ይቤ ከደጃች.ውቤ
እረኛ እና በረኛ የሚባሉት ቃላት ድምፃቸው ይመሳሰላል፤ 99 በመቶ ሊባል በሚችል መልኩም የፊደሎቻቸው ቅርጽና ድምጽም ይቀራረባል፤ ትርጉማቸውም ይቀራረባል ብል እንዳትገረሙ ፤ አደራ! እናም እረኛና በረኛ አንድም በጥበቃ አቻ ሆነው ሲገናኙና ብቸኛ ዝምድና ያላቸው ሲመስሉ፤ በምግባር ግን ሲለያዩ ይታያሉ። ልዩነት ውበት ስለሆነ ግን እንቀበለው፤ ልዩነቱ ግን ከአንድነት ያልተፋታ መሆን አለበት። ልዩነትን ብቻ ማቀንቀን ያስከተለውን ጣጣ እያያነው አይደል።
በረኛ የሚለውን ቃል ሳስበው በእረኛ ከሚለው ቃል የመጣ ነው እንዴ? እላለሁ ለራሴ፤ አንዳንዴ የስነፅሁፍ አድባር ስትጠራኝና ስታመራምረኝ ማለት ነው። ሰዎች በእረኛ በእረኛ ሲሉ ቆይተው ‹‹እ›› ፊደልን መጥራቱ ስለታከታቸው እና የሥራ ሰአታቸውን ስለተሻማባቸው ‹‹እ›› ፊደል ይዋጥ በቃ ማለቴ ይሙት በቃ ብለው ፈርደውበት (በመንደር ሽማግሌዎች ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብኩ) በረኛ የተባለ ይመስለኛል። አይፈረድባቸውም ታዲያ ወርቃማ የሥራ ሰዓታቸውን ይሻማበቸው እንዴ? እነሱም እኮ ከድህነት መውጣት ይፈልጋሉ።
እናም እላችሁለሁ የምወዳችሁና የምትወዱኝ አንባቢዎቼ በረኛ ቀስ በቀስም ለዘበኛ ከዚያም ለጥበቃ አቻ ሆኖ ቁጭ አለ። ቁጭ አለ ስላችሁ ታዲያ ዙፋን ላይ አይደለም ቆጥ ላይ ነው። ከፈለጋችሁ ቆጥ ላይ ቁጢጥ አለ በሉት። ወይኔ ! የስነ ቃል ተመራማሪ አለመሆኔ ከፋኝ። ቢከፋኝም ለስነቃል ተመራማሪዎች ግን ፍንጭ ስለሰጠኋቸው ኮራሁኝ። ተመራምረው ይደርሱበትና ምላሽ ይሰጡንና ያኮሩናል ብዬ አስባለሁኝ።
እረኛ እና በረኛ ሲፍታቱ ጥበቃ ጠባቂ የሚል ፍቺ አላቸው። ሁለቱንም ቃላት የሚያዛምዳቸው ነገር ያለ ይመስላል። በዘመናችን በረኛ የሚለው ቃል ለእግር ኳስ ግብ ጠባቂዎች /goal keepers/ በእነ ታላቁ የስፖርት ሰው ይድነቃቸው ተሰማ የተሰጠ ስያሜ ነው ይባላል።
የጥንቱ የጠዋቱ አማርኛ ግን ̎በረኛ̎ ን በር ላይ ሆኖ ቤት የሚጠብቅ በሚል ይፈታዋል። እኛ ዘበኛ ስንለው የኖርነው አሁን ደግሞ ጥበቃ የምንለው ማለት ነው። እንደ ሐረር ጀጎል ግምብ የመሳሰሉ ጥንታዊ ከተሞች ምሽት ላይ የከተማው መግቢያ በሮች ተዘግተው በረኞች እየጠበቁ ያድሩ ነበር።
ከላይ እንደጠቀስኩት ሁለቱን ቃላት ጠባቂ የሚለው ቃል ቢያመሳስላቸውም እረኛ የሚለው ቃል በገደምዳሜ ስናየው ሠፋ ያለ ትርጓሜ ያለው ይመስለኛል። እረኛ ጠባቂ ብቻ ሳይሆን መጋቢም ሆኖ የሚያለግል ነው። እረኛ የከብት ጠባቂ መሆኑን ማንም አይስተውም፤ በገጠር ላደጉ የሥራ መጀመሪያቸው ወይም መለማመጃቸው አንድም እረኝነት ነው፤ በተለይ ለወንዶቹ፤ ሴቶቹማ ለቤት ውስጥ ስራ ነው የሚታጩት። ወንዶቹ በልጅነት ዘመናቸው የሥራን ሀ ሁ የሚማሩትና የሚለማመዱት በእረኝነት በመሰማራት ነው።
ስለ እረኝነትና በረኛነት ካነሳን ዘንዳ ውሾችስ ዘበኛ ሆነው እንደሚሠሩ በእረኝነትም እንደሚሠማሩ ስንቶቻችን እናውቃለን? ብሉይ ኪዳን እረኞች መንጋቸውን በውሾች ያስጠብቁ እንደነበር ያመለክታል። እረኞች ወደ ስራቸው ሲሰማሩ ከብቶቻቸውን በማብላትና በማጠጣት የመጋቢነት ግዴታቸውን ይወጣሉ፤ ቡቃያ ወይም የደረሰ ሰብል እንዳያጠፉ ፣በተከለከለ የግጦሽ ስፍራ ዝር እንዳይሉ ያግዳሉ።
አንድ እረኛ ከብቶቹን ወደ ከሎ ወይም ግጦሽ ስፍራ ሲያሰማራ ቀበሮና ተኩላዎች በጎቹንና ፍየሎቹን እንዳይበሉበትም ይጠብቃል። ንሥርም በሰማይ እየበረረች ዐይናዋ የገባውን ግልገል ወርዳ ሞጭልፋ ለመሄድ የሚመቻት እረኞች በሌሉ ጊዜ ስለሆነ እረኝነት ብዙ ሃላፊነት አለበት።
እረኛ ይህን ሁሉ እያረገ ታዲያ በጥሩ አይን የማይታይበት ሁኔታ አለ። የከተማ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በገጠር ያሉትም ይህን ውለታውን ወደ ጎን ትተው ለእረኛ ያላቸው አመለካከት የደከመ ነው። ተራ ሰው አርገው ያዩታል። ከብቶቻቸውን ከአውሬ እና ከሌባ እየተከላከለ የሚውል ባለውለታ ለምን ተራ ሰው ይባላል ጎበዝ!
በአጼ ቴዎድሮስ የንግስና ዘመን ህዝቡ ቆለኛ እረኛ እያለ ያንሾካሽክ ነበር አሉ። እረኛ (ልጅ) ስለሆነ የዘር ሐረግም ስለሌለው (የሰለሞን ዘር ስላልሆነ ንግሥና አይገባውም) በሚል ንጉሡን ህዝቡ ያማቸው ነበር። በነገራችን ላይ ግን አባወራ እና እማወራም ልጆች በትምህርት እና ሥራ ምክንያት ከራቁ እረኛ ሆነው ከብቶቻቸውን ያግዳሉ። አዲስ ጎጆ ወጪም ልጆቹ እስኪደርሱ እርሻውንም እረኝነቱንም አጣምሮ ያስኬደዋል። ስለዚህ እረኝነት የልጆች ሥራ ብቻ አይደለም።
በነገራችን ላይ እረኛ ሁሉ እግረኛ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፤ እኛ ሃሳቡን ባንቃወምም አንደግፍም። አንዳንዴ እረኛ እንዳቅሙ በፈረስ ፣ በበቅሎና በአህያ እየሄደ መንጋዎቹን ያሰማራል፤ እግረ መንገዱንም ዘና ይላል ማለት ነው፤ እንዳቅሚቲ። በሌሎች ሀገሮች በባጃጅ፣ በሞተር ቢስክሌት ሆነው ከብታቸውን የሚያሰማሩ እረኞች አሉ። በነገራችን ላይ እረኞች በአህያ ግልቢያ ይታወቃሉ ይባላል። ይህ ደግሞ ለፈረስ ግልቢያ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
እረኛን መናቅ ጥንትም የነበረ ነው፤ አረኝነት ያለውን ፋይዳ እስካየን ድረስ የሚቀለው አረኝነት ሳይሆን አቅላዩ ነው። ያለንበት ወቅት የበአለ ገና መዳረሻ እንደመሆኑ ከእረኝነት ጋር የተተያዘ ነገር ላንሳ።
̎እረኝነት ትንሽ የወረዳ ግብር
ብሎ ሰው በድንገት ደንግጎ ነበር
የብዙ ሰው ራስ መሆኑን እረኛ
ክርስቶስ ሲወለድ ተረዳነው እኛ ̎
የሚለው የክርስትና እምነት የልደት መዝሙር ከላይ እንደጠቀስነው ጥንትም እረኛ ሲናቅ እንደነበር የሚያመለክተው ቢኖርም፣ እረኝነት ታላቅ ተግባር መሆኑን የእምነቱ አስተምህሮ ይጠቁመናል። በከብቶች በረት የተወለደው ክርስቶስ በወንጌል መልካም እረኛ እኔ ነኝ ብሏል። እረኞችም ከመላዕክት ጋር በጌታ ልደት እንደዘመሩ በሉቃስ ወንጌል ተጠቅሷል። ዳዊትም በመዝሙር 23 ላይ እግዚአብሔር እረኛዬ ነው ይላል።
አንዳንድ ሰዎች ለሰው ያላቸውን ንቀት ለመግለጽ ሲሉ ይሄ ምን ያውቃል እረኛ አይደል? ብለው ይተቻሉ። ይህ ንግግራቸው ባለማወቅ በማናናቅ የሚናገሩት ስለሆነ ንቀን መተው ነው የሚያዋጣው።
ቃሉን ጠባቂና መጋቢ አድርገን ከፈታነው ዘንዳ ሰዎች ሁሉ እንደደረጃቸውና አቅማቸው በሕይወታቸው በእረኝነት ህይወት ውስጥ ያልፋሉ፤ በከተማ የሚኖሩት ጭምር። አባወራና እማወራ ለቤታቸው እረኛ ናቸው። ልጆቻቸውን ይጠብቃሉ ይመግባሉ። ወደ ትምህርት ስንሄድ ርዕሰ መምህር የትምህርት ቤቱ እረኛ ነው። የጊቢው መምህራን፣ ድጋፍ ሠራተኞችና ተማሪዎችን በሚመለከት ኃላፊነት አለበት። መምህሩም ለተማሪው እረኛ ነው ተማሪውን በስነምግባር ይጠብቃል ፤ በዕውቀት ይመግባል።
‹‹ፖሊስ የሰላም ዘብ›› ወደሚባለው ተወዳጅ ዜማ እንሂድና ፖሊስን ስናንሳ በእረኝነትና በበረኝነት ያገለግላል። ወታደሩም ለሀገሩ ለዳር ድንበሩ በእረኝነትና በበረኝነት እየጠበቀ ይዋደቃል። የመሥሪያ ቤት ዳይሬክተር ሆነ የሀገር መሪ እንደየደረጃቸው የእረኝነት ኃላፊነት አለባቸው።
በአጠቃላይ መንግስት የሀገርና የህዝብ እረኛ ነው። ህዝብን የመጠበቅ ሃላፊነት /በያዘነው አገባብ መሰረት እረኝነት/ በየደረጃው ላለው አካል የተሰጠ ቢሆንም፣ ያ አካል ይህን ሃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ በቀጣይ ያለው እርከን ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።
መንግስት በትግራይ ክልል የህግ የበላይነትን ለማስከበር ያከናወነው ተግባር እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየወሰደ ያለው እርምጃም ሀገርንና ህዝብን ከመጠበቅ አኳያ የሚደረግ እንደመሆኑ የእረኝነት ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ያመለክታል።
እረኝነትን ካላቀለሉት በስተቀር ትርጉሙ ሰፊ ነው።ሁላችንም እረኞች ነን፡፤ራሳችንን ከመጠበቅ አንስቶ ህዝብና ሀገርን የመጠበቅ ሃላፊነት አለብን። እረኝነትን ያቀለለ በራሱ የቀለለ ነው ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013