ዳግም ከበደ
የሰሞኑ ክስተት ብዙ አሳይቶናል። የሚበጀንንና የማይለየንን ወዳጅ እንድንለይበት ምክንያት የሆነም ነበር። የመከራ ወቅት ወዳጅ ጠላትህን ትለይበታለህ እያለ ብልሃትን በሚያስተምር ማህበረሰብ ውስጥ ስለምንኖር አጋጣሚውን ለዚሁ እየተጠቀምንበት ነው። ምንም እንኳን በክፉ ጊዜ ችግርህ ላይ የምታተኩር ቢሆንም ቅሉ ነገሩ በረድ እያለ በመጣ ቁጥርና ማስተዋል አድማሱን ሲያሰፋ በዙሪያህ የሚሆነውን ሁሉ መታዘብ ስለማይቀር እኛም እየሆነብን ያለውን ሁሉ መመዝገብ ጀምረናል።
ጠላት ከሩቅ አይመጣም እንዲሉ ብሂሉ ተግባር ላይ ውሎ ጉያችን ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችን ጦር ሰብቀውብን እንደ እየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ጎኗን በጦር ወግተዋታል። ይህ አልበቃ ብሏቸው ሰላም ፈላጊነታችን ላይ ተሳልቀዋል። ወንድም ወንድሙን ሲያማው እንደሚሰቀጥጠው ሁሉ በዙሪያችን እየተሽከረከሩ ተጨማሪ ጠላት ሊሸምቱልን ላይ ታች ደፋ ቀና ሲሉ አስተውለን እንዳላየ አልፈናል።
ታሪክ እንዲህ ይለናል። ኢትዮጵያ ከጉያዋ በሚወጡ ባንዳዎች ለዘመናት ጀርባዋን ስትወጋ ኖራለች። ጀግኖች አርበኞቿ ደግሞ ይህን ዓይን ያወጣ ብልግና ሲመክቱ አገራቸው ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ደጀን ሲሆኑ ኖረዋል።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተገኝተው ወንበዴዎቹ አገር ለማፍረስ ሲታትሩ ድል እንደተመቱ ይፋ ሲያደርጉ ምን ነበር ያሉት፤ ‹‹እንግዲህ ምን ታደርጉት እኛም ያባቶቻችን ልጆች ነን። ጀግንነታቸውን በጎ አላማቸውን ወርሰናል›› በማለት አገር ለማፍረስ ከሰይጣን ጋር ተወዳጅተው በእኩይ አላማቸው ነሁልለው ዘራፍ የሚሉትን የባንዳ ልጆች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በታላቅ ድል መክቶ የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ እንደከተታቸው ሲናገሩ በታላቅ ወኔና ኢትዮጵያዊ መንፈስ ነበር።
ከሁሉም ከሁሉም ግን ወንድሞቻችን ጦር ሰብቀው ስለወጉን ብቻ አልነበረም ቁጭትና እልህ ውስጥ የገባነው። ይልቁንም የዚህን እኩይ ቡድን አላማ ከውጭ ሆነው ፖለቲካዊ ጥቅማቸውን ለማሳካት ሲሉ መደገፋቸው ይበልጥ የሚያንገበግብ ነበር። ለዚህ ነው ክፉ ጊዜ ወዳጅና ጠላትን ለመለየት ይጠቅማል የሚለው የአገሬ ሕዝብ።
ታሪክ ደግሞ እንዲህ ይለናል። ቀድሞውንስ ቢሆን የውጭ ኃይሎች ሉዓላዊነታችንን በፀጋ ለመቀበል መች ፈልገው ያውቃሉ? ለሺህ ዘመናት የተገነባ አገረ መንግሥት ያላት ኢትዮጵያ ግን በውስጥ ጉዳይ ላይ ሊፈተፍቱ የሚሹ እኩያንን ስትመክት ዳር ድንበሯን ስታስከብር ኖራለች።
ከሰሞኑ ደግሞ ዓለም አቀፍ ተፅእኖ መፍጠር እንችላለን የሚሉ አካላት መንግሥትን ለመወጠር እና ቅርቃር ውስጥ ለመክተት የሚያደርጉት መንፈራገጥ እያስገረመን ነው። አንዳንዶች የኢትዮጵያውያንን አኩሪ ታሪክና ሉአላዊነት በማክበር በሕግ ማስከበርና በውስጥ ጉዳያችሁ አንገባም ብለው እጃቸውን ሲሰበስቡ፤ በተቃራኒው ግን በሰው ጉዳይ ላይ እንደ እርጎ ዝንብ በመግባት ሰፊ ታሪክ ያላቸው አካላት እጃቸውን ለመዶል ሲጋጋጡ እያስተዋልን ነው።
በፌዴራል እና በትግራይ ክልል መንግሥታት መካከል ድርድር ይካሄድ የሚሉ ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ድርጅቶችም ይሁኑ አገራት በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውንና እየተካሄደ ያለውን በትክክል ያልተገነዘቡ ናቸው። በርካታ አስተያየት ሰጪዎች የድርድር ጊዜው ማለፉን ገልጸዋል። ይሄ ሃሳብም በሁሉም መመዘኛ ትክክል ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተገኝተው ላለፉት ዓመታት መንግሥት ከጁንታው ቡድን ጋር ድርድር ለማድረግ እጅግ ብዙ ጥረቶችን ማድረጉን ጠቅሰዋል፤ ቡድኑ ግን የመፍትሄ ሃሳቦችን ሲገፋና በንቀት ልቡን ሲወጥር ቆይቷል። አሁን ላይ ግን የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገርና ጊዜ ለመግዛት ድርድር ፈላጊ አስመስሎ ራሱን አቅርቧል። የአደራድሩኝም እየዬውንም በውጭ አገራት ባሰማራቸው ግልገል ባንዳዎች እስከ ሽንፈቱ ዕለት ድረስ ሲነዛ ቆይቷል።
ጁንታው ለማደናገሪያነት ወቅታዊው ችግር በፖለቲካ መፍትሔ እንዲያገኝ ደጋግሞ የጠየቀ ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ ድርድር እንደማይኖርና የመጨረሻ የተባለው ሕግ የማስከበር ተግባር በቀጣይ ቀናት እንደሚከናወን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ግልፅ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ይህን እቅዱንም ሙሉ ለሙሉ በማሳካት ቃሉን ወደ ተግባር ቀይሮታል። የትግራይን ሕዝብ ከዚህ እኩይ ቡድን በመነጠል ቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ እንዲመሽግ አድርጎታል።
በዚህ ሰዓት ነው እንግዲህ አንዳንድ ምዕራባውያንን ጨምሮ የቀድሞ ዲፕሎማቶች መቅበዝበዝ የጀመሩት። ሁሌም ቢሆን በሰላም ማስከበር ስም ዳግማዊ የቀኝ ግዛት ሰንሰለት ለመዘርጋት የሚጥሩ መሆናቸው ይታወቃል። በዚህ ምክንያት ነው አገራቱ የጁንታው አከርካሪ መሰበር አልዋጥ ብሏቸው በየሚዲያው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ለሙሉ የደገፈውን ዘመቻ ሲያብጠለጥሉ የተደመጡት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ለዚህ ቁርጥ ያለ መልስ የሰጡ ይመስለኛል።
በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ኢትዮጵያ በነጮች ዓለምን እንደፈረስ የመጋለብ ቅጥ ያጣ ህልምና የቀኝ ግዛት መቧቸር ውስጥ ያልተካተተች ሉአላዊ አገር መሆኗን ታሪክን በማጣቀስ አስረድተዋል። ይህቺ የሥልጣኔ ጀማሪ የሰው ልጆች ልክ መገኛ ከአፍሪካ አገራት በብቸኝነት ቅኝ ካለመገዛቷም ባሻገር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች መሆኗንም ጠቅሰዋል።
ታዲያ ይህን ሁሉ ምሳሌ ሲያጣቅሱ እንዲሁ ለይስሙላ እንዳልነበር ገልፀዋል። ይልቁንም ምዕራባውያኑም ሆኑ አንዳንድ የዓለም አቀፍ ተቋማት የትህነግን እስትንፋስ ለማስቀጠል ተደራደሩ ማለታቸው ኢትዮጵያውያን ካላቸው የብዙ ዘመናት አገርን የመምራት ታሪክ አንፃር ሊቀበሉት የማይችሉት ግፊት መሆኑን ለማስረዳት ተጠቅመውበታል።
በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል የወጣውን እባጭ ለማስተንፈስ በውስጥ አቅም ሕግን የማስከበር ዘመቻ ተደርጎ ወሳኝ ድል መገኘቱን አመልክተው፣ የውጭ ኃይሎች ግፊት ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከሊህቅ እስከ ደቂቅ የሚደገፍ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን በመካከላችን የሃሳብ ልዩነት ቢኖረንም፣በአገር ሉአላዊነት ላይ የማንደራደር መሆናችን ነው። በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስገነዘቡት ‹‹ምንም ደሃ ብንሆን ለራሳችን ክብር አለን። የእርዳታ ፍርፋሪ ለመቀበል ሲባል በተፅእኖ ስር የምንወድቅ አይደለንም›› ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። ሉአላዊ ነን ስንል በተግባር ትርጉሙን፤ የነፃነትን ጥልቅ ስሜትን የምንረዳ ለዚያም የሚመጥን አገረ መንግሥት ያለን ኩሩ ሕዝቦች ነን።
ከዚህ መነሻ በአገራችን በመላው አካባቢ የተጀመረው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በውስጥ አቅምና ብቃት የሚያልቅ እንጂ እንደ እርጎ ዝንብ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት በሚግተለተሉ ምኞተኞች ፍላጎት የሚፈፀም አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
ለዚህ ነው በዚህ የአጭር ቀን የሕግ የማስከበር ዘመቻ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ጠላትና ወዳጃቸውን ለይተዋል የሚል ሃሳብ ለማንሳት የወደድኩት። ትህነግ ላለፉት 30 ዓመታት የኢትዮጵያውያንን ልብ ሰብሮ መርዙን እስኪተፋ ድረስ የልቡን እየፈፀመ የኖረ ባንዳ መሆኑ ግልፅ እንደሆነው ሁሉ፤ እርሱን አደብ ለማስገዛት በተደረገው ዘመቻ ላይ አሰላለፋቸውን ከመርዘኛው ቡድን ጋር ያደረጉ ጠላቶቻችንን ለይተንበታል።
በተቃራኒው ደግሞ በትህነግ ሴራ ጠላት አድርገን ፈርጀናት የቆየናትን ኤርትራ የኢትዮጵያውያን የቁርጥ ቀን ወዳጅ መሆኗን አረጋግጠንበታል። ሉአላዊነታችን በጎውንም ክፉውንም እንድንለይ ያደረገን አጋጣሚ ያስቃኘን የነፃነታችን ምሳሌ የአንድነታችን መሠረት ነው። ለዚህ ነው ሉአላዊ ነን ስንል ዓለም በዚህ መንገድ እንዲገነዘበን የምንሻው! ሰላም
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012