ራስወርቅ ሙሉጌታ
ለሰው ልጅ ህይወት መቃናትና የእለት ከእለት እንቅስቃሴን ቀላል በማድረግ ረገድ ቴክኖሎጂ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በመረጃ ልውውጥ ረገድም ዛሬ አለም የደረሰችበት የቴክኖሎጂ ደረጃ በሰኮንዶች ውስጥ ለበርካታ ሰዎች በቀላሉ የፈለጉትን ማድረስ ተችሏል። እነዚህን መሰል የቴክኖሎጂ ጠቀሜታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ዛሬ ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ መረጃዎች ከጥቅማቸው ባልተናነሰ የተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶችን እያስከተሉ ይገኛል።
ለዛሬም ስሜት ቀስቃሰሽ ተንቀሳቃሸ የወሲብ ምስሎች በወጣቶች አዕምሮ ላይና በማህበራዊ ግንኙነታቸው ረገድ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ እንዲያብራሩልን በኢምፓከት ኢትዮጵያ የሳይኮሎጂካል አገልግሎቶችና የማኅበረሰብ ጤና ማማከር ማኅበር የሥነልቦና አማካሪና የማኅበረሰብ ጤና የሆኑትን ወይዘሮ ሙሉ መኮንን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከሉላዊነት እና ከበይነ መረብ ጋር በተያያዘ መልካም ነገሮችን የመጠቀማችንን ያህል ብዙ የሰውን ልጅ ተፈጥሮና ማንነትን የሚገዳዳሩ ክስተቶችን በቅርበት በምናገኛቸው ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት እያስተናገድን እንገኛለን። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የሆነው ሰዎች በቀላሉ ሊያገኙት የሚችሉትና ቀስበቀስ ተጠልፈው የሚወድቁበት ጉዳይ ተንቀሳቃሽ የወሲብ ምስሎችን የመመልከት ልምድ ወይን ሱስ ነው።
ኢትዮጵያ ብዙ ወጣት የሚኖርባት አገር የመሆኗን ያህል በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስራዎች አናሳ ናቸው። እንደ ማህበረሰብም ልክ እንደ ሰደድ እሳት እየጨመረ የመጣውን ተንቀሳቃሽ የወሲብ ምስል የማየት ሱስ በብዙ መልኩ የሚያደርሰውን ጉዳት በተመለከተ በቂ ግንዛቤ የተያዘ አይመስልም።
ለዚህም ማሳያው በተለያዩ አጋጣሚዎች ለጊዜውም ወይንም በቋሚነት ለልጆች የሚሰጡ እንደተንቀሳቃሽ ሰልክ፤ ላፕቶፕ እና ታብሌት ያሉ ቁሳቁሶችን ያለገደብና ክልከላ ወይም የወላጅ ጥበቃ በሌለበት ሁኔታ እደፈለጉ ሲጠቀሙ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። በዚህ ደግሞ የቱ ትክክል የቱ ስህተት እንደሆነ ያልተገነዘቡና የሚመለከቱት ነገር ከጊዜያዊ ደስታ ባለፈ በዘላቂ ህይወታቸው ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ ከግምት የማያስገቡ ልጆች፤ ወጣቶች እና አዋቂዎች ጭምር ውስብስብ ለሆኑ ችግሮች ተጋላጭ ለመሆን ይዳረጋሉ።
የዘርፉ ባለሙያዎች ባደረጓቸው ጥናትና ምርምሮች ወሲብ ቀስቃሽ ተንቀሳቃሸ ምስሎች አዕምሮን የሚጎዱ፣ ማህበራዊ ግንኙነቶችን የሚያስተጓጉሉ እንዲሁም ከአመንዝራነት (ሂያጅትነት)ና ከወሲብ ንግድ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። እነዚህን ነገሮች አብዝተው የሚከታተሉ ግለሰቦችም እውነተኛ የፍቅር ግንኙነታቸውን የሚያኮስስ ብሎም የሚገድል እንደሆነ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎችም ያመለክታሉ። የሰው ልጅ በትክክለኛ ህይወቱ ውስጥ እውነተኛ ፍቅር፣ እውነተኛ ሰውና ተፈጥሮን ያማከለ ሂደት እንዲኖረው ይፈልጋል።
ነገር ግን ሰዎች ለወሲብ ቀሰቃሽ ተንቀሳቃሸ ምስሎችና ስዕሎችን መከታተል ከጀመሩ በኋላ ግን የባልንጀሮቻቸውን ገጽታ፤ ችሎታና የፍቅር ማሳያዎችን ችላ በማለት ከእውነታው አለም ከራቀው ትይንት ጋር የራሳቸውን የወሲብ ህይወት ጋር ማወዳደር ይጀምራሉ።
በተጨማሪም ግለሰቦች ለወሲብ ቀስቃሽ ምስሎች ከተጋለጡ በኋላ በተደጋጋሚ በፍቅር አጋሮቻቸው ላይ እምብዛም አለመተማመንና ግንኙነቶቻቸው እንደተገደበ ሆኖ ሊሰማቸውም ይችላል። በዚህ ምክንያት የሰዎችን እውነተኛ የወሲብ ልምድ፣ ከራስ ወዳድነት የፀዳና ትርጉም ያለው ፍቅርን ለማቅረብ ያላቸው ችሎታ ላይ ተፅኖ እያሳደረ ይመጣል።
ከተፈጥሮ ሂደትም ጋር በተያያዘ ልክ እንደ አደንዛዥ ዕፅ እና ሌሎች ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮች ሁሉ ወሲብ ቀስቃሽ ምስሎች እንደ ዶፓሚን ያሉ የአንጎል ኬሚካሎችን በብዛት በማመንጨት አንጎልን ይሞላሉ። ከጊዜ በኋላ አንጎል በቋሚ ኬሚካሎች ከመጠን በላይ በመጫኑ ከፍተኛ የወሲብ ቀስቃሽ ምስሎችን የማየት ፍላጎት ውስጥ በመግባት ጥገኛ ለመሆን ይገደዳል።
በውጤቱም መጀመሪያ ላይ የተመለከቱት የወሲብ ምስል አስደሳችነቱ እየቀነሰ ካዩት የተለየ የበለጠ የወሲብ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን የማየት ፍላጎታቸው እየናረ ይመጣል። ይህ ሱስ ውስጥ ላሉ ሰዎች የወሲብ ፊልሞችን ሳይመለከቱ ለተወሰነ ጊዜ በሄዱ ቁጥር እንዲሰናከሉ ወይም እንዲረበሹና ጸባያቸው እንዲቀያየር እያደረጋቸው ይመጣል።
በተፈጥሮ አንጎል አስደንጋጭ ወይም አስገራሚ ነገሮችን ሲመለከት ኬሚካሎችን ያመነጫል። በዚህም ተደጋጋሚ የሆነ ተንቀሳቃሸ የወሲብ ምስሎችን የሚመለከቱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከፍ ያለ በመፈለግ ውስጥ እራሳቸውን የሚያገኙት።
እ.ኤ.አ 2012 አንድ ሺህ አምስት መቶ የሚሆኑ የወሲብ ፊልሞችን የሚመለከቱ ወንዶች ላይ በተደረገ ጥናት ሀምሳ ስድስት በመቶ የሚሆኑት የወሲብ ፍላጎታቸው ‹‹በጣም የከፋ ወይም የተሳሳተ›› ሆኖ ተገኝቷል። ተደጋጋሚ የወሲብ ፊልሞችን የሚመለከቱ አንጎላቸው ቀድሞ ካዩዋቸው የወሲብ ድርጊቶች ጋር በፍጥነት ስለሚላመድ ስሜታቸውን ለመቀስቀስ ከፍ ወዳሉት መሄዳቸው የተለመደ ነው።
በሰው አንጎል ውስጥ “የሽልማት መንገድ ”(Reward pathway) የሚባል ሂደት አለ። የእዚህ ሂደት ተግባር ጥሩ ስሜት የሚሰጠንን አንድ ነገር ስናደርግ የደስታ ኬሚካሎችን በመልቀቅ መሸለም ነው። በዚህም ድግግሞሽ ሰዎች ለጥገኝነትና ሱሰኝነት ለመጋለጥ ይበቃሉ። በአንጎል ውስጥም የሚመነጨው የኬሚካል ብዛት የወሲብ ምስል ተመልካቹን የኬሚካል ልቀትን በመጨመርና በመቆጣጠር የወሲብ ባህሪው ችግር ውስጥ እንዲገባ በሚያደርግ አዲስ የአንጎል ጎዳና ይመራዋል።
በተጨማሪ ሰዎች በእንደዚህ አይነት ምናባዊ ዓለም ውስጥ በቆዩ ቁጥር ከነባራዊው ሁኔታና ከእውነታው ተቃራኒ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። በዚህም የወሲብ ቀስቃሽ ተንቀሳቃሽ ምስል ተጠቃሚዎች ከተፈጥሯዊ ሰው ጋር በአካል ከመሆን ይልቅ ብቻቸውን በኮምፒዩተር ፊት በመቀመጥ እንዲነቃቁ በማድረግ ተፈጥሯዊ የሆነውን ግንኙነት የመፈፀም ችሎታቸውን ይገድላሉ።
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ተጽዕኖዎች የሚያደርሱት ጉዳት በግለሰብ ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ችግሩ ከትዳር አጋርም ጋር የማያስማማ በመሆኑ ለቤተሰብ መፍረስና ተከትለው ለሚመጡ ቀውሶች ይዳርጋል። በተጨማሪም በርካታ ወጣቶችን ካለ እድሜያቸውና ካለበቂ ዝግጅት ጾታዊ ግንኙነት እንዲጀምሩ በማድረግ ለተለያዩ የጤና ችግሮችና ማህበራዊ ቀውስ እንዲዳረጉ በር ይከፍታል።
በመሆኑም ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ የሚያደርሰውን ማህበራዊ ቀውስ በመገንዘብ በሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ፤ እንዲሁም ወላጆች ልጆቻቸውን በቅርበት በመቆጣጠር ሊፈጠሩ የሚችሉትን የትዳር መፍረስ የቤተሰብ መበተንና ማህበራዊ ቀውስ መታደግ ይገባል ሲሉ ባለሙያዋ ወይዘሮ ሙሉ ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20/2013