አስናቀ ፀጋዬ
በተለያዩ የግልና የመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከአምስት አመታት በላይ በመምህርነት አገልግለዋል። በህዝብ ትምህርት ቤቶችም በሙያቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጥተዋል። መምህርነትን ተቀጥረው ቢሰሩም የራሳቸውን ትምህርት ቤት መክፈት የሁልጊዜም ምኞታቸው ነበር።
ይህ ምኞታቸው ሰምሮ ዛሬ የራሳቸውን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማቋቋም በቅተዋል- የሰበታ ቅዱስ ገብርኤል ሙአለ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሊዲያ ኃይሉ።
ወይዘሮ ሊዲያ ኃይሉ ትውልድና እድገታቸው በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሰበታ በሚገኘው ሙሉጌታ ገድሌ ትምህርት ቤት ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሰበታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም የቀድሞ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በመግባት በአማርኛና እንግሊዝኛ ትምህርታቸውን ለሶስት አመታት ተከታትለው በ1996 ዓ.ም በዲፕሎማ ተመርቀዋል።
ቀጥለውም ከዚሁ ኮሌጅ በአማርኛና እንግሊዘኛ ኢዱኬሽን በ2004 ዓ.ም ዲግሪ አግኝተዋል። በመቀጠልም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሊደርሽፕና ክሬቲቭ ማኔጅመንት ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ይዘዋል።
በተማሩት የመምህርነት ሙያ አዲስ አበባ በሚገኝ ብሪሊያንስ በተሰኘ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ ተቀጥረው ስራን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት ወይዘሮ ሊዲያ በዚህ ትምህርት ቤት አንድ ዓመት የሰሩ ሲሆን ሳር ቤት በሚገኝው ስኩል ኦፍ ኔሽን በተሰኘ ትምህርት ቤት ደግሞ ሁለት ዓመት አገልግለዋል።
በመቀጠልም ጃን ሜዳ አካባቢ በሚገኘው አዲስ ብርሃን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለት አመት እንዲሁም በህብረት ፍሬ ትምህርት ቤት ለአንድ ዓመት በመምህርነት ሰርተዋል። እንዲሁም በአጼ ናኦድ የህዝብ ትምህርት ቤት በበጎ ፍቃደኝነት በሙያቸው አገልግለዋል።
በሙያቸው በተለይ ደግም በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ በመስራት ሰፊ ልምድ ያዳበሩት ወይዘሮ ሊዲያ የራሳቸውን ትምህርት ቤት ለማቋቋም ተገፋፉ። በግል ትምህርት ቤቶች በነበራቸው ቆይታ የተመለከቷቸውን አሰራሮችና ልምዶች እንደግብአት በመውሰድም የባለቤታቸው ድጋፍ ታክሎበት በ2001 ዓ.ም በሰበታ ከተማ በተከራዩት ቤት ሙአለ ህፃናት ከእህታቸው ጋር በመሆን በ80 ሺ ብር ካፒታል ከፈቱ።
ትምህርት ቤቱን ሲከፍቱ ሙሉ አቅም ያልነበራቸው ወይዘሮ ሊዲያ እርሳቸውና እህታቸው እንደ መምህር፣ ፀሃፊና አስተዳደር በመሆን ስራቸውን ጀመሩ። ለትምህርት ግብአት ማሟያ የሚሆን ገንዘብ በመሃል ስላጠራቸውም በ2003 ዓ.ም አዋጭ የተሰኘውን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር በመቀላቀል 20 ሺ ብር ተበደሩ።
በዚሁ ብር ብረቶችን በመግዛትና ባለሙያ በመቅጠር የተማሪ ወንበሮችን፣ የቢሮ እቃዎችንና ሌሎች ለትምህርት ግብአት የሚውሉ መሳሪያዎችን አሟሉ።
ከአዋጭ የተበደሩትን ብድር ወዲያውኑ በመክፈልም ተጨማሪ 20 ሺ ብር ብድር በመውሰድና ተጨማሪ ግብአት በማሟላት ትምህርት ቤታቸውን ከሙአለ ህፃናት ወደ አራተኛ ክፍል ደረጃውን አሳደጉ። ከዚሁ ማህበር እንደገና 80 ሺ ብር ብድር በመወሰድም ለመኖሪያ የሚሆን ቦታ አለም ገና ከተማ ውስጥ በመግዛት ከኪራይ ቤት ኑሮ ተላቀቁ።
እንደገና ከአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር በእርሳቸውና በባለቤታቸው ስም 400 ሺ ብር ተበድረው ከሙአለ ህፃናት እስከ አራተኛ ክፍል ያስተምር የነበረውን ትምህርት ቤታቸውን ተጨማሪ ህንፃ በመከራየት እስከ ስምንተኛ ክፍል ከፍ አደረጉ።
እንዲህ እንዲህ እያለ እያደገ የመጣው የወይዘሮ ሊዲያ የሰበታ ቅዱስ ገብርኤል ሙአለ ህፃናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአሁኑ ወቅት ባጠቃላይ ለሙአለ ህፃናቱና ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ለማስተማሪያነት በኪራይ ለሚጠቀመው ህንፃ 98 ሺ ብር በወር ይከፍላል። ሃያ አምስት ለሚሆኑ መምህራን የስራ እድል የፈጠሩ ሲሆን አጠቃላይ ካፒታሉም ሶስት ሚሊዮን ብር ተጠግቷል።
ቀጥሮ ለሚያሰሯቸው መምህራንም በትንሹ 3ሺ ከፍ ሲል ደግሞ ከ5 እስከ 6 ሺ ወርሃዊ ደመወዝ ይከፍላል። ተማሪዎች የሚከፍሉት ክፍያ ከአዲስ አበባ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ቢሆንም ሙአለ ህፃናት ላይ ያሉ 500 ብር በወር ሲከፍሉ ከአንደኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ደግሞ 550 ብር ይከፍላሉ።
‹‹እንደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ሁሉ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት የኔም ትምህርት ቤት በእጅጉ ተፈትኗል›› የሚሉት ወይዘሮ ሊዲያ፤ በተለይ ወረርሽኙ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ ትምህርት መቋረጡን ተከትሎ ለህንፃ ኪራይ ለመክፈል በእጅጉ ተቸግረው እንደነበር ያስታውሳሉ።
በወረርሽኙ ወቅት ሂሳብ ያለባቸውን ተማሪዎች ለማስከፈልም ከፍተኛ ውጣ ውረድ እንደነበርና ከተማሪ ወላጅ የመክፈል ችግርና ትምህርት ቤቱ በኪራይ የሚሰራ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በወረርሽኙ ወቅት ከባድ ፈተና ገጥሟቸው እንደነበርም ያስረዳሉ።
በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ውጣውረዱን ተቋቁመው ማለፍ ያቃታቸው በርካታ ትምህርት ቤቶች የመዘጋት እጣ ፋንታ እንደደረሰባቸውም ወይዘሮ ሊዲያ ጠቅሰው፤ ይሁንና ጉዳዩን የተረዱ የተማሪ ወላጆች እገዛ ታክሎበትና እርሳቸውም ከትምህርት ቤቱ አስተዳደርና ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ችግሩን ተቋቁመው እንዳለፉ ይናገራሉ። በራሳቸው ለቀው ከሄዱት በስተቀር አንድም መምህር እንዳልቀነሱም ይጠቅሳሉ።
ያለባቸውን ውዝፍ ክፍያ ከፍለው ልጆቻውን ወደ ትምህርት ቤት የላኩ ወላጆች እንዳሉ ሁሉ ያለባቸውን ሂሳብ ያልከፈሉም እንዳሉ የሚናገሩት ወይዘሮ ሊዲያ፤ ይህም ችግር አሁንም እንደቀጠለና ትምህርት ቤቱ የገንዘብ እጥረት አጋጥሞት እንደነበር ይጠቁማሉ።
ችግሩን በመገንዘብ ግዴታቸውን ለተወጡና ክፍያ ለፈፀሙ ወላጆች የተለያዩ ትምህርት ኖቶችንና መልመጃዎችን ለልጆቻቸው በማዘጋጀትና በቴሌግራምና በሌሎች ማህበራዊ ትስስር ገፆች እንዲደርሳቸው በማድረግ በግዜው ያጋጠመውን ችግር ለማለፍ ጥረት ማድረጋቸውንም ይገልፃሉ። መጽሐፎችን ለተማሪዎች ቀድሞ በመሸጥ የመምህራን ደመወዝ ለመሸፈን መቻሉንም ያስረዳሉ።
መንግስት ጥንቃቄ ታክሎበት ትምህርት እንዲቀጥል ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎም በየአካባቢው በራሪ ወረቀቶችን በመበተንና ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ጥረት ማድረጋቸውንም ይናገራሉ። ከትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና ሰበታ ከሚገኘው የግል ትምህርት ቤቶች ማህበር ጋር በመሆን ለገጠማቸው ችግር መፍትሄ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውንም ያስረዳሉ።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ቅድሚያ ጤናን ታሳቢ ባደረገ መልኩና የተማሪ ወላጆችንም ችግር በመረዳት ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ወይዘሮ ሊዲያ ይገልፃሉ።
በክፍሉ ውስጥ በአንድ ወንበር ላይ አንድ ተማሪ እንዲቀመጥ በማድረግ፣ መኝታ ክፍሎችን ወደ መማሪያ ክፍሎች በመቀየር፣ ተጨማሪ ወንበሮችን በማስገባትና ተማሪዎችም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ በማድረግ ትምህርቱ በግማሽ ቀን እየተሰጠ እንደሚገኝም ያብራራሉ።
ኮሮናን ጨምሮ በበርካታ ውጣውረዶች ውስጥ በማለፍ ትምህርት ቤቱ እዚህ መድረሱን የሚናገሩት ወይዘሮ ሊዲያ፤ ትምህርት ቤታቸው ትምህርትን ለተማሪዎች እየሰጠ ያለው በተከራየው ህንፃ በመሆኑ በቀጣይ የከተማ አስተዳደሩ ህንፃ መስሪያ ቦታ ከሊዝ ነፃ የሚያመቻችለት ከሆነ የራሳቸውን ህንፃ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸውና ለኪራይ ሲያወጡ የነበረውን ገንዘብ ለትምህርት ማስፋፊያ ማዋል እንደሚፈልጉም ይገልፃሉ።
ትምህርቱን ባሰፉ ቁጥር ለመምህራን ተጨማሪ የስራ እድል መፍጠር እንደሚፈልጉም ይጠቁማሉ። የተማረ የሰው ሃብት በማፍራት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ትውልድ የማበርከት ፍላጎት እንዳላቸውና ትምህርት ቤቱን ለማስቀጠል ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ይናገራሉ።
በተመሳሳይ በዚሁ የትምህርት ዘርፍ ልክ እንደርሳቸው መስዋእትነት ከፍለውና ሰርተው መለወጥ ለሚፈልጉ ሰዎች በተለይ እንደወጣት በቅድሚያ አካባቢያቸውን ማወቅና የህብረተሰቡን ፍላጎትና አቅም መረዳት እንዳለባቸው መልእክት ያስተላልፋሉ። ትልቁን ነገር ሳያስቡ ባላቸው እውቀትና አቅም ከትንሽ ካፒታል ጀምረው ትምህርትን ለህብረተሰቡ ማድረስ እንደሚችሉና ቀስ በቀስ እያሳደጉ መምጣት እንደሚችሉም ይጠቁማሉ።
የፋይናንስ ችግር ሲገጥማቸውም አዋጭን ከመሰሉ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ገንዘብ በመበደርና ለሚፈለገው አላማ በማዋል ተቋማቸውን ማሳደግ እንደሚችሉም ይጠቅሳሉ። ሁሌም ቢሆን ከመንግስት ብቻ መፍትሄ መጠበቅ እንደሌለባቸውና አንዳንዴም ራሳቸውን የችግራቸው የመፍትሄ አካል ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይመክራሉ።
መፍትሄ ሁሌም ከችግር የሚመጣ ከመሆኑ አኳያም ችግሮችን እንደመልካም አጋጣሚ በማየት የተሻለ ነገር ለማግኘት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
በተለይ ደግሞ እንደእርሳቸው ያሉ ወጣቶች ወደ ትምህርት ዘርፍ ገብተው መስራት ከፈለጉ የትምህርት ተቋማትን አሰራር በሚገባ ማወቅና ገንዘብ የሚያገኙበትን መንገድ ከሌሎች ልምድ መውሰድ እንዳለባቸው ይጠቁማሉ። በስራ መውደቅም ሆነ መነሳት ያለ በመሆኑ ይህን አምነው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውና አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባቸው ያስረዳሉ።
‹‹እዚህ ለመድረሴ የራሴ ጥረት እንዳለ ሆኖ ከአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ያገኘሁት ብድር የራሱን አስተዋፅኦ አብርክቶልኛል›› የሚሉት ወይዘሮ ሊዲያ ሌሎችም ገንዘብ ሲበደሩ ለምን ዓላማ መሆኑንና ብድሩንም ሲወስዱ በምን መልኩ መክፈል እንደሚችሉ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ። በተበደሩት ገንዘብም የሚያዋጣቸውን የስራ መስክ መምረጥ፣ አካባቢያቸውን ማየት፣ የገበያ ጥናት ማድረግና ገንዘባቸውን በመረጡት ስራ ላይ በአግባቡ ማዋል አንዳለባቸው ይጠቁማሉ። ገንዘቡን የሚበደሩበትን አላማ በሚገባ ከተረዱ በእርግጠኝነት ብድራቸውን ከፍለው ማጠናቀቅ እንደሚችሉም ይጠቅሳሉ።
‹‹ከብድሩ በተጓዳኝ እዚህ ደረጃ ላይ ልደርስ የቻልኩት ስራዬንም በማክበሬ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ሊዲያ ማንም ሰው ብቻውን የትም እንደማይደርስና ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ አካባቢ፣ መምህራኖችና ሌሎችም ለእርሳቸው ህይወት መሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍል ለምሳሌ ተማሪዎችን፣ መምህራኖችን፣ ፅዳትና የአስተዳደር ሰራተኞችንና ወላጆችን ማክበራቸውም የተሻለ ስራ እንዲሰሩ እንዳገዛቸውም ያስረዳሉ።
ስኬት በገንዘብ ብቻ እንደማይለካም ወይዘሮ ሊዲያ ተናግረው፤ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ለመስራት መሞከራቸውና ሞክረው እንኳን ባይሳካላቸው ይህ አንዱ የስኬት መንገድ መሆኑንም ይጠቁማሉ። ሆኖም የትምህርት ሴክተሩ የበርካታ ሰዎች ሃላፊነት መሸከምንና በርካታ ሰዎችም ዘርፉ ከመኖራቸው አኳያ እንደሌሎቹ ዘርፎች ቀላል እንዳልሆነም ይጠቅሳሉ።
ወይዘሮ ሊዲያ በመምህርነት ተቀጥረው ከመስራት ጀምረው የራሳቸውን ትምህርት ቤት በማቋቋም ህይወታቸውን ከማሻሻል በዘለለ የአካባቢያቸውን ማህረሰብም የእውቀት ባለቤት ለማድረግ ያደረጉትን ጥረት እያደነቅን በተለይ ለአካባቢው ማህበረሰብ እያደረጉ ያሉትን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት የከተማ አስተዳደሩ ያለባቸውን የቦታ ችግር ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ እናምናለን።
ወይዘሮ ሊዲያ ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ናቸውና የእርሳቸውንና የሌሎችን ስኬታማ ሰዎች አርአያነት መከተል ይበጃል። ከመቀጠር ወደ ሰራተኛ መቅጠር የተሸጋገሩ ጠንካራ ሴት በመሆናቸው ነገ ደግሞ በተሻለ ደረጃ እንጠብቃቸዋለን። ይሄም እንዲሳካላቸው እንመኛለን። ሰላም!!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013