አዲስ አበባ፡- የቤት ባለቤቶቹ ሳያውቋቸው በማህደራቸውና በቤት ቁጥራቸው ለ 94 ሰዎች መታወቂያ እንደወጣላቸው ማረጋገጥ መቻሉን በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሶስት አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዋስይሁን ባይሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በወረዳው ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የነበረውን ሰነድ ለማጥራት በተሰራው ስራ ድርጊቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል፡፡
ለማጥራቱ ሂደት መነሻ የሆነው በወረዳው የሚገኘው የቤት ቁጥር 441 ነዋሪ የነበሩት ግለሰብ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ በተፈጠረው የቤት ማስተላለፍ ሂደት በክፍለ ከተማው የሚሰራ አንድ ባለሙያ ከወረዳው ወሳኝ ኩነቶችና ነዋሪዎች አገልግሎት ባለሙያዎች ጋር በመመሳጠር በቤት ቁጥሩ ለሌላ ሰው መታወቂያ አውጥቶ በመገኘቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩም በፕሮሰስ ካውንስል ተገምግሞ በድርጊቱ ተባባሪ ሆነው በተገኙ ሁለት የወረዳው የወሳኝ ኩነትና ነዋሪዎች አገልግሎት ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች ላይ የዲሲፕሊን ክስ ቢመሰረትም ኮሚቴው ያሳለፈው ውሳኔ ግን በቂ እንዳልነበር ገልፀዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ወረዳው የጉዳዩን ክብደት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለካቢኔው ካቀረበ በኋላ ችግሩን የፈፀሙት ግለሰቦች እንዲባረሩ መደረጉን ዋና ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ድርጊቱ በተፈፀመባቸው ባለፉት 12 ዓመታት በወረዳው የአመራሮችና የባለሙያዎች መቀያየር እንደነበር ያስታወሱት ስራ አስፈጻሚው እያንዳንዱን ድርጊት ማን እና እንዴት እንደፈጸመው ለማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገውና በዚህም የተነሳ ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በእነዚህ መታወቂያዎች ምን ዕኩይ ተግባር እንደተፈፀመባቸውም ሆነ ለምን ዓላማ እንደወጡ አይታወቅም ያሉት አቶ ዋሲሁን በቀጣይም ጉዳዩን ለማጣራት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
በክፍለ ከተማው ወረዳ አራት ላይ ተመሳሳይ ችግር መኖሩን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ የውጭ አገር ዜግነት ላላቸው ነዋሪዎች ጭምር መታወቂያ መሰጠቱን መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አዲሱ የመታወቂያ አሰጣጥ ከመጀመሩ በፊት በየወረዳው ያሉትን ሰነዶች ማጥራትእንደሚገባም ሃላፊው አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 20/2011
ፍዮሪ ተወልደ