አስናቀ ፀጋዬ
አረብ ሀገር ተሰደው ከቀን ስራ እስከ መኪና እጥበት ፈታኝ የሆኑ የጉልበት ስራዎችን ሰርተዋል። ከስደት ወደሃገራቸው ከተመለሱም በኋላ ስራን ሳይንቁ በሆቴል፣ ጋራዥና በንግድ ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው አገልግለዋል፤ አልፎ አልፎም የራሳቸውን ተባራሪ ስራ ሰርተዋል።
በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው በአምስት ሺ ብር ካፒታል የጀመሩት የእንጨት ስራ በአዳዲስ ፈጠራ ታጅቦ በመቅረቡ ራሳቸውን ከማስተዋወቅ በዘለለ የበርካታ ደምበኞችን ቀልብ ስቦላቸዋል። ይህ የንግድ እንቅስቃሴያቸው ዛሬ ላይ ጎልብቶ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ባለቤት ለመሆን አብቅቷቸዋል። የአሹ ኢንተርናሽናል ፈርኒቸር ዓለምና የኪንግ ኦፍ አፍሪካ ቱር ኤንድ ትራቭል ኤጀንሲ ባለቤትና መስራች አቶ አሸናፊ ሙሴ።
አቶ አሸናፊ ሙሴ ትውልድና እድገታቸው ምስራቅ ጎጃም ሲሆን በልጅነታቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሃይሉ ተስፋዬና ራጉኤል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። ከስምንተኛ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ከተሸጋገሩ በኋላ ራሳቸውን ለማስተዳደር የአቅም ችግር ስለገጠማቸው ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተሰደዱ።
ይሁንና በስደት ከሄዱ በኋላ በሀገራቸው የሚወራውና እዛ ያለው ፈፅሞ የሚጣጣም ሆኖ አላገኙትም። ሳኡዲ አረቢያ በነበራቸው ቆይታም ከበርካታ ፈተናዎች ጋር ተጋፍጠው ከቀን ስራ ጀምሮ እስከ መኪና እጥበት ድረስ የተለያዩ ስራዎችን ሰሩ።
የሁለት ዓመት የሳዑዲ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደሃገራቸው ከተመለሱ በኋላ አቶ አሸናፊ በሆቴሎች፣ ጋራዦችና ንግድ ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው መስራት ቀጠሉ። ከዚሁ ጎን ለጎንም ተባራሪ ስራዎችን ይሰሩ ጀመር። ለሰባት ወራት ያህልም በአንድ የግለሰብ እንጨት ቤት ተቀጥረው በመስራት በሳምንት 27 ብር እየተከፈላቸው እጃቸውን አፍታቱ።
በ2002 ዓ.ም በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው በአምስት ሺ ብር ካፒታል የራሳቸውን አነስተኛ የእንጨት ስራ አዲስ አበባ ከፍተው መስራት ጀመሩ። በወቅቱ ከመንግስት ያገኙት ድጋፍና ስልጠና ወደተሻለ ምእራፍ እንዲንደረደሩ በር ከፈተላቸው። በጊዜው በእንጨት ስራ ዘርፍ ለመሰማራት ያነሳሳቸው ዋነኛ ምክንያትም በሙያው በቀላሉ ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ በመረዳት ነበር።
በፈርኒቸር ዓለም ትንሽ ከምትባለውና በ25 ብር ዋጋ ከሸጧት ዱካ አንድ ብሎ የጀመረው የአቶ አሸናፊ የእንጨት ስራ በሂደት ሶፋዎችን፣ ወንበሮችን፣ ጠረጴዛዎችን፣ አልጋዎችንና ሌሎች የእንጨት ውጤቶችንና ጥገና ስራዎችን ማከናወን ቀጠለ።ቀስ በቀስም ራሳቸውን እያደራጁ መጥተው ልዩ ልዩ የእንጨት ስራዎችን በመስራት በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት በአዲስ አበባ ደረጃ ሞዴል ለመባል በቁ።
በውስጣቸው ሳይታወቅ ተቀብሮ የነበረ ተሰጥኦቸውም በእንጨት ስራዎቻቸው ላይ ይንፀባረቅ ጀመር። አብዛኛዎቹ ስራዎቻቸውም ከመደበኛው አሰራር ወጣ ያሉና በፈጠራ የታጀቡ ነበሩ። በጊዜው የሚያመርቷቸው አልጋና ሶፋዎችም ከመተኛነትና ከመቀመጫነት በዘለለ ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶች እንዲሰጡ ታስበው የሚሰሩ ነበሩ። በዚህ የፈጠራ ስራቸውም ከጀርመን መንግስት ሽልማት እስከማግኘት ደርሰዋል። ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴርም የእውቅና ሰርተፍኬት አግኝተዋል።
እነዚህ የፈጠራ ስራዎቻቸው አቶ አሸናፊን ይበልጥ እያስተዋወቋቸውና በርካታ ደምበኞችን እየሳቡ መጡ። የእንጨት ስራ ምርቶቻቸውም በገበያ ይበልጥ ተፈላጊ ሆኑ። እርሳቸውም በተለያዩ ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ምርቶቻቸውን ይበልጥ አስተዋወቁ።
ወደፊት ማደግ እና ተጨማሪ አዳዲስ ስራዎችን ሊሰሩ እንደሚችሉ የተረዳው የከተማ ልማት ሚንስቴርም በ2004 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አካባቢ 432 ካሬ መስሪያ ቦታ ተሰጣቸው።
ሆኖም ሚንስትሩ የሰጣቸውን ቦታ ወረዳው ነጠቃቸው። አንድ ዓመት ፍርድ ቤት ከተከራከሩ በኋላም 10 ሺ 700 ብር ከፍለው ቦታውን ለመልቀቅ ተገደዱ። ይሁንና ዳግም አገግመው ቤት ተከራይተው ያሉበት አካባቢ በ200 ብር ቦታ ተከራይተው የእንጨት ስራቸውን ጀመሩ።
በአሁኑ ጊዜም በእንጨት ስራ ድርጅታቸው በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ የሚገኙ ሲሆን ከውጪ ሀገር በብዙ ብር ወደሀገር ውስጥ የሚገባውን ሶፋ ሊያስቀር የሚችልና መቶ ሺ ብር የሚጠጋ ዋጋ ያለው ሶፋ በማምረት አስደሳች ስራ ለመስራት ችለዋል። በዚሁ የእንጨት ስራም እስካሁን ባለው ሁኔታ ባጠቃላይ ከ20 ለማያንሱ ሰዎች የስራ እድል ፈጥረዋል።
ከባንክም ሆነ ከግለሰቦች እስካሁን ድረስ ብድር ወስደው የማያቁት አቶ አሸናፊ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በርካታ ፕሮጀክቶችን እያከናወኑ የሚገኙ ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ መንግስት በሊዝ በሰጣቸው መሬት ላይ በ28 ሚሊዮን ብር ወጪ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በራሳቸው ወጪ እየገነቡ ነው። አሁን ግንባታው 75 ከመቶ ደርሷል።
እስካሁን ባለው የግንባታው ሂደትም ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ፈጥሯል። በቀጣይ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባም እስከ 270 ለሚሆኑ ዜጎች በተለያየ መልኩ የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
ለቱሪስት መስህብ ወሳኝ በሆነው በጢስ አባይ ፏፏቴ አካባቢ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ሎጅ ለመግንባትም በማሌዢያውያን ፕሮጀክቱ ተገምግሞና አልፎ በአሁኑ ወቅት ግንባታውን ለማከናወን በሂደት ላይ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሺ የሚሆኑ ቪ ኤት መኪኖች ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ በኪንግ ኦፍ አፍሪካ ቱር ኤንድ ትራቭል ኤጀንሲያቸው በኩል ዘመናዊና የተሟላ የቱሪስት ጉዞና ጉብኝት አገልግሎት ለመጀመር አቅደዋል።
ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ለመንገድና ትራንስፖርት ሚንስቴር፣ ለባህልና ቱሪዝም ሚንስቴርና ለጠቅላይ ሚንስቴር ፅህፈት ቤት ጥያቄ ቀርቧል። ይህም ፕሮጀክት የታሰበው በቀጣይ ወደሃገሪቱ የሚፈልሰውን ቱሪስት ታሳቢ ያደረገ ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ሲሆን ከኢትዮጵያ ንግድና ከግል ባንኮች ጋር ንግግር ተደርጎ ባለሃብቶች 30 ከመቶውን ከፍለው 70 ከመቶውን ቀስ ብለው የሚከፍሉበት መንገድ ተመቻችቷል።
በተጨማሪም ‹‹ሴት ታክሲ›› በሚል ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የስራ እድል ፈጠራው ላይ በማተኮር ቢያንስ ለ2 ሺህ ሴት አሽከርካሪዎች የስራ አድል ለመፍጠር አልመዋል። ይህም ፕሮጀክት በሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን ሴቶቹ 30 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ በመቆጠብና 70 ከመቶውን ባንክ እንዲሸፍንላቸው በማድረግ 2 ሺህ የሚሆኑ ታክሲዎች ወደሀገር ውስጥ ገብተው አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል። ይህም ሴቶች ባለንብረት እንዲሆኑ ከማስቻል በዘለለ ኢኮኖሚያቸውን ለማሻሻል ይረዳቸዋል።
ይሁን እንጂ በሀገሪቷ በአሁኑ ወቅት ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ነግዶ ለማትረፍ የሚቻልበት ባለመሆኑና ከዚህ ይልቅ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ አቶ አሸናፊም እነዚህን ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ልክ አንቀሳቅሶ ለውጤት ለማብቃት ግዜ ወስደው እየሰሩ ይገኛሉ።
በቀጣይ በሀገሪቱ የተሻለ የሰላም ሁኔታ ሲፈጠር ፕሮጀክቶቹን ከግብ ለማድረስም ፍላጎቱ አላቸው። እነዚህን ፕሮጀክቶች ለማስፈፀም ከባንኮች ጋር መስራት የግድ ስለሚልም በቀጣይ በተለይ ከንግድና ከሌሎች የግል ባንኮች ጋር ለመስራት እቅድ ይዘዋል።
‹‹ራሴን እንደ ባለሀብት ብቻ አድርጌ አላይም›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ የፈጠራ ሰው እንደሆኑና ነገሮችን የማየት አቅማቸውም ከፍ ያለ እንደሆነ ይመሰክራሉ። ማንኛውንም ስራ ሲሰሩ ፈጠራ አክለውበት እንደሆነና በሰዎች ዘንድም ስራቸው ተመራጭ መሆኑንም ይናገራሉ።
በዚህም የእርሳቸው የእንጨት ስራ ከሌላው እንደሚለይ ይገልፃሉ። በሌላ በኩል በደግሞ ራእያቸው ሰፊና ትልቅ መሆኑንና በቀጣይ ከባለሀብት ይልቅ ባለፀጋ የመሆን ፍላጎት ህልም አላቸው። ባለፀጋ ለመሆን መድከማቸው ከተቀረው ባለሃብት እንደሚለያቸውም ይገልፃሉ።
በቀጣይም የጀመሯቸውን ሁሉንም ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅና ፍሬ አፍርተው ለሀገርና ለትውልድ እንዲተርፉና ለአፍሪካም ጭምር ሞዴል እንዲሆኑ የማድረግ እቅድ እንዳላቸው አቶ አሸናፊ ይናገራሉ።
እርሳቸውን መከተል ለሚፈልጉ ወጣቶችም አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ድርጅቶች እንዲሆኑ አጥንክረው እንደሚሰሩም ይጠቁማሉ። ፕሮጀክቶቹ አንዱ ሌላውን የሚፈጥር ቢዝነስ እንዲሆን የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውም ይገልፃሉ።
በሜካናይዝድ ግብርና ስራ ውስጥ በስፋት የመግባት እቅድ እንዳለቸውም የሚገልፁት አቶ አሸናፊ፤ በተለይ ሀገር በሁለት እግሯ እንድትቆም ከተፈለገ በግብርናና ኢንዱስትሪ ላይ አተኩሮ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ እርሳቸውም በቀጣይ በዘመናዊ ግብርና ላይ ይበልጥ አተኩረው እንደሚሰሩ ይናገራሉ። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግም መንግስትና ህዝቡ ተባብሮ ግብርናውንና ኢንደስትሪውን ማዘመን እንዳለበትም ይጠቁማሉ።
‹‹የተሳካ ህይወት ለመኖር ሰው የሚያስፈልገው እምነት፣ድፍረትና ጥበብ ነው›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ እርሳቸውም ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት እምነት፣ድፍረትና ጥበብ ስለአላቸው መሆኑንም ይገልፃሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዳቸውም እንዳይጎሉ አጥብቀው ሲታገሉ እንደቆዩና አላማቸውን ለማሳካት ሁሌም ብርቱ መሆናቸውንም ይናገራሉ።
መንግስት በህግ ማስከበሩና በፖለቲካው ያገኘውን ድል በኢኮኖሚውም መድገም እንዳለበትና በተለይ ኢንቨስትመንት ውስጥ በመግባት በሚያዋጣውና ገንዘብ በሚያመነጭ ነገር ብቻ ካተኮረው ባለሃብት ይልቅ ለሀገሩና ለህዝቡ ቅድሚያ የሚሰጠውን ባለፀጋ መለየት እንደሚገባውም አቶ አሸናፊ ያሳስባሉ። ባለሃብቶችን ከማፍራት ይልቅ በርካታ ባለፀጎችን ማፍራት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ያስረዳሉ።
በኢኮኖሚው ባለስልጣኑና ባለሃብቱ የጋብቻ ፊርማቸውን ካልቀደዱና በተለይ ደግሞ ኢኮኖሚውና ፖለቲካው ካልተለያየ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የታሰበው ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደማይችልም ያላቸውንም ስጋት ይገልጻሉ። መንግስትና ህዝብ ተማምኖ በጋራ መስራት እንዳለበትም ይጠቁማሉ።
በተመሳሳይ ሌሎችም እርሳቸው በሄዱበት መንገድ ተከትለው ውጤታማ መሆን ለሚፈልጉ ሰዎች ‹‹ሰው አልረዳኝም፤ መንግስትም አልደገፈኝም›› ከማለት ይልቅ በቅድሚያ አምነውና ደፍረው ራሳቸውን ለመለወጥ በጥበብ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው ይመክራሉ። ገንዘብ ለማግኘት ከማሰባቸው በፊት በመጀመሪያ ገንዘቡን እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰዎች ያሰቡት ደረጃ ላይ ለመድረስ ከፈለጉ ቅንነትን፣ሰላምንና ሀገራቸውን ማስቀደም እንዳለባቸው ይናገራሉ። ሀገሪቱ የሚሰራላት እንጂ የሚሰራባት እንዳትሆን ማድረግ እንደሚገባቸውና በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸውም መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።
አቶ አሸናፊ ሙሴ ስራን ሳይንቁ ከቀን ሰራተኝነት ጀምረው የራሳቸውን እንጨት ቤት በመክፈትና ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴ እያደነቅን በተመሳሳይ ሌሎችም የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ መልእክታችንን እናስተላልፋለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013