መላኩ ኤሮሴ
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰሞኑ የኒዩክለር ሃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል በኢትዮጵያና በሩስያ መካከል የተደረገውን የትብብር ስምምነት ረቂቅ አዋጁን መረምሮ ማጽደቁ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ የዝግጅት ክፍላችን በዘርፉ እውቀትን ካካበቱ እንግዳ ጋር ቆይታ አድርጓል። ከእንግዳችን ጋር ባደረግነው ጭውውት ምክር ቤቱ አዋጁን ማጽደቁና የኒዩክለር ሀይልን መጠቀም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ፤ ምን ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ፣ ኢትዮጵያ ካላት አቅም አንጻር ኒዩክለር ሀይልን መጠቀም ምን ያህል አዋጭ ነው? የሚለውን ጉዳይ ጨምሮ ማበልፀግ ከመጀመሯ በፊት ምን አይነት ዝግጅቶች ማድረግ እንዳለባት እና መወሰድ በሚኖርባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ዙሪያ ተጨዋውተናል። የዛሬው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል የኒዩክለር ፊዚክስ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ጥላሁን ተስፋዬ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኒዩክለር ሃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል በኢትዮጵያና በሩስያ መካከል የተደረገውን የትብብር ስምምነት ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል። ይሄ አዋጅ መፅደቁ ምን ፋይዳ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ጥላሁን፡- ምክር ቤቱ ሁለቱ አገራት አብረው ለመስራት የተዋዋሉትን ስምምነት ማጽደቁ በጣም የሚደገፍ እርምጃ ነው። ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ትልቅ ውሳኔ ነው። ምክር ቤቱ ይህን ውሳኔ በማሳለፉ ሊመሰገን ይገባል። በአገራችን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ታሪክ ውስጥ ትልቁ እርምጃ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ይህ ሲባል በበቂ ምክንያት ነው።
አንደኛው የሰው ልጅ በምርምር የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ መልሰን መጠቀም መቻል በማንኛውም ሁኔታ እና ጊዜ አስፈላጊ ነው። በአገራችን የኒዩክለር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፍላጎቶች በህክምና፣ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ መኖሩን የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶች አሉ። በጤና መስክ የሚታየው ጥናት የሚፈልግም አይደለም። የጨረር ሕክምና በብቸኝነት የሚሰጠው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን መመልከት በቂ ነው።
የኒዩክለር ሳይንስን መጠቀም ብቻ ሳይሆን ለእድገቱም አስተዋጽኦ ማድረግ የሚበዛብን አይደለም ፤ የሚቻልም ነው። ይህ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአገር ውስጥ መኖሩ ከዘረመል-ምህንድስና እስከ ማዕድናት አምራች ኢንዱስትሪዎች አቅም ይፈጥራል። በተጨማሪ የመከወን እና የፈጠራ አድማሳቸውን ያሰፋል። የአገራችን ወጣቶች በመስኩ ለመማር፣ ለመመራመርና ለመስራት እንዲችሉ በር ከፋች የሆነ አርቆ ያሰበ እና ያለመ እርምጃ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ለኢትዮጵያውያን የሚፈጥረው በራስ የመተማመን ነው። በሳይንስና ቴክኖሎጂ የመገስገስ በጎ እና አዎንታዊ ስሜት በብዙ አገሮች የታየ በመሆኑ በኛ አገርም መከሰቱና ከዳር እስከዳር መነቃቃትን መፍጠሩ አይቀርም። ስለዚህ ከሩሲያ ጋር ለመስራት መፈራረማችን አስፈላጊም ተገቢም ነው።
ሆኖም በብዙዎች ዘንድ አንድ የተሳሳተ እሳቤ አለ። ኢትዮጵያ ድሃ አገር ስለሆነች ‹‹ኒዩክለር ሳይንስ የቅንጦት ቴክኖሎጂ ነው›› አያስፈልጋትም ተብሎ ይታሰባል። ይህ እጅግ ስህተት ነው። ለዚህ ደግሞ አንዳንድ ማሳያዎችን ማየት ይቻላል።
በ1930ዎቹ አካባቢ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን የወደፊቱን አይተው የበረራ ቴክኖሎጂን (አውሮፕላንን) ወደ ኢትዮጵያ ባያመጡ ዛሬ የሚታየው ጠንካራ አየር መንገድ ኢትዮጵያ አይኖራትም ነበር። ያን ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሞላ መንገድ በሌለበት ነው አየር መንገድ ስራ ላይ የዋለው። ስለዚህ አንድን ቴክኖሎጂ ለማምጣት ሆድ እስኪሞላ፤ ልብስ እስኪሟላ እንጠብቅ ሊባል አይገባም።
በተጨማሪ የሞባይል ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የገባው የቤት ውስጥ (የመስመር) ስልክ በኢትዮጵያ ውስጥ ተዳርሶ ሳያልቅ ነው። የቤት ስልክ ሳይዳረስ የሞባይል ስልክ አያስፈልግም ቢባል ኖሮ የሚሆነውን ማሰብ ይቻላል። ሞባይል ንግድን፣ ጤና ጥበቃን፣ የኢንፎርሜሽን ልውውጡን እጅግ በጣም አቀላጥፎታል። ሌላው ቀርቶ የመስመር ስልክን የማዳረስ አቅምን አጎልብቶ ሌሎችንም መስኮች የሚደጉም አገራዊ አቅም ለመሆን በቅቷል።
ቴክኖሎጂን በፍጥነት ማላመድና በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ስራ ላይ ማዋልን በተመለከት ሌላም ተጨማሪ ማሳያ ማንሳት ይቻላል። ሰሞኑን የድሮን ቴክኖሎጂ ህግና ስርዓትን በማስከበር ረገድ የተጫወተውን ሚና ማንሳት ነጥባችንን አጉልቶ ለማሳየት ይረዳል ብዬ አምናለሁ። ይህ ቴክኖሎጂ ባይኖር፤ ሰሞኑን የነበረው ህግና ስርዓትን የማስከበር ክንውን ባየነው አይነት ቅልጥፍና እና አስደናቂ ፍጥነት አይከናወንም ነበር። በዚህ ረገድ ዝግጁ ሆነን መገኘታችን በርካታ ህይወት ታድጓል፤ ንብረትንም አድኗል። ስለዚህ አንድን ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እኛ ገና ነን ሊባል አይገባም።
በማንኛውም ሁኔታ ቴክኖሎጂን ለመቀበል እና ተጠቃሚ ለመሆን እኛ ገና ነን መባል የለበትም። የዓለም ቴክኖሎጂም ይህንኑ ነው የሚያሳየን። ሕንዶች ነጻ እንደወጡ ዓመት ወይም ሁለት ዓመት ሳይቆዩ ነው የኒዩክለር ቴክኖሎጂን ስራ ላይ ያዋሉት። አሁን በራሳቸው የበለጸግ የኒዩክለር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከመሆን አልፈው ለሌሎች አገራት የተረፉት በምግብ እንኳን ራሳቸውን ሳይችሉ ስለጀመሩት ነበር። ይህ ብቃታቸው አሁን የምግብ ፍላጎታቸውን በማረጋገጥ በኩል ሁነኛ ሚናም አለው።
ሲጠቃለል በማንኛውም ሁኔታ ቴክኖሎጂን መቀበልና ማቀፍ ተገቢና ትክክል ነው። በተለይም የኒዩክለር ቴክኖሎጂ ሌሎች ፍላጎቶች እንዲሟሉም የሚያግዝ አቅም መገንቢያም በመሆኑ ትኩረት ማግኘቱ ተገቢ ነው። ለምሳሌ አሁን የኒዩክለር ቴክኖሎጂ ቢኖር ኖሮ የምግብ ዋስትና የተሻለ ይሆን ነበር። የጤና አጠባበቅ ስርዓታችን የበለጠ ስኬታማ ይሆን ነበር። ስለዚህ በፈቀደ መጠን ቶሎ ማቀፍና መጨበጥ ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያን የኒዩክለር ሳይንስ ሁኔታ ስናይ በአፍሪካ ደረጃም ቢሆን ቀዳሚዎች አይደለንም። ከ10 በላይ አገራት የኒዩክለር ቴክኖሎጂን በተለያየ ደረጃ እየተጠቀሙና ስራ ላይ እያዋሉ ነው። በጥናትና ምርምር፣ በሀይል ምንጭ፣ በጤና ጥበቃ፣ በሃይል ወዘተ ብዙ እርምጃ ተራምደዋል።
በአፍሪካ ደረጃ እንኳ የኢትዮጵያ ውሳኔ የዘገየ እንጂ የፈጠነ ውሳኔ አይደለም። የአፍሪካ አገራት እንኳን በብዙ ዓመት ቀድመውናል። በሩብ እና በግማሽ ምዕተ ዓመት ቀድመውናል። ኮንጎ እንኳ ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በኒዩክለር ቴክኖሎጂ ስትጠቀም ኖራለች። ግብጽና ደቡብ አፍሪካ ጥናትና ምርምር አልፈው ሀይል ወደ ማመንጨት ገብተዋል።
ይህ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱ ታላላቅ ግኝቶች መካከል ወደር የማይገኝለት፣ በኢንዱስትሪው ዓለም አስተማማኝ የሃይል ምንጭነቱ የማይዋዥቅና የተረጋገጠ፣ በሳይንሱ ደግሞ ፍጥረተ ዓለምን የምንረዳበትን መንገድ ከመሰረቱ የቀየረ፣ በፍልስፍናም ጭምር የላቀ አንደምታ ያለው ትልቅ ጉዳይ ነው። ይህ ጉዳይ ግንዛቤ አግኝቶ በመንግስት ደረጃ እርምጃ መጀመሩ በእውነቱ ትልቅ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የኒዩክለር ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ለምን ጉዳይ ሊውል ይችላል?
ዶክተር ጥላሁን፡- የጉልበት ተደራሽነት ለኢኮኖሚ እድገት እጅግ መሰረታዊ ግብዓት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሀይል ምንጮችን ብንመለከታቸው አብዛኛው ከውሃ የሚመነጩ ናቸው። በመጠኑ የንፋስ ሀይል አለ። ጅምር የሆነ የጂኦ ተርማል ሀይል አለ። ሌላው የነዳጅ ዘይት ጄኔሬተሮች ናቸው።
እነዚህ የሀይል ምንጮች አብዛኞቹ ብዙ ቦታ የሚጠቀሙ፣ አካባቢ የሚበክሉ እና አስተማ ማኝነት የላቸውም። ለምሳሌ በኢት ዮጵያ ውስጥ ለሁለት ወይም ሶስት ዓመታት ተከታታይ ድርቅ ቢከሰት የምንቸገረው ለእርሻ ብቻ አይደለም። እቤታችን የሚመጣው ኤሌክትሪክም ይደርቃል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ያላትን የሀይል ምንጮች ብዙ አይነት ማድረግ ያስፈልጋታል። በሌላ አነጋገር በአንድ አይነት ምንጮች መወሰን ከፍተኛ የሆነ የጉልበት እጥረት ተጋላጭነት ያስከትላል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ እየሄደ እና በጣም እየሰፋ ያለ ኢኮኖሚ ነው። ከጥቂት ዓመታት በኋላ አሁን ያሉንን የሀይል ምንጮች አሟጠን ብንጠቀም እንኳን የምናመርተው የኤሌክትሪክ ጉልበት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚፈጠረውን የኤሌክትሪክ ጉልበት (ኢነርጂ) ፍላጎት መሸከም የማይችሉበት ደረጃ ላይ መደረሱ አይቀርም። የሀይል ምንጭ አቅርቦት ደግሞ ችግሩ ሲመጣ አይደለም የሚታሰበው። አስቀድመህ ተዘጋጅተህ፣ አቅደህ ከስር ከስር እየሞላህ፤ የዛሬ 5 ዓመት የሚኖርህን ፍላጎት ዛሬ እየሞላህ የምትሄድ አይነት ካልሆነ በስተቀር አዳጋች ነው።
ስለዚህ የኒዩክለር የሀይል ምንጭ አስፈላጊ ነው። በተለይ ከኢኮኖሚ አንጻር በጣም አስፈላጊ ነው። የኒዩክለር ሀይል እንደሌሎቹ የሀይል ምንጮች ለተፈጥሮ፣ የአየር ሁኔታዎች ተለዋዋጭነት የሚበገር አይደለም፤ አይለዋወጥም። ለምሳሌ አውሮፓና አሜሪካ አካባቢ ያየን እንደሆነ ቤዝ ላይን ሎድ የሚባለው የኤሌክትሪክ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት ከኒዩክለር ሀይል ነው። የኒዩክለር ሀይል ተለዋዋጭ ሳይሆን አስተማማኝ የሀይል ምንጭ ነው። ቤዝ ላይን ሎድ የሚባለው የሀይል አቅም ሊኖረን ይገባል።
ሌላኛው የኒዩክለር ሀይል ጠቃሜታው ወጣ ገባ አይደለም። በጣም የተረጋጋ የሀይል ምንጭ ለማግኘት ይጠቅማል። በተለይ እንደኛ ያለ ድሃ አገር የሃይል ነጻነትና ደህንነት ያስፈልገዋል። ይህ ደግሞ ለአገር ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መረጋጋት በጣም ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነገር ነው። እዚህ ላይ መሰራት አለበት። በነዚህ ምክንያቶች ለኢትዮጵያ የኒዩክለር ሀይል አስፈላጊነት ቅንጦት አይደለም፤ አስፈላጊ ነው። መሰረታዊ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሃይል መጠቀማችን የትኞቹን ዘርፎች በቀዳሚነት ተጠቃሚ ያደርጋል?
ዶክተር ጥላሁን፡– ለኢትዮጵያ ዋነኛው ነገር የኢነርጂ ፍላጎት ማሟላት ነው። ሁለተኛው የኒዩክለር ቴክኖሎጂ በጤና ጥበቃ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ለምሳሌ የጨረር ህክምና፣ የጨረር ምርመራ መነሻው የኒዩክለር ቴክኖሎጂ ነው። በሀገራችን ውስጥ ብቸኛው የካንሰር ማከሚያ ሆስፒታል ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው። ተራ ሳይደርሳቸው የሚያርፉ ብዙ የካንሰር ህመምተኞች አሉ። ቦታው ሞልቶ በየበረንዳው ሰዎች ወረፋ ሲጠብቁ ይታያል። ይህ ለምን ይሆናል?
የኒዩክለር ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲጀመር ብዙ ተዛማጅ ጥቅሞች ተያይዘው ይፈጠራሉ። ለምሳሌ ለኒዩክለር ህክምና የሚያገለግሉ የአቶም ዝርያዎችን (አይዞቶፖችን) ማምረት ያስችላል። እስከአሁን የምንጠቀመው ከውጭ በገቡ አይዞቶፖች ሲሆን ተጓጉዘው፣ በጉምሩክ ቆይተው ስለሚገቡ በፍቱንነታቸው ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ በመኖሩ ይህን ተፅዕኖ በሀገር ውስጥ በማምረት የሚወገድበት ዕድል ይፈጠራል።
ከኒዩክለር ሪአክተር የሚገኝ የኒዩትሮን ጨረር እጅግ በጣም ብዙ የምርምር ጥቅሞችን ያስገኛል። ከነዚህ ጥቅሞች ጥቂቶቹን ልግለጽ፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ታንታለም ታመርታለች። ከአፈር ውስጥ የሚወጣው የታንታለም ጥሬ ነገር ምን ያህል ታንታለም ተሸክሟል፣ ምን ያህል ሌሎች ማዕድናት አሉት፣ ምን ያህል ዩራኒየም አለው የሚለው የሚመረመረው ውጭ ሀገር እየተላከ በዶላር እየተከፈለ ነው። ውጭ ተመርምሮ የላብራቶሪ ውጤት አገር ውስጥ እየመጣ ለኤክስፖርት ሰርቲፊኬት እየተሰጠ ነው የሚላከው። ይህ በብዙ የልዩ ቁስ ትንተና (የኤሌሜንታል አናሊሲስ) በሚፈልጉ የኢንዱስትሪ መስኮችም ያለ ነገር ነው።
ኢትዮጵያ የኒዩክለር ፓዎር ፕላንት አላት ማለት ብዙ የማዕድን ዘርፎች የኤሌሜንታል አናሊሲስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተዛማጅ ጥቅም አለው። ኢትዮጵያ የውቂያኖስ ዳርቻ ስለሌላት እንጂ ብዙ የውቂያኖስ ዳርቻ ያላቸው አገሮች ውሃን ከጨው ለማጽዳት የሚጠቀሙበት የኒዩክለር ቴክኖሎጂ አለ። በእኛም አገር በመንገድ ስራ እና በማዕድን ፍለጋ ላይ የኒዩክለር ቴክኖሎጂ በሰፊው በጥቅም ላይ ይውላል።
በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የኒዩክለር ቴክኖሎጂ አቅም የሚያስገርም ነው። እንደሚታወቀው በምግብ ራስን መቻል ማለት ብዙ ማምረት ብቻ ሳይሆን ብክነትንም መቀነስ ነው። በዚህ ረገድ የኒዩክለየር ቴክኖሎጂ ሁነኛ ሚና አለው። የመጠበቂያ እና የማከማቻ ዘዴ ያስፈልጋል። ኒዩክለር ቴክኖሎጂ እንዲህ አይነት ጥቅም አለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመረተው አትክልትና ፍራፍሬ 30 በመቶ ገደማ የሚሆነው በክምችት ችግር ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ ይሆናል። ብዙ አገሮች እንደ ሽንኩርት፣ ድንችና እና ሌሎች ምርቶችን በጨረራ በማከም የመቆያ ጊዜያቸውን ያስረዝማሉ። ለምሳሌ ሽንኩርትን ጨረራ በመጠቀም ሳይበላሽ የሚቆይበት እድሜ (ሸልፍ ላይፍ) ይረዝማል። ሳይበላሽ የሚቆይበት እድሜ ረዘመ ማለት ከሚጣል እየወጣ ወደ ሚበላ ገባ ማለት ነው።
ኢንዱስትሪ ውስጥ በእኛ አገር የሚመረተው ጨርቃ ጨርቅና ፕላስቲክ ነገሮች ናቸው። መቼ ነው እኛ የሞባይል ክፍሎችን የምናመርተው፣ ቴሌቪዥኖች እዚህ ይገጣጠማሉ፣ የሚገጣጠሙ በአንድ ስኩየር ሴንቲ ሜትር ላይ በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ የኤሌክትሪክ እትበት አካሎች የሚሰሩት በጨረራ ቴክኖሎጂ ነው። በሰው ብሎን እየታሰረ አይደለም የሚሰራው። እንዲህ አይነት ነገሮች የሚጋገሩት በጨረር ቴክኖሎጂ ነው። ኢንዱስትሪ ውስጥ የኒዩክለር ቴክኖሎጂ ትልቅ ሚና አለው። አንድ ኒዩክለር ሪአክተር ኢትዮጵያ ውስጥ ተቋቋመ ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ሁሉ በትልቅ እርምጃ ከፍ ይላሉ ማለት ነው። ብዙ ዘርፎች የሚያዳርስ አቅም በአገር ውስጥ ይፈጠራል ማለት ነው።
የኒዩክለር ቴክኖሎጂ ለኢንዱስትሪዎች፣ ለኢነርጂ፣ ለጤና ዘርፎች ካሉት ጥቅሞች በተጨማሪ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት ከፍተኛ ሚና ይጨወታል። የኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማት የኒዩክለር ሳይንስና ቴክኖሎጂን አገር ውስጥ ማሰልጠን ይጀምራሉ። አገር ውስጥ የሰው ሀይል ማፍራት ይጀመራል ማለት ነው። ይህ ማለት ልጆች ሲማሩ ዝም ብለው ያለውን ነገር ተጠቃሚ አይደለም የሚሆኑት። አዳዲስ ቴክሎጂዎችን እና አገልግሎቶችን ይከፍታል።
እነዚህ የሳይንስና የምርምር መስኮች አገር ውስጥ የሚፈጥሩት አቅም አለ። ይህ አቅም ወደ ሌሎች ዘርፎች ሁሉ የሚዛመት ነው። የመሸጋገር አቅም ነው። ስለዚህ ጥቅሞቹ ዝም ብሎ አንድና አንድ ሁለት የሚባል አይነት አይደለም። እጅግ በጣም ዘርፈ ብዙ እና በጣም መሰረታዊ ጥቅሞች አሉት።
ስለቦንብ የሚወራውን ብቻ መረጃ ያለው ሰው ኒዩክለር ቴክኖሎጂን በአዎንታዊነት ሊለያይ ይችላል። የኒዩክለር ቴክኖሎጂ በታሪክ አጋጣሚ በቦንብ ይጀመር እንጂ ከዚያ ወዲህ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በሰላማዊ የኒዩክለር አጠቃቀም ብዙ ርቀት ተሂዷል። ሰላማዊ ጥቅሞቹ በጣም በርካታ ናቸው።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012