ግርማ መንግሥቴ
የአመቱ ትምህርት ተጀምሯል። የጀመሩም፣ እየጀመሩ ያሉም አሉ። የጀመሩት ከጀመሩ አንድ ወር የሞላቸው አሉ። ከእነዚህም አንዱ በመዲናችን የሚገኘው ሶሊያና አካዳሚ ነው።
ሶሊያና አካዳሚ ዘመኑ ካፈራቸው የግል ትምህርት ተቋማት አንዱ ሲሆን ከ1 – 8ኛ ክፍል (የመጀመሪያና ሁለተኛ ሳይክል) ይሰጣል።
ከትምህርት ባለሙያዎችና ወላጆች ባገኘነው ጥቆማ መሰረት የዛሬው የልጆች አምድና የትምህርት ጉዳያችን አካል ልናደርገው ወደድንና ላንቻ አካባቢ ወደ ሚገኘው የአካዳሚው ቅጥር ግቢ አመራን። ገባን፤ በትምህርት ቤቱ አስተዳደርና መምህራንም አቀባበል ተደረገልን። አስጎበኙን።
በጉብኝታችንም ፀጥ እረጭ ያለና ለመማር-ማስተማር ተግባር ምቹ የሆነውን ፅድት ያለ ግቢ ከፊትና ከኋላው አገላብጠን ተመለከትነው። በትምህርት ገበታቸው ላይ ያሉ፤ ንቅት፣ ፅድት ያሉ ባለ ደምብ ልብስ ተማሪዎችንና በማስተማር ስራ ያሉ ባለ ነጭ ገዋን መምህራኖቻቸውንም እንደዛው። በተለይም በአንድ ክፍል ከ13 ያልበለጡ ተማሪዎችን በማየታችን ርቀት መጠበቁን ተገነዘብን።
በተለይ በተለይ በመንደር ጫጫታና በመኪና ጡሩምባ በሚከሰት የድምፅ ብክለት ምክንያት በመማር ማስተማሩ ስራ ውጤታማ መሆን ያልቻሉና ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያሚያዘነብሉ ትምህርት ቤቶችን ባሰብን ጊዜ ሶሊያና አካዳሚን አደነቅን። ቀሪውን ለትምህርት ባለሙያዎች ትተን ወደ አካዳሚው ተማሪዎች አስተያየት እንሂድ።
ያየነውንና የተነገረውን ከሚመለከታቸው ለማረጋገጥ ተማሪዎችን አነጋገርን። ካነጋገርናቸው ተማሪዎች አንዷ ቅልጥፍ፣ ንቅት ያለች የ10 አመቷ ታዳጊና የ4ኛ ቢ ክፍል ተማሪዋ ሩት ግርማ ነች። ሩትን ስናነጋግራት በራስ የመተማመን ስብእናዋ ደስ ይላል።
ሩትን “ትምህርት እንዴት ነበር?” አልናት። “ጥሩ ነው። ደስ ይላል።” አለችን። “ከኮቪድ በኋላ የትምህርት ቤት መከፈት ምን ስሜት ፈጠረብሽ?” አልናት። “በጣም ነው ደስ ያለኝ። በጣም። መከፈቱ አስደስቶኛል። ከጓደኞቻችን ጋር (ይህንን ሀሰቧን የጨረሰችው በፈገግታ ነው)።”
“ትምህርቱስ እንዴት ነው? የመምህራኖቹ ሁኔታስ?” ላልናትም ጥያቄ ተማሪ ሩት “ሁሉም ጥሩ ነው። መምህራኖቻችንም በጣም ጥሩዎችና ጎበዞች ናቸው። የጎደለብን ነገር የለም።” በማለት ነው የመለሰችልን።
ኮቪድንና ጥንቃቄውን በተመለከተም ሩትን ጠይቀናት ነበር። “በደንብ እየተከላከልን ነው። ሁሉም ተማሪ ማክስና ሳኒታይዘር አለው። መምህራንም ያደርጋሉ። ያልያዘ ካለም ትምህርት ቤቱ ይሰጣል። በክፍል ውስጥ 12 እና 13 ተማሪዎች ስለሆንን የምንቀመጠው ርቀታችንም የተጠበቀ ነው።” በማለት መልሳልናለች።
የክፍል ንፅህናንም በተመለከተ ጥሩ መሆኑን የገለፀች ሲሆን ትምህርት ከተጀመረ በዚህ በአንድ ወር ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ትምህርቱ እየተሰጠና ሞዴል (መለማመጃ) ፈተናም እንደተፈተኑ፤ እሷም ለትምህርቷ ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥና የቤተሰቦቿም ክትትልና ድጋፍ እንዳልተለያት ነግራናለች።
ልጆች እናንተስ የምትማሩበት ትምህርት ቤት ልክ እንደ ሶሊያና አካዳሚ በሚገባ የተያዘ ነው? መምህራኖቻችሁስ? እናንተስ ልክ እንደ ሩት ግርማ ጎበዞችና ትምህርታችሁን በንቃት የምትከታተሉ ናችሁ? እንደምትሆኑ አልጠራጠርም።
በሉ ልጆች ደህና ሁኑ፤ ሳምንት ሌላ ጎበዝ ተማሪ ይዤላችሁ በመምጣት አስተዋውቃችኋለሁ። እስከዛው መልካም የትምህርት ሳምንት!!!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013