የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ባሳለፋቸው ዓመታት አንግቦ የተነሳቸውን ዓላማዎች ለማሳካት የወቅቱን ተልዕኮ በትክክል ተገንዝቦ በብቃት ለመፈጸምና የህብረተሰባዊ ለውጥን ለማፋጠን፤ የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ልማት ተሳትፎ ብሎም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፤ እና ለሊግ አባላት የመታገያ መድረክ ሆኖ ለማገልገል ተጨባጭ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ መቆየቱን፣ ሰሞኑን በሀዋሳ በተካሄደው የሊጉ አራተኛ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የወጣው የአቋም መግለጫ ያሳያል፡፡
መግለጫው እንደሚያመለክተው፤ ሊጉ ለወጣቶች ምቹ የመታገያ መድረክ በመሆንና ፖለቲካዊ አቅማቸው እንዲጎለብት በማድረግ ለእናት ድርጅቱ ተኪ አመራር መፍለቂያም ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ይህ መልካም ተግባር እንዳለ ቢሆንም ውጤቱ ወጣቱ በሚፈልገውና ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ የደረሰ አይደለም፡፡ እኛም ለዘሬው የወጣቶች አምዳችን በጉባኤው ተሳታፊ ከነበሩ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ አባላትና አመራሮችን አነጋግረን በወጣትነት፣ ወጣትነትን ለፍሬ ከማብቃት አኳያ እንዲሁም በሊጉ ተግባርና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያጋሩትን ሀሳብ ይዘን ቀርበናል፡፡
ወጣት አብዱራህማን ክብረት፣ ከአዲስ አበባ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ የጉባኤው ተሳታፊ ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው፤ ወጣትነት ትልቅና ሁሉም ህልም እንዲሳካ መሰረት የሚጣልበት ነው፡፡ ወጣትነት ለሁለት ነገር የሚጠቅም እሳት ይዟል፤ አገር ሊገነባም፣ አገር ሊፈያፈርስም የሚችል፡፡ ምንም ማድረግ እንደማይሳንና ታላቅነት የሚታሰብበትም የእድሜ ዘመን ነው፡፡ ይሄን የተገነዘቡ የኢትዮጵያ ወጣቶችም የእሳትነት እድሜያቸውን የድህነት ተራራን ለመናድና አገር ለመገንባት ሲጠቀሙበት፤ በተቃራኒው የተሰለፉ ጥቂቶች ደግሞ አይጠፉም፡፡ ሆኖም ወጣትነት ሁሉን ነገር ማድረጊያ፤ ታሪክ ከማንበብ ባለፈ ታሪክ የሚሰራበት የእድሜ ደረጃ እንደመሆኑ በዋዛ ፈዛዛ ማለፍ ስለሌለበት እነዚህን ወጣቶች እንዴት አገር ወደመገንባት ማምጣት ይገባል የሚለው የሁሉም የቤት ስራ ይሆናል፡፡
‹‹ትልቁ ዓርአያዬ ዶክተር ዐብይ አህመድ ነው›› የሚለው የድሬዳዋ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ፊራንኦል ቡልቻ በበኩሉ፤ ወጣትነትን ‹‹ለለውጥም፣ ለነውጥም የምንጠቀምበት እድሜ ነው›› ሲል ይገልጸዋል፡፡ የአንድ ማህበረሰብ ምንነትና የአስተሳሰብ ደረጃም የሚታወቀው ወጣቱ በያዘው የአስተሳሰብ ደረጃ መሆኑን በመግለጽም፤ የወጣትነት ትርጉሙም፣ ስሜቱም ሆነ ምግባሩ በምላስ የቀረ ሳይሆን በልብም የዘለቀ ሊሆን እንደሚገባ ያስረዳል፡፡ ይህ ሲሆን ወጣቱ ጠንካራና ለለውጥ የሚተጋ እንደሚሆንም ይናገራል፡፡
እንደ ወጣት ፊራንኦል ገለጻ፤ ወጣቱ ለአገር ጠቃሚ የሚሆን ተግባር ለማከናወን አንድም መማርና ማወቅ፤ አንድም ባወቀው ልክ ለመስራት ተደራጅቶ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ አሁን ያለውን ለውጥ ጠቃሚ በሆነ መንገድ ለማስቀጠልም በዚህ አግባብ መጓዝ ይጠበቅበታል፡፡ ለውጡን አስቀጥሎም ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚችል መሆን አለበት፡፡ ሊጉም የድርጅት ክንፍ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ረገድ ወጣቱ ግንባር ቀደም የሚሆንበት ሂደት ላይ በስፋት መክሯል፡፡ ወጣቱ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ መስክ ግንባር ቀደም ሆኖ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥበትን መንገድ ለማስፈን የሚያስችል አቅጣጫም አስቀምጧል፡፡
ወጣቶች ያለፈ ታሪካቸውን በማየት የወደፊት ልጆቻቸው የሚኖሩባትን አገር የማቆየት ኃላፊነት እንዳለባቸው መገንዘብ አለባቸው፡፡ ለእዚህም አገሪቱ በሁሉም መስክ የእድገት ግስጋሴዋን የሚያስቀጥል አጀንዳ በመቅረጽ ረገድ የምታደርገውን ጥረት በዋና ተዋናይነት ማገዝ አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ ጉዟቸው የማህበረሰቡን እድገትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ተገንዝበው በማስተዋል ሊራመዱም ይገባል፡፡
ይሄን እውን ከማድረግ አኳያ ሊጉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አንድም ወጣቶችን አብቅቶ ለእናት ድርጅቱ ተተኪ አመራርን በሚያቀርብበት፣ አንድም በራሱ ውስጥ አቅም ያላቸው ተተኪ ወጣቶች እንዲገቡ ለማድረግ በሚቻልበት አግባብ ላይ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ረገድ አዳዲስ ወጣቶችን ማሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ለውጡን በግንባር ቀደምትነት ያመጡት እንደ ቄሮ፣ ፋኖና ሌሎችም ወጣቶችና አደረጃጀቶች ቢሆኑም፤ እነዚህን በመደገፍ ረገድ ሊጉ ክፍተት አለበት፡፡ እናም በሚኒስትሮች ደረጃ ያለው ሪፎርም ወደ ወጣቱ መውረድ ስላለበትም ሊጉ ሪፎርም ያስፈልገዋል፡፡
ወጣት አብዱራህማን በበኩሉ እንደሚለው፤ ሊጉ በ2001 ዓ.ም የተመሰረተው በኢህአዴግ ስር ሆኖ የወጣቶች የዴሞክራሲ ተሳትፎ ለማሳደግ ነበር፡፡ ዓላማውም የእናት ድርጅቱ ኢህአዴግ ተተኪ አመራሮች መፍለቂያ ሆኖ እንዲያገለግል እና ዘመኑን የሚመጥን የፖለቲካ ድርጅት እውን ለማድረግ እንዲያግዝ ነው፡፡ በተለይ ወቅቱን የሚመጥን የአስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም ማራመድ የሚችል ድርጅት መፍጠር ተገቢ በመሆኑ ይሄን እውን ለማድረግ እንደመሞከሪያ ሆኖ ተቋቁሟል፡፡ ከእነዚህ ዓላማዎች አንጻር ሲታይም ብዙ የተሰሩ ነገሮች ቢኖሩም፤ በርካታ የሚቀሩ ጉዳዮችም አሉት፡፡
ለምሳሌ፣ ለእናት ድርጅቱ ተተኪ አመራርን ከማፍራት አንጻር በቂ ነው ባይባልም በተወሰነ መልኩ የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡ በዚህም ከወጣት ሊጉ የወጡ አመራሮችን ማየት ተችሏል፡፡ እነዚህ አመራሮች ደግሞ በአስተሳሰብ ረገድም የዘረኝነት ፖለቲካ ከማራመድ የወጣ ሀሳብ ያላቸው ሲሆን፤ በዚሁ ልክ እየተቃኙ ያሉ ወጣቶች አሁንም አሉ፡፡ ይህንን ከተለመደው የተለየ ሀሳብ የሚያመጣ ሰው ከመበረታታት ይልቅ መኮርኮም ይታያል፡፡ በተለይ የግል ፍላጎት ያላቸው የእናት ድርጅት መሪዎች አብዛኞቹ ቦታቸው እንዲነጠቅም አይፈልጉም፡፡
እንደ ወጣት አብዱራህማን ገለጻ፤ የዚህ ሂደት መሸፈኛው ዴሞክራሲ ቢሆንም ውስጥ የተበላሹ አሰራሮች አሉት፡፡ ይሄን የማጋለጥ ተግባር ደግሞ የወጣቱ በተለይም በሊጉ ውስጥ የተሰባሰቡ ወጣቶች እንደመሆኑ ይሄን ከማድረግ አኳያ ጅምሮች ይኑሩ እንጂ በሂደት የተኮላሹና በዚህ ዘመን መታየት የሌለባቸው ነገሮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በእናት ፓርቲው ያሉ ግለሰቦችን የታገለ ተባሯል፤ በአንጻሩ እድሉ ቀንቷቸው ያሉና አሁን ለታየው ለውጥ የራሳቸውን ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረከቱና እያበረከቱ ያሉ ወጣቶች አሉ፡፡ ከዚህ አንጻር እናት ድርጅቱ ወደ ፓርቲነት እንዲመጣ አሁንም ያሉ ወጣቶች ከርዕዮተ ዓለምም ሆነ ፕሮግራም አንጻር ለኢትዮጵያ የሚጠቅሟት ነገሮች ምንድን ናቸው በሚለው ላይ እየሰሩ ነው፡፡
በተለይ ዓለም ወደ አንድ እየሄደች ባለችበት ወቅት በዘር ላይ ተንጠልጥሎ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ እያሉ ተከፋፍሎ መሄድ ይጠቅማል ወይ? የትስ ያደርሰናል የሚለውን ነገር ሲታይ የትም የሚያደርስ፣ ወደየትም የሚያሻግር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከውቂያኖስም ያለፈ ትልቅ አገር ሆና ሳለና በዚሁ ልክ ማሰብ ሲገባ ኩሬ ውስጥ ተደብቆ በኩሬ ልክ ማሰብ አይገባም፡፡ እናም ከዛ ኩሬ መውጣት አለብን የሚል ዓላማ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በአገር አንድነት እሳቤያቸውና በአገር ወዳድነታቸው ተምሳሌት በመሆናቸው በሁሉም ላይ መነቃቃትን ፈጥረዋል፡፡
ወጣቱ ደግሞ ለመልካምም ሆነ ለመጥፎ፣ ለልማትም ሆነ ለጥፋት አቅምም ሆነ ልምድ እንዳለው ከ2008 ጀምሮ የነበሩ ጥፋቶችን፣ እንዲሁም የለውጡን ጉዞ መመልከት በቂ ነው፡፡ እናም በውጭ ሆነው አገርን ለማሳደግ የሚያስችል ትልልቅ እውቀት ያላቸው በርካታ ወጣቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሰብሰብ ብለው በሊጉ ገብተው ልምድ በመለዋወጥና በመማማር መሄድ ከተቻለ ፓርቲ ወደ መመስረቱ ይደረሳል፡፡ ፓርቲውም ለአገር ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ተምሳሌት መሆን ይችላል፡፡
ወጣት ፊራንኦል በበኩሉ እንደሚለው፤ ድርጅቱ ህብረ ብሄራዊ መሆንና ቢያንስ ኢትዮጵያዊ ሽታ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ እንዲሆን የትኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት የሊጉ አባል ብቻ ሳይሆን አመራር ጭምር ሆኖ እንዲያገለግል የሚያስችለው ነው፡፡ ይህ ሲሆን የአመራርነት ሚና በብሔር ኮታ መሆኑ ቀርቶ በእውቀትና ለአገር ሁለንተናዊ ለውጥ ባለው አስተሳሰብና ትጋት እንዲሆን ያደርጋል፡፡ በዚህ የሚያኮርፍ ቢኖርም በተቻለ መጠን አስረድቶና አቅፎ መሄድ የሚገባ ሲሆን፤ ይሄን ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ ችግሮችን እያስታመሙና እያከሙ ጭምር ለተሻለ ውጤት መብቃት ይገባል፡፡ ወጣትነት ኃላፊነት ላይ ሲደርስ መኮፈስን ሳይሆን፤ በርካታ እድሉን ሳያገኙ ከእነ እውቀትና አማራጭ ሀሳቦቻቸው በየቦታው የቀሩ ወጣቶች መኖራቸውን ተመልክቶ ዝቅ ብሎ ህዝብን ማገልገልን መለማመድ የግድ ይለዋል፡፡
ሊጉም ወጣቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ መደገፍ ስላለበትም አቅጣጫ አስቀምጦ ይሰራል፡፡ እናት ድርጅቱም ከቀድሞው በተሻለና በበሰለ መንገድ ለለውጥ የተዘጋጀውን ሊግ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ሊጉ አሁን ከቀደመው የልማድ አሰራር ወጥቶ ራሱን በለውጥ ጎዳና ላይ ያስገባና እናት ድርጅቱንም ለማገዝ አየተጋ ነው፡፡
ወጣት አብዱራህማንም እንደሚገልጸው፤ በጉባኤው የነበረው የመድረክ ነጻነት ሊጉ ሀሳቦች በመሳሪያ አፈሙዝ ሳይሆን በሃሳብ መሸነፍ እንዳለባቸው እደሚያምን የሚያሳይ ሲሆን፤ ሀሳብን በጠመንጃ የማሸነፍ ሂደት ከዚህ በኋላ እንደማይሰራም ማረጋገጫ ነው፡፡ ወጣቱም እያለ ያለው ለእኛ የሚበጀን፣ የሚጠቅመንና የሚያሳድገንም ኢትዮጵያዊነት ነው፤ ከኢትዮጵያዊነትም አልፈን አፍሪካም ማቀፍ አለብን የሚል ነው፡፡ እየሰራ ያለውም በብሔር ያለ መገፋፋትን እናስወግድ፤ ስልጣንም በዘመድ ሳይሆን ለአገርና ህዝብ ተጠቃሚነት ባለው እውቀት፣ ራዕይ፣ ሀሳብና ለውጡን ከማስቀጠል ባለው ፍላጎት መሰረት እንዲሆን ነው፡፡
ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው ሂደት አቅም ያላቸውን ወጣቶች ወደ ድርጅቱ ከማካተት አኳያ ክፍተት መኖሩ በጉባኤው ተለይቷል፡፡ ይህ ደግሞ ነገ ወንበሬን ይነጥቀኛል ከሚል ስጋት እንጂ አገሬን ያሳድግልኛል የሚል አስተሳሰብ እየገነባን ያለመሆኑ ውጤት በመሆኑ አቅምና ፍላጎት ያለው የትኛውም ወጣት በሊጉ ውስጥ ገብቶ መስራትና መምራት እንዲችል በሩ ክፍት ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
ወንድወሰን ሽመልስ