የትግራይ ህዝብ በተለያዩ ዘመናት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበርና ሀገሪቱን ከውጭ ወራሪ ኃይል በመታደግ ረገድ የማይተካ ሚና ሲጫወት የቆየ ህዝብ ነው፡፡በሀገር ውስጥም ቢሆን የፊውዳልና ደርግን አምባገነን አገዛዝ በመታገልና ነጻነትና ፍትህ በሀገሪቱ እንዲሰፍን በርካታ መስዋዕትነቶችን የከፈለ፤ነጻነቱ ቀናኢ የሆነ ኩሩ ህዝብ ነው፡፡
ይህ ኩሩ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ሃይማኖተኛ ህዝብ ከመሆኑም ባሻገር እንግዳ ተቀባይና ያለውን አካፍሎ ሀዘንና ደስታን በጋራ የሚያሳልፍ ድንቅ ባህል ያለው ህዝብ ነው፡፡የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን ጋራ ለዘመናት ክፉና ደግ ያሳለፈና የሀገሩን ዳር ድንበር ላለማስደፈር በዱር በገደሉ የተጋደለ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
በተለይም አምባገነኑን የደርግ አገዛዝ ገዝግዞ ለመጣል በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ የትግራይ ህዝብ የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በተደረገው ትግል የትግራይ እናት ያለምንም ስስት ልጇን ለነጻነት፣ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለዴሞክራሲ እንዲዋደቅ ከጉያዋ አውጥታ የሰጠች የነጻነት ተምሳሌት ነች፡፡በዚህም ለነጻነትና ለእኩልነት ስትል እያንዳንዷ የትግራይ እናት ቢያንስ አንድ ልጇን አጥታለች፡፡
ሆኖም ግን የትግራይ እናቶች የከፈሉት መስዋዕትነት ከዳር ሳይደርስ በህወሓት ጁንታ ተጠልፎ ከዳር ሳይደርስ መክኖ ቀርቷል፡፡ ከደርግ ጋር በተደረገው ተጋድሎ ወደ ስልሳ ሺህ የሚጠጉ የትግራይ ወጣቶች መስዋዕት ሆነዋል፡፡በርካታ እናቶችም ያለጧሪ ቀርተዋል፡፡
ይህን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለችው የትግራይ እናት ግን አመድ አፋሽ ሆናለች፡፡ የትግራይ እናትም ሆነች ሌላው ህዝብ ከደርግ በባሰ መልኩ በአፈና ውስጥ ህይወቱን እንዲመራ በህወሓት ጁንታዎች ተፈርዶበታል፡፡ የመሰብሰብ፣ የመናገር፣ የመደራጀትና የመቃወም መብቶች ደብዛቸው ጠፍቶ በምትካቸው አምባገነናዊ አስተዳደር ነግሶ ቆይቷል፡፡የሰማእታት ዓላማ ገቢር ይሁን፣ እኩልነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ይስፈን ያሉ ወጣቶች መጨረሻቸው ወህኒ ሆኗል፡፡
የጁንታው አባላት ልጆች በአውሮፓና በአሜሪካ ውድ በሚባሉ ቤቶች እየኖሩና ዘመን አመጣሽ መኪና ሲያሽከረክሩ አራት ልጇቿን ለጦርነቱ የገበረች እናት ግን መንገድ ላይ ወድቃ ምጽዋት በመጠየቅ ላይ እንደምትገኝ የጁንታውን ቡድን የሚያውቁ ሰዎች እያጋለጡ ነው፡፡ዛሬ በርካታ የሀገራችን ከተሞች ያሳኩት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለመቀሌና አክሱም ነዋሪዎች ቅንጦት ነው፡፡
የትግራይ ህዝብ የሚያስፈልገው ልማት ሆኖ ሳለ ጁንታው መሳሪያ ሲያከማች፣ ልዩ ኃይል ሲያስታጥቅ፣ ምሽግ ሲሰራና ለጦርነት ሲዘጋጅ መቆየቱ አላንስ ብሎት የትግራይ ህዝብ የሚገለገልባቸውን መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ስልክ፣ መብራት፣ ባንክ እና አውሮፕላን ማረፊያ በማውደም አሳፋሪ ተግባር ፈጽሟል፡፡ግብዓተ መሬቱ መቃረቡን ያወቀው ይህ የጥፋት ኃይል የህዝቡን መገልገያዎችን በማውደም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ካለችው እንስሳ የከፋ አስተሳሰብ እንዳለው አሳይቷል፡፡
በክፋት ተጠንስሶ በክፋት ያደገው የህውሓት ሴረኛ ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት የመጨረሻ ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሞ ወንጀለኞች በሚታደኑበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የትግራይ ህዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ የነጻነት አየርን መተንፈስ ጀምሯል፡፡ በመላው ሀገሪቱና በሕዝቦች ላይ መከራ ሲዘራና ሲያሳጭድ ከአራት አሠርት ዓመታት በላይ በሽፍትነት እንዲሁም 27 ዓመታት በሀገር አስተዳዳሪነት የቆየው የዚህ እኩይ ቡድን ለፍርድ መቅረብ የሰማዕታት ደም ደመከልብ ሆኖ እንዳይቀርና የትግራይ እናቶችም እንባ እንዲታፈስ የሚያደርግ ነው፡፡
በመሆኑም የዚህ ጁንታ ቡድን አባላት ተይዘው ለፍርድ እስኪቀርቡ ድረስ በርካታ መከራና ሰቆቃ ያሳለፈው የትግራይ ህዝብ ከአዲሱ አስተዳደርና ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር በመሆን ጁንታውን በማደኑ ተግባር ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆን ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2/2013