“ቃል የእምነት እዳ ነው!” ይላሉ አበው፤ እናም አንድን ነገር ለማድረግ ሲዘጋጁ ወይም አንድን ኃላፊነት ለመውሰድ ሲታጩ ቀጣይ ስራቸውን በእምነት ለመፈጸም ቃል ይገባሉ። እናም ቃላቸውን ጠብቀው የተቀበሉትን ከግብ ያደርሳሉ። ኢትዮጵያም ለዘመናት የነጻነት ፋና የመሆኗም ምስጢር ይሄው የአባቶች በቃል የመገኘት፣ ቃልን ለመፈጸም የተከፈለ መስዋዕትነት ውጤት ነው።
ዛሬም የአባቶቹን የቃል ጽናት የሚያውቀውና የኢትዮጵያዊነትን ልዕልና ከአባቶቹ ያገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት፤ የቃልን የእምነት እዳነት ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያዊነት ከፍታን፣ የአገር ፍቅር ልዕልናን በተግባር አሳይቶናል። ምናልባት፣ ቃል በሁለት ነገር ሊገለጽ ይችላል። አንደኛው፣ በፖለቲከኛውና በመንግሥት ሠራተኛው የሚገለጽ ጥቂት ጊዜን ሰጥቶ ሌሎችን የማገልገል ኃላፊነትን መወጣት ነው። ሁለተኛው ግን እንደ መከላከያ ሠራዊታችን የራስ ህይወትን እስከመስጠት ደርሶ ሌሎችን በማኖር ውስጥ የሚገለጽ ነው።
ታዲያ እነዚህ ሁለት ቃልን በተግባር የመግለጫ አውዶች ዛሬ ላይ በኢትዮጵያችን በሁለት ጽንፍ ቆመው ለመቀራረብ ቀርቶ ለመተያየት አቅም ያነሳቸው ይመስላል። ምክንያቱም ፖለቲከኛው እና የመንግሥት ሠራተኛው ጥቂት ጊዜን ሰጥቶ ህዝብ የማገልገል ኃላፊነትን ለመወጣት ተስኖት፣ ህዝብ ለእንግልትና ሮሮ ሲዳረግ ማየት የተለመደ ሆኗል። ኢትዮጵያም፣ ህዝብን በቅንነት ከማገልገል ይልቅ በእጅ መንሻ ማማረር፤ በፍቅር ከማስተናገድ ይልቅ በዘርና ጎጥ ተሳስቦ መጠቃቀም፤ ከመተዛዘን ይልቅ መጨካከን ነግሶ፣ የገቡትን ቃል አስበው ሳይሆን የደም ሃረግ ቆጥረው የሚቧድኑትን ፖለቲከኞችና የመንግሥት ሠራተኞች መፈልፈያ ሆና ዘመናትን ገፍታለች።
ይሄንኑ ከአገርና ህዝብ በላይ ስለራስና በዙሪያ ስለተሰባሰቡ አካላት ብቻ እያሰበ የሚታትር ከፋፋይ የፖለቲካ እሳቤ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥም ሊተክሉበት ብዙ ሴራና ደባ ቢሰሩበትም፤ ከኢትዮጵያዊነት ከፍታው ላይ ሊያወርዱት አልቻሉም። ይሄንንም በጥቅምት 24ቱ ምሽት በጁንታው የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያዊነት ውሃ ልክን ያሳዩ አያሌ ጀግኖችን መኖራቸውን ተመልክተናል።
ምክንያቱም የጁንታው ስብስብ በጣት የሚቆጠሩ ተላላኪ የእናት ጡት ነካሾችን ማታለል የተቻለ ቢሆንም፤ ከመከላከያ ወንድሞቹ ጋር አብረው የግፍ ጽዋ የተጎነጩ እንደ ሃምሳ አለቃ ሓየሎም ነጋ አይነቶችን እልፍ የአገር ኩራቶች ማግኘት ተችሏል። የአገር ፍቅርና የህዝብ አደራ ሸክማቸው በሆዳቸው ከያዙት የስድስት ወር ጽንስ ገዝፎ፣ እርግዝናቸውን ዘንግተው ለሦስት ቀናት ያለ እህል ውሃ በበረሃ የተዋደቁ እንስት የመከላከያ ሠራዊት አባላትን አሳይቶናል።
በድል ጉዟቸው በእያንዳንዱ ከተማ በጦርነት ምክንያት ሊደርስ የሚችልን ጥፋት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰው፤ ንጹሃን ዜጎችን ከጁንታው በመለየት እርምጃ ወስደው፤ ይሄንንም በጥበብ መርተው የድል ችቦን በመለኮስ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ከምንም በላይ መሆኑን በተግባር ያስመሰከሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና መኮንኖችንም ተመልክተናል።
ኢትዮጵያም ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በላይ መሆኗን በመስዋዕትነታቸው ጽፈው አስነብበውናል። አሁን ላይ በዘር ስካር የወደቁ፣ በግል ጥቅም የታሰሩ፣ በፓርቲ ጥገኝነት ኑሯቸውን የመሠረቱ ፖለቲከኞችም ሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች መመልከት ያቃታቸውን ታላቅ ህዝብና ትልቋን ኢትዮጵያ በሞታቸው ሰንደቋን ከፍ አድርገው አስመልክተውናል።
የማያውቀውን የደም ሀረግ እየፈለገ የሚቧደን የተበላሸ ፖለቲካ ውስጥ ሆነውም፤ ንጹህ ኢትዮጵያዊነታቸውን በጀግንነት አሳይተዋል፤ የአገር ፍቅራቸውን እና የህዝብ አደራ ቃላቸውን ተወጥተዋል። ለአገርና ህዝብ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ጦር ግንባር ኦሮሞ አማራን ለማዳን፣ አማራው ወላይታውን ለማዳን፣ ወላይታው ሲዳማውን ለማዳን፣ አፋሩም ሱማሌውን ለማዳን፣ በጥቅሉ ከጎኑ ቆሞ ለአገርና ህዝብ ህልውና የሚዋደቀውን እንደ እናቱ ልጅ የሚያየውን ጓዱን ለማዳን ያሳዩት ጀግንነት ከፍ ብሎ ተገልጿል።
ይህ ሲሆን ግን ስለ ወገኖቻቸው በፍቅር እራሩ፣ ስለተፈጸመው ግፍ አዘኑ፣ ስለ ጓዶቻቸው አለቀሱ፣ ስለ ህልውናቸው ደግሞ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ተዋጉ እንጂ፤ ስለ ፈጸሙት ጀብድ ብቻ እያሰቡ አልፎከሩም። ምክንያቱም እነሱ የከፍታ ምልክቶች፣ የአገር ፍቅር ማሳያ ዓርማዎች፣ የአንድነት መሰረት ገመዶች ሆነው የተሰለፉ፤ ለታይታ ሳይሆን ለዓላማና ለገቡት ቃል ታምነው የሚኖሩ፤ ምን ተደረገልን ብለው ሳይጠብቁ ለአገራቸው አንድያ ነፍሳቸውን እየሰጡ ያሉ ናቸው።
ከዚህ ከፍታ ሁሉም ኢትዮጵያዊው ሊማር፤ ራሱንም ሊመረምር ይገባል። ከፍ ማለት በሌብነት ሳይሆን በፍቅር ነው፤ ከፍ ማለት በዘር ከፋፍሎ በማባላት ሳይሆን ሰው ሆኖ ስለሌሎች ራስን አሳልፎ በመስጠት ነው፤ ከፍ ማለት ሽርፍራፊ ሰዓቶችን ሳያባክኑ ለህዝብ ለማገልገል የተገባን ቃል በመፈጸም ነው። መከላከያ ያስተማረን ይሄንን ነው። ክብርና ሞገስ ለሃገር መከላከያ ሠራዊታችን!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2013