ራስወርቅ ሙሉጌታ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ስርጭቱን ለመከላከል መንግሥት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል መደበኛውን የትምህርት እንቅስቃሴ ማቋረጥ አንዱ ነበር። ሆኖም የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሊከታተሉባቸው የሚችሉ ሁኔታዎችን ሲያመቻች ቆይቷል። በቅርቡም ተማሪዎች በፈረቃ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
ይህም ሆኖ በአብዛኛዎቹ የግልም ሆነ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለማስጀመር እየተከናወኑ ያሉት ዝግጅቶች ኮሮናን ለመከላከል በሚያስችሉ የጽዳት ሥራዎች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ናቸው። ለትምህርት መቋረጡም ሆነ አሁን ባለበት ሁኔታ ለመጀመሩ ምክንያቱ ወረርሽኙ ስለሆነ፣ ኮሮናን ለመከላከል የሚደረገው ጥንቃቄ ተገቢ መሆኑ አያጠራጥርም። ሆኖም ከዛው ባልተናነሰ ለተማሪዎች የሥነ ልቦና ዝግጅትም ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ይነገራል።
ወይዘሮ ሙሉ መኮንን በኢምፓክት ኢትዮጵያ የሳይኮሎጂካል አገልግሎቶችና የማኅበረሰብ ጤና ማማከር ማኅበር የሥነልቦና አማካሪና የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያ ናቸው። እርሳቸው እንደሚያብራሩት በ2020 በዓለም ላይ በመቶ ስልሳ አንድ አገራት የነበሩ ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን በላይ ተማሪዎች በኮሮና ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ተለያይተዋል።
ይህም በኢትዮጵያም ጭምር አጠቃላይ የነበረው የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ጫና ፈጥሮና የትምህርት ሥርዓቱን አዛብቶት ቆይቷል። በትምህርት መቋረጥ የተነሳም ልጆች በትምህርት ቤት ቆይታቸው ሊያገኙት የሚገባቸውን እውቀትና ክህሎት ከማጣት ባልተናነሰ በሥነ ልቦናቸውም ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ አለ።
ትምህርት ቤቶች ለልጆች ከመደበኛ እውቀት መገብያነት ባሻገር ማኅበራዊ ከህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ነው። ልጆች በትምህርት ቤት ቆይታቸው የሚያገናኟቸው ጓደኞች ከተለያየ ማኅበረሰብና ቤተሰብ የሚውጣጡ በመሆናቸው፣ ከሰው ጋር እንዴት መግባባት እንዳለባቸው፤ ሰውን ማክበርን፤ በመዋዋስ፣ በመረዳዳትና በመተዛዘን ለሰው ቅድሚያ መስጠትን እንዲሁም ሰዎችን እንዴት መምራት እንዳለባቸው በጨዋታ ጭምር ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ነው።
እንዲህ አይነት ክህሎቶችን አንዳንዶች ከሰፊ ቤተሰብ ሲወጡ የሚያገኙት ቢሆንም አብዛኞቹ ልጆች በተለይ ከእድሜ እኩዮቻቸው ይህን የሚቀስሙት በትምህርት ቤት ቆይታ ነው። ይህም በቀጣይ ሕይወታቸው ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት ጤነኛ እንዲሆን ሲያግዝ በተጓዳኝ ጥሩ ማኅበረሰባዊ ግንኙነት ያላቸው ልጆች አእምሯቸውም ጤነኛ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። በአንጻሩ ልጆች የተገለሉ፣ ከሰው የማይገናኙና ብቸኛ ከሆኑ ውጤቱ በተቃራኒው ይሆናል።
ትምህርት ቤት መዋል የለመዱ ልጆች ቤት በመዋላቸው ሁለንተናዊ እድገታቸው ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል። ሁለንተናዊ ሲባል ልጆች ከአካላዊ እድገት ባለፈ በአእምሮ መጎልበት እና በስሜት መዳበር ስለሚጠበቅባቸው ነው። ልጆች ማግኘት ያለባቸውን ነገር በወቅቱ ማግኘት ካልቻሉ፣ አእምሯቸው ማደግ ባለበት ደረጃ እንዳያድግ ይሆናል። ከጓደኞቻቸውና ከትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ጋር ያላቸውን ግንኙነትም ስናነሳ፣ ቤተሰብ ቤት ለዋሉ ልጆች ትምህርት ቤት ይደረግላቸው በነበረው ደረጃ እንክብካቤ ሊያደርግላቸው አይችልም።
ሌላውና ቤት ውስጥ መዋልን ተከትሎ ጎልቶ የተሰማው ጉዳይ የቤት ውስጥ ጥቃት ነው። በቤት ውስጥ የሚከሰተው ጥቃትም አካላዊ ብቻ ላይሆን ይችላል። እንደሚታወቀው ልጆች ማጥፋታቸው አይቀርምና፣ ነገር ግን ቤት በሚውሉ ጊዜ ይህ ጥፋት ሲደጋገም፣ አእምሯዊ የሚጎዳ ንግግር፣ ወሲባዊ ጥቃትና ትንኮሳ፣ ድብደባ ሊከተል ይችላል።
እንዲሁም ከልጆቸ ጋር ረጅም ጊዜ ማሳለፍ ጥንቃቄ ትዕግስት የሚጠይቅ እንደመሆኑ፣ በሌላ ጉዳይ የተበሳጨ የቤተሰብ አባል በልጆች ላይ ንዴቱን ሊወጣ ይችላል። እነዚህ አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የሚፈጸሙት በቅርብ ሰው ነው በመሆኑም ከዚህ አንጻርም ትምህርት ቤት ለልጆች የተሻለ ጥበቃ ያለበት ቦታ ነው ለማለት ይቻላል።
በተጨማሪ ሁሉም ቤተሰብ በእኩል የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኝ ስለማይሆን፣ ከቤት ውስጥ አስፈላጊው ክትትል ላይደርግላቸው ይችላል። አቅሙ ያለው ቤተሰ እንኳን ቢሆን፣ ለሌሎች ጉዳዮች ተወጥሮ የእለት ኑሮውን ለማሸነፍ ወደ ሌላ ሩጫ ያዘነብላል። አቅም ያለው ሰው የግል መምህርም ቀጥሮ ቢሆን በመደበኛ ትምህርት ያልተሸፈኑትን እንዲማሩ ሊያደርግ ይችላል ።
ራሱ ለማስተማር እውቀት ያለውም ከሆነ ከሌላው ግዜ በተለየ ቀርቦ ማስተማር መከታተል በኢንተርኔትና በቴሌቪዥን ይሰጡ የነበሩትን እቅድ አውጥቶ ማስተማር ይችል ይሆናል። ነገር ግን ልጆች በትምህርት ቤት ቆይታቸው ከመምህሩ ድጋፍና ክትትል ባለፈ ጓደኞቻቸውንም በመመልከት የሚሠሯቸው ሥራዎች የሚማሯቸው ትምህርቶችና የሚያገኟቸው እውቀቶች አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ በቤት ወስጥ ሟሟላት አይቻልም። በመሆኑም ልጆች እነዚህን ሁሉ ችግሮች አልፈው ትምህርት እንደሚጀምሩ ግንዛቤ መያዝ አለበት።
በሌላ በኩል እቤት የዋሉት ልጆች በሙሉ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የቆዩ አልነበሩም በመሆኑም የነበሩበትን ሁኔታ ከግምት በማስገባት የተሻለ እውቀት እንዲያገኙ ለማስቻልም ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች አሉ። ከዚህም የመጀመሪያው የእእምሮ ዝግጁነት እንዲኖራቸው የመጀመሪያ ደረጃ የስነልቦና እርዳታ እንዲሰጡ ለመምህራኖች አጫጭር ስልጠናዎች መስጠት።
በተጨማሪ በቤት ውስጥ ቆይታቸው ጥሩ የትምህርት ዝግጅት ሊያደርጉ የሚችሉ መኖራቸውን ያህል ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ቆይተው ካለ ዝግጅት የሚመጡ ልጆችም ስለሚኖሩ እነሱንም ከግንዛቤ ያስገባ ትምህርት ሊሰጥም ይገባል።
በተጨማሪ ልጆች እቤት በመዋላቸው የጸባይ መለዋወጥ ድባቴ ለነገሮች ትኩረት አለመስጠት የትኩረት መዛባት አይነት የስነ ልቦና ችግሮች ሊገጥማቸው ስለሚችል ወላጆች ስሜታቸውን እንዲገልጹ ማገዝ መከታተልና እንዲህ አይነት ችግሮች ሲስተዋሉ ደግሞ በአካባቢ ለሚገኝ የስነ ልቦና ወይንም የጤና ባለሙያ በማማከር ችግሮችን መፍታት ይጠበቅበታል። በልጀነት የሚደረግ የአእምሮ እንክብካቤ እስከ እድሜ ልክ የሚዘልቅና የነገ ማንነታቸውንም የሚወስን በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ይሆናል ሲሉ ባለሙያዋ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2013