት የቻሉ ሰው ናቸው። በዚህ የፈጠራ ስራቸው በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በአህጉር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የፈጠራ ባለቤትነት ሽልማቶችን አግኝተዋል ። ከእነዚህም መካከል የተወሰኑ ስራዎቻቸው በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለ አዕምሮ የፈጠራ ባለቤትነት ተመዝግበዋል።
ይህን ተሰጧቸውን በመጠቀም ለአገር ብሎም ለተለያዩ ወገኖች የስራ እድል ለመፍጠር በማሰብ፤ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ለማግኘት በ2008 ዓ.ም ፕሮፖዛል ለባንኩ ያስገባሉ ። የስራ እቅዱ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል። አቶ ሰለሞን ብድር ሲጠይቁ ያስገቡት ፕሮፖዛል ለአጠቃላይ ስራ ማስኬጃ 15 ሚሊዮን 571ሺህ 680 እንደሚያስፈልግ እና ከዚህም መካከል 12 ሚሊዮን 551ሺህ 400 (80 ነጥብ 6በመቶ) ብር ለfixed investment ፣ 550,000 (3 ነጥብ 5 በመቶ ) ብር ደግሞ ደግሞ ለpre-production expense ቀሪው 2 ሚሊዮን 470 ሺህ 280 (15 ነጥብ 9 በመቶ) ብር ደግሞ working capital ነው ።
አጠቃላይ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 6 ነጥብ 78 ሚሊዮን የሚሆነው ብር በስራ ፈጣሪው የሚሸፈን ሲሆን፤ 12 ነጥብ 55 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደሚሸፈን ፕሮፖዛሉ ያመላክታል።
ከዚህ በተጨማሪ ምን ምን ማሽን እንደሚያስፈልግ በግልፅ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ ይህን ማሽን ምን ምን እንደሚያመርት እና ምርት ለማምረት የሚያስችለው በ194ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ እንደሚያስፈልግ በፕሮፖዛሉ ተመላክቷል። ይህም ቦታ በአዲስ አበባ በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ 02 እንደሚገኝ ፕሮፖዛሉ ግልጽ በሆነ መልኩ ያመላክታል ።
ከዚህ ባሻገር በፕሮፖዛሉ ላይ የተቀመጠው ድርጅቱ የሚያመርተው ምርት የሚኖረውን ሃገራዊ ፋይዳ ይጠቁማል። በዚህ መሰረት ፋብሪካው ያለቀላቸውን እና በጥሬ እቃነት የተለያዩ መለዋወጫዎች ለተለያዩ አምራቾች ድርጅቶች ማቅረብ ያስችለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከእንጨት እና ከብረት የሚሰሩ የሜዲካል ፈርኒቸሮችን እና ቁሳቁሶችን በዋናነት ስለሚያመርት (Important medical furniture and equipment manufacturing) የሚባሉትን ( forging, stamping, bending, forming, and machining, used to shape individual pieces; and other processes, such as welding and assembling, used to join separate parts together) በዚህም ድርጅቱ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ችግር በመቀነስ ሚናውን በአቅሙ ይጫወታል ይላል ።
በዚህም መሰረት ጥራት ያላቸውን በቴክኖሎጂ ያደጉ ዘመናዊ ህክምና ፈርኒቸሮችን እና ቁሳቁሶች በማምረት የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት፣ የማኑፋክቸሩን ዘርፍ ማዘመንና ለተለያዩ አካላት የስራ እድል መፍጠር እና መንግስት ከድርጅቱ ከሚያገኘው ግብር በተጨማሪ በድርጅቱ ተቀጣሪዎች ከሚያገኙት ገቢ ለመንግሥት የሥራ ግብር እንዲያስገኝ ማስቻል እና ሌሎችም የድርጅቱ መነሻ ዋና ዓላማ ወይም ግቦች መሆናቸውም በፕሮፖዛሉ ተብራርቷል።
በዚህም መሰረት ከላይ ያሉትን የተቋሙን አላማ፣ የመሥሪያ ቦታ እና ስፋት ፣ የሚያመርተውን የምርት አይነት እና ድርጅቱ የጠቀሳቸውን ምርቶች ለማምረት የሚያስፈልግ ማሽኖች በመመልከት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሶለሰብ የቤት እና የእቃዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ብርድ ይፈቅድላቸዋል ። በዚህም መሰረት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር አፅዳቂ ቡድን አጠቃላይ ዋጋ ውስጥ ብር 12,586 231/ አስራ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰማኒያ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ አንድ ብር በፀደቀው የብድር ስምምነት መሰረት የካፒታል እቃው Ethio-Arab International General trading L.L.C ከተባለ የተባበሩት አረብ ኤምሬት (UAE)አቅራቢ ድርጅት እንዲገዛ በተወሰነው መሰረት ግዥ ተፈፅሟል ።
እነዚህ ማሽኖች በሊዝ ብድር ወይም በኪራይ የሚተላለፉ ናቸው። ማለትም ባንኩ አበዳሪ ወይም አከራይ ሶለሰብ የቤት እና የእቃዎች ማማረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ደግሞ ተበዳሪ ወይም ተከራይ ናቸው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአከራይ እና በተከራይ መካከል ህዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም የተፈፀመውን የካፒታል እቃ ዱቤ ግዢ እና ኪራይ ውል መነሻ በማድረግ ከዚህ ሰነድ ጋር በተያያዘው ዝርዝር መግለጫ ( specification or packing list ) መሰረት Ethio-Arab International General trading L.L.C ከተባለ የተባበሩት UAE አቅራቢ ድርጅት የተፈቀዱ የማሽን ግዥ ተፈፅሞ የፕሮጀክቱ ሳይት የደረሱ ሰማኒያ ዘጠኝ ማሽኖች መጋቢት 4 ቀን 2010 ዓ.ም ንብረቱ በሚገኝበት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፤ የካ ክፍለ ከተማ ፣ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር Shee/ 19 በሆነው ቦታ ላይ ጊዜያዊ ርክክብ ተፈፅሟል።
እንግዲህ ከዚህ በኋላ በባንኩ እና ሶለሰብ የቤት እና የእቃዎች ማማረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መካከል ስምምነት ላይ መደረስ አለመቻሉን የሚናገሩት የሶለሰብ የቤት እና የእቃዎች ማማረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማናጀር አቶ ሰለሞን ሰብስቤ ናቸው። ለዚህም ዋናው ምክንያት በብድር/ በሊዝ ኪራይ ውሉ ላይ ባንኩ የተስማማነውን ስምምነት ስላልፈፀመ ነው ይላሉ።
አቶ ሰለሞን ያቀረቡትን አቤቱታ ለመፍረድ ይመች ዘንድ የውል ስምምነቱ ምን ይላል? የሚለውን በወፍ በረር መመልከት ያስፈልጋል። የውል ስምነቱ ከአንቀጽ አንድ በፊት እንዲህ ይላል ። ተከራይ በዚህ ውል መሰረት “ፕሮዤው “ ተብሎ የሚጠራውን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ክልል ውስጥ የቤት እና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅት ለማቋቋም አጠቃላይ ዋጋው ብር 12 ሚሊዮን 586 ሺህ 2መቶ 31 የሚያወጣ በዚህ ውል የተጠቀሰውን፡- medical manufacturing ማሽነሪ/ የካፒታል ዕቃ ከ Ethio-Arab International General trading L.L.C ከተባለ የተባበሩት UAE አቅራቢ ድርጅት እና ቶዮታ ፒካአፕ Ethio-Arab International General trading L.L.C ከተባለ የተባበሩት UAE አቅራቢ ድርጅት ለማቅረብ ባንኩ መስማማቱን ይገልፃል። ይህ የሚሆነው በአንቀፅ ሶስት ላይ ተከራዩ ወይም ተበዳሪው የሚጠበቅበትን ካከናወነ ነው ይላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የብድር ውሉ አንቀፅ ሶስት ምን ይላል የሚለውን ማየት ተገቢ ነው ።
በውሉ 3 ነጥብ 1 ላይ ተከራይ በዚህ ውል አንቀፅ አንድ ስር የተጠቀሰው እቃ ከመገዛቱ በፊት እና ይህን ውል በሚመለከት አስፈላጊ ፎርማሊቲዎች ሁሉ ከተጠናቀቁ በኋላ ለፕሮዤው ስራ ማስኬጃ የሚውል የራሱን መዋጮ ብር 3 ሚሊዮን 146 ሺህ 588 / ሶስት ሚሊዮን አንድ መቶ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ሰማኒያ ስምንት ብር / በጥሬ ገንዘቡ በባንኩ የማይንቀሳቀስ ሂሳብ / Blocked Account/ ውስጥ ማስቀመጡ ሲረጋገጥ፤ በዚህ ውል አንቀፅ አንድ መሰረት የእቃው መግዣ ገንዘብ ለአምራቹ ወይም ለአቅራቢው ይከፈላል ይላል።
በ3 ነጥብ 2 ተከራይ በዚህ በላይ በተጠቀሰው አንቀፅ መሰረት ከራሱ መዋጮ ለባንኩ ገቢ ያደረገው ገንዘብ፤ የኪራይ እቃውን የማምረቻ መሳሪያውን መረከቡን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ለባንኩ ማቅረቡ ሲረጋገጥ ለስራ ማስኬጃ እንዲውል ከዚህ ቀጥሎ በተመለከተው አኳኋን ከተከራይ ሂሳብ ላይ ወጪ ይደረጋል ።
አንደኛ፡- ብር 2 ሚሊዮን 667 ሺህ 112 / ሁለት ሚሊዮን አንድ መቶ አስራ ሁለት ብር / ለስራ ማስኬጃ ለተከራይ ይለቀቃል ይላል።
ነገር ግን አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፤ ከተከራዩ የሚጠበቀውን ነገር ቢያሟላም ቅሉ በካፒታል ዕቃ ዱቤ እና ኪራይ ውል መሰረት ባንኩ ከማሽኖች በተጨማሪ ቶዮታ ፒካአፕ Ethio-Arab International General trading L.L.C እንደሚገዛ ተስማምቶ የነበር ቢሆንም የስራ መኪናው ባልተገዛበት ሁኔታ እና ከዚህ በተጨማሪ በካፒታል ዕቃ ዱቤ እና ኪራይ ውል አንቀፅ 3 የተከራይ መዋጮ የሚል በተጠቀሰው አንቀፅ ያሉትን ስምምነቶች ባለማክበር ማለትም የኪራይ እቃውን የማምረቻ መሳሪያውን መረከቡን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ሳይሰጣቸው እና ከእርሳቸው የሚጠበቅባቸውን መዋጮ ካወጡ በኋላ እና የማሽኖቹ ግዢ ከተፈፀመ በኋላ በአንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ የተጠቀሰውን ለስራ ማስኬጃ ይለቀቅልሃል የተባለውን ገንዘብ ሳይለቁልኝ ወደ ስራ እንድገባ የሚጠይቅ በቀን 05/8/2010 ዓ.ም ከምስራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የተፃፈ ደብዳቤ ወደ ስራ እንዲገቡ የሚል መልዕክት የደረሳቸው መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹በዚህም ጊዜ ለስራ ማስኬጃ የተቀመጠውን እና በአንቀፅ 3 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የመስሪያ ካፒታል እንዲለቀቅልኝ ብጠይቅም የጠየኩትን ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ለሁለተኛ ጊዜ ከባንኩ የዲስትሪክት ኃላፊ በቀን 26/08/2010 ዓ.ም የማሽነሪ ተከላ ስራ አጠናቀው ማምረት እንዲጀምሩ በድጋሚ ስለማሳሰብ የሚል ደብዳቤ ተፃፈልኝ›› ይላሉ።
ኖቬምበር 16 ቀን 2018 በእንግሊዘኛ በተፃፈ ደብዳቤ ሌላ አዲስ ነገር በመጨመር ስራ እንዳትጀምር የሚል ከምስራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ደብዳቤ የተፃፈላቸው መሆኑን በመጠቆም፤ በዚህ ሳቢያ ከአንደኛው ችግር ሳይወጡ ሌላኛው የተደረበባቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
አዲሱ ደብዳቤ የሚለው ‹‹አሁን ያለህበት ቦታ ምርት ለማምረት ጠባብ ስለሆነ በዚህ ምርት ማምረት ስለማትችል ሰፊ ቦታ ያስፈልግሃል›› የሚል መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፤ በመጀመሪያ በቀረበው ፕሮፖዛል ማሽኖቹ ታውቀው ብድር ከተፈቀደ በኋላ ቀድሞ ብድር ሲጠየቅ በፕሮፖዛሉ ላይ ያለው የቦታ ስፋት አይበቃህም ማለት ሲገባቸው ማሽኑ ከተተከለ በኋላ ያለህ ሼድ ጠባብ ነው ብሎ ምርት እንዳያመርቱ መከልከል ግራ የሚያጋባ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ይህ ሁሉ አልፎ ከባንኩ ጋር በመስማማት በለገጣፎ አንድ ሼድ እንድከራይ ሆነ፡። ለዚህ ሼድ ለሁለት አመት 500 ሺህ ብር ከከፈልኩ በኋላ የተከራየኸውን ቤት ካርታ ማምጣት አለብህ የሚሉ እና ሌሎች ሰንካላ ምክንያቶች እየፈጠሩ ሲያጉላሉኝ ከቆዩ በኋላ፤ ቤት አከራይ ካርታ ለቤት ተከራይ አይሰጥም›› የሚል ምላሽ መስጠታቸውን እና ‹‹እንደውም አይሆንም ከአሁን በኋላ ስራህን በአስቸኳይ የማትጀምር ከሆነ ማሽኖችን ከአንተ ነጥቅን ለሌላ አምራች ይሰጣል›› መባላቸውን አቶ ሰለሞን ይናገራሉ።
‹‹ጊዜዬን እና ሀብቴን ከማባከን አልፎ አሁን ላይ ለከፍተኛ የጤና እክል ተጋልጫለሁ፤ የሞራል ውድቀት ደርሶብኛል›› የሚሉት፤ አቶ ሰለሞን የህክምና ውጤታቸውን ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በማቅረብ አሳይተዋል።
አቶ ሰለሞን ፤ ካቀረቡት ሰነድ መካከል ከአሁን በፊት በቅርንጫፍ ባንኩ በ05/8/2010 ዓ.ም እና በድጋሚ በ26/8/2010 ዓ.ም በተፃፉ ደብዳቤዎች ድርጅቱ የማሽነሪ ተከላ /Instalation/ ስራ ተጠናቆ በአስቸኳይ ወደ ስራ እንዲገባ ማሳሰባችን ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪ ከካፒታል እቃዎች ግዥ እና አቅርቦት ዳይሬክተር በ19/08/2010 ዓ.ም እና በድጋሚ በ4/10/2010 ዓ.ም በተላከ የውስጥ ማስታወሻ ፕሮጀክቱ የማሽን ተከላ እና ተያያዥ ስራዎችን አጠናቆ ባስቸኳይ ወደ ምርት እንዲገባ እንዲሁም የገጠመውን የመስሪያ ቦታ እጥረት በቂ የሆነ መጋዘን በመከራየት ስራ እንዲጀምር ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማይፈፀም ከሆነ ማሽኖቹን ለሌሎች ደንበኞች የሚያስተላልፍ መሆኑን ይገልፃል።
በመሆኑም የተባሉትን ተግባራት አጠናቀው በአስቸኳይ ወደ ስራ እንዲገቡ በድጋሚ እያሳሰብን ይህ ሳይሆን ቢቀር ባንኩ ማሽኖችን ለሌሎች ደንበኞች ለማስተላለፍ የምንገደድ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን የሚል ደብዳቤ በድጋሚ ለአቶ ሰለሞን ደርሷቸዋል ።
በ12/12/2010 ዓ.ም የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደረሰኝ የሚሉት የሶለሰብ የቤት እና ቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማናጀር አቶ ሰሎሞን፤ በቀን 10/4/2011 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የማሽነሪ ስራ ተጠናቆ ስራ እንዲጀመር የሚል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ
የተፃፈላቸው መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ ደብዳቤም ከተሰጠው ማስጠንቀቂያ ቀን ጀምሮ ባሉት 30 /ሰላሳ/ ተከታታይ ቀናት ውስጥ ድርጅቱ የማሽነሪ ተከላ / Instalation/ ስራውን አጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ ለመጨረሻ ጊዜ እያሳሰብን ይህ ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆኑ ባንኩ ማሽነሪዎችን መልሶ ለመረከብ የሚገደድ መሆኑ እና በውሉ መሰረት በአጠቃላይ ይህንን ማሽነሪ በድርጅቱ ምርጫ ለመግዛት የደረሰበትን አጠቃላይ ኪሳራ እና በውሎ አበል መቆረጥ ምክንያት በባንኩ የሚደርሰውን ጉዳት እንዲሁም የካፒታል ዕቃውን መልሶ በመረከብ ሂደት ለሚያወጣቸው ወጭዎች በህግ አስገዳጅነት የሚጠይቅ መሆኑን እናሳስባለን የሚል ነው ።
በዚህ መሰረት የሶለሰብ የቤት እና ቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማናጀር አቶ ሰሎሞን በቀን 27/12/2011 ዓ.ም ለባንኩ በፃፉት ደብዳቤ ድርጅታቸው ባንኩ ባደረገላቸው ድጋፍ የህክምና መሳሪያዎችን ለማምረት የሚያስችሉ ማሽነሪ የገዛላቸው በመሆኑ የማምረት ስራቸውን ለመጀመር ዝግጅታችን ማጠናቀቃቸውን፤ ነገር ግን የተጠቀሱትን የማምረቻ መሳሪያዎች ማስፈሪያ ቦታ አዘጋጅተው ወደ ማምረት ለመግባት ከባንኩ ጋር በተፈራረሙት ውል መሰረት የማሽነሪዎች ርክክብ እስካሁን ድረስ በባንኩ እና በድርጅታቸው መካከል አለመፈፀሙ እና ርክክብ ተካሂዶ የምስክር ወረቀት ባለማግኘታቸው በእርሳቸው በኩል ያስያዙት የስራ ማስፈፀሚያ ገንዘብ እንደማይለቀቅላቸው እና ይህ ለጥሬ እቃ አቅርቦት እና ለስራ ማስኬጃ የሚውለው ገንዘብ ካልተለቀቀ ወደ ምርት መግባት እንደማይችሉ አሳውቀዋል።
ማህበራቸው የማምረት ስራውን በቶሎ ለመጀመር እንዲችል ለስራው የሚያስፈልገውን commissioning , Tasting machine , tasting machine with programmer , adjusting machine parameter, adjusting machine limit as desired, loading programmer file to machine , transferring programmer to machine እና የሰው ኃይል መልምሎ በማሰልጠን ተገቢውን ዝግጅት ያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። የማሽኖቹ ርክክብ ተፈፅሞ የምስክር ወረቀት ቀርቦ የስራ ማስሄጃ እና የጥሬ እቃ ገንዘቡ ወዲያውኑ ሲለቀቅ ወደ ምርት መግባት እንደሚችሉም ጠቁመዋል ።
ስለዚህ ቅርንጫፉ ይህን አስተዳደራዊ መፍትሄ የሚያስፈልገውን ምክንያት ተመልክቶ የማሽኖችን ርክክብ በባንኩ እና በማህበሩ መካከል በአፋጣኝ እንዲፈፀም፣በውል ስምምነቱ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ርክክቡን የሚያረጋግጠው የምስክር ወረቀት ለባንኩ ቀርቦ ለስራ ማስኬጃ እና ለጥሬ እቃ የሚውለውን ገንዘብ ከማህበራችን ሂሳብ ላይ ወጭ ተደርጎ እንዲሰጣቸው እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለስራቸው ክንዋኔ የሚጠቀሙበት ተሽከርካሪ ግዥም በባንኩ በኩል እንዲፈፀም ማመልከታቸውንም በሰነድ አስደግፈው ለዝግጅት ክፍሉ አቅርበዋል።
በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ11/12/2012 ዓ.ም ደብዳቤ ፅፏል። በባንኩ በተቋቋመ የአጥኝ ቡድን በቀረበ ሪፖርት ላይ በተደረገ ውይይት በተደረሰው ውሳኔ መሰረት ማህበሩ ማሽኖችን በራሱ ተክሎ ለስራ ፍጥነት መንቀሳቀሱን አድንቀው ማህበሩ ስራዎችን በተፈለገው አኳኋን ያከናውን ዘንድ ባንኩ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል ። በዚህም የውሳኔ ሃሳብ መሰረት የመስሪያ ሼዱን ለማስፋት አንደኛ ማሽኖች በተተከሉበት ቦታ አካባቢ ሌላ መጋዘን ይከራይ፤ አለበለዚያም የሼድ ማስፋፊያ ያድርግ የሚሉ ናቸው ። ከእነኝህ ሁለት ሃሳቦች አንደኛውን መርጠው በአንድ ሳምንት ውስጥ ለባንኩ እንዲያሳውቁ የሚል ነው ።
ከእነኝህ ሁለት አማራጮች የመጀመሪያውን ባንኩ በፕሮፖዛሉ ከተቀመጠው ውጭ እና በብድር ስምምነት ውሉ ከተስማማበት ውጭ ሌላ አላስፈላጊ የጉልበት እና የገንዘብ ወጭ የሚጠይቅ እና የስራ አዋጭነቱንም በዚያው ልክ የሚጎዳ እንደሚሆን የሶለሰብ የቤት እና ቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማናጀር አቶ ሰለሞን ሰብስቤ ይናገራሉ።
ምንም እንኳን ከስምምነቱ ውጭ ቢሆንም የሚሉት አቶ ሰለሞን ፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 11/12/2012 ዓ.ም በፃፋው ደብዳቤ ባንኩ በጠየቀው መሰረት የሶለሰብ የቤት እና ቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራውን ቶሎ ለመጀመር ፍላጎት ስላለው የማህበሩ ማናጀር አቶ ሰለሞን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ማስፋፊያ እንዲሰጣቸው ያመለክታሉ። ይህንን ማመልከቻ የተመለከተው የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ4/13/2012 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ መሰረት ለአቶ ሰለሞን 177 ካሬ ሜትር ማስፋፊያ የሰጣቸው መሆኑን ይናገራሉ ።
ይሁን እንጂ ባንኩ አሁን ላይም 177 ካሬ ሜትር ማስፋፊያ ሲያደርግ የሶለሰብ የቤት እና ቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማናጀር ለሼድ ማስፋፊያው ባንክ ካለኝ የመስሪያ ገንዘብ ይለቀቅልኝ ብለው ቢያመለክቱም ምንም ምላሽ ስላላገኙ ሼዱን ለማሰራት ባላቸው አቅም የተፈቀደውን መሬት ከ70 በመቶ በላይ ሰርተው ለባንኩ አሳይተዋል ። ይሁን እንጂ አሁንም ባንኩ ምክንያቱን በውል ሳያሳውቅ ለስራ ማስኬጃ የተቀመጠውን ብር አልለቅቅላችሁም ማለቱን ይናገራሉ ።
በዚህም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተንዛዛ እና ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ የስራ ማስኬጃ ገንዘባቸውን ስለያዘባቸው የተገዛው ማሽን ከስራ ውጭ በመሆኑ አቧራ ውጦት ለብልሽት ሊዳረግ መሆኑን ያመለክታሉ።
ድርጅቱ እስከ አሁን ያስያዘው ገንዘብ በውሉ መሰረት ተለቆለት ማምረት ቢጀምር ኖሮ አንደኛ አገሪቱ ለህክምና ቁሳቁስ መግዣ ከውጭ በአንድ አመት ብቻ እስከ 30 ሚሊዮን ብር የምታወጣ መሆኑን እና በዚህ ድርጅት ይህንን ወጪ መቀነስ ይቻል እንደነበር አስታውሰው፤ ያለፈው ቢያልፍም አሁን ላይ ደግሞ ማሽኑ ያለምንም ስራ በመቀመጡ ለብልሽት ይጋለጣል የሚል ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ያመለክታሉ።
በተጨማሪ የስራ እድል ከመፈጠሩም ባሻገር መንግስት የስራ ገቢ ግብር እስከ 5 ሚሊዮን ብር ማግኘት ይችል እንደነበር ጠቁመው፤ የድርጅቱንም የብድሩን 60 በመቶ መክፈል ይቻል እንደነበር ያስረዳሉ። ይህን መክፈል ቢቻል ደግሞ ባንኩ ለሌላ አካል ብድር የሚያበደርበት አግባብ ይፈጠር እንደነበር እና የሶለሰብ የቤት እና ቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርም የተጣራ 15 ሚሊዮን ብር ማግኘት ይችል ነበር ይላሉ። ነገር ግን ባንኩ በውላቸው መሰረት የተያዘባቸውን መስሪያ ገንዘብ ያለቀቀላቸው በመሆኑ እና ቤተሰባቸው ላይ በተፈጠው ጫና እርሳቸው ለከፍተኛ የጤና እክል መጋለጣቸውን የህክምና ሰነድ ማረጋገጫ አቅርበዋል።
በጉዳዩ ላይ የፌደራል አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አስፋው አበበ እንደሚናገሩት፤ አቶ ሰለሞን የፈጠራ ስራዎችን በመስራት የሚታወቁ ሲሆን፤ ከባንኩ ጋር ያለባቸውን ችግር ለማጣራት ሞክረዋል። የልማት ባንክ ማድረግ ያለበትን ድጋፍ ለማድረግ አቶ ሰለሞን ያሉበት ቦታ በስማቸው ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሚፈልግ መሆኑን አረጋግጠዋል። ወረዳ ላይ ያሉ ሰዎች ይሄ ቦታ ለስራ መስሪያ ለአቶ ሰለሞን ተሰጥቷል የሚል ውል ማቅረብ እና ውሉን መስጠት አለባቸው ። የአቶ ሰለሞን ጉዳይ በዚህ መካከል ያለ ችግር እንደሆነ በቅርቡ ከባንኩ ጋር ባደረጉት ውይይት ተረድተዋል።
አቶ ሰለሞን ከባንኩ የሚፈልጉትን ድጋፍ ለማግኘት ከወረዳው የሚጠበቀውን የስራ ማስኬጃ ቦታ ፍቃድ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። የልማት ባንክ ደግሞ ያንን መረጃ ይዞ ማድረግ ያለበትን ድጋፍ ማድረግ አለበት ። ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ ለማምረቻ በሚል ያዘጋጀው ያለው ሁለት ቦታ ነው ። ባንኩ ደግሞ ለቁጥጥር ስለማይመቸው ይህ እንዲሆን እንዳልፈለገ መረዳታቸውን ያመለክታሉ።
መጀመሪያ 194 ካሬ ሜትር ይበቃኛል ብለው በፕሮፖዛላቸው አስገብተው በዛ መሬት ማምረት እንደሚቻል ባንኩ ፈቅዶ ፤ በኋላም ቦታው በቂ አይደለም ሲባል፤ ተጨማሪ 177 ካሬ ሜትር ማስፋፊያ ከወረዳ 02 ማግኘታቸውን ለዝግጅት ማሳወቃቸውን በመጥቀስ ስለማስፋፊያው ወረዳው ለልማት ባንክ ማሳወቁን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አስፋው ወረዳው 02 ማረጋገጫ ለአቶ ሰለሞን ከፃፈላቸው ማረጋገጫውን ሰነድ ይዘው መቅረብ እንደሚችሉ እና እነርሱ እንደገና ነገሩን በማጤን ችግራቸው እንዲፈታ ለማድረግ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርጉ መልስ ሰጥተዋል። ጨምረውም የራሳቸውን ባለሙያዎች ልከው እንደሚያጣሩ በመጠቆም፤ አቶ ሰለሞን ለሚፈልጉት ነገር አብረው መፍትሄ ለማምጣት የሚሰሩ መሆኑን ገልፀዋል። ውድ አንባቢያን የልማት ባንክ ሌሎች የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላትን ምላሻቸውን እንዳገኘን አስተያየቶቻቸውን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2013