ራስወርቅ ሙሉጌታ
ዛሬ ዛሬ በዓለም ላይ የምናያቸው አንዳንድ ግጭቶችና የተለያዩ ችግሮች የሚከሰቱት ሃላፊነት በጎደላቸው ሰዎች ስራና አንዳንዶችም ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ነው። አንዳንድ ግዜም ሰዎች ከነፍስ ማጥፋት ጀምሮ ህሊና ካለው ፍጡር የማይጠበቅን ነገር አድርገው ምንም የጥፋተኝነት ስሜት ወይንም ፀፀት ሳይሰማቸው ሲኖሩም ይታያሉ።
ይህ ሁሉ ሃላፊነት ካለመሰማት የሚመነጭ ነው። ለመሆኑ ሃላፊነት መውሰድ፣ ሃላፊነት መወጣትስ እንዴት ይገለጻል ስንል የማህበራዊ ልማትና አመራር ባለሙያ ከሆኑትና በቲቪ ዘጠኝ የክሊፍ ሞቲቬሽን ወይም አፋፍ ለመድረስ ዝግጅት አዘጋጅና አቅራቢ አቶ ዘላለም ይትባረክ የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበናል።
ሃላፊነት ማለት ይመለከተኛል ከሚል የባለቤትነትና የተጠያቂነት ስሜት በመነሳት አንዳንዴም ለሚፈጠረው ስህተት ወይም ለሚደርሰው ትችትና ወቀሳ ራስን በመዘጋጀት ልናደርግ የሚገባንን ማድረግ፤ ልንሆን የምንችለውን መሆን ማለት ነው። በተጨማሪ ለራሳችን ከራሳችን ከምንለው ባለፈ ከሌሎች ተከፍሎልን እየከፈልን የምንኖረው ህይወት እንዳለብን መረዳት ማለት ነው። በሌላ በኩል ሃላፊነት የጎደለው ማለት “ለስልጣን ምላሽ የማይሰጥ”፤ “የተጠያቂነት ስሜት የሌለው ወይም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለሚደርሱ ስህተቶች ሃላፊነት ወስዶ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን” ማለት ነው።
ብሎም “ህሊናን ማጣት ወይም ለህሊና ድምጽ ምላሽ ለመስጠት አለመቻል ወይም አለመፍቀድ” እንደማለት ይሆናል። ይሄ ችግር ያለባቸው ሰዎች ባህሪያቸው የሚዋዥቅና ተለዋዋጭ ሲሆን ግዴለሾች፣ ሽፍታዎች፣ እምነት የማይጣልባቸው፣ ያልተረጋጉ፣ ውሳኔ መወሰን የማይችሉ ሆነው ይገኛሉ።
እነዚህም ሰዎች የራሳቸውን ስህተት በማህበረሰቡ፤ በመንግስት፣ በአካባቢ፣ በፈጣሪ፣ በቤተሰብ፣ በአገር በእድል … ወዘተ ላይ በማላከክ ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት የሚጥሩ ናቸው። አንዳንዶች ዛሬ ለተከሰተ ችግርም ትናንትን አልያም የትናንት ማንነታቸውን ተጠያቂ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። ለምሳሌ ሲጋራ አጫሽ ለመሆኔ ተጠያቂው ያደኩበት
ማህበረሰብ ነው፤ ወይንም አልኮል ሱሰኛ እንድሆን ያደረገኝ በሀገሪቱ ያለው የተበላሸ የአስተዳደር ስርአት ነው እንደሚሉት ማለት ነው። እንደዚህ አይነት ሰዎች ላሉበት አልያም ለፈጠሩት ችግር ምክንያቱን ሌላ አካል እንዲወስድ ስለሚያደርጉ መፍትሄውንም ከራሳቸው ለመፈለግ እድሉ አይኖራቸውም።
በመሆኑም ከችግራቸው ለመላቀቅም አይሞክሩም። በእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸውም ስራ የሚሰሩት ሲታዘዙ፣ ሲነገሩና ሲቆጡ ብቻ ይሆናል፤ የባርነት፣ የመገፋት ስሜት ውስጥ ስለሚሆኑም አንዳንዶቹ ምግብ እንኳ የሚበሉት ታዘው እስከመሆን ይደርሳል።
ለሰው ልጅ ውጤታማ ሰብእና ግንባታ ሃላፊነትን መውሰድ፤ ብሎም መለማመድና መተግበር ወሳኝ በመሆኑ የሚያሳድግ፣ የሚያጠነክር፣ የሚያበረታና የሚያሻሽል ሲሆን በተቃራኒው ሲሆን ደግሞ ሀሳብንም ተግባርንም ያቀነጭራል፣ ያከስማል በስራም ሆነ በማህበራዊ ግንኙነት ልፍስፍስ ያደርጋል።
የሃላፊነት አይነቶች በብዙ መልኩ የሚከፋፈሉ ቢሆኑም በዋነኝነት የግል (Personal) እና ማህበራዊ (Social) በመባል በሁለት ይለያሉ። የግል ሃላፊነት ስንል ሰዎች ስለራሳቸው ያላቸው ድርሻ ወይም ባለቤትነትን ሲሆን በተፈጥሮ የተሰጠን ችሎታ፣ ብቃት፣ አቅም፣ ጥበብ፣ እውቀት፣ ክህሎት ወዘተ የማሳደግ፣ የመጠቀምና የመውጣት ሃላፊነትን ያካትታል። የማህበራዊ ሲባል ደግሞ ሰዎች ስለሌሎች የተሰጣቸው፣ የሚሰማቸው ወይም የሌሎችን ችግር ከመፍታትና ከማቃለል አንጻር የሚወስዱትን ድርሻና እንቅስቃሴ ያካትታል። አንድ ሰው ወይም አንድ ግለሰብ ምንም ያህል ስኬታማና ሃብታም ሊሆን ቢችልም የግልን እንጂ የማህበረሰብን ችግር እስካልፈታ ድረስ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል ወይንም ታላቅ ሰው ሊባል አይችልም።
ሃላፊነትን የመውሰድና የመወጣት ጠቀሜታ
- ስለ እኛ በሚጨነቁና ሃላፊነት በሚሰማቸው ሰዎች እንድንከበብ ያደርገናል።
- ባሪያ፣ ፈሪ፣ እስረኛ ወይም ተገዥ ከመሆን ተላቀን ነፃነት ያለን በራሳችን የምንመራ እንድንሆን ያደርገናል።
- በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር በጥሩ ሰብዕና የተሞላንና ባህሪያችንንና የስም ዝናችንን በበጎው የገነነ እንዲሆን ያደርገዋል።
- ከተጠያቂነት፣ ከፀፀት ወይም ቁጭት ማምለጥ ያስችላል።
- ምርታማነትን እና በብዙ ስራ ውስጥም ሆነን ስኬታማ ለመሆን ያበቃናል።
- በስራ ቦታዎቻችንም ሆነ የግል ንብረቶቻችንን በሀላፊነት እንድንጠቀም በማስቻል ከብክነትና ከጥፋት በመታደግ የንብረቶቻችን እድሜ የሚያረዝም አጠቃቀም እንዲኖረን ያስችለናል።
- ከሌሎች ጋር በመከባበርና በመግባባት መኖር
- የምንችልበትን አቅም ያጎናጽፈናል።
- • የግልም ሆነ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚያስችል ብልሀት ባለቤት እንድንሆን ያበቃናል።
- ሃላፊነትን መውሰድና መወጣትን እንዴት ማጎልበት ይቻላል?
ሃላፊነት መውሰድ ክህሎት ነው። ልናጎለብተውና ልንተገብረው የምንችለውም በጊዜ ሂደት ውስጥ ብቻ ሲሆን በተጨማሪ ራሳችን ከምናስለምደውና ከምናስተምረው ባለፈ ከሌሎች ለምሳሌ መምህራን፣ ወላጅና በልመድና በጥሩ ስነ ምግባር ከሚበልጡን የምንቀስመውም ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ሃላፊነት ለመውሰድ ከሚያስችሉ ብልሃቶች መካከል አንድ ሰው ሃላፊነት ሲወስድ ስህተት ሊፈጠር እንደሚችል ይህንንም ተከትሎ ተጠያቂነት እንደሚመጣ ማመንና ለዚህም ራስን ማዘጋጀት ይጠበቃል።
ሃላፊነት መውሰድን በመለማመድ ረገድ ከሌሎች በበለጠ የቤተሰብ ሚና በጣም ከፍተኛ ነው። በእኛ ሀገር ተሞክሮ ልጆች ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን ከደረሱ በኋላ እንኳን አንዳንድ ቤተሰቦች ልጄ ምን ያውቃል? ምን ታውቃለች? እያሉ ስለሚያፍኗቸው ከቤት ሳይወጡ ጥገኛ ሆነው ለመቆየት ይገደዳሉ። በዚህ ሁኔታ ያደጉ ልጆች አንዳንድ አጋጣሚዎች ተፈጥረው የህይወት ውሳኔ መወሰን ቢያስፈልጋቸው እንኳን በራሳቸው ሀላፊነት ወስደው ለመወሰን ልምዱ ስለማይኖራቸው በህይወታቸው ላይ ትልልቅ የሚባሉ ጉዳዮችን ሳይቀር ለሌሎች አሳልፈው ሲሰጡ ይስተዋላሉ።
ሞት የማይቀር ነው! ሁሉም ሰው ይሞታል ነገር ግን ምን ሰርተን እንለፍ የሚለው ትልቅ ጥያቄና ሁላችንም ልንመልሰው የሚገባን ነው። እንደሚሞት ሰው መኖር ከሚያስብሉን አኗኗሮች መካከልም ሃላፊነትን መወጣት አንዱ ነው። ለእኛ መኖር በርካቶች ሃላፊነት ወስድው የሰሯቸው ስራዎች አሉ በመሆኑም እኛም እንደ ግለሰብ ለራሳችን ለቤተሰባችንና ለማህበረሰባችን ብሎም ለሀገር በማሰብ ሀላፊነት መውሰድ ሃላፊነት የሚሰማውም ቤተሰብ መመስረት እንደሚጠበቅም ባለሙያው አቶ ዘላላም ይትባረክ ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2013