የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በግብጽ ካይሮ ከፕሬዚዳንት አል ሲሲ ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ዶቼ ቬሌ ዘግቧል፡፡ ማክሮን በግብጽ የሚፈጸመው የሰብኣዊ መብት ጥሰት የሀገሪቱን ገጽታ እንዳያበላሽ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ለግብጹ አቻቸው አብዱል ፈታ ኤልሲሲ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች ባለፈው ሰኞ በካይሮ ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ማክሮን በሰብዓዊ መብትና ነጻነት ላይ ሀገራቸው ግብጽን ልትረዳት እንደምትፈልግ ገልጸውላቸዋል፡፡
ኤል ሲሲ ወደ ስልጣን የመጡት በግብጽ በተደረገው የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አሸናፊ የነበሩትን ከሙስሊም ወንድማማቾች ህብረት ፓርቲ የመጡት ሞሀመድ ሙርሲ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ እ.አ.አ በ2014 ነው፡፡ ከዚህን ግዜ ጀምሮ ኤል ሲሲ በሙርሲ ደጋፊዎችና ጸረ መንግሥት አመለካከት አላቸው በሚሏቸው ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ ይነገራል፡፡ በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን አስረዋል፡፡ እንደውም ግብጻውያን ፈላጭ ቆራጭ ነው በሚል ከስምንት ዓመታት በፊት በህዝባዊ ተቃውሞ ያስወገዱት የሆስኒ ሙባረክ መንግሥት በሚዲያዎች ላይ ያደርግ የነበረው ቁጥጥርና አፈና አሁን በኤል ሲሲ አስተዳደርም ሁለትና ሶስት እጥፍ በመጨመር በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የሚዲያ ነጻነት አፈና እንዳለ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የመብት ተሟጋቾች መግለጻቸውን አልጀዚራ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ .
ማክሮን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ትኩረት ያደረጉት ግብጽ የተረጋጋ ሰላሟን ለማረጋገጥ የህግ የበላይነትንና የግለሰቦችን ክብርና መብት መጠበቅ እንደሚገባት ነው፡፡ ሀገርን የተረጋጋ ማድረግ ማለት ራስን ከተጠያቂነት ማግለል አይደለም ያሉት ማክሮን እ.አ.አ ከ2017 ጀምሮ በግብጽ እየታየ ያለው አለመረጋጋት በሀገሪቱ ላይ አሉታዊ ገጽታ እንደፈጠረ አስታውሰዋል፡፡ ጋዜጠኞች፣ ሞጋቾችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በእስር ቤት ውስጥ መገኘታቸውም የዚሁ ማሳያ እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ግብጽ ሰብዓዊ መብት የማይከበርባት ሀገር ተብላ መጠቋቆሚያ እንዳትሆን ማስተካከያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልጋት መክረዋል፡፡
ኤል ሲሲ የማክሮንን ምክር አዘል ንግግር አስመልክተው ለሮይተርስ እንደተናገሩት ስለዜጎች መብት መከበር ስናወራ ስለቀጠናው ቀውስና ከአሸባሪዎች ጋር የገባንበት ፍጥጫ ከግምት ማስገባት ግድ ይላል፡፡ ግብጽ ከንትርክና ካለመግባባት የምታተርፈው አንድም ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ለመጪው ትውልድ የሚሆን ነገር ማቆየት የሚቻለው እያንዳንዱ ዜጋ ከመንግሥት ጋር ያለውን እሰጥ አገባ ትቶ ሥራን መሥራት ሲችል ነው ብለዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት ኢኮኖሚያዊና ልማታዊ ስምምነቶችን ያደረጉ ሲሆን በተለይም ፈረንሳይ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማገዝ ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች፡፡ ማክሮን የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ተከትሎ ፈረንሳይ ለግብጽ በምታደርገው የጦር መሳሪያ አቅርቦት የግብጽ ዜጎች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ ተብለው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ማክሮን መልስ ሲሰጡ ፈረንሳይ ለግብጽ የምታቀርብላት የጦር መሳሪያ ዓላማው ለወታደራዊ አገልግሎት እንዲውል እንጂ ህዝብ እንዲጠቃበት አይደለም ብለዋል፡፡ ማክሮን አያይዘውም ፈረንሳይ ለግብጽ በርከት ያለ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ተስማምታለች መባሉን አስተባብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
ኢያሱ መሰለ