ኢትዮጵያ የቀደመ ስልጣኔና አያሌ የድል ታሪኮች ባለቤት በመሆን ለጥቁር ህዝቦች ጭምር ተምሳሌት ሆና የኖረች አገር ብትሆንም፤ ይህንን ገናና ታሪኳን ግን አስጠብቃ ማቆየት አልቻለችም። ይልቁንም እነዚህ ታሪኮች ከጊዜ ወደጊዜ እየተበላሹ አንዴ በድርቅ፣ ሌላ ጊዜ በጦርነት ስሟ ሲነሳ ቆይቷል። ለዚህ ዝብርቅርቅ ታረኮቿ ደግሞ በየዘመናቱ የነበሩ መሪዎቿና በየደራጀው ያሉ አስተዳዳሪዎቿ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ።
በ27 አመታት የኢህአዴግ አገዛዝ ዘመንም በርካታ አዎንታዊ ስራዎች የመሰራታቸውን ያህል ለዘመናት የማይሽሩ በርካታ ቁስሎችም ተፈጥረዋል። በተለይ ወንጀለኛው የጁንታ ቡድን ህብረተሰቡን ለመከፋፈልና እርስ በርስ እንዳይተማመን የሰራቸው የተንኮል ሴራዎች እና መርዘኛ አስተሳሰቦች መታከም የሚገባቸው በሽታዎች ናቸው።
ይህ ቡድን ገና ከመጀመሪያው አነሳሱ ጀምሮ ይዞ የተነሳው ዓላማ በህዝቦች መካከል መርዘኛ አስተሳሰቦችን ማስረፅና ህዝብን ለብሶት በመዳረግ እርስ በርሱ እንዳይተማን ማድረግ ነበር። በዚህ የተነሳ አንዱ ብሄር ጨቋኝ፤ ሌላው ተጨቋኝ እንደሆነ ለማሳየት የሃሰት ትርክቶችን በመፍጠር እና በህብረተሰቡ ውስጥ በማስረጽ ህብረተሰቡ እርስ በርሱ እንዳይተማመን የመጀመሪያውን እርሾ ጠነሰሰ። ከዚያም በኋላ ለአገዛዝ ይመቸው ዘንድ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ የሙጥኝ በማለት እያንዳንዱ ዜጋ ካለው የጋራ ማንነትና እሴት ይልቅ ልዩነቱን እንዲፈልግና በዚህ ላይ ብቻ ተመስርቶም ሌላውን እንዲጠራጠር በየጊዜው ብሶት መመገቡን ተያያዘው።
ከሁሉ በላይ ችግሩን ከባድ ያደረገው ደግሞ ቡድኑ በተለይ በታዳጊዎችና በወጣቶች ላይ የዘራው የልዩነት እና በአቋራጭ የመክበር አባዜ ነው። ከትምህርት ስርዓቱ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች አዲስ የሚመጣው የህብረተሰብ ክፍል የራሱ ማንነት እንዳይኖረው ያለመታከት ሰርቷል። በተግባርም ህብረተሰቡ የሞራል ልዕልና እንዳይኖረው አድርጓል።
ለምሳሌ፣ በአመዛኙ ሀብት ሲያፈሩ የነበሩትና የተሻለ ኑሮ ሲኖሩ የሚታዩት አንድም በሙስና ውስጥ የተዘፈቁና ከጁንታው ቡድን ጋር ጥብቅ ቁርኝነት ያላቸው በመሆናቸው ከዚህ ውጪ ሀብታም መሆን እንደማይቻል የአስተሳሰብ ለውጥ እንደሚመጣ በማድረግ በኩል ትልቅ ስራ ሰርቷል።
በዚህ የተነሳ በርካታ ወጣቶች ለህሊናቸው ታማኝ በመሆን በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ሰርተው ወደ ብልፅግና ለመጓዝ ከመጣር ይልቅ በአቋራጭ ለመክበር ሲሄዱ ይስተዋላል። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ አንድም ምክንያታዊ አስተሳሰብ እየኮሰመነ እንዲሄድና በምትኩ አድርባይነትና ተልመጭማጭነት እንዲሰፍን፤ በሌላ በኩል የከፋ ስግብግብነትና አልጠግብ ባይነት እንዲዳብር አድርጓል።
ጁንታው ይህንን ለዘመናት የማይነቀል ክፉ አስተሳሰብ ሲያሰርፅ በዋናነት ጠያቂ እና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው ህብረተሰብ እንዳይፈጠር ነው። ምክንያቱም ጠያቂና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው ማህበረሰብ ከተፈጠረ ይህ ስግብግብ ቡድን እንደለመደው ከሚያግበሰብሰው ሀብት ትርፍራፊውን ለነዚህ አካላት እየወረወረ እንደፈለገ ለመኖር ስለማያስችለው ነው።
ወንጀለኛው ጁንታ ይህንን አስተሳሰብ ሲያሰርፅ ደግሞ ነገ አገር የሚረከበው ማነው የሚል ጥያቄም አላሳሰበውም። ምክንያቱም ቡድኑ ያላሸቀው የራሱን ልጆች ጭምር ነውና። አብዛኞቹ የጁንታው ልጆች በተለያዩ ውድ የሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩና እንዲሰሩ ቢያደርግም መልካም ስብእናና የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲያዳብሩ ባለማድረጉ ከራሱም ልጆች ሀገርን የሚረከብ ዜጋ ማውጣት አልቻልም። ለራሱ ልጆች “የነገዋ ኢትዮጵያ ሳትሆን፣ የነገዋ አውሮፓ ትበልጣለች” በሚል ከወዲሁ የውጭውን ዓለም እንዲለማመዱና ሀብታቸውም እዚያው አከማችተው እንዲኖሩ ሲሰራ ኖረ።
የዚህ ዋነኛ ዓላማ ደግሞ እነሱ በህይወት እስካሉ ድረስ ያላቸውን ሀብት በመጠቀም እዚህ እንደፈለጉ ለመሆንና ከነሱ ህልፈት በኋላ ልጆቻቸው ሀብታቸውን ይዘው በውጭ ሀገር በሰላም እንዲኖሩ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር አስበው ነው። እዚህ ያለው ህዝብ ግን እርስ በርሱ እንዲበላላ እና አገሪቷም ከነሱ ህልፈት በኋላ በራሷ መቆም የማትችል በማድረግ በመጨረሻ ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር ማጥፋት ትልቁ የነገ የቤት ስራቸው አድርገው ሲሰሩ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የቆየ ታሪክ ያላት፣ ህዝቦቿ ለሀገራቸው ቀናኢና ፈጣሪአቸውን የሚፈሩ በመሆናቸው ይህ እጣ ሳይገጥማቸው ወንጀለኛው ጁንታ የማታ ማታ ፅዋው ሞልቶበት ሴራው ሊከሽፍ ችሏል። በዚህም በአንድ በኩል እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፣ ህዝቦቿ እርስ በርሳቸው ይበላላሉ በማለት ቢያሟርትም ከዚህ በተቃራኒ ቡድኑን ወደመቃብር ለመሸኘት በአንድ ልብና መንፈስ በመተባበር ዳግም የአንድነት ክብራቸውን መልሰዋል። በዚህም ከጎሰኝነት ይልቅ ኢትዮጵያዊ አንድነትና ፍቅር አሸንፏል።
አሁን ቀሪው የቤት ስራ አንድና አንድ ብቻ ነው፤ የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ማድረግ። ይህ የሚመጣው ደግሞ በአንድ በኩል የመነጣጠልና የልዩነት ግንቦችን በማፍረስና የአንድነት እና የመደጋገፍ ማማዎችን ማጠናከር ሲሆን፤ በሌላም በኩል ለውጥና እድገት የሚመጣው በጠንካራ መዳፍ፣ በበሰለ አእምሮና በላብ መሆኑን በመገንዘብ እና ለዚህም በመትጋት ለእድገታችን በመጣር ነው። ስለዚህ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ዛሬን በትጋት እንጠቀምበት።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2013