ይቤ ከደጃች ውቤ
በአንድ ወቅት አንድ አዛውንት ስለ ቀበሌ መዝናኛ ክበባት ሲያጫውቱኝ ቀደም ሲል እኮ ‘ኑሮ በዘዴ’ የተባለ ትምህርት ይሰጥ እንደነበር፣ስለተመጣጠነ ምግብና ስለ አገልግሎቱ መማራቸውን፣የተመጣጠነ ምግብ ለሰው ህይወት ፣ጤንነትና ውበት አስፈላጊ ስለመሆኑ ትምህርት መቅሰማቸውን ገለጹልኝ። አዛውንቱ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ደሞ ሽሮ እንደሚቀርብላቸው ፣አንዳንዴ እንደውም ውሃ በሽሮና በጨው ተበጥብጦ በእንጀራ ቀርቦ ምሳ ይበሉ እንደነበር ያስታውሳሉ። ‹‹በድህነታችን አቅማችን ይሄው ነው። ቀበሌ ፓስታና ማኮሮኒ ሲመጣ ቤት ራት ይቀርብልኛል። አልፎ አልፎ ድንች፣ ጎመን ይዘጋጅ ነበር። ድህነቴ ነው መሰለኝ ጎመን ይመቸኛል፤ተረቱም፣ ኮ ‘በድሃ ቤት ጎመን የተቀቀለ ዕለት ሲጨበጨብ ያድራል’ ነው የሚባለው።
የተመጣጠነ ምግብን በደብተር እንጂ በተግባር አላቀውም ነበር። አልፎ አልፎ ትንሽ ገንዘብ ሳገኝ ግን የቀበሌ መዝናኛ ክበብ መጠቀም ያምረኛል የሚሉት አዛውንቱ፣ በተመጣጠነ ዋጋ የተመጣጠነ ሸጋ ምግብ ይቀርባል ይላሉ። ለአዛውንቱ አሁንስ የመዝናኛ ክበባቱ ከዘመኑ ጋራ አልተሻሻሉም? የሚል ጥያቄ አነሳሁላቸው፤ እሳቸው መልሰው በማጣጣል ስሜት እጃቸውን እያወራጩ “ ምን ያሻሽሉታል ብለህ ነው?መዝናኛ ክበቡን እኮ መናኛ አደረጉብን “ሲሉ መለሱልኝ።
በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ መዝናኛ ክበባት ከጠዋት እስከ ምሽት የተለያዩ መጠጦች የሚስተናገዱባቸው ቦታዎች ናቸው። በዚህም ከምግብ አቅርቦት ይልቅ በመጠጥ ቤትነት የሚታወቁ ናቸው። መቼም መጠጥ ማስተናገድ የለባቸውም የሚል አመለካከት የለኝም። ነገር ግን ቀደም ሲል የነበረውን መልካም ስምና አገልግሎት ይመልሱት። በተመጣጣኝ ዋጋ የምግብ አገልግሎት እንዲኖረው ይደረግ፤ ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ይመቻች። ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተገንብቶ ለነዋሪዎች ዳቦ ማቅረብ ጀምሯል። ብዙ ሰዎችም በፋብሪካው የሥራ ዕድል ማግኘት ችለዋል። በተጨማሪም ከትራንስፖርት ስምሪት አገልግሎት ውጪ የሆኑ የአንበሳ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት አገልግሎት ያቆሙ አውቶብሶች ለዳግም አገልግሎት ተዘጋጅተው በተመረጡ ቦታዎች ለሸገር ዳቦ መሸጫ ተደርገዋል። ሥራ እንደ ጀመሩ ወረፋ ይበዛባቸው ነበር፤በወቅቱ ብዙም መረጃ ስላልነበረኝ ይህን ሰልፍ ተመልክቼ የሚያሳፍሩ መስሎኝ መሰለፌ ትዝ አለኝ ።
ሸገር ዳቦ ለዜጎች ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ እንዲያገኝ ያስቻለ ከመሆኑ በተጨማሪ የሥራ ዕድል አስገኝቷል። አገልግሎቱ እንደኔ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውና ለልደታቸውም ሹገር ኬክ ለማይቆረሱ ሸገር ዳቦ እየቀመሱ (መጠኑ ትንሽ ስለሆነ እየበሉ ለማለት አዳገተኝ) የሚያከብሩበት አማራጭ ይመስለኛል።
የሸገር ዳቦ ፋብሪካ የሜድሮክ ነው፤የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ ዳቦ ቤቱ እውን እንዲሆን ብዙ ደክሟል። የሸማቾች ማኅበራት በአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አማካኝነት ብቃት ያላቸው አገልጋዮችና አመራሮች ቢኖሩ ኖሮ ዳቦ ቤቶችን መክፈት ይችሉ ነበር። እንደ ሸገር ዳቦ አይነት መሸጫዎች በየቦታው ለዝቅተኛው ማኅበረሰብ አስፈላጊ ናቸው።
በሸገር የሚገኙ የሸማቾች ማኅበራት ይህንን በመሥራት ግንባር ቀደም ሆነው መገኘት ነበረባቸው። ማኅበራቱ በሸማቾች ስም ተመስርተው የሸማቹን ፍላጎት ማርካትና ማሳካት ያልቻሉ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። የከተማው መስተዳድር ይህን በአግባቡ ቢመለከተው መልካም ይመስለኛል። አገልግሎቱን ማሻሻልና መቀየር የማይችሉ አመራሮች ቢቀየሩ እላለሁ።አምባሳደሮችና ሚኒስትሮች ሲቀየሩ እናያለን፤የኤጀንሲው አመራሮች ግን የሚደርስባቸው የለም፤በዕድሜ ይፍታህ አይነት መልኩ የተቀመጡ ያስመስላቸዋል ።
በአዲስ አበባ በየወረዳው ያሉ የህዝብ መዝናኛ ክበባት በሸማቾች ማኅበራት ሥር የሚገኙ ናቸው።የሸማቾች መዝናኛ ክበባቱ የምግብና የመጠጥ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆኑ፣ በደርግ ዘመን የቀበሌ መዝናኛ ክበባት ይባሉ ነበር። የቀበሌዎች የኅብረት ሱቅ አገልግሎት እንዲፈርስ ተደርጎ ከዓመታት በኋላ የሸማቾች ማኅበራት ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲሰጡ ተቋቋሙ።
በመዲናዋ 205 የህዝብ መዝናኛ ክበባት ነበሩ፤ የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚጠቁመው ፤ በመልሶ ማልማትና በተለያየ ምክንያት የፈረሱት ቀርተው አሁን 198 መዝናኛ ክበባት በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሥር ታቅፈዋል(እንደ ህፃን ተኝተዋል)። መዝናኛ ክበባቱ ከሐምሌ 2009 ጀምሮ በሸማቾች ማኅበር ሥር ሆነው በአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የታቀፉ ናቸው። ነገር ግን ህብረተሰቡ የሸማቾችን ስም ታቅፎና ተደግፎ ለሸማቾች መሥራት ያልቻሉ ማኅበራት ናቸው ሲሉ አገልግሎታቸውን ይነቅፋል።
በአንድ ወቅት አንድ መዝናኛ ክበብ ምሳ ለመብላት እግረ መንገዴንም ለመቃኘት ጎራ አልኩ። ቀይ ወጥ አዘዝኩ፤ገና ስቀምሰው እንጀራ በወጥ ሳይሆን እንጀራ በጨው ያዘዝኩ መሰለኝ። አንድ ክበብ ደግሞ ተመሳሳይ ምሳ መጥቶልኝ ስቀምሰው ወጡ ውሃ ውሃ ስለሚል አልጣመኝም። እንደውም እንደ አለቃ ገብረሃና “ይሄን እህል ውሃ ያደረገው ማነው?” እንዳሉት ማለት አሰኝቶኝ ነበር። ልሸልመውi ለማለት ፈልጌ ነበር። ዳሩ ግን አለቃና ምንዝር የሌለባቸው መዝናኛዎች ስለሆኑ ተውኩት። አገልግሎታቸውም እየወረደና እየቀነሰ የመጣው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል። ለአገልግሎታቸው ደመወዝ ሲከፈላቸው ሠራተኞቹ እንዲተጉ ቢደረግ የምግቡ መስተንግዶ አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ይቀርባል።
የወረዳ መዝናኛ ክበባቱን እርስ በርስ ማወዳደርና በአገልግሎት ጥራትም መሸለም ይገባል። የአንድ ወረዳ መዝናኛዎችን በአገልግሎት ማወዳደር የክፍለ ከተማ መዝናኛዎችን በጥቅል በአገልግሎት እንዲወዳደሩ ማድረግ ለሥራ ያነሳሳቸዋል ብዬ አምናለሁ።
አገልግሎቱ ጥራቱን እንደጠበቀ ብዛቱ ሲሆን በብዛት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ህይወታቸውን በካምፕ ውስጥ እንዲመሩ ተገደዋል፡፡ በሶማሊያ አሁንም ቢሆን በትምህርት እጥረት፣ በመሰረተ ልማት ምቹ አለመሆን፣ በገንዘብ እጦትና አስፈላጊውን
እንዲጨምር ጥረት መደረግ አለበት። ከዚሁ ጎን ለጎን የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮና የሚመለከታቸው አካላት ዋጋም ጥራትም እያሳነሱ በሚዛን የሚበድሉ የዳቦ ቤት ነጋዴዎችን መመልከት ይገባቸዋል። በንግድ ቤቶች በተለይ ዳቦ ቤት፣ ልኳንዳ (ስጋ ቤት)፣ እህል ንግድ ቤት እና አትክልት ቤቶች ላይ የገበያ ምርትና የሚዛን ጥራት ላይ ቁጥጥር ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ቁጥጥሩ ዜጋውን ከጤንነት ለመከላከልም ሆነ የሚዛን ትክክለኛነትን ለመቆጣጠር ፣ የንግድ ፍቃድ ያላቸውንና የሌላቸውን እንዲሁም ተጨማሪ እሴት ታክስ መጠቀም እያለባቸው የማይጠቀሙትን ለመለየት ይረዳል።
ነጋዴውም ‘ደንበኛ ንጉሥ ነው’ የሚለውን ብሂል አክብሮ ስሙንም አስጠብቆ መጓዝ አለበት። በሚዛን የሚበድሉ ነጋዴዎች ላይ ‘ክትትል እያደረግን ነው’ የሚለው የኃላፊዎች መግለጫ ብቻውን ለውጥ ሲያመጣ አላየንም። መንግሥት የነጋዴውም የሸማቹም፣ የወዛደሩም የወታደሩም፣ የአስተማሪውም የተማሪውም ወላጅ ወይም አሳዳጊ ነው።ሁሉን አቃፊ ነው። ነጋዴዎችም በሚዛን ሳይበድሉ (ሳይጨቁኑ) አትራፊ እንዲሆኑ ማድረግ ሸማቾችም ሳይበደሉ (ሳይጎዱ) እንዲጠቀሙ ማድረግ ይጠበቅበታል።
ክበቦቹ ጠዋት ጠዋት ብትሄዱ ቁርስ የሚባል ነገር የላቸውም። ሻይ ቡና አልያም ድራፍትና ቢራ በገፍ ሲስተናገድ ልታዩ ትችላላችሁ። ከመዝናኛ ክበባቱ ይልቅ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥር ያሉ የሠራተኛ ክበቦች ለሠራተኞች ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ለውጭ ሰዎች በተወሰነ ክፍያ ጭማሪ የምግብ አገልግሎት ይሰጣሉ።
ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ጥሩ ሥራ ከሠሩ ሸማቹ ለመልካም ሥራቸውና አገልግሎታቸው ተጨማሪ ደንበኛ ይዞላቸው ይመጣል። ‘ለጥሩ ዕቃ ማስታወቂያ አያስፈልገውም’የሚለውም የምዕራባውያን ብሂል በተግባር ተተርጎሞ ልታዩት ትችላላችሁ። ችግሩ ተቆጣጣሪ አካልም ስለሌለ ነጋዴው በባሌም በቦሌም ብሎ ነግዶ ለመክበር ሲጥር እንጂ መልካም ስሙን ለማስከበር ሲጥር አይታይም።
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም