ልዕለ ሃያሏን አገር በበላይነት ለመምራት ነጩን ቤተመንግስት ከመረከባቸው አስቀድሞ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት «ብትመርጡኝ እፈፅማቸዋለሁ» ያሏቸውን ተግባራት ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ ለመፈጸም አፍታም አልቆዩም፡፡
የዓለም አገራት መሪዎች ከረዥም ድርድር በኋላ አምጠው የወለዱትን የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንደማይቀበሉ በማስረገጥ አገራቸውን ከስምምነቱ ነጥለዋል። አገራቸው ከዚህ ዓለም ጋር የምታደርገውን የንግድ ልውውጥ ሂደትም በመቀየር በተለይ ከአውሮፓና ከቻይና በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ጥለዋል።
ፕሬዝደንቱ ሀገራቸዉን ዳግም ታላቅ ለማድረግ ሲያልሙ ደግሞ ለቀሪዉ አለም የምታደርገዉን ድጋፍ መቀነስ፣ ስደተኞች ወደ ሀገራቸዉ እንዳይገቡ መከልከል ሌሎች እርምጃዎች ውስጥ ገብተዋል፡፡ በተለይ ስደተኞችን በመከላከል ረገድ አገራቸው ከሜክሲኮ ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር ማጠር በምርጫ ቅስቅሳቸው ወቅት ቃል ከገቧቸው ዋነኛ ተግባራት መካከል ተጠቃሹ ነው።
ይሁንና አገራቸው ከምትዋሰናቸው «የአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ» በሚሏቸው ሜክሲኳውያን ድንበር ላይ የግንብ እጥር ማኖር ግን አልሆነላቸውም። በወቅቱ አገራቸው ሳትሆን ሜክሲኮ ራሷ የግንቡን ወጪ እንደምትሸፍን በሙሉ ልብ ሲናገሩ የተደመጡት ትራምፕ፤ ወንበራቸውን ከተረከቡ በሁዋላ ግን የአጥር ውጥናቸው ባቀለሉት መልኩ አልሆነላቸውም። ጎረቤታቸው ሜክሲኮም ብትሆን በውሳኔው ከመሳለቅ በዘለለ እጇን ለትብብር የምትዘረጋ ሆኖ አልታየችም።
ፕሬዚዳንቱ በኮንክሪት ግንብ ስደተኞችን በመግታት ሀገራቸውን ከደህንነት ስጋት ለማላቀቅ 5ነጥብ ሰባት 7ቢሊየን ዶላር ወጪ ማድረግ የግድ እንደሚል በማመላከት ኮንግረሱ እንዲያፀድቅላቸዉ ቢጠይቁም፣ ይህን ያህል ገንዘብ በቀላሉ ማግኘት ግን አልቻሉም።
ከውሳኔአቸው በተቃራኒ ጎራ የቆሙት ዲሞክራቶች ይህን ያህል በርካታ ገንዘብ ድንበርን ለማጠር ወጪ እንዲሆን መጠየቅ በአገሪቱ ታክስ ከፋዮች ገንዘብ እንደመቀለድ ይቆጠራል በማለት ተችተዋቸዋል።
አገርን በአጥር በመሸፈኑ እቅድ በርካታ ወገኖች ፕሬዚዳንቱን በመቃወም ጎራ ቢቆሙም፤ሃሳቡን የሚደግፉትም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። የግንቡን ውጥን ቢተውት ቃል አባይ እንደሚያደርጋቸው የተረዱት ትራምፕ፤ በደጋፊዎቻቸው ላለመወረፍ፤ቃል አባይ ላለመሆን አጥር መገንባቱን የስልጣን መሰረት የህልውና ማስረገጫ አድርገውት ታይተዋል።
ፕሬዚዳንቱ በተቃውሞና ድጋፍ ማዕበል እንዲሁም የቅቡልነት ወጀብ ውስጥ ሆነውም አጥሩን ከመገንባት ሃሳባቸው አላፈገፈጉም። ይህን ሀሳባቸውን እውን ለማድረግ የኮንግረሱን ይሁንታ ማግኘት ቢያዳግታቸውም የአጥሩን ግንባታ ለማረጋጋጥ ያደርሳሉ በሚባሉ መንገዶች ሁሉ ሳይታክቱ መመላለሳቸውን ቀጥለዋል።
«የግንብ አጥሩ እውን እስካልሆነ አገራችን ምንም አይነት ብሄራዊ ደህንንት አይኖራትም›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ዴሞክራቶቹ ይህን ጠንቅቀው ቢረዱትም በፖለቲካ ጨዋታ ተጠምደዋል፤ ይህ ግን ፈፅሞ መቆም አለበት›› ሲሉ በቲውተር ገፃቸው አስፍረዋል።
የኮንግረሱን አብላጫ ወንበር የተቆናጠጡት ዲሞክራቶች በአንፃሩ ፕሬዚዳንቱ አጥር እንዳይገነቡ የሚያግዷቸውን መንገዶች በሙሉ በመዝጋት ተጠምደዋል። ዴሞክራቶቹ ፕሬዚዳንቱን ከመቃወም ባሻገር ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የመውሰድ አዝማሚያም አሳይተዋል።
ሪፐብሊካኑ በአንፃሩ የቀድሞውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን የጤና መድህን ለመጣል የተጓዙበትን የምከር ቤቱን ህጋዊ አካሄድና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ባጣመረ መንገድ ለመሄድ መወሰናቸው ተመላክቷል።
በዚህ መልኩ ውጥናተው ወደ ተግባር ለመቀየር ከዲሞክራቶቹ በኩል ጠንካራ ተቃውሞ ያደረሰባቸውና አስፈላጊውን የግንባታ በጀት ማግኘት ያልቻሉት ትራምፕ፤ የፈለጉትን ለማግኘት በሄዱበት ግትር አቋም የተነሳም በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ተዘግተው እንዲቆዩ ምክንያት መሆናቸው አይዘነጋም።
የትራንስፖርት፤የግብርና፣ የንግድና የፍትህ የመሳሰሉት ዘጠኝ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችና ሌሎች ኤጀንሲዎች ከአንድ ወር በላይ ተዘግተዋል፤ከ800ሺ በላይ ለሚሆኑ ቋሚና ኮንትራት ሰራተኞች ደመወዝ አልባ ሆነዋል። የተቋማቱ መዘጋት ውጤትም ስራዎች እንዲስተጓጎሉ በተለይም ከ42 ሺ በላይ ስደተኞችም ጥያቄ የሚሰማላቸው ቢሮ እንዲያጡ ምክንያት ሆኖም ቆይቷል።
ትራምፕ በአንፃሩ ይህን ሁሉ ችግር አይቶ እንዳላየ እና ሰምቶም እንዳልሰማ ከመሆን በስተቀር አንዳችም የማስተካከያ እርምጃ ለማድረግ ሳይዳደኑ አልዳዱም።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ሰራተኞችና ዲሞክራቶች በሌላ ወገን የመንግስት ተቋማት መዘጋት እልባት እስካላገኘ ድረስ በግንቡ በጀት ላይ ለመደራደር ፍላጎት እንደሌላቸው የፀና አቋም አሳይተዋል።
«ለዚህ ሁሉ ቀውስ ፐሬዚዳንቱ ሊወቀሱ አለፍ ሲልም ሊጠየቁ እንዲሁም የመንግስት መስሪያ ቤቶቹ በአፋጣኝ ወደ ስራ ሊገቡ የግድ ይላል ሲሉ፤ በቲውተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ጠንካራ ተቋሟቸውን ያንፀባረቁት የፐሬዘዳንቱ ዋነኛ ተቃዋሚና የዲሞክራቶቹ መሪ ናንሲ ፔሎሲም፤ተቋማት መዘጋት እልባት እስካላገኘ ድረስ በግንቡ በጀት ላይ መደራዳር የሚለው እንደማይታሰብ የፀና አቋም ማሳየታቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ መልክ የሚስተዋለው የሪፐብሊካኑና የዲሞክራቶቹ የአልሸነፍ ባይነት ትግል ከግንቡ በጀትም በላይ ፖለቲካዊ የበላይነት ለማሳየት ወደ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክር መሸጋገሩና አንዳቸው የአንዳቸውን አሸናፊነት ላለማመን እልህ እስጨራሽ ፍጥጫ ውስጥ ስለመግባታቸው መጠቆም ጀምሯል።
ይህ ግን መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ እንደተጠቀሰው 800 ሺ የመንግስትና በርካታ የኮንትራት ሰራተኞች ለሌላ ሁለተኛ ወር ያለስራ እንዲቆዩ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ የሙሉ ሰዓት ሰራተኞች ያልተከፈላቸውን ደመወዝ በቀጣይ የሚያገኙ ቢሆንም፣ ያለምንም ክፍያ አስከፊ ህይወት እንዲመሩ የተፈረደባቸው እነዚህ የኮንትራት ሰራተኞች እንዲማረሩ አድርጓል።
ከኮንትራት ሰራተኞቹ አንዷ የሆነችው ዮቪት ሂክስ«ዜጎች የሚከፍሉት አጥተው ቤታቸው፤ መኪናቸውና ሌሎች ንብረቶቻቸውንም ሊነጠቁ ነው፤ እኔ የልጆች እናት ነኝ፤ ቤተሰቦቼን አስተዳድራለሁ ፤ይሁንና የተቋማቱ መዘጋት ህልውናዬን እየፈተነው ነው፤ እናም ወርሃዊ ወጪያችንን የማትከፍሉን ከሆነ ወደ ስራችን መልሱልን፤ የእኛ ጥያቄ ይህ ነው »ስትል ተደምጣ ነበር።
በመሰል የአልሸነፍ ባይ ነት ፍልሚያ ወደ ሁለተኛ ወሩ የተሸጋገረው አገርን በድንበር የማጣር ውጥንና ተከትሎ የመጣው መዘዝም እንዲያበቃም የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ምሁራን የመፍትሄ ሃሳባቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል።
ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ሁለቱም ወገኖች መቻቻል በሚል መርህ መራመድ እንዳለባቸውና ይህ ካልሆነም የመንግስት ተቋማቱ መዘጋት ቀጣይነቱ አይቀሬ መሆኑንም ጠቁመዋል። ፕሬዚዳንቱም ሆኑ የእቅዳቸው ተቃዋሚዎች ከግትር አቋማቸው ሊላቀቁ የግድ እንደሚል ያመለከቱበት ሃሳብ ግን ምናልባትም አዋጩ መንገድ ሆኖ ታይቷል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከቀናት በፊት ከግትር አቋማቸው መለሳለስ በማሳየት ያልተጠበቀ ትልቅ ውሳኔ አሳልፈዋል። በአገሪቱ ታሪክ ለረጅም ጊዜያት የቆየው የመንግስት መስሪያ ቤቶቹ ተዘግቶ መቆየት በከፊልም ቢሆን እልባት እንዲያገኝ አድርገዋል።
ፕሬዚዳንቱ የመንግስት መስሪያ ቤቶቹ ከቀናት በፊት በከፊል እንዲከፈቱ ቢያደርጉም፣አሁንም ቢሆን ግንቡን እውን ለማድረግ የመደቡት የግንባታ በጀት ማግኘት አልቻሉም፡፡ በበጀቱ ላይ የዲሞክራቶቹ ይሁንታ እስከ አሁን አልተረጋገጠም ።
እንደ ቮክስ የዜና አውታር ከሆነ የአገሪቱ መንግስት የተዘጉ መስሪያ ቤቶቹን ዳግም የመክፈት ተግባር ቢጀምርም፤ አንዳንድ የመንግስት ተቋማት ዳግም ለማስከፈት ረጅም ጊዜ ይወስዳል። የሲኤን ቢሲ ዘገባ በበኩሉ፤ በተለይ የኮንትራት ስራተኞቹ ለወራት ያለክፍያ መቆየት ከባድ ቀውስ ማስከተሉና በአማራጭነት የሚቀርቡ ማካካሻዎች የግድ እንደሚሉት አመላክቷል።
ምንም እንኳን አሁን የመንግስት ተቋማቱ እልባት ማግኘት ሃቅ ቢሆንም ለፕሬዚዳንቱ ድንበር የማጠር እቅድ እውን መሆን ግን አስፈላጊ የሚባለው ገንዘብ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል የተረጋገጠ ከመተማመንም የተደረሰበት አጀንዳ አልሆነም።
ይህ ከሆነ ጉዳዩ እንዴት መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል በሚለው ላይ የፖለቲካ ተንታኞች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። አንዳንዶች ሰውየው የሚፈልጉትን የገንዘብ መጠን ለማግኘት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚያውጁ ቢያስታውቁም፣ይህን አቋማቸውን የሚቃወሙት ወገኖች ደግሞ ይህን ማድረግ ከባድ ውዝግብ እንደሚያስነሳም ይናገራሉ፡፡ ከህጋዊነት ጋር ተያይዞ የሚያስከትለው ችግር እንዳለም ይጠቁማሉ።
እንደ ዴሞክራቶቹ ሴናተሮች ሀሳብ ከሆነ ደግሞ ቢሊየን ዶላሮችን ወጪ አድርጎ አጥር ከመገተር ይልቅ አሁን ባለዉ አሰራር በድንበር አካባቢ ያለዉን ጥበቃ ማጠናከርና ለዚህ የሚመደበውን የሰው ኃይል ቁጥር መጨመር ያዋጣል፡፡ ይህ መንገድ ፕሬዝደንቱ ከሚሉት የብረት አጥር የተሻለና ብዙ እንደማያስወጣና ውጤታማ መሆኑ ታምኖበታል።
በአሁኑ ወቅት ድንበር የማጠሩ ውሳኔ ምንም እንኳን የመንግስት ተቋማቱ ዳግም መከፈት ቢረጋገጥም በድጋፍና በተቃውሞ ታጅቦ ወደ ሁለተኛ ወሩ ተሸጋግሯል። ውጤቱም በተለይ የአገሪቱን መንግስት ስተራተኞችን ከባድ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቅቡልነትም እንዲቀንስና በአስተዳደራቸው ላይ የሚቀርቡ ተቋውሞዎች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል። ይህም በተለይ በቀጣዩ ምርጫ ፕሬዚዳንቱን ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል ብዙዎች ተስማምተውበታል።
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
ታምራት ተስፋዬ