ከ72 ዓመታት በፊት በግርማዊ ቀዳማዊ ዓጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጉዞውን ጥልቅ ራዕይ ይዞ ጀመረ። ዲሲ 3 በምትባል አውሮፕላን ከአዲስ አበባ በአስመራ አቋርጦ ወደ ግብጽ ካይሮ በረራውን አሃዱ ብሎ የተነሳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወጥነት ባለው የአገልጋይነት መንፈስ የአገሪቱን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ከፍ በማድረግ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ኩራት እንደሆነ ይገለፃል። በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ተደራሽ በመሆን ከ119 ዓለም አቀፍና ከ20 በላይ የአገር ውስጥ መዳረሻዎች በመብረር ለአገሪቱ ብሎም ለመላው አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ፤ ባህላዊ እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
አየር መንገዱ ታዲያ ትናንት ትልቅ የምረቃ ሥነሥርዓት አካሂዶ ነበር። የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ማስፋፊያና የኢትዮጵያ ስካይላይት ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል። የእለቱ የክብር እንግዳ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው። በዕለቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሐመት፣ አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታዳሚ ሆነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እዳሉት ጠንካራ ራዕይ፣ ጠንካራ የሥልጠና ማዕከል አብራሪዎች፣ ጠንካራ ሠራተኞች በተቋሙ የሚያስገኙትን ውጤት ትምህርት በመውሰድ በብሔርም ሆነ በሃይማኖት መከፋፈል ሳይኖር የተሳካ ሥራ በማከናወን አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ቀዳሚ ተግባርና ዕምነት ሊሆን ይገባል። አየር መንገዱ ያስመረቀው ሆቴልም ትልቅ መሆኑና በርካታ ጎብኚዎችን መጋበዝ የሚያስችል መሆኑ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ በሚደራጀው ዩኒቨርሲቲ ተቀጥሮ የሚሰራበት ብቻ ሳይሆን ባለቤት በመሆን በእኔነት ስሜት ትጋትን ማሳደግ ይችላል።
የአየር ማረፊያ ማስፋፊያው አገሪቱ መስራት ከሚገባት በብዙ ርቀት ላይ እንዳለች ያሳያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት 22 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን ያስተናግዳል። ሕዝቡ ግን 100 ሚሊዮን ነው። የውጭ ሳይጨመር ለአገሪቱ ብቻ አንድ ለአምስት አቅም ያለው አየር መንገድ ነው ያለው። በቀጣም በትንሹ የሕዝቡን ቁጥር መሠረት ያደረገ ጠንካራ አየር መንገድ ከሚያስፈልጉት ተጨማሪ መሠረተ ልማቶች ጋር በማሟላት ዕውነተኛ የአገር ኩራት ሊሆን ይገባል።
በቀጣይም በአሁኑ ወቅት በተሰራው ሥራ ባለመዘናጋት ትልቁን ስራ ለመጀመር እንዲነሳሳ አደራ ሰጥተዋል። አየር መንገዱ እንደ አቶ ግርማ ዋቄ ያሉ በሥራቸው ስኬታማ ዋና ሥራ አስፈፃሚዎችን በማፍራት የሚታወቅ ነውና ሌሎች የአፍሪካ አገራት በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ አካላት ከኢትዮጵያ አስተዳደር ቢገኝ እንደ አገሪቱ መበርታትና ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ እንዲያስቡ አድርጓልም ብለዋል።
ወቅቱ በሚጠይቀው ደረጃ አብራሪዎችን ለመፍጠርም የአስተናጋጆች የአብራዎችና የቴክኒክ ስልጠና ብቻውን በቂ ስላልሆነ የአቪየሽን ዩኒቨርሲቲ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲው በርካታ ሙያተኞችን ከአገሩ አልፎ ለአህጉሪቱ የሚያፈራ የአገሩን ስምና ዝና የሚያስቀጥል እንዲሆን የግል ዘርፉንም በማሳተፍ ለአፍሪካ ጭምር ብርቅዬ ዩኒቨርሲቲ እንደሚገነባና በአሁኑ ወቅት ከሚሰራ ሥራ በተጨማሪ በርካታ ሙያተኞችን በማፍራት ስሙን ይበልጥ መጠበቅ አለበት ብለዋል። ለዚህም አየር መንገዱ የአገልጋይነት መንፈስን አዳብሮ ለአገሩና ለአህጉሩ ኩራት መሆኑን እንዲያስመሰክር አደራ ብለዋል።
በሥነስርዓቱ ላይ ተጋባዥ የነበሩት የቀድሞ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ግርማ ዋቄ፤ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ለ2025 እየሰራ ሲሆን፤ ለ2030 ደግሞ ዕቅድ እያወጣ መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን አንድ ተቋም የሚቀጥለው በአንድ ሰው ጉልበት አይደለምና መተካካት ሌሎችንም ማብቃት ይገባል፤ የውስጥ ጥንካሬን መፍጠርም ተገቢ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ በ363 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አየር ማረፊያ ማስፋፊያና በሆቴል ዘርፉም በ65 ሚሊዮን ዶላር ያስገነባውን ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል አስመርቋል። በዚህም ቀደም ሲል 12 ሚሊዮን ያልዘለለ ተሳፋሪ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት ወደ 22 ሚሊዮን ያሳድገዋል። ሆቴሉ በአገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ሲሆን በአፍሪካ ከፍተኛው የቻይና ሬስቶራንትንም የያዘ ነው።
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ላለው 16 ሺ ሠራተኞች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚሰራ ሲሆን በዚህም ከዚህ ቀደም ለ1 ሺ 200 ሠራተኞች መኖሪያ ቤት ሰጥቷል። በቀጣይም 12 ሺ አፓርትመንቶችን በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ለሠራኞቹ ለማስረከብ ተዘጋጅቷል። በአሁኑ ወቅት ለተገነባው ሆቴልም ሠራተኞች የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራው ተመቻችቷል።
በዓለም ላይ ቴክኖሎጂ ያፈራው አለ የሚባል የደህንነት መቆጣጠሪያ አሉት።
ከዚህ በፊት መንገደኞች በየመሳሪያ መግቢያው ሲዘልቅ ለመውጣት ይቸገር ነበር። በአሁኑ ወቅት የተሰራ ማስፋፊያ ግን ይህን የነበረውን ችግር በመቀፍ የጋራ ፍተሻውን ካለፈ በኋላ ዘመናዊ የሆኑ ሱቆች ሬስቶራንቶች በመኖራቸው መንገደኛው የበረራ ሰዓቱ እስኪደርስ የሚዝናናበት በጣም ሰፊ ቦታ አለው። ተጓዥ መንገደኞችን ተሸከርካሪዎች አምጥተው መመለስ መቻላቸውም ለየት ያደርገዋል። በርካታ ተግባራትን ታሳቢ አድርጎ ተሰርቷል።
ሶስት ምዕራፎችን ያቀፈው ፕሮጀክቱ አዲስ ለምረቃ የበቃው ማስፋፊያና ቀደም ብሎ ሥራ የጀመረው ሶስት መሳፈሪያ በሮች ያሉት ማስፋፊያ ተደማምሮ የመንገደኛ ቁጥሩን ከፍ ያደርገዋል። ለቪአይፒ ራሱን የቻለ ህንፃ ግንባታ ይደረጋል። አውሮፕላንም እዛው ያስቆማል። ባለፉት አምስት ዓመታት አየር መንገዱ ያሳየው ፍጥነት 30 በመቶ በመሆኑ በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ ያደገ አስብሎታል።
ተጨማሪ አውሮፕላን ማቆሚያ በስተምስራቅ በኩል ግንባታ ተጀምሯል። በደቡብ በኩልም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ላይ ሲሆን ይህም ሌላ ማስፋፊያ ያሰራል ይህም 2025 ድረስ ይጠናቀቃል።
በአሁኑ ወቅት አፍሪካውያኖች ዱባይ በማምራት ይሸምታሉ። አየር መንገዱም በዚሁ መሸመት የሚያስችላቸውን ሁኔታ ይፈጠራል። እአአ በ2010 ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ አየር መንገድን ተከትሎ አራተኛ ደረጃ ላይ እንደነበር በማስታወስ ባፉት ስምንት ዓመታት በተሰራ ሥራ በብዙ ብልጫ አንደኛ ሆኗል። በዚህም በአሁኑ ወቅት ትልቁ ግዙፍ አየር መንገድ በመሆኑ 111 አውሮፕላን ይዟል። በሁለተኛ ደረጃ የሚከተለው የግብጽ አየር መንገድ 68 አውሮፕላኖች ይዞ በሰፊ ልዩነት ይከተላል።
የአገሪቱ ቱሪዝም በተፈለገው ደረጃ ባለማደጉ ይህ ሆቴል መከፈቱ የመሪ ሚናውን ይዞ የውጭ ገቢን ከማሳደግ ጀምሮ የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅሙንም ያሳድጋል። ጎብኚ ከገባ በኋላ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አለመኖር ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችንም ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል። በዓለም ላይ በሚገኙ ከ120 በላይ ቢሮዎች ቴኬቱንና የሆቴሉን አገልግሎት አብረው እንዲያቀርቡ የሚያስችልም ነው። ሆቴሉ በአገሪቱ ትልቁና በአጠቃላይ 1 ሺ ክፍሎችንም የያዘ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ አየር መንገዱ ብዙ መለያ ባህሪዎች አሉት። የአገሪቱ ዜጋ በሄደበት ሁሉ ከኢትዮጵያ መሆኑን የሚሰማ ያልተገዛች አገር ከማለቱ ጎን ለጎን የአየር መንገዱንም ስም ይጠራሉ። አየር መንገዱ ከነፃነቷ ዕኩል እንድትታወቅ ያደረገ ተቋም ነው። ለዚህም አየር መንገዱ ኢትዮጵያን አንግቦ የሚንቀሳቀስ የዜጎቹ ሁሉ ኩራት የሕይወት ዋጋ ውጤት የሆነውን ሠንደቅ ዓላማ የያዘ በመሆኑ ከሁሉ ተቋማት በተለየ መንገድ የአገሪቱ መለያ ሆኖ የሚያገልግል ነው።
ተቋሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር ያደረገውና ከነፃነት ቀጥሎ እንዲጠራ ያደረገው የሰነቀው ራዕይ ያሉት ጠንካራ የአስተዳደር አካላት እንዲሁም በየደረጃው በተቋሙ ውስጥ የሚሰሩት ሠራተኞች የተቀናጀ ርብርብ ውጤት ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 20/2011
በፍዮሪ ተወልደ