የሀገር መከላከያ ሰራዊት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት፣ የሀገርን ዳር ድንበርና ሉአላዊነት የሚያስከብር፤ ከህዝብ የወጣ የህዝብ ታማኝ ልጅ ነው። አፈር ልሶ አፈር መስሎ፣ ጸሀይና ቁር ተፈራርቆበት፣ ዳገት ሸንተረሩን ወጥቶ ወርዶ፣ አካሉን አጉድሎ እና ህይወቱን ገብሮ የህዝብ ለዘመናት አለኝታነቱን አስመስክሯል። ለእኔና ለቤተሰቤ ሳይል ታላቂቱን አገር ኢትዮጵያን እያሰበና እያስቀደመ ህዝብና ሀገር የሰጡትን አደራ በብቃት ተወጥቷል። እሱ ደምቶና ተሰውቶ ህዝብን ከስደት፣ ሀገርን ደግሞ ከወረራና ከመፈራረስ ነፃ አውጥቷል።
ይሄ የኢትዮጵያ ህዝብ ኩራት የሆነው የመከላከያ ሰራዊት የሀገራችን ታሪካዊ ክብሯ ተጠብቆ፣ የጀግንነት ስሟ ዳግም በዓለም ላይ እንዲናኝም አድርጓል።‹‹ህዝብ ያልቃል፣ ሀገር ይፈርሳል፣ ይበተናል›› እያሉ ሲያሟርቱና በዓይነቁራኛ ሲከታተሉ የነበሩትን የውጪ ሀገራት በሰራው ታላቅ ጀብድ አሳፍሯል፤ አንገትም አስደፍቷል። በአንጻሩ ዳግም ኢትዮጵያውያንን በጀግንነታችን አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንጓዝ አድርጓል።
ከህዝብ ወጥቶ ለህዝብ እየሞተ ያለው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በተለይ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በጁንታው ከሀዲ ቡድን በተፈጸመበት አረመኔያዊ ጥቃት መላው ህዝብ ከዳር እስከዳር በቁጭት ተነሳስቶ አጋርነቱን በተለያየ መልኩ ገልጿል። ደም ለግሷል፤ የቤት እንስሳትና ሌሎች ቁሳቁሶችን መከላከያ ያለበት ድረስ ልኳል፤ አነሰ በዛ ሳይል የመንግስት ሰራተኛው ደመወዙን ሰጥቷል። ነጋዴው፣ ባለሀብቱ እና ሌላው ህዝብ ከትንሽ እስከ ትልቅ ገንዘቡን፣ ሀብትና ንብረቱን ሁሉ ለመከላከያ ሰራዊቱ ለግሷል።
ሙያተኛው በሙያው ለማገልገል ዘምቷል። በእነዚህ ድርጊቶች ሁሉ መላው ህዝብ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን መቆሙን በአደባባይ አስመስክሯል። አነሳሽና ቀስቃሽ ሳያሻው በራሱ ውዴታ ወጥቶ አጋርነቱንም አረጋግጧል። ይሄ
ደግሞ ለመከላከያ ሰራዊቱ ከምንም በላይ ትልቅ ሞራል ሆኖታል። ይሄንን የህዝብ ድጋፍና የሞራል ስንቅ ሰንቆም ተልዕኮውን በአጠረ ጊዜ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ በመወጣት በድል ላይ ድል ተጎናጽፏል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊቱም ከራስ በላይ ለህዝቤ የሚል እሴትን ያነገበ ነውና በተሰማራበት ሁሉ ቃሉን በተግባር አሳይቷል። ህዝብ የሚኖረው፣ ሀገር ሀገር ሆና መቀጠል የምትችለው፣ ወጥቶ መግባት መስራት ማቀድ፣ መማር… የሚችለው የተሟላ የተረጋገጠ ሰላም ሲኖር ነው። ይሄንን የሚያረጋግጥ ለህዝብና ለሀገር ሰላም መከበር ሌት ከቀን የቆመው መከላከያ ሰራዊቱ ነው። ከዚህ አንጻር ጀግናው መከላከያ ህዝብና መንግስት የሰጡትን ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን የማስከበር አደራውን በብቃት ተወጥቷል። በመሆኑም ህዝብ ካለመከላከያ ሰራዊት፣ መከላከያ ሰራዊቱም ካለህዝቡ ድጋፍ ለየብቻቸው መቆም እንደማይችሉም ታይቷል። አንዱ ለአንዱ ዋልታና ማገር ነውና የሰራዊቱ ጥቃት የአገርና የህዝብ፤ ድሉም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። በዚህም መነሻነት መላው ህዝብ የተለያየ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን አሳይቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም እንደሌላውም የሀገሪቱ ክፍሎች ሁሉ ለሰራዊቱ ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ ነው። ድጋፉ አጠቃላይ በገንዘብ ሲተመን ከአንድ ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ነው። ይህም በአዲስ አበባ ለመከላከያ ሰራዊቱ ለተደረገው ድጋፍ የእውቅና መርሀ ግብር በተካሄደበት ወቅት ተገልጿል። ይሄ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በአጭር ጊዜ ፣ያለ ማንም ቀስቃሽና ጎትጓች የተሰበሰበ ነው። ይሄ የሚያሳየው መከላከያ ሰራዊቱ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነትና በእያንዳንዱ ህዝብ ልብ ውስጥ የሰረጸ መሆኑን ነው።
ህዝቡ በዚሁ መልኩ ድጋፉን የቸረው የአገር መከላከያ ሰራዊት እውነትም የአገር ደጀን መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ በመሆኑ ነው። በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የተሰራው ሪፎርም መከላከያ ሰራዊቱ ‹‹የእኛና የእነሱ›› የሚለውን በሰዎች ዘንድ የነበረውን አስተሳሰብ የሰበረ ነው። አደረጃጀቱ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች ያቀፈና የስልጣን ተዋረዱም ሁሉንም በእውቀትና ብቃት ያማከለ መሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ፤ ለኢትዮጵያ ሀገራችን እንጂ ለየትኛውም ፓርቲ ያልቆመ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረበት ነው።
በቅርቡ የተገኘው ውጤትም የዚሁ ውጤት ማሳያ ምስክር ነው። ህዝቡም በአንድ ድምጽ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን እቆማለሁ ሲል የተደመጠው በዚሁ መነሻነት ነው። ለዚህም ነው መከላከያ ሰራዊቱ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ሰርጾ ገብቷል የምንለው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/213