ሶሎሞን በየነ
“እንደ አገር መከላከያ ሰራዊት ከጀርባዬ ስድስት ልጆች በወለደችልኝ ባለቤቴ የተወጋሁና ከፊት ለፊቴ ደግሞ በብሔር ፍትህን በሚሰጡ ፈርያ እግዚያብሄር በሌላቸው አረመኔዎች የደማሁ ሰው ነኝ” ሲሉ ፍረዱኝ ባይ አቶ አፈወርቅ ክብረት የዛሬ ሳምንት ማለትም ረቡዕ ታህሳስ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ያቀረቡትን የመጀመሪያ ክፍል አቤቱታ የዝግጅት ክፍላችን ይዞ መቅረቡ ይታወሳል።
ቅሬታ አቅራቢው ‹‹ሃብቴ›› በሚሉት፤ ከኒያላ የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ድርጅት ጋር ተያይዞ ተፈጽሞብኛል ስላሉት በደልና ፈቃደኛ የሚሆኑ ከሆነም፤ በዳይ የተባሉት ባለቤታቸውን እና የሌሎች አካላትን ምላሽ ይዘን እንቀርባለን ብለን ቃል የገባን ቢሆንም፤ የድርጅቱን ጉዳይ በሶስተኛው ክፍል የምንቀጥል ሲሆን፤ በዚህኛው ክፍል የአቶ አፈወርቅ ባለቤት ወይዘሮ ብርዛፍ ክንዴ ‹‹ቅሬታ አቅራቢው የሰጡት ማስረጃ ከእውነት የራቀና ሃሰተኛ መረጃ ነው›› ሲሉ በተወካይ ልጃቸው ወይዘሮ ራሄል አፈወርቅ በኩል ያቀረቡትን ምላሽ እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል።
የወይዘሮ ብርዛፍ ክንዴ ልጅና ህጋዊ ወኪል ወይዘሮ ራሄል እንደሚሉት፤ ረቡዕ ታህሳስ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በወጣው የፍረዱኝ አምድ አባታቸው አቶ አፈወርቅ ክብረት ያቀረቡት አቤቱታ ፍጹም ሀሰትና ከዕውነታው ጋር የማይገናኝ ነው።
ወይዘሮ ራሄል እንዳብራሩት፤ አባታቸው በ1960 ዓ.ም በፖሊስ መሃንዲስ መምሪያ በእንጨት ስራ ባለሙያነት አስመራ ከተማ ተመድበው እየሰሩ ባለበት ወቅት ከእናታቸው ከወይዘሮ ብርዛፍ ክንዴ ጋር ተዋውቀው፤ ትውውቃቸው ወደ ፍቅር አምርቶ ለጋብቻ በቅተዋል።
አስመራ ከተማ የበኩር ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ አባታቸው ዝውውር አግኝተው በ1966 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ከነሙሉ ቤተሰባቸው ተመልሰዋል።
እናታቸው ከአስመራ አቶ አፈወርቅን አግብተው ሲመጡ ወይዘሮ ብርዛፍ ገና የ15 ዓመት ልጅ እንደነበሩ ጠቁመው፤ አባታቸው አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ በፖሊስ መሃንዲስ መምሪያ ስራቸውን ሲሰሩ ቆይተው ሰው ገለው እስር ቤት ይገባሉ።
አባታቸው እስር ቤት ሲገቡ እናታቸው ወይዘሮ ብርዛፍ ቤት ሙሉ ልጆች ይዘው እስከ ልጆቻቸው ጦማቸውን እያደሩ የሰቆቃ ጊዜን ያሳልፋሉ። በዛ ጊዜም ቢሆን የሰው እጅ እያዩ ከሚያገኙት ላይ ወይዘሮ ብርዛፍ አቶ አፈወርቅን እስርቤት ድረስ ምግብ እየወሰዱ አባታቸውን ሲንከባከቡ እንደነበር ይናገራሉ።
ወይዘሮ ራሄል አባታቸው ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ የሚከፈላቸው የወር ደሞዝ አነስተኛ ከመሆኑ ባሻገር፤ ከወንጀሉ ጋር ተያይዞ ስራ ቦታ ስማቸው ስለጠለሸ ስራ ላይ ተረጋግተው መስራት ሲያቅታቸው በአነስተኛ ካፒታል የጫማ ስራ ጀምረው በሚያገኙት ገቢ የተሻለ ኑሮ መኖር መጀመራቸውን ያስታውሳሉ።
አባታቸው የጫማ ስራውን እየሰሩ ጎን ለጎን ደግሞ እናታቸው የህንጻ መሳሪያ መሸጫ ከፍተው ሲሰሩ፤ የተሻለ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ንግዳቸውን በማሳደግ ኒያላ የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ድርጅት በጋራ ማቋቋማቸውን ወይዘሮ ራሔል ይጠቁማሉ።
በአጠቃላይ በልቶ ለማደር አስቸጋሪ ከነበረ ህይወት ወጥተው የተሻለ ደረጃ ደርሰው አምስት ልጆችን በጋራ ካፈሩ በኋላ፤ አባታቸው የእናታቸውን የቅርብ ጓደኛ አንዲት ግለሰብ እንደ ሚስት ሌላ ቦታ አስቀምጠው ልጅ መውለድ መጀመራቸውን እንዳረጋገጡ ይናገራሉ።
የወይዘሮ ራሔል እናት ትዳራቸው የተባረከ እንደሆነና ባላቸውም የስራ ሰው እንደሆነ ሲያስቡ እንደነበር የሚገልፁት ወኪሏ፤ አቧት እናታቸውን እቤት አስቀምጠው ሲያደርጉ የነበረውን አጸያፊ ድርጊት በተደጋጋሚ ሲከታተል የነበረ አንድ ግለሰብ ‹‹ለ10 ዓመት በህይወትሽ እየተጫወተብሽ ነው።
የልብ ጓደኛዬ ብለሽ ካቀረብሻት ሴት ባለቤትሽ ወልዶ በድብቅ አስቀምጧታል›› በሚል ለእናታቸው ደብዳቤ መላኩን ይናገራሉ።
እናታቸው ‹‹ይሄ ጉዳይ ምንድን ነው?›› በሚል ባለቤታቸውን ሲጠይቁ በፍጹም እንዳላደረጉት መካዳቸውን ወይዘሮ ራሄል ገልጸው፤ እርሳቸውና ወንድማቸው ሲከታተሉ ግን የእናታቸው የቅርብ ጓደኛ በድብቅ ሚስት ተደርጋ መቀመጧን እንዳረጋገጡ እና ግለሰቧም፤ አቶ አፈወርቅ ‹‹ከወደቀ ቤት አውጥቼ ህይወትሽን እቀይርልሻለሁ›› ብለው እንዳታለሏቸው መግለፃቸውን ይናገራሉ።
እንደወይዘሮ ራሔል ገለፃ፤ ልጆቹ የተፈጠረውን ጉዳይ ለእናታቸው ነግረው የአባታቸውን ጀርባ የበለጠ ሲያጠኑ፤ ከሌሎችም ከተለያዩ ሴቶች ከሰባትና ከስምንት ልጅ በላይ በትዳራቸው ላይ እየማገጡ መውለዳቸውን ማረጋገጣቸውን ይገልፃሉ።
የወይዘሮ ራሔል እናት ለአቶ አፈወርቅ ‹‹በእኔ ላይ እየማገጥህ ለምን ክብሬን ትነካለህ›› በሚል ባለቤታቸውን ሲጠይቁ አባት ‹‹ ይቅር በይኝ›› በማለታቸው፤ እንደገና አብረው ወደ ትዳራቸው ተመልሰው መኖር ቢጀምሩም፤ አቶ አፈወርቅ ከሴትየዋ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዳላቆሙ በመታወቁ ወይዘሮ ብርዛፍ ሲበሳጩ፤ አቶ አፈወርቅ ከሴትየዋ ልጅ መውለዳቸውን ገልፀው፤ ለልጆቹ በየወሩ ተቆራጭ ከተቆረጠ ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያቋርጡ ቃል መግባታቸውን ወይዘሮ ራሄል ይናገራሉ።
ነገር ግን አቶ አፈወርቅ ቃል ከገቡ በኋላ ከእንጨት ፋብሪካው ያለደረሰኝ በወንድ ስም የተለያዩ የፈርኒቸር ምርቶችን እያወጡ በድብቅ እዛው የእንጨት ፋብሪካው አጠገብ በወቅቱ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አውጥተው ልጅ ለወለዱላቸው ግለሰብ ህንጻ ሰርተው እንዳስረከቡ እናታቸው ከሰው ማስረጃ ማግኘታቸውን ተከትሎ፤ ወይዘሮ ራሔል ከታላቅ ወንድማቸው አቶ ሳሙኤል አፈወርቅ ጋር በተከታተሉበት ወቅት አባታቸው አስቤዛ ይዘው ሴትዮዋጋር ሲገቡ እንደያዙዋቸው ይናገራሉ።
ወይዘሮ ራሄል እንደገለፁት፤ አባታቸው የሴትዮዋን ስም አጥፍታችሁዋል በሚል ከነወንድማቸው ከሰዋቸው ቃሊቲ ለሁለት ውር ተፈርዶባቸው እንደነበር እና እርሳቸው በወቅቱ አራስ እንደነበሩ ይግባኝ በማለታቸውም ለአንድ ሳምንት ታስረው መፈታታቸውን ያስታውሳሉ።
እንደወይዘሮ ራሔል ገለፃ፤ አባታቸው ለእናታቸው ለወይዘሮ ብርዛፍ ‹‹ይቅር በይኝ እግርሽ ላይ ልውደቅ ካሳ ልካስሽ በድዬሻለሁ በጋብቻዬ ላይ ዝሙት ስለፈፀምኩኝ የራሴን ድርሻ የቦሌውን ቤት ስጦታ ልስጥሽ›› በማለት፤ የቦሌውን ቤት ሃምሌ 27 ቀን በ1993 ዓ.ም ውል እና ማስረጃ ሄደው ስጦታውን ሰጥተዋቸዋል።
ቀድሞም ቢሆን ቤቱ የተመዘገበው በእናታቸው ስም እንደነበር በመግለፅ፤ ቢሆንም ግን የጋራቸው በመሆኑ አቶ አፈወርቅ ድርሻቸውን በስጦታ ለወይዘሮ ብርዛፍ መስጠታቸውን ያብራራሉ።
‹‹ሰው ወርቅ፣ መኪና ወይም እንቁ ይክሳል። በድያታለሁና ትዳሬንም ከማጣ ልካሳት ብሎ ‹የእኔን ድርሻ ወድጄ እና ፈቅጄ ማንም ሳያስገድደኝ ሰጥቻታለሁ› ብሎ ውልና ማስረጃ ፈርሟል።
ሙሉ በሙሉ ቤቱን በሷ ስም ካደረገ በኋላ በስጦታ ካስተላለፈላት ማለትም ከ1993 እስከ 2002 ዓ.ም ትዳሩ ቀጥሏል›› በማለት የሚናገሩት ወኪሏ፤ ነገር ግን አባታቸው ይቅርታ ብለው ለእናታቸው ካሳ ከሰጡ በኋላም ከሴትየዋ ልጅ መውለዳቸውን ባለማቆማቸውና አስቤዛ እየገዙ ሲገቡ በመገኘታቸው እናታቸው ትዳራቸውን ለመፍታት መወሰናቸውን ይናገራሉ።
ነገር ግን አባታቸው አቶ አፈወርቅ ‹‹ከቤቴ እራቁቴን በግፍ ተባሪሬያለሁ›› ብለው አቤቱታ ማቅረባቸውን አስታውሰው፤ ይህ ከእውነት የራቀ ነው የሚሉት ወይዘሮ ራሔል፤ ፍቺው የተፈፀመው ከሴትዮዋ ጋር ቆይተው ሲመጡ በተፈጠረ አለመግባባት እንዳይገቡ በመከልከላቸው በዛው መቅረታቸውን ያስረዳሉ።
አቶ አፈወርቅ ከቤት ከወጡ በኋላ መፋታታቸው ሲሰማ፤ ‹‹እገሌ የሱ ልጅ ነው፤ እገሌም የሱ ልጅ ነው››፤ ብዙ ልጆች እንዳላቸው መነገሩን ገልጸው፤ አባታቸው ከቤት ከወጣ በኋላ ሲጣራ ከብዙ ሴቶች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በመታወቁ እናታቸው በቃኝ ብለው ትዳሩ መፍረሱን ይናገራሉ።
‹‹ትዳሩ ፈርሶ ወደ ንብረት ክፍፍል ሲገባ ትዳሩ ከመፍረሱ በፊት እናታቸውን ለበደላት በደል ማካካሻነት በገዛ ፈቃዳቸው በስጦታ የሰጡትን ቤት ባለቤቴ ባለጊዜ ስለሆነች በዘመዶቿና በብሔሯ ተመክታ እጄን ቆልምማ የወሰደችው ነው›› ማለታቸው ሐሰት መሆኑን ለዚህም ማስረጃ እንዳላቸው በመጠቆም የሰነድ ማረጋገጫ አቅርበዋል።
በሰነዱ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቃቂ ቃሊቲ ምድብ 2ኛ ፍርድ አፈጻጸም ችሎት በመዝገብ ቁጥር 24392 በቀን 02/10/2006 ዓ.ም አቶ አፈወርቅ የካቲት 17/2006 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት የዳግም ዳኝነት ይታይልኝ አቤቱታ ላይ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፤ አመልካች አቶ አፈወርቅ ባቀረቡት የዳግም ዳኝነት አቤቱታ ላይ የስጦታ ውሉን ለባለቤታቸው የፈጸሙት በልጆቻቸው ተጽኖ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፤ ይህም አቶ አፈወርቅ የባለቤቴ ዘመዶች ከህይወትህና ከነብረትህ አንዱን ምረጥ ብለውኝ ተገድጄ ነው በሚል ያቀረቡት አቤቱታ መሰረተቢስ መሆኑን ይናገራሉ።
በተጨማሪ እንደወይዘሮ ራሔል ገለፃ፤ እናታቸው አንድ ኩላሊታቸው እንደማይሰራ ሲነገራቸው ኩላሊታቸውን ለማስቀየር አባታቸው ገንዘብ ቢጠየቁ ‹‹ቤቱን በስጦታ ሰጥቼሻለሁ›› ሲሏቸው፤ እናታቸው ለህንጻ ማስጨረሻ በሚል በቤቱ ዋስትና ተበድረው ታክመዋል።
እናታቸው ህክምና በኋላ አባታቸው በየቦታው ንብረት በመበተናቸው ለእናታቸው መተዳደሪያ በሚል ለእናታቸው እርሳቸውና ወንድማቸው የህንጻ መሳሪያ ላይ እየሰሩ ባለሁለት ፎቅ ህንጻ ሰርተውላቸዋል።
ስለዚህ አባታቸው ‹‹ቤቱን የሰራሁት እኔ ነኝ።›› የሚለው ሃሰት ነው የሚሉት ወይዘሮ ራሄል፤ ቤቱ ግንባታው ተጠናቆ እርሳቸው 1998 ዓ.ም ትዳር ሲይዙ ቤቱን ለናሚቢያ ኤምባሲ እናታቸው አከራይተው ሌላ ገቢ ስለሌላቸው እየተጦሩበት መሆኑን ይናገራሉ ።
እናታቸው ለናሚቢያ ኤምባሲ አከራይተው እየኖሩ ሳለ፤ ለትንሿ ሊዲያ አፈወርቅ ‹‹እናትሽን ጉድ ላደርጋት ነው። ቤቱን አታገኘውም ›› ማለታቸውን ገልጸው፤ እናታቸው ‹‹የሰጠህኝን ሰጦታ በፍርድ ቤት አፅድቅልኝ›› ሲሉት ‹‹አላጽድቅልሽም ድሮም የሰጠሁሽ አፍሽን እንድትይዥ ነበር›› ሲሏቸው የተሰጣቸውን ስጦታ ወይዘሮ ብርዛፍ፤ ለእናታቸው ከስድስት እና ከሰባት ዓመት በኋላ፤ በመሀል ‹‹ለምን ሰጠሽ›› ብለው ሳይቃወሙ እያወቁ አብረው መኖራቸውን ይናገራሉ።
አሁንም ወይዘሮ ብርዛፍ የተሰጣቸውን ስጦታ ለእናታቸው ቢሰጡም ስሙ ግን አሁንም በእናታቸው ስም አለመዞሩን በማስታወስ፤ ምክንያቱም እናታቸው የኩላሊት ታማሚ ስለሆኑ እና አቶ አፈወርቅ ብር አልሰጥም በማለታቸው ስለከለከሏቸው ቤቱን አስይዘው 800 ሺህ ብር በመበደራቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
አባታቸውም ለህክምና ነው ብድር የጠየቅነው እኔ መሰክርላታለሁ ባለቤቴ ናት ብሎ ምስክሩ ላይ ፈረመ እንጂ በቤቱ ብድሩን የተበደረችው እናታችን ናት የሚሉት ወኪሏ፤ ሰጥቶኛል እኔ ለእናቴ ሰጥቻለሁ ሲሉ ግን በብድር ስለተያዘ ስም እንዳልዞረላቸውም ያስረዳሉ። በዚህ ሂደት ፍቺ ላይ ሲደረስ ከቤቱ ውጪ ያሉ ቃሊቲ እና ቦሌ የሚገኙት ንብረቶች የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጋራ መሆናቸውን ወስኗል።
ወደ ሰበር ሲቀጥልም ወይዘሮ ብርዛፍ ‹‹ይሄ እኮ የተሰጠኝ የከሳ ስጦታ ነው።›› ብለው ማስረጃ ቀርቦ ‹‹የሰጠኋት ወድጄና ፈቅጄ ነው›› የሚለውን ማሻር አለመቻላቸውን ምክንያቱም ዝሙት በመፈጸሙ የሰጠው ባይሆን እና ቤቱን የሰጠው ተገዶ ቢሆን ኖሮ ለሌላ ሰው ሲሰጥ በዛን ሰአት መቃወም ይችሉ እንደነበር ወይዘሮ ራሔል ያስረዳሉ።
ወይዘሮ ራሔል ወደ እናታቸው ሲተላለፍ ሁለት አመት አልፎ ሰባት አመት ቆይቷል በዛ ጊዜ ሳይጠይቁ ቆይተዋል ካሉ በኋላ፤ ለዛውም ‹‹በጋብቻ ላይ ዝሙት መፈጸም ያስጠይቅ እንደነበር፣ ተገልፆላቸው ነገር ግን ወደ ሶስተኛው ሰው ተላልፏል፣ ወደሶስተኛ ሰው እንዳለ ሆኖ ይህ ስመ- ሀብቱ የወይዘሮ ብርዛፍ ክንዴ ነው። ምክንያቱም በጋብቻ ላይ ዝሙት ፈጽሞ የሰጠው የካሳ ስጦታ በመሆኑ የወይዘሮ ብርዛፍ ነው ተብሎ ሀምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም የተወሰነ መሆኑን ያመለክታሉ።
ከተወሰነ በኋላ ፌዴሬሽን ምክርቤት ድረስ ጉዳዩ መድረሱን እና ‹‹የህግ ስህተት ተፈጽሞብኛል ህገመንግስት ትርጉም ይሰጠኝ›› ሲሉም ማመልከታቸውን ጠቁመው፤ 147 አባላት ባሉት ፓርላማ ታይቶ የህግ ግድፈት የለበትም፣ ብለው ውድቅ ማድረጋቸውን ወይዘሮ ራሄል ይናገራሉ።
ውድቅ ሲያደርጉባቸው አሁንም ስር ፍርድቤት ሄደውና ሌላ ማስረጃ አግኝተው፤ ሲል እንደ አዲስ ዳኝነት ጠየቀ የሚሉት ወይዘሮ ሒሩት፤ ‹‹ምንም ያልታየልህ ማስረጃ ስለሌለ አያስቀርብም›› ተብለው የተዘጋባቸው መሆኑን ይገልፃሉ። በእልህ ያላደረጉት ነገር እንደሌላ እናታቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ዕቃ ዘርፈዋል በሚል እና በተለያየ ሰበብ እያሳሰሩ፣ በማግስቱ እየተጣራ እንደሚፈቱም ይገልፃሉ።
‹‹ስርዓቱን በመጠቆም አቶ አፈወርቅ በህውሓት እናታችን ተጠቅማለች ማለቱ ፍጹም ስህተት ነው›› ካሉ በኋላ፤ እንደውም ፍርድቤት ሲሄዱ ‹‹እኔ ትግሬ ነኝ፤›› እያሉ ቋንቋውን ስለሚችሉ እየተናገሩ እየተጫወቱባቸው እንደነበር ያስረዳሉ።
እንደወይዘሮ ራሄል ገለፃ፤ እንደውም እናታቸው ውሳኔ ያገኙት ከለውጡ በኋላ ነው። የመጨረሻ ውሳኔ የተገኘው እና የተፈረደው በ2012 ነው። ከዛ በፊት ግን አቶ አፈወርቅ ጠቅላላ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር ሊያውሉት ነበር።
አቶ አፈወርቅ ‹‹ከቤት የተባረርኩት እራቁቴን ነው›› የሚሉት ውሸት መሆኑን እና እነ ወይዘሮ ራሄል የሚያውቁት ባለሀብት መሆናቸውን እንደሆነ ጠቅሰው፤ ኮከብ ህንፃ አጠገብ 24 ቀበሌ ፊትለፊት ባለሰባት ወይም ባለስምንት ህንፃ እየሰሩ እንደሆነ እንዲሁም ከአንድም ሁለት ፎርድ ፒካፕ መኪና ያላቸው መሆኑን እንዲሁም፤ ሚስታቸው እና ልጆቻቸውን የሚያኖሩት አንዴ አሜሪካ አንዴ ሌላ ሀገር እያሉ መሆኑን ገልፀው፤ አስመስለው ሲናገሩ እውነት ቢመስልም እናታቸው በውሸት የተወነጀሉ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
‹‹ሌላ ትዳር የመሰረተ ሰው ወቅታዊውን የፖለቲካ ትኩሳት ተጠቅሞ ይችን ጊዜ አገኘሁ ብሎ እናታችንን ለማሸማቀቅ ‹እንደመካላከያ ሰራዊት ከጀርባዬ የተወጋው ሰው ነኝ› ብሎ በጋዜጣ መውጣቱ እጅግ አሳዝኖናል።›› ወይዘሮ ራሔል ይላሉ።
‹‹ከ2007ዓ.ም ጀምሮ ከአባቴ ጋር ፍርድ ቤት የቀረብኩት እኔ ነኝ። ማስረጃው ሁሉ የሚለው ራሔል አፈወርቅ ነው። እሱ በጠበቃ እኔ ያለጠበቃ መመሪያ እና ህግን ይዤ እውነትን ተሞርክዤ አሸንፌያለሁ።›› የሚሉት ወይዘሮ ራሔል፤ ከዚያም ተወስኖ ካርታ ይውጣ ከተባለ በኋላ ቦታውን ለማጠር ሲባል ሁከት እየፈጠሩ እየተንገላቱ መሆኑን ይገልፃሉ።
አቶ አፈወርቅ በስማቸው የተመዘገበ ሽጉጥ ቤት ትተው የወጡ መሆኑን አስታውሰው፤ የወይዘሮ ራሔል አባት ሽጉጤን አልሰጥም ብለውኛል በማለት ያቀረቡት ውንጀላም ሐሰት መሆኑን በመግለፅ፤ እነርሱ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው በማመልከት ሽጉጡ ይወሰድልን የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም በፍርድ ቤት የተመዘገበ በመሆኑ፤ ፍርድ ቤት ደብዳቤ ካልፃፈ አንቀበልም መባላቸውን ተናግረዋል።
ሌላው ሰበር ቤቱም የባንክ እዳውም የእናታቸው ነው ብሎ ከወሰነ በኋላ ቤቱና የባንክ እዳው የጋራ ስለሆነ እዳውን እኩል ይክፈል ብላ ከሳለች ብለው ያነሱት ቅሬታ፤ ጠበቆቹን በገንዘብ እየገዙ ፍርድ ያስቀለብሱ ስለነበር በወይዘሮ ብርዛፍ በኩል የነበረውን ጠበቃ ካባረሩት በኋላ ጠበቃው ተደልሎ በራሱ ያስገባው ክስ እንጂ የእናታቸው ክስ አለመሆኑን ለፍርድ ቤት አስረድተው መዝገቡ መዘጋቱን በማስታወስ፤ ወይዘሮ ብርዛፍ ለፌዴራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት ን/ስ/ላ/ክ/ከ ምድብ 5ኛ ፍታብሄር አፈጻጸም ችሎት በመ/ቁጥር 69697 በ08/07/2005 ዓ.ም ባቀረብሁት ማመልከቻ የአሁን አመልካች እኔ አቶ አፈወርቅ የባንክ እዳው ግማሹ እንዲከፍሉ ቀደም ሲል በ28/04/2006 ዓ.ም ያቀረብሁትን ጥያቄ ያነሳሁ ወይም የተውኩ መሆኔን አረጋግጣለሁ ማለታቸውን ተከትሎ አቶ አፈወርቅ በአቤቱታቸው ባለ ሁለት ፎቅ ቤት በጋራ ሰርተናል በማለት ያቀረቡት ክርክር የሀሰት ከመሆኑም በላይ በዚህ መዝገብ ከተያዘው ጉዳይ ጋር ግንኙነት የሌለው ስለሆነ ውድቅ እንዲደረግልኝ በሚል አመልክተው የቀረበው ክስ ውድቅ እንደተደረገ ተናግረዋል።
‹‹ቤቱም የእናታችን ዕዳውም የእናታችን ነው በሚል ተቀብለን ከፍለናል።›› ካሉ በኋላ፤ ‹‹እናታችን ፍርድ ቤት ቆማ መናገር አትችልም። እኔ ነኝ የቆምኩላት። ለምን ጠበቃዎችን በገንዘብ እየገዛባት ጉዳዩ ስለሚሞት፤ የህግ መፅሃፍት ማንበብ ጀመርኩ። የህግ መፅሃፍ አንብቤ በፈጣሪ እርዳታ እስከ ሰበር የረታሁት እኔ ነኝ።›› ብለዋል።
በአጠቃላይ የተካሄደብን የስነልቦና ጉዳት ሰለባ አድርጎናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረድልን ማለት የነበረብን እኛ ነበርን ካሉ በኋላ፤ ብዙ ሰው ትግሬ ስለሆነ ተጠቃሚ አይደለም የሚሉት ወይዘሮ ራሔል፤ ውልና ማስረጃ ከፈረሙ ከሁለት ዓመት በኋላ የሰጠሁት ሽጉጥ ተደቅኖብኝ ማለታቸው ትክክል ካለመሆኑም ባሻገር፤ ተገድደው ቢሆን ኖሮ የሥጦታ ውሉ ሁለት ዓመት ከመሙላቱ በፊት በይርጋ ማንሳት ይችሉ እንደነበር ገልፀዋል።
ሌላኛዋ የአቶ አፈወርቅ ልጅ ወይዘሮ ሊዲያ አፈወርቅ እንደምትናገረው፤ በ1993 ዓ.ም አቶ አፈወርቅ በስጦታ የሰጠው ወዶ እና ፈቅዶ እንጂ በሽጉጥ ተገዶ አይደለም። ስጦታው በጋብቻ ላይ ዝሙት ስለፈፀመ ነው። ይህንን ፍርድ ቤቱም አረጋግጦታል። በማለት ገልፀዋል።
በወይዘሮ ብርዛፍ ክንዴ በኩል ከቀረበው የሰነድ ማስረጃዎች መካከል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መ/ቁጥር 85731 የተሰጠ ውሳኔ አንደኛው ነው። በሰነዱ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 19 የቤት ቁጥር 731 የሚታወቀው ቤት የባልና የሚስቱ የጋራ ሀብት ነው ወይስ አይደለም በሚል በተካሄደ ክርክር ላይ የተላለፈ ውሳኔ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ በሁለቱ ማለትም በአቶ አፈወርቅ ክብረት እና በወይዘሮ ብርዛፍ ክንዴ መካከል የነበረው ጋብቻ ሚያዚያ 12 ቀን 2002 ዓ.ም በፍርድ ቤት ፈርሷል።
ነገር ግን ትዳሩ ከመፍረሱ በፊት በሐምሌ 27 ቀን 1993 ዓ.ም በውል እና ማስረጃ በህግ ፊት በሚፀና የሥጦታ ውል አቶ አፈወርቅ በትዳር ዘመን እያሉ ከሌላ ሴት ልጅ በመውለዳቸው ምክንያት ለደረሰው በደል ካሳ ይሁን ብለው በመስጠታቸው ንብረቱ የጋራ መሆኑ ቀርቶ የወይዘሮ ብርዛፍ ሆኖ እንዲቀጥል ወደው እና ፈቅደው ያሰጡት ስጦታ መሆኑ ተቀምጧል።
በቀጣይ አቶ አፈወርቅ ክብረት በኒያላ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅታቸው ያቀረቡትን አቤቱታና በዚህ ጉዳይ ላይም የወ/ሮ ብርዛፍ ክንዴ የሰጡትን ምላሽ ይዘን እንቀርባለን፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 21/2013