አዲስ አበባ ፡- የንግዱ ማህበረሰብ ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ትናንት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ
እንዳሉት፤ በሀገሪቱ እዚህም እዛም እየተከሰቱ ባሉ ችግሮች ምክንያት የተስተጓጎሉ የልማት ስራዎች እንዲያንሰራሩ የንግዱ ማኅበረሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መስራት አለበት፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ በስጋት ምክንያት ገንዘቡን ባንክ አስቀምጦ አነስተኛ ገንዘብ ማንቀሳቀሱን በመተው እንደቀድሞ በሙሉ አቅሙ ወደ ገበያው በመግባት ሊሰራ ይገባል፡፡ ይህም ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት የበኩሉን እንዲወጣ ያስችለዋል፡፡
በሀገሪቱ ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥና የተረጋጋ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና አጠቃላይ የማይክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲፈጠርም የንግዱ ማኅበረሰብ ጠንክሮ በመስራት ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በተጨማሪም የንግዱ ማኅበረሰብ ከኮንትሮባንድ ንግድ፣ ከህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና የጦር መሳሪያ ንግድ ራሱን በማቀብና መረጃዎች ሲኖሩት ለሚመለከተው አካል በመጠቆም ህጋዊ አሰራሮችን ብቻ እንዲከተልም አሳስበዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ በሰላም እጦት ምክንያት ተጎጂ ከሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የንግዱ ኅብረተሰብ አንዱ መሆኑ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተስተውሏል፡፡ ይህም ሰላም ምን ያህል ለንግድና ኢንቨስትመንት መሰረትና እስትንፋስ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ንግድና ኢንቨስትመንት የሥራ ዕድል በመፍጠርና ገቢ በማስገኘት የልማት እንቅስቃሴ ዋነኛ ምክንያት በመሆን ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ኅብረተሰቡ ወዳልተፈለገ ተግባር እንዳይገባ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ፡፡
ፕሬዚዳንቷ ‹‹ጠንካራ ንግድና ኢንቨስትመንት በራሱ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት፣ ለጋራ ሰላም፣ ለወንድማማችነትና ለመተባበር የበኩሉን አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ የንግዱ ኅብረተሰብና ምክር ቤታችን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ አሳስባለሁ›› ብለዋል ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
የትናየት ፈሩ