ራስወርቅ ሙሉጌታ
ስራ አጦችንና የምርጫ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ስራ ፈት የሆኑትን መለየት ቢያስቸግርም በኢትዮጵያ በከተማም ሆነ በገጠር በርካታ ስራ አልባ ወጣቶች መኖራቸው ያደባባይ ሚስጥር ነው። ስራ ፈትነት ደግሞ ከሚፈጥረው የኢኮኖሚ ችግር ባለፈ የሚያሳድረው የስነ ልቦና ተጽእኖም በርካቶችን ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጣቸው ይገኛል።
እኛም በዛሬው እትማችን ስራ አለመኖር የሚያሳድራቸውን ስነ ልቦናዊ ተጽእኖዎችና እነሱን ተከትለው የሚመጡትን ተዛማጅ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውን እንዲያብራሩልን በኢምፓክት ኢትዮጵያ የሳይኮሎጂካል አገልግሎቶችና የማኅበረሰብ ጤና ማማከር ማኅበር፤ የሥነልቦና አማካሪና የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑትን አቶ አለማየሁ ጥበበን አናግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ስራ አለመኖር ከሚያስከትላቸው መሰረታዊ ተጽእኖዎች አንዱ የስነልቦናዊ ጫና መፍጠር ነው። ሰዎች ስራ ጀምረው ወደ ስራ ባለመሄዳቸውና ከስራ ሊያገኟቸው የሚችሉ ጥቅሞችን ማግኘት አለመቻላቸው የአእምሮ ጭንቀትና ውጥረት መፍጠር ምክንያት ይሆናል።
በተጨማሪም ስራ አጥነት የዝቅተኝነትና የማፈር ስሜቶች እንዲፈጠሩ ብሎም በራስ መተማመንን የሚያሳጣ ይሆናል። ሁሉም ማህበረሰብ የሚያስቀምጠው የራሱ የአኗኗር ደረጃዎችና የሚጠበቁ ግምቶች አሉ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሁኔታ መማር፤ ተምሮ መመረቅ፤ ከዛ ስራ መስራትና የራስን ህይወት መጀመር የተለመዱት ሲሆኑ ማህበረሰቡም እነዚህን ላሟሉ የሚሰጠው የራሱ የሆነ ክብርና ተቀባይነት ያለው ሲሆን በአንጻሩ ሳይሳካላቸው የቀሩትን የሚያየው በተለየ መንገድ ነው።
ይህንን ማህበረሰቡ ያስቀመጠውን ደረጃ ማሟላት ያልቻለ ግለሰብም ከማህበረሰቡ መገለል እንደሚደርስበት አድርጎ ሲሰማው፤ በማህበረሰቡ ወስጥ ዋጋ የለኝም ብሎ እንዲያስብና ስለራሱ ጠቃሚነት እንዳይገነዘብ ብሎም በራስ የመተማመን መንፈሱ ደካማ እንዲሆን ያደርገዋል።
ይህ ጭንቀት በማንኛውም ሰው ላይ ሊፈጠር የሚችል ሲሆን እየቆየ ሲመጣ ግን ድባቴ ለሚባለው የአእምሮ ችግር እያጋለጠ ይመጣል። የሚፈጠረውም ድባቴ በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ሲሆን በስፋት የሚስተዋሉት ምልክቶች ግን ራስን ማግለል፤ ደስተኛ አለመሆን (ከዚህ በፊት ያስደስቱ ለነበሩ ነገሮች አሁን ስሜት ማጣት) አንዳንድ ግዜም ችግሩ እየበረታ ሲመጣ እራስን ለማጥፋት ማሰብ ቀዳሚዎቹ ናቸው።
እነዚህ ስሜቶች የሚፈጠሩባቸው ሰዎች በተለይ ወጣቶች ደግሞ ራሳቸውን ለመደበቅና ግዜ ለማሳለፍ በሚል አብዝቶ አልኮልና ሌሎች ሱስ አምጪ ነገሮችን ወደ መጠቀምና እነዚህ ነገሮች ሲደጋገሙም ለደባል ሱሶች ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ከዚህ በኋላ እነዚህ ሱሶች በራሳቸው የሚያመጧቸው ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ፤ ስነልቦናዊና የጤና መጓደሎች በግለሰቡ ላይ ተደራቢ ችግር ሆነው ይመጣሉ ማለት ነው።
ከላይ የተዘረዘሩት ስራ አለመኖር የሚያስከትላቸው ችግሮችና የሚፈጥረው የተጽእኖ ደረጃ የሚወሰነው ግን ስራ በሌለው ሰው አቀባበልና በአካባቢው ባሉ የቅርብ ሰዎች ምላሽ ይሆናል።
በመሆኑም በመጀመሪያ ደረጃ ስራ አጥነት በየትኛውም ሀገር ያለ ማንኛውም ሰው ለአጭር ግዜም ሆነ ለረጅም ግዜ ሊያጋጥመው የሚችል የግለሰብ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ችግር መሆኑን በመረዳትና በመቀበል ለመፍትሄው መንቀሳቀስ ከሁሉም ሰው ይጠበቃል። እንደ አንድ ሥራ አልባ ሰው በቅድሚያ ችግሩ በእሱ ጥረት በግዜ ሂደት እንደሚፈታ በማመን ዛሬ ባይሆን ነገ ስራ ሊያገኝ እንደሚችል ለራሱ በመንገር ሙከራዎችን ያለመታከት መደጋገም።
በዚህ ሂደትም ስራ ላያገኝ የቻለው በእሱ አለመጣር አልያም ከእሱ አቅም በላይ በሆነ ሊቆጣጠረው ባልቻለ ምክንያት መሆኑን በመለየትና ያለውን እውነታ በመቀበል ስራ ለማግኘት በራሱ ሊያደርግ የሚችለውን ነገር በየቀኑ መከወን።
ምን አልባት በተሳሳተ አቅጣጫ እየተጓዘ ሊሆን ስለሚችልም ስራ እየፈለገበት ያለውን መንገድ መረጃ አሰባሰብ ስራ አጠያየቅና የሚፈልግበትን ቦታ መቀያየር መልመድ። ያለውን ፍላጎትና ምልከታ መለዋወጥ መቻል ለምሳሌ ከተመረቀበት አልያም ሙያው ከሆነውና ከሚወደው የስራ መስክ ውጪ በሌሎችም መስኮች ለግዜውም ቢሆን ለመስራት ራስን ማዘጋጀት።
ለዚህ ደግሞ ምን አቅም ምንስ አማራጭ አለኝ የሚለውን በማንሳት ራስን መፈተሽ። እቅድ ሲያወጣም በዚህ ግዜ ስራ አግኝቼ የሚል ነገር ማስቀመጥ የተለመደ ቢሆንም ላይሳካ ቢችል በሚል ራስን ማዘጋጀት ተገቢ ነው።
ነገር ግን ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው ስራ ማግኘት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ሰው ስራ የለውም ማለት በየቀኑ የሚሰራው ስራ የለም ማለት ሊሆን አይገባም። የተለያዩ እንደ በጎ ፈቃድ ያሉ ማህበራዊ አገልግሎቶች፤ በቤት ውስጥ ቤተሰብን ለመደገፍ የሚሰሩ ስራዎችን መከወን መጀመር ይጠበቃል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ መቼም ቢሆን የሰው ልጅ ለማህበረሰቡም ሆነ ለራሱ የሚያደርገው አስተዋጽኦ እንዳለና ሊኖር እንደሚችል ለራስ በመንገር ራስን ዋጋ ቢስ አድርጎ ከማየት መውጣት።
በተጨማሪ ስራ አጥነት የሚፈጥራቸውን ችግሮች በግለሰብ ደረጃ ብቻ መቅረፍ የሚቻል ባለመሆኑ በቤተሰብም በኩል ስራ አጥነት በግለሰቦች ስንፍና ብቻ የሚፈጠር አለመሆኑን ብሎም ትኩረት ካልተሰጠው በርካታ ተያያዥ ችግሮችን ሊያመጣ እንደሚችል በመገንዘብ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆንና በሞራል ለመደገፍ መዘጋጀት።
አንድ ስራ አጥ ወጣት ስራ ማግኘትና ራሱን መቀየር እንደማይችል፤ ተስፋ እንደሌለው፤ የማይረባ ሰው እንደሆነ በቃልም ሆነ በተለያየ መንገድ ከቤተሰቡ የሚደርሰው ከሆነ ዋጋ የለኝም ለሚለው ውስጡ ለተፈጠረው ስሜት ማረጋገጫ ያገኝና በራስ መተማመኑ ጠፍቶ ወደ ሌላ ነገር ለመግባት ይገደዳል።
ድጋፍ ሲደረግም በአንድ ወገን ስራ አጥ የሆነውን ሰው ሞራል የሚነኩ ነገሮችን በመናገር ራሳቸውን እንደጥፋተኛ እንዲቆጥሩና እንዲወቅሱ ከማድረግ መቆጠብ። በሌላ በኩል አንድ ወጣት ስራ ሳይኖረው ገንዘብ ካገኘ ለሱስ አስያዥ ደባል ሱሶች የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ስለሚሆን ስራ አለመኖሩ ሊረብሸው ይችላል በሚል ከሚገባው በላይ የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ መቆጠብ።
ይህንን ብቻ ነው መስራት ያለብህ ከሚል ሀሳብ በመውጣት ይልቁንም ስራ አጡ ሊያያቸው የማይችሉ አቅጣጫዎችን ማመላከት ከእያንዳንዱ ቤተሰብና የቅርብ ሰው የሚጠበቅ ይሆናል ሲሉ ባለሙያው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013