የሀገር መከላከያ ሠራዊት በጁንታው ላይ ድል በመቀዳጀት የትግራይ ክልልን ከጁንታው ቁጥጥር ነፃ ማውጣቱን ተከትሎ በክልሉ በአሁኑ ወቅት መልሶ የማልማት ሥራ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ የማቅረብ እና ወንጀለኞችን አድኖ በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው። በዚህም ጁንታው ያወደማቸውን የመሰረተ ልማት አውታሮች በመጠገን ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፤እየተደረገም ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በትግራይ ክልል አብዛኛው አካባቢ ከአንድ ወር በላይ ተቋርጠው የነበሩት የኤሌ ክትሪክ እና የቴሌ ኮም አገልግሎቶች ሥራ ጀምረዋል።
ሰብዓዊ ድጋፍ የማጓጓዝ ሥራም እየተከናወነ ይገኛል። እስከ አሁንም መጠነ ሰፊ የምግብና የመድህኒት አቅርቦቶች ወደ ክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ደርሰዋል። ከህብረተሰቡ ጋር ውይይቶች እየተካሄዱም ይገኛሉ። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም ካቢኔውን አቋቁሞ ትናንት ወደ ሥራ ገብቷል። ይህ ሁሉ ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበረው የትግራይ ክልል ወደ መረጋጋት እየመጣ መሆኑን ያመለክታል።
ይህ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የትግራይ ህዝብ የመሰረተ ልማት አገልግሎትና የመሳሰሉት በአፋጣኝ እንዲጀመርለት በጠየቀው መሰረት መንግሥት ሌት ተቀን በመሥራት አደጋ የደረሰባቸውን የመሰረተ ልማት አውታሮች በመጠገን ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ አድርጓል። በዚህ መልኩ መንግሥት ኃላፊነቱን እየተወጣ ከሆነ ደግሞ፤ ህዝቡም በክልሉ የመጣውን መረጋጋት ይበልጥ ዘላቂ ለማድረግ በቁጥጥር ስር ያልዋሉትን የጁንታውን አባላት በማጋለጥ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። ከህዝብ እይታ የሚሰወር የለምና ወንጀለኛ የጁንታውን ቡድን አባላት አሳልፎ መስጠት ይጠበቅበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከትናንት በስቲያ በመቀሌ ተገኝተው ከሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅትም ይህንኑ አስገንዝበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ህዝብ የተደበቁትን እነዚህን ወንጀለኞች ለህግ በማቅረቡ ሂደት የጎላ ተሳትፎ እንዲያደርግ አደራ ብለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተሰጠውን የመጀመርያ ተልዕኮ መቶ በመቶ ማሳካቱን ጠቅሰው፣ ድሉ ሙሉ መሆን የሚችለው ግን ወንጀለኞቹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ነው ብለዋል።
የተደበቁት የጁንታው አባላትም አሁን እየሸሹ ያሉት በቡድን ሳይሆን ተበታትነው ነው። ሆኖም የትም አልሄዱም፤ ህዝብ መሃል ሰርገው ነው የገቡት፤ እነዚህን ወንጀለኞች ለቅሞ አዲስ ለተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ወይም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ማቅረብ ከሁሉም ዜጋ በተለይም ከትግራይ ክልል ህዝብ ይጠበቃል። ይህ ሲሆን የክልሉ ሰላምና መረጋጋት ይበልጥ ይጠናከራል፤ ክልሉም ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት መመለስ ይችላል።
ህዝቡ ወንጀለኞችን አሳልፎ በመስጠት ሃገር የሚገነባበት ጊዜ ወንጀለኛን በማሰስ እንዳይባክን ማድረግ ይኖርበታል። የሚጠቅመውን ስለሚያውቅ፣ ከወንጀለኛ ነፃ የሚሆንበትን መብት ተጠቅሞ፣ ወንጀለኞችን ከተደበቁበት በማውጣት ህግ ፊት እንዲቀርቡ የማጋለጥ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ልብ ሊባል ይገባል።
እናም ከመንግሥት ልማትና ድጋፍ መጠየቅ እንደሚገባ ሁሉ፤ ዜጎች ወንጀለኞችን ካሉበት ይዞ አሳልፎ ለህግ መስጠት ግዴታቸው መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል። በርግጥ በአሁኑ ወቅት ወንጀለኞች እየተያዙ ሲሆን፣ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ወንጀለኞቹ በሙሉ ተለቅመውና ተይዘው ህዝብም ሆነ መንግሥት ቶሎ ወደ ዋና ሥራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ መረባረብ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው።
በክልሉ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጡ ሥራ መከላከያ ሠራዊት አሁንም ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በተጨባጭ አረጋግጧል።የህግ የበላይነት የማስከበሩን ዘመቻ በአጭር ጊዜ፣ በከፍተኛ ጥንቃቄና በንጹሐን ዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት ሳይዳርስ ለማጠናቀቅ በገባው ቃል መሰረት ግዳጁን በስኬት መፈጸም ችሏል።
በመከላከያ ሰሠዊቱና በጁንታው መካከል ያለው ልዩነት መከላከያ መቀሌን አስከተቆጣጠረበት ቀን ድረስ ሮኬት አልተኮሰም። ምክንያቱም ወንጀለኛው ቡድን በህዝብ መካከል እንዳለ ስለሚታወቅ ነው። አሁን በህዝብ ውስጥ የቀረው ወንጀለኛ ቡድን ለህግ መቅረብ የሚችለው በመከላከያ ሠራዊቱ ጥረት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የትግራይ ህዝብ የማጋለጥ ግዴታውን ሲወጣ ጭምር መሆኑ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል።
በመሆኑም የትግራይ ህዝብ ወንጀለኞቹን ለህግ በማቅረብ በኩል ትብብር ማድረግ ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንዳለበት ተገንዝቦ ይህን ኃላፊነቱንና ግዴታውን መወጣት አለበት።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2013