ህብረ ብሄራዊነት በጉልህ የሚታይባት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ “ትንሿ ኢትዮጵያ” በሚለው ቅጽል ስሟ ትጠራለች፤ ማራኪ የአየር ጸባይ፣ ውብ ጎዳናዎች፣ ለዓይን በሚስብ ባለቀለም አልባሳት የተዋቡ ህዝቦችና የሰው ብቻ ሳይሆን የአእዋፍን ልብ አሸፍቶ በዙሪያው ያሰፈረ ሀይቅ ባለቤት ናት፤ ሐዋሳ። በአራተኛው የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ጉባኤ ለመሳተፍ ከትናንት በስቲያ ከጓዳዋ ያሳደረቻቸው ወጣቶች ትናንት ማልደው ወደ ጉባኤው አዳራሽ ሲያመሩ በሐዋሳ ውብ መንገዶች ላይ ሲታዩ እውነትም ኢትዮጵያ እንደ አቶ ብናልፍ ገለጻ፤ ምንም እንኳን ወጣቱ የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎው እያደገ ቢሆንም፤ ያሏቸው ጥያቄዎች ግን አሁንም እንዳልተፈቱ ኢህአዴግ በቅርቡ ባካሄደው ጉባኤው ለይቷል።
እነዚህ ችግሮች እስካልተፈቱለትና ጥያቄዎቹም እስካልተመለሱ ደግሞ ለውጡ ቀጣይ እንደማይሆን በመገንዘቡም የወጣቶችን ጥያቄ ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። ይሁን እንጂ ስራው ያለወጣቱ ተሳትፎና አጋርነት ከዳር ስለማይደርስ በዚሁ አግባብ ተገንዝቦ መስራት ይኖርበታል። ምክንያቱም ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በስሜት ሳይሆን በምክንያት ተጉዞ ችግሮችን የሚፈታ፤ መብትና ግዴታውን አውቆ የሚሰራና የሚጠይቅ፤ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል፤ እንዲሁም አገራዊ ሃላፊነቱን በቁርጠኝነት የሚወጣ ወጣት ትፈልጋለች።
ዛሬ ላይ ለላቀ ሃላፊነት ታጭተው በዩኒቨርሲቲ ያሉ ወጣቶችም ይሄን ተገንዝበው አንድነትና ሰላማቸውን መጠበቅና ነገ አገር ከእነርሱ የምትፈልገውን ለማበርከት መስራት ይኖርባቸዋል። የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግም በቆይታው አዳዲስ ወጣቶች የሚቀላቀሉበትን፤ በራሱ አጥር ውጪ ሌሎችን የሚያሳትፍበትን አቅጣጫ መመልከት ይገባዋል።
የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ሙቀት ታረቀኝ እንዳለው፤ የተገኘው ለውጥ አንድም በወጣቱ የማይገባ የሕይወት መስዋዕትነት፤ አንድም በኢህአዴግ ውስጥ ባሉ ጥቂት የቁርጥ ቀን ልጅ አመራሮች እንደመሆኑ ሁሉም አካል ከለውጡ አመራሮች ጋር በመሆን መስራት ይጠበቅበታል። ሊጉም በዚሁ አግባብ የሚሰራ ሲሆን፤ በቀጣይም ከአባት ድርጅቱ ኢህአዴግ ጋር በመሆን አገርና ህዝብ ከወጣቱ የሚጠብቁትን ለማበርከት የሚችልበትን እድል ለመፍጠር ይሰራል። ወቅቱም የአገር ገጽታ እየተገነባ፣ ወጣቱም ተደራጅቶ ለመስራት የተዘጋጀበት፣ ነጻነትና ዴሞክራሲ የተከበረበት ነገር ግን በአግባቡ ካልተያዘ ስጋት መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልግበት እንደመሆኑም ወጣቱም ይሄን ተገንዝቦ መስራት ይጠበቅበታል።
“እያንዳንዱ ዘመን የራሱ ጀግና ይፈልጋል” ያለው ወጣት ሙቀት፤ አባቶች በባህላዊ መሳሪያ ታግዘው የውጭ ወራሪን በማንበርከክ ታሪክ የማይዘነጋው ገድል እንደፈጸሙ ሁሉ፤ የዚህ ዘመን ትውልድም ያለውን እውቀትና ዘመናዊ መሳሪያ ተጠቅሞ የኢትዮጵያን የድህነት ካባ ማውለቅ እንደሚጠበቅበት አሳስቧል። ይህ የሚሆነው ደግሞ በአንድነትና በፍቅር ተደምሮ ለጋራ ልማትና ሰላም መስራትን የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝቦ መስራት አለበት። ሊጉም በዚሁ አግባብ የሚሰራ ይሆናል። ሊጉ በሶስት ቀናት ጉባኤው፣ ያለፉት ሂደቶችን የሚገመግምና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር ሲሆን፤ በማጠቃለያውም የሊጉን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር የሚመርጥ መሆኑ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ጥር 20/2011
ወንደሰን ሽመልስ