በትግራይ ክልል የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሲካሄድ የቆየው የህልውና ዘመቻ መጠናቀቁን ተከትሎ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካክል ወንጀለኞችን አድኖ በቁጥጥር ስር ማዋል እና በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ምግብ እና መድኃኒት የመሳሰሉትን የማቅረብ ስራ ይጠቀሳሉ። በዚህም ወንጀለኞችን በሕግ ጥላ ስር ለማዋል የሚከናወነው ተግባር በፌዴራል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች እየተከናወነ ይገኛል።
በሌላ በኩል ግን ጁንታው በመከላከያ ኃይል መሸነፉን ሲገነዘብ በርካታ የክልሉን መሰረተ ልማቶች እያወደመ ነው የፈረጠጠው። በዚህም የመከላከያ ኃይል እየገሰገሰ ሲደርስበት ተስፋ ቆርጦ ማድረግ የቻለው በሀገር ሕዝብ ሀብት የተገነቡ በርካታ ድልድዮችን፣ መንገዶችን፣ የአውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በርካታ ጥፋቶችን ፈጽሟል። በሀገር መከላከያ ውስጥ ባደራጀው ከሀዲ ቡድን ሰሜን ዕዝ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት ሲፈጽም በቅድሚያ የስልክና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል።
ይህ ኃላፊነት የማይሰማው ቡድን ይሄን ቢፈጽምም፣ ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት ግን እነዚህን መሰረተ ልማቶች ለመጠገን በአስቸኳይ ተንቀሳቅሷል።ይሁንና በእነዚህ መሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ የጥገናው ስራ ከባድ ሆኖ ቆይቷል።ጁንታው መቀሌን ለቆ ከወጣ ወዲህም መሰረተ ልማቱን ሙሉ ለሙሉ ጠግኖ መብራት መልቀቅ አልተቻለም።
በቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ የደረሰው ጉዳትም የከፋ መሆኑን ከኢትዮ-ቴሌኮም የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።በእነዚህ መሰረተ ልማቶች ላይ ተመስርተው የሚሰሩ እንደ የጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና የመሳሰሉት አገልግሎቶችም ስራ ላይ እንዳልሆኑ ይታወቃል።ስራ ላይ ቢሆኑ እንኳ በሚፈለገው ልክ ሊሰሩ አይችሉም።
ይህን ሁሉ በሚገባ የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይን መልሶ እንደሚገነባ በገባው ቃል መሰረት በጁንታው ጉዳት የደረሰባቸውን የመሰረተ ልማት አውታሮች መጠገኑን ተያይዞታል። ጉዳት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶች ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት የሕግ የበላይነት የማስከበሩ ስራ እስከሚጠናቀቅም አልጠበቀም።የሕግ የበላይነት በተከበረባቸው አካባቢዎች ሁሉ የጥገናው ስራ እንዲካሄድ ሲያደርግ ቆይቷል።
የመንገድ መሰረተ ልማቱ መጠገን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሰሞኑን እንዳስታወቀው፤ ከመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ጎን ለጎን በተጀመረው የሰብዓዊ ድጋፍ ስራ በፌዴራል መንግስት ቁጥጥር ስር እየዋሉ በመጡት አካባቢዎች ጭምር ከስር ከስር የምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ ተደርጓል፤እየተደረገም ነው።
ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በ44 የጭነት መኪና የተላከው ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁስ ሽሬ ከተማ ደርሷል፤ በ30 የጭነት ተሽከርካሪዎች የተጫነ እህልም መቀሌ ደርሷል።በባለፈው ወር የመጀመሪያው ዙር ሰብዓዊ ድጋፍና የሕክምና ቁሳቁስ ወደ ዳንሻ፣ ወልቃይት፣ ቃፍታ/ሁመራ እና ደባርቅ አካባቢዎች መላኩ ተጠቁሟል።የመቀሌ ከተማ በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር ከዋለች ጀምሮ ደግሞ በሙሉ አቅም የሰብዓዊ ድጋፍ ስራው ከተባበሩት መንግስታትና አጋር አካላት ጋር እየተከናወነ መሆኑም ተመልክቷል።
በቅርቡም ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ወደ መቀሌ፣ አዲግራትና ሽሬ ከተሞች ተጓጉዟል። በተለያዩ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች እንደሚሰራጭ ይጠበቃል።ከመድኃኒቶቹ መካከል ድንገተኛ የኩላሊትና ለስኳር ሕሙማን እንዲሁም ለእናቶችና ሕጻናት ጤና አገልግሎት የሚውሉ ይገኙበታል።
ድጋፎቹ ወደ ተጠቀሱት የክልሉ አካባቢዎች ስለመድረሳቸው የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ያመለክታሉ።ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ይህ ርብርብ መንግስት በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ድጋፉን እያደረሰ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
መንግስት የሕግ የበላይነትን በአጭር ጊዜ እና በንጹኃን ላይ የከፋ ጉዳት ባላስከተለ መልኩ አጠናቋል።ዘመቻው በእዚህ መልኩ የተጠናቀቀው በርካታ የጥንቃቄ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ነው።ሰብዓዊ ድጋፍ የማቅረቡንም ስራ እንዲሁ መንግስት ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ አጠናክሮ ይቀጥላል።
የትግራይ ሕዝብ እና ህወሓት አይነጣጠሉም ሲል የቆየው ጁንታው፣የለኮሰው እሳት እየለበለው ሲመጣ እንደለመደው አጥፍቶ መጥፋት ውስጥ ገብቷል።በዚህም የትግራይ ሕዝብ ብርሃን ያየባቸውን መሰረተ ልማቶች አውድሞ ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ ጨለማ ውስጥ በመክተት ኑሮውን የዳበሳ አርጎታል።
አሁን የጁንታው ምዕራፍ ተዘግቷል።አሁን ትግራይን መልሶ ስለማልማት ነው የሚታሰበው።የመንግስትም አቋም ይሄው ነው። ከሁሉም በፊት ሰው ይቀድማልና መንግሥት ኃላፊነት እንደሚሰማው መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረሰ ያለበት ፍጥነትና ሁኔታ አድናቆት ሊቸረው ይገባል። ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ይህን የመንግስት ጥረት በተለያዩ መንገዶች በመደጋገፍ አጋርነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2013