ዳግማዊት ግርማ
ዕድሜው ለስራ የደረሰ ሁሉ ሰርቶ በማግኘት ህግ ይገዛል ።ሰርቶ ባገኘው ገንዘብም ያለአንዳች ከልካይና ገልማጭ ይጠቀማል። ገቢው ይብቃም አይብቃም ያገኘውን እንደነገሩ እያብቃቃ ኑሮን ይኖራል። ያውም ተመስገን ብሎ። ተመግቦ መኖር የሻተ ሁሉ ሰርቶ ማደር ግዴታው ነው ።ከፋም ለማም የሰራ የወዙን ፍሬ ይመገባል ።የስራውን ያህል ባያገኝ እንኳን ይሰራል፣ ይለፋል፣ ይደክማል ።ስራ የብዙ የነፍስ ቁስል ፈውስ ነው ።ሰው ሁሉ የዘራውን ያጭዳልና ነገሮች ሁሉ በስራ ሚዛን ነው የሚሰፈሩት። አንዳንዶች ከስራው በሚያገኙት የሳንቲም መጠን ስራን ሲያከብሩ ሌሎች ደግሞ ስራን በስራነቱ ብቻ አክብረውት ይኖራሉ ።የዛሬ የኑሮ እንግዳችንም ወቅት የሰጠቻቸውን አቅማቸው የቻለውን ስራ ሰርተውና ስራቸውን አክብረው የሚኖሩ ወይዘሮ ናቸው፡፡
ወይዘሮ መስቀሌ ወልዴ ይባላሉ ።በጉልበታቸው አዳሪ፤ በላባቸው ኗሪ ናቸው ። ድህነት ያተረማመሰው፣ ብሶት ያዘለው ፊታቸው ከእድሜያቸው በላይ የኖሮ አዛውንት አስመስሏቸዋል ።የህይወት ዳገት ቁልቁለት የቀይ ዳማ ፊታቸውን ሊያጠቁር ትግል ገጥሟል ።እሳቸው ግን ወይ ፍንክች ብለው ላለመሸነፍ ይታትራሉ ። በኑሮ ክፋት የዳመነ ገጽታቸው በሁኔታዎች ያልተቀማ የተፈጥሮ ፈገግታን ፈገግ ይሉበታል ።ደንበኞቻቸውን አስደስተው ለነገ ደግሞ የገበያ መንገዳቸውን ለማሳካት ስራቸውን ከጨዋታ ጋር እያዋዙ ነው የሚያስኬዱት።
ወይዘሮ መስቀሌ በመንገድ ዳር ላይ ቁጭ ብለው የድንች ቅቅል በሚጥሚጣ ማባያ ሲሸጡ ነው ያገኘናቸው ።በመሀል ፒያሳ ወደ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ሆቴል በሚወስደው መንገድ ላይ ። እዚች ቦታ ላይ ድንች እየሸጡ ሁለት መስከረሞችን አሳልፈዋል ።ከተቀቀለ ድንች ሽያጩ በፊት ክረምቱን ደግሞ በቆሎ እሸት ጠብሰው ይሸጡ ነበር፤ ያውም 20ና ከዚያ በላይ ዓመታትን ሙሉ ።
ታዲያ የበቆሎ እሸት ንግድ ያላደረጉትና ያላደረጋቸው ነገር እንደሌለ ያስታውሳሉ ።ደመኞች ናቸው፤ ቂም ተያይዘዋል። የእድሜያቸውን ብዙ ዓመታት ቀቅለው ጠብሰው ፍዳውን አሳይተውታል፤ እሱም ወጣትነታቸው፣ እምቡጥና ለጋነታቸውን አስገብሯቸዋል። ጠብሰው የቀቀሉት በቆሎ ፊታቸውን ጠብሶ ያለመልካቸው መልክ አሰጥቷቸዋል። ያዘጋጁት በቆሎ አልሸጥ ሲላቸው እሳቸውም በንዴት ጥብስ ብለዋል።
የትውልድ ቀያቸው በጠንካራ ሰራተኛነታቸው ከሚመሰገኑት ከጉራጌዎች ምድር ከወልቂጤ አለፍ ብሎ ባለ ቀጭራ ወሰራ በሚባል ስፍራ ነው ።ትውልዳቸው እዛ ቢሆንም የእድሜያቸውን ጥቂቱን እንኳን በዛ አላሳለፉም። አዲስ አበባ ከከተሙ ብዙ አስርት ዓመታት አልፈዋል። ጉልበታቸውን ተማምና ቢሆንም ደገኛዋ አዲስ አበባ ሳትከፋ ተቀብላቸዋለች። አስተናግዳቸዋለች።
ወጣትነት ወጥቶ መግባት፣ መሮጥ፣ መሯሯጥ ይሄ ሁሉ ደስ ያሰኛል፤ ውስጡ ብዙ አቅም አለው ። አዳዲስ ነገሮች አይጠፉም ።ወይዘሮ መስቀሌ ግን ወጣትነታቸው ለውጥ የነበረውና የተለያየ ነገርን ያዩበት አልነበረም ።በተቃራኒው ሲነጋም ሲመሽም የበቆሎን ፊት ሲያዩ የኖሩበት እንጂ ። የለጋነት ዘመን ብርታትና ሙሉ አቅማቸውን አሳልፈው የሰጡት ለበቆሎ ሽያጫቸው ነው፡፡
ከዚችም ኑሮ መወካከቡ ይበዛል ።ሁለት ሴትና አንድ ወንድ ልጆቻቸውን ያሳደጉት በቆሎ ሸጠው ነው ። አባወራቸው የጤና እክል አለባቸውና የቤት ውስጥ ሙሉ ሀላፊነቱ እሳቸው ላይ የተጣለ ነው። ያለ ደጋፊና ረዳት የብቻ ህይወት በአንድ እጅ ማጨብጨብ ሆኖባቸዋል ።የቤታቸው ቀዳዳ ብዙ ነው ።ጠብ ያለውን ሁሉ መድፈን ብርቱ ትከሻቸውን አዝሎታል፡፡
ደጋፊ ፍለጋ ቢሮጡም በጄ ባይ አጥተዋል ።የመኖሪያም ሆነ የመስሪያ ስፍራ እንዲሰጣቸው ለመንግስት ቢጮሁም ሰሚ አጥተው ተስፋ ወደ መቁረጡ ናቸው ።ከእሳቸው በኋላ የጠየቁ ተሳክቶላቸው ቢያዩም መንገዱን ባለማወቃቸው ወይዘሮ መስቀሌ ግን ዛሬም ድረስ ቀን አልወጣላቸውም። የባለቤታቸውን አቅመ ደካማነት ተናግረው የቤት ኪራይ 2500 ብር ከፍለው እየኖሩ መሆኑን ጠቅሰው መላ በለን፤ ከቤትህ አሳድረን ብለው ለመንግስት ጮኸዋል ። ጩኸታቸው አቤት ባይ አጥቶ እርዳታን ከሰማዩ ጠይቀው ወደ ሰማይ አንጋጠው ትተውታል፡፡
የኮሮና መከሰት ደግሞ ኑሮን አክብዶ የህይወትን ክፋት አክርሮታል፤ ብዙ ነገሮች ዋጋቸው በጣም ጨምሯል ። ከወራት በፊት በነበረበት ዋጋ የተሸጠ ምንም ነገር የለም ። ድንች በጥሬ ከሚገዛበት የመሸጫ ስፍራው እስከ ቤታቸው ድረስ ለሚያመጣው ወዛደር ክፍያን ጨምሮ የኩንታሉ ዋጋ 1500 ብር ድረስ ይፈጃል ።ይህን ያህል አውጥተው ብርድና ቁር ተፈራርቆባቸውም ታዲያ የቅቅል ድንቹ ዋጋ እጅና አፋቸውን ከመራራቅ ቢታደጋቸው እንጂ ቅንጦት የማይታሰብ ነገር ነው ።እሳቸው ደግሞ ከአስር ብር ጀምሮ ድንች ቀቅሎ ይሸጣል ።ወፍራሙን ሶስት ቀጭኑን አራት ፍሬ አስር ብር ይሸጣል ።
የድንቹን መጠን አስተውለውት ባያውቁም ከነ ድንቹ ዋጋ በቀን እስከ 300 ብር ይሰራሉ ።ከዚህ መሀል ትርፉ በጣም ትንሽ ነው ።ድንች ቅቅላቸውን ሸጠው ህመም ለጎዳቸው ባለቤታቸውና እጅ እጃቸውን ለሚጠብቁ ልጆቻቸው ይደርሳሉ ።ጉልበታቸው ስንት እንደሚያወጣ አንድም ቀን ገምተውት አያውቁም። ደሀ ጉልበቱን አይቆጥርም በሚለው የሂሳብ ስሌት ነው የሚተዳደሩት። ዋናቸውን አንስተው ትርፏን ለቀን ማደርያቸው ያውሏታል ።ውሀቸውን ቀድተው ይጠጣሉ፤ ሳሙናቸውን ገዝተው ይተጣጠባሉ፡፡
እግረ መንገዱን በድንች መሸጫ ስፍራቸው ያደረገ መንገደኛ ሁሉ ድንቻቸውን ቀምሶ ያልፋልና ባለውለታቸው ነው ።ተማሪ ሰራተኛው በመሸጫቸው ሲያልፍ ያገደመ ሁሉ ረሀብ ከፀናበት በእሳቸው ድንች ቅቅል ረሀቡን ያስታግሳል ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የድንች መግዣ ዋጋቸው ጨምሮ ከነበረቻቸውም ትንሽ ገበያ ኮሮና መጣና ያሏቸውን ደንበኞች ቀነሰባቸው ።አንዱ የነካውን መመገቢያ ሌላው ደፍሮ አይነካም። በእሳቸው እጅ የሚነሳን ድንች ማን ተቀብሎ ፤ ማንስ በድፍረት ተቀምጡ ሊመገብ ብቻ ኮሮና ፈተናም፣ መፈተኛም ሆናቸው።
አምናና ካቻምናን ከድንች መቀቀያቸው ጎን በቆሎም ይታይ ነበር፤ የዘንድሮው ገበያ ግን ኮሮናን ሰበብ አደረገና በበቆሎ የታገዘ አይደለም ።የበቆሎ አለመኖር ደግሞ ገቢያቸውን በእጅጉ ቀንሶባቸዋል፡፡
ዘመነ ኮሮና ሌላም ነገር አምጥቶባቸዋል ።ያመጡትን ድንች ሳይጨርሱ ባይገቡም ስራ ቦታ የመቆያ ጊዜያቸውን ግን አብዝቶባቸዋል ።ከዚህ ቀደም ጨለማ ምድሪቷን ሲተዋወቅ (አንድ ሰዓት አካባቢ) ወደ ቤታቸው ያመራሉ። አሁን አሁን ግን እድሜ ለኮሮና ለእኩለ ሌሊት ሶስት ሰዓታት ብቻ ሲቀር ወደ ጎጇቸው ያቀናሉ፤ ሰካራሙን ማጅራት መቺውንም ያዝልኝ እያሉ ።ወይዘሮ መስቀሌ ታዲያ ይሄ ሲሆን አንዴም አምላካቸውን አማረው አያውቁም ተመስገን ከማለት ውጪ። የእሳቸው የየእለቱ ፀሎት ጤና ስጠኝ ነው። ደግሞስ ከጤና በላይ ምነ ሀብት አለ። ጤነኛ መሆናቸው ከሀብትም በላይ ነውና በቆሎ እሸታቸውን አገላብጠው ድንቻቸውን ቀቅለው የራበውን መንገደኛ ረሀብ ያስታግሳሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም